ዘረኝነትና ጥላቻ ከራሴ ገጠመኝ ምሳሌ ከሁሉ በፊት መፍተሄ የሚሻ (ሰርፀ ደስታ)

ለራስህ ሊያደርጉብህ የማትፈልገውን በሌሎች አታድርግ! የሙስሊሙም የክርስቲያኑም የሌላውም መሠረታዊ የእምነት መርሆ ነው! እውነታዎች ግን ከዚህ በተቃራኒው ናቸው፡፡ጽሁፌ ከወትሮውም ረዝም ያለ ነው፡፡ በተለይ የኦሮሞ አክራሪዎች ይሄን ጽሁፌን ቢያንቡት ደስ ይለኛል፡፡ ላለፉት 4-5 ዓመታት በተለይ የኦሮሞን ፖለቲካ ዋና ጉዳዬ አድርጌ ስፅፍ ነበር፡፡  የምጽፋቸው ነገሮች ፈጥሬ አደለም፡፡ የምረዳውን ያህል መናገሬ እንጂ፡፡ እስኪ ዛሬ ስለራሴ ትንሽ ፍንጭ ልስጣችሁ፡፡ አንዳንዶቻችሁ ብትደግፉትም ሌሎች በተለይ ብዙ ኦሮሞ ነን የሚሉ ነገሬን ከበጎ አያዩትም፡፡ ሆኖም ግን የምጽፈውን ለመስተባበል  የሚችሉበ አቅም ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ዛሬ ግን ፍንጭ ልስጥና በእኔው የሆነውን እንደምስክርነት በማቅረብ ዘረኝነትና ጥላቻ ምን ያህል የብዙዎች ሕሊና እንደፈተነ ታዘቡ፡፡  እኔና ወያኔ ድሮውንም ይቅር የማንባባልባቸው ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ አንዱ ወያኔ ሆን ብላ አገሪቱን ከአለወደብ ያስቀረችበትና ሌላው የዘር ፖለቲካ የዘረጋችበትን ሴራዋን ነው፡፡

ዛሬ ኦሮሞ ብዬ የምጠቅሰው በትክክልም የእኔ ልምድ በዚሁ ማህበረሰብ ከወጡ ጋር ስለሆነ እንጂ እውነታው ሁሉም ቦታ እንደሚኖር እረዳለሁ፡፡ እኔ እውነቱን ንገረን ከአላችሁ ዛሬ ኦሮሞ ተጨቁኛለሁ፣ በቋንቋችን እንዳናወራ እንድንሸማቀቅ ይደረግ ነበር፣ ኦሮሞ በኦሮሞነቱ ልዩ መገለል ደርሶበታል ምናምን የሚሉ ነገሮች ተወልጄ በአደኩበት አካባቢ ስለማይነጸባረቅ እነዚህን ነገሮች ለመቀበል እስካሁንም አልተቻለኝም፡፡ በታሪክም ያሉ ነገሮችን ሳስተውል ምንም የተለየ እውነት አላየሁም፡፡ ግን አንድ እውነት ያለ ይመስለኛል በአንዳንድ አካባቢዎች ችግሮች እንደነበሩ እገነዘባለሁ፡፡ እንደገባኝ እነዚህ በአንዳንድ አካባቢዎች ኦሮሞነትን ያገሉሉ ሁኔታዎች በመላው ኦሮሞ በሀሳብ ተቀርጸው በመላው ሕዝብ የተሰራጩ ይመስለኛል፡፡ ዛሬ በማንነቴ ተጨቁኛለሁ የሚለው ሁሉ ከታሪክ እውነታ ጋር የተያያዘ ነገር ሳይሆን ተጨቁኛለሁ የሚለውን አስተሳሰብ ስለተሰራጨበት ስለተቀበለው ይመስላል፡፡ ጭቆና አልነበረም አደልም፡፡ እዚህ ጋር የማወራው ማንነትን መሠረት ያደረገ ጭቆና ማለቴ እንጂ፡፡ በእርግጥም በአንዳንድ አካባቢዎች ያስተዳድሩ የነበሩ ሰዎች ሰዎችን በማንነታቸው ጨቁነው እንደነበር ከላይ እንደጠቆምኩት እረዳለሁ፡፡ ወደእኔው አስተዳደግ ስመጣ ከዚህ የተለየ ነው፡፡

እኔ በአደኩበት አካባቢ በእምነትም ዛሬ በመጣው በብሔርም የተለያየን ሰዎች የእምነት ልዮነታችን ሳይቀር እንደተባለውም የሚያስደምም ውበት ሆኖ የኖርንው፡፡ ዛሬን አያድርገውና እኛ ቤት ለፋሲካ አክፋይ የሚመጣልን ከሙስሊም ጎረቤቶቻችን ነበር፡፡ የእኛም ወላጆች የሙስሊም ጎረቤቶቻችን ቤት ለአረፋና ለሞሊድ ይመስለኛል ግን አሁን ረስቼዋለሁ ይዘው የሄዳሉ፡፡ በሞትና በሰርግማ ተውት፡፡ እሱ እስከቀርብ ጊዜም ነበር ግን እየቆየ የእምነት አክራሪነቱም የዘር አክራሪነቱም እያየለ መጥቶ አሁን ላይ ሳያጠፋው አይቀርም፡፡ እንዲህ ያደኩት እኔ ታዲያ ዩኒቨርሲቲ ገብቼ አንድ ከጎጃም የመጣ ጓደኛዬ ግራ በሚያጋባኝ ሁኔታ የማልረዳውን ነገር ተናገረኝ፡፡ በወሬ ወሬ እስላም ቤት ገብቶ መብላት በክርስትና አይፈቀድም የሚል ጽኑ ዕምነቱን እኔው ፊት ተናገረ፡፡ ልብ በሉ ግን በቤተክርስቲያን ዕውቀት ከቤተሰብ ጀምሮ እኔ የተሻለ ግንዛቤ አለኝ፡፡ እኔና እሱ ሁለታችንም ክርስቲያኖች ብንባለም በእምነት በጣም እንደምንራራቅ ታዘብኩ፡፡ የእኔና የእሱ ልዮነት ግን የመሠረታዊ አስተምሮ ሳይሆን የአስተዳደግ ልዮነት እንደሆነ ታዘብኩ፡፡ ከዛ በኋላ በእርግጥም ብዙዎች ከአንድ አይነት ማሕበረሰብ አካባቢ የሚመጡ ሌላውን ለመረዳት እንደማይችሉ ታዘብኩ፡፡ ከዚህ ጓደኛዬ ውጭ ሌሎችም ተመሳሳይ እምነት አላቸው፡፡ ሐጂቴና ሐጂ ያሳደጉት እንደኔ ያለው ደግሞ በእነዚህ ክርስቲያኖች አይን ግፋ ቢል ንዑስ ክርስቲያን ቢሰጠው እንጂ የፈለገውን የክርስትናውን መሠረታዊ አስተምሮ ቢረዳ እንደሙሉ ክርስቲያን አይቆጠርም፡፡  እኔ ግን አላሸማቀቀኝም፡፡ አስተዳደጌ እንደነገርኳችሁ በክርስትናው የተሻለ መረዳጽ ከአላቸው ቤተሰብ ስላልሆ ከእነሱ ይልቅ እኔ የተሸለ የእምነት ፍልስፍና እንዳለኝ እተማማናለሁና፡፡  ለብዙዎች የማይገባን እውነት ክርስትና በሉት እስልምና ሁለት ትዕዛዛት ብቻ ላይ መሠረት ያደረገ ነው፡፡ አስርቱ ትዛዛት ይባላል፡፡ እውነታው አስር ትዛዝ የለም፡፡ ያሉት ሁለቱ ብቻ ናቸው፡፡ ይህን በደንብ አውቃለሁ፡፡ ይህን ደግሞ በተለይ ለክርስቲያኖች የተናገረው ጌታ ራሱ ነው የራሴ አስተሳሰብ እንዳይመስላችሁ፡፡  ከትዛዛት ሁሉ የትኛይቱ ትበልጣለች በአሉት ጊዜ፡- እግዚአብሔር አማላክህን በፍጹም ነብስህ ኃይልህ አምልክ፣ ይልና ሁለተኛይቱንም ተመሳሳይ ናት ይላታል፡፡ ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ! ሕግ ሁሉ በእነዚህ በሁለቱ ተካቷል፡፡ እውነቱ ይሄ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ማምለክ ሰማያዊ ሚስጢራት ኃይል የሚገኝበት ነው፡፡ ባልንጀራን መውደድ ደግሞ ምድር ላይ ያሉትን ሕጎች ሁሉ መፈጸም ነው፡፡ ሰው ሌላውን ሰው ከወደደ በሌላ ቦታ ለራስህ ሊያደርጉልህ የምትፈልገውን ለሌላው አድርግ በአንት ሊያደርጉብህ የማትፈልገውን በሌሎች አታድርግ ተብሎ አንደተጠናቀቀው ነው፡፡

ልመልሳችሁ የእኛ አካባቢ ማሕበረሰብ ዛሬን አያድርገውና ቤተክርስቲያን የሚሰራ ሙስሊም መስኪድ የሚሰራ ክርስቲያን ሆኖ ነበር የሚኖረው፡፡ ይሄ ለብዙዎች ተረት ተረት ይመስላል፡፡ ከላይ በጠቆምኩላችሁ ትዕዛዝ መሠረት ሕዝቡ እንደወረደ ትዕዛዙን ይኖረው ነበር፡፡ በቀርቡ አፈንዲ ሙተቂ የተባለ ብዙዎቻችሁ ታውቁታላችሁ የሀረር ልጅ አንድ የሙስሊም በአለአባት ኃይለስላሴ ጋር ሄዶ ቤተክርስቲያን መሥራት እንደሚፈልግና ታቦት እንዲሰጠው የጠየቀበትን ታሪክ አስነብቦናል፡፡ አዎ በአላባቱ እሱ በሚያስተዳድረው አካበቢ ጥቂት ክርስቲያኖች ይኖሩ ነበር እና የሞተባቸው ሰው ለመቀበር እንኳን ብዙ ቀን ተጉዘው ቤተክርስቲያን ያለበት ይሄዱ ስለነበር ለእነሱ ብሎ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ እውነታዎች ውስጥ ያደግን እኛ የዛሬው አስተሳሰብን ተቋቁሞ መኖር በራሱ በጣም ከባድ ነው፡፡ ይህ የአፈንዲ ነው፡፡ እኔው ሳውቅ በደርግ ጊዜ የእኛን ቤተክርስቲያን የኖረ ነው ለማደስ ሙስሊም በነበረ የቀበሌ አስተባባሪነት ነበር የታደሰው፡፡ አስተባባሪ ስላችሁ የራሴ ሥራ ነው በሚል እንጂ አስተባብርልን ተብሎ አደለም፡፡ ማደስ አለብን በሚል ነው፡፡

ወደ ዘር ጉዳይ ስመጣ እስከ 1983 ድረስ ከላይ በነገርኳችሁ መልኩ ከሙስሊምና ክርስቲያኑም በተጨማሪ ኦሮሞ አማራ ሌላም ሊኖር ይችላል አብረው ይኖራሉ፡፡ ለእኛ ማንነት ሳይሆን አንድ ነገር ትዝ ትለኛለች፡፡ የአማርኛ ተባጋሪ ቤተሰብ ልጆች ኦሮምኛ ለመናገር የኦሮምኛ ተናጋሪ ቤተሰብ ልጆች ደግሞ አማርኛ ለመናገር የሚደረገው ጥረት ዛሬን አያድርገውና ይገርመኛል፡፡ አሁን ሳስበው ቤተሰቤ የሚናገረውን ቋንቋ ተማርኩት አልተማርኩት ምን ይጠቀመኛል፡፡ ከቤተሰቤ ስለማውቀው ማለቴ እንጂ አያስፈልግም አደለም፡፡ እና ትክክል ነበርን ማለት ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ባለሁለት ቋንቋ ተናጋሪ መሆን እንዴት እንደሚያስደስተን ነበር፡፡ ቀን ከሌጆች ጋር ውለን ያወቅናትን በቤተሰብም ላይ እንለማመድ ነበር፡፡ በእርግጥ ቤተሰብም በብዛት አንዱ የሌላውን ቋንቋ ስለሚናገር ቀን ያወቅናትን ስንለማመድባቸው እንደውም የተሳሳትንውን እያረሙልን ነበር፡፡ በዚህ ሄደት ውስጥ አድገን ሁለት ቋንቋ ሌላም ከአለ ሶስትም አራትም አውቀን ነበር የአንድ ማሕበረሰብ ውላጁ ወያኔ የመጣብን፡፡ ከ1983 በኋላ ነበር ቋንቋ ከዘር ጋር እንደሚገኛኝ ያወቅኩት፡፡ አውቃለሁ አይገናኝም ግን በአስተሳሰብ እንዲህ ብሎ ሰመጣብህ ምን ማድረግ ይቻላል፡፡ ለብዙዎች ኦሮምኛ በብዙዎች ዘንድ እየተነገረ የመጣው ከ1983 በኋላ ሊሆን ይችላል፡፡ ለእንደኔ ያለው ግን አደለም፡፡ ከ1983 በኋላ ኦሮምኛ የምናገርበት ምክነያቱም ጠፋኝ፡፡ ብዙ ወዳጆችም ተለያየን፡፡ ኦሮምኛ ከዛ በኋላ ብዙ ተሻሽሏል፡፡ አንዳንድ በልጅኔቴ የማቃቸው ቃላትም ከእነጭርሱ በሌላ ተተክተው ዛሬ ሌላ ሆነዋል፡፡ ኦሮምኛ ቃላት ስላልሆኑ አደልም ግን የአንዳንድ አካባቢዎች በበላይነት የመሩት የድህረ 1983 ዘረኛ አካሄድ የራሳቸውን ስላስፋፉ  እንጂ፡፡ ዛሬ ኦሮምኛ ወጥ ሆኗል፡፡ እኔ ከ1983 በኋላ ሙልጭ ብዬ ከኦሮምኛ ወጣሁ፡፡ ወድጄም አደለም ብዙ ገጠመኞች አሉኝ፡፡ እመጣበታለሁ፡፡ አሁን አሁን ራሴን ስታዘብ የድሮ የእኔ ያደኩበት ሽማግሌዎች የሚናገሩት በደንብ ይገባኛል በደንብ አወራቸዋለሁ ዘመናዊውን ግን ይቸግረኛል፡፡ ቃላቶቹ ፍጹም እኔ ከማውቃቸው ውጭ ይሆኑብኛል፡፡ እነሱ እንደሚናገሩትም መናገር አልችልም፡፡ የልጅነት ቋንቋዬ ስለሆነ ግን የምናገራቸውን ቃላት በአክሰንት ምክነያት አላበላሻቸውም፡፡ ዜና ምናም ግን ግን አልተቸገርኩም፡፡

ለምን ተውከው ትሉኝ ይሆናል፡፡ በአጭሩ ዘረኞችና በጥላቻ ራሳቸውን የበከሉ ሰዎች ነጠቁኝ እንጂ እኔ አልተውኩትም፡፡  የእኔ አይነት ገጠመኝ በሺዎች ምን አልባትም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ገጥሟቸዋል፡፡ ምን አልባትም ከዚህ ቀጥሎ የምጽፈውን የሚያነቡ የቀድሞ ጓደኞቼ ግን እነሱም ኦሮሞነት(አማራነትም ቢሆን ሌላም ያው ነው) ልክ የሆነ አስተሳብ ነው ብለው የሚያምኑ ቢያንስ የምናገረውን እውነትነት ሊክዱ አይችሉም፡፡ ዩኒቨርሲቲ እያለሁም የከፋ አልነበረም ለእኔ ምክነያቱም በስነልቦናም በቋንቋም ስለምንግባባ የፈለገው ጽንፈኛ ኦሮሞ ቢሆን ከእኔ ጋር ችግር የለበትም፡፡ እንደውም እናገራለሁም ግን የምናገረው ማንነት ከማንቋሸሽ ወይም ከጥላቻ ሳይሆን ከቁጭት ስለነበር ኃይለቃል ስናገር እንኳን የእኔ አስተሳሰብ አሸናፊ ነበር፡፡ እኔ ፊትም አላስፈላጊ ወሬ ለማውራት አይደፍሩም ነበር፡፡ ይህን ስላችሁ ከልብም ከሌላ አካባቢ ከሚመጣ ተማሪ ይልቅ ከኦሮሞ ተማሪዎች ጋር የተሻለ መግባባት ስለነበረኝ ነው፡፡

ከዩኒቨርሲቲ ወጣንና ሥራ ፍለጋ ተሰማራን፡፡ ያው እኔ ኦሮምኛ እችላለሁ በሚል ድፍረት አንድ የኦሮሚያ ክልል ማስታወቂያ ወጣና ሄድኩ፡፡ ጓደኞቼንም እዛው አገኘኋቸው፡፡ በአጋጣሚ የሥራ ቀጣሪው መስሪያ ቤት በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ያመጡ ከላይ ያሉ ተማሪዎችን ብቻ ስለሚወስድ እኔ በዛም እድል አለኝ በሚል ነበር፡፡ መስሪያቤቱን አልጠቅስም ከእኔ ጋር የነበሩ በደንብ ያስታወሳሉ የሆነውን፡፡ ቅጥሩ ግን ቦሌ መንገድ የሚገኘው ጨፌ ነበር፡፡ እዛ ተገኛኝተን እንደ ወሬ ተነሳ እሱም ስለኦሮሞ ባሕልና የጥንቱ ሥርዓት ነበር፡፡ ጓደኞቼ የሄ ነው ይሄ አደልም እያሉ የጨቃጨቁ ገቡ፡፡ እኔ አዛ ከተሰበሰብነው ሁሉ የተሻለ ግንዛቤ ስለነበረኝ ስለታሪኩ እውነታነት መናገር ስጀምር አንድ የተሻለ ታሪኩን በጨረፍታ የሚያውቅ ጓደኛዬ እኔ እንዴት የዛን ያህል በጥልቀት እንዳወኩት ገርሞት ነበር፡፡ እኔ ግን እያወራሁ ያለሁት የነበረው ታሪክ ሳይሆን በአይኔ ያየሁትን የኖርኩበትን እስከዛ ጊዜም ድረስ እኔ በአደኩበት የሚታወቅ እውነት ነበር፡፡ ለቃለ መጠይቅ እስከምንጠራ ነበር በእነድነዚህ የመሳሰሉ ጉዳዮች ስንነጋገር የነበረው፡፡ ከዛ ፈታኞች መጡና ሰበሰብ አድርገውን ቃለመጠይቁ እንዴት እንደሚቀጥል ከመናገራቸው በፊት እያንዳንዳችንን በሥም እየጠሩ መኖር አለመኖራችንን ማረጋገጥ ነበረባቸውና ሥም መጥራት ጀመሩ፡፡ የሚጠራው እየጠራ መጥቶ እኔ ሥም ጋር ሲደርስ “ሠርፀ” የሚለወን መጥራት ግር ይለውና ጓደኞቼ አስተካከሉት ሰውየው በኦሮምኛ “ኩን ኢሞ ኤሳ ኑቲ ዱ(dhu)ፌ አለ ይሄ ደግሞ ከየት መጣብን ማለት ነው፡፡ ምንም ከክፉ አልወሰድኩትም እኔም ምክነያቱም ለብዙዎች ይህ ሥም ስለሚያስቸግር ሌላም ጊዜ ያስቸገራቸው ሰዎች የሚያሳዩት አይነት ከክፉ ያልሆነ ስሜት ስለመሰለኝ፡፡ ከዛ ተራዬ ይደርስና ገባሁ፡፡ የምቀጠረበት ሥራ በእርግጥ ኦሮምኛ ያን ያህል መሠረታዊ አደለም፡፡ ሌላ ቦታ ይህ ሥራ ቃለ መጠይቁ በኢንግሊዘኛ ነው፡፡ ስገባ ቃለ መጠይቁ በኦሮምኛ መሆኑ ብዙም አላስደነቀኝም፡፡ በእርግጥም ጠብቄው ነበር፡፡ ያስደነቀኝ ነገር ግን ቃለ መጠይቁ ራሱ ነው፡፡ ሥራው ከሙያ ጋር የተገናኘ ቢሆንም አንደም ከሙያው ጋር በተገናኘ የተጠየኩት ነገር አልነበረም፡፡ ሙሉ ለሙሉ ስለዘር ማንነቴ ነበር ቃለ መጠይቁ፡፡ ሥም ከእነአያት ተጠየቅሁ፡፡ በእርግጥም መናገር ነበረብኝና ተናገርኩ፡፡ ከዛስ አለኝ ጠያቂው፡፡ ያኔ ገባኝ እስኪ ትንሽ ከአያቴ በኋላ ስለማውቀው አንዱን ነገርኩት ከዛስ ጨመርኩለት፡፡ የእኔ ከአያቴ በኋላ ያለው ሥም ከእነጭርሱ ሰውዬው መስማት የማይፈልገው አይነት ነበር፡፡ ገረ ሐርማ ኬቲሆ አለኝ፡፡ በእናትህስ በኩል ማለቱ ነው፡፡ ይታያችሁ በቃ ቃለ መጠይቁ ይሄና ይሄው ብቻ ነበር፡፡ ስወጣ ቀድመው የገቡት ጓደኞቼ እነዳልተመጨኝ ገብቷቸዋል፡፡ የምጠላውን የዘር ነገር እንደተጠየቅሁ አውቀዋልና፡፡ እነሱም እንደዛው ነው የተጠየቁት ግን እነሱ ለሴውየው የሚስማማው ሥም ነው ያላቸው፡፡ የእኔ የቋንቋ ችሎታ ምንም አያስፈልግም ነበር፡፡ ቋንቋ ከመቻል ይልቅ አንድም ቃል ባልናገር ግን ሰውዬው የፈለገውን አይነት ሥም ቢኖረኝ በእርግጠኝነት ከተወዳደሩት ሁሉ በአንደኝነት እቀጠር ነበር፡፡ ለዛ ሥራ የትምህርት ወጤት ከፍተኛውን ድርሻ ስላለው እኔ ከተወዳደሩት የተሻለ ውጤት ነበረኝና፡፡ የሚፈለገው ቢያንስ 5 ሰው ነው ይመስለኛል፡፡  ከዛ ሁላችንም ተፈትነን ወደየመጣንበት ተመልሰን ውጤት ስንጠብቅ ውጤቱ ወጣ የሚል ወሬ ሰማወሁ፡፡ ያው ነገሩኝ ጓደኞቼ፡፡ ከተወዳደሩት ሁሉ የመጨሸው ዝርዝር ላይ ሥሜ መጻፉን፡፡ እኔ ውጤቱ ስነገር ሌላ ቦታ ተመሳሳይ ሥራ አግኝቼ  እዛ ሥራ ጀምሬ ነበር፡፡ እንዲህ ያለ ነገር የገጠማቸው በሺዎች ሳይሆኑ በሚሊዮኖች ነው፡፡ በግልጽ አንተ ወይም አንቺ እንዲህ ስለሆንከ/ስለሆንሽ አንቀጥርህም/ሽም የተባሉ ከገዛ ወንድሜ ጀምሮ መዓት ናቸው፡፡ እኔስ ቢያንስ በወረቀት ላይ ነው መጨረሻ የሆንኩት፡፡

ግን እኔም አልቀረልኝም ከዘመናት በኋላ አሁንም ሥም አልጠቅስም ግን በኦሮሚያ ውስጥ ሊንቀሳቀስ ያሰበ አንድ አክሲዮን ኑና ተመዝገብ በተለይ የኦሮሚያ ተወላጆች እያለ ማስታወቂያ ሰማሁና ከአንድ ሥሙ በጣም ጓደኛዬ ጋር አክሲዮኑ ወደሚሸጥበት ቦሌ መንገድ አንድ ሕንጻ ሄደን የመጣንበትን ነግረን ለመመዝገብ ተዘጋጀን፡፡ መታወቂያ አሉን በአጋጣሚ ሁለታችንም የያዝንው ፓስፖርት ነበርና የምታስተናግደን ልጅ የጓደኛዬን ፓስፖርት ተቀበለችው የእኔን ግን የቀበሌ መታወቂያ ከሌለህ አንቀበልም አለችኝ፡፡ ይን ብቻም ሳይሆን ገና ሥሜን ስታይ የሄማ የቀበሌ መታወቂያ የግድ ያስፈልገዋል አለች፡፡ ልብ በሉ ይሄ ንግድ እነግዳለሁ ብሎ አክሲዮን ገንዘብ የሚሰበስብ ነው፡፡ የገዛ ገንዘቤን እኮ ነው የምሰጠው፡፡ ኦሮሞ ነን የምትሉ ዛሬ ልጠይቃቸሁ!! ኦሮሞነት በዚህ ያህል ርቀት ሚሊዮኖች እንዳሳዘነ ትረዱታላችሁ?  እኔ ግን አዘንኩ አንጂ ዛሬም ቢሆን ቂም አልያዝኩም፡፡ የችግሩ ምንጭ የት እንደሆን አስውላለሁ፡፡ የአደኩበትን እሴቶች ሁሉ ከማጣቴም በላይ በዚህን ያህል ርቀት ነበር በማንነቴ ምክነያት እንዴት ሌሎች እንደሚጠሉኝ የታዘብኩት፡፡ ለእኔ ግን ዛሬም የሕሊና ነጻነት አለኝ አንድም የሚያሳፍር ነገር አልሰራሁም፡፡ የምናገረውም የምጽፈውም የችግሩን ሥር መስደድ በደንብ ስለማውቅ ነው፡፡ እስኪ መለስ ብላችሁ የጻፍኩትን አንብቡት፡፡ ዛሬ እነ አብይና ለማን እኮ እኔ የምረዳቸው ስለተናገሩ አደለም ገና ሳይናገሩ የሚገቡኝ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ አሁንም ምን ያህል ሸከም እንዳለባቸው እረዳለሁ፡፡ ይህን የምለው እንደው ራሴን ምሳሌ ላድርግ ብዬ እንጂ ሌሎች ብዙዎች ከእኔ በላይ ሆነዋል፡፡ እኔ ልዑል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን ምንም አልጎደለብኝ፡፡ ግን የምርም ተቸግሮ ሥራም የሁን ወይም ሌላ አገልግሎት ፈልጎ በማንነቱ በመገለሉ ለሌላ ችግር የተዳረገውን አስባለሁ፡፡ በራስ ሊያደርጉብህ የማትፈልገውን በሌሎች አታድርግ የሚለውን ሁሉም ያነበንበዋል፡፡

ለአብይና ለማ እኔ ሌላ ቦታ ያለውን ችግር ስለማላውቅ ይሆናል ግን ኦሮሚያ ውስጥ ያለው ችግር ብዙ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ በእርግጥም አሁን ራሱ ሳይ ሌሎች ቦታዎች አነስም በዛም በለውጡ ተደስተው ሊመጣ ያውን በተስፋ እየተጠባበቁም ወደዛውም እያመሩ ነው፡፡ ይሄ ግን ኦሮሚያ ውስጥ እየሆነ አደለም፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ያላችሁትን እናንትነ ጨምሮ ሌሎችንም በኢትጵያዊነታቸው ብቻ እንዲታዮ የሚጥሩትን ከዚሁ ማሕበረሰብ የሆናችሁትን ሳይቀር ለማጥፋት ስንት ሴራ እየተሴረ ያለው እንደተባለው ከወያኔ  አደለም፡፡ ወያኔ ቢኖርበትም በዋናነት ኦሮሞ ነን ከሚሉ ነው፡፡ የመረጃውን ጭብጥ እስካሁን አልገባኝም ግን ሰሞኑን በታዬ ደንደኣ ላይ ጥቃት ተሞከረ የሚል ሰማሁ፡፡ በእኔ ትርጉም ታዬ ኦሮሞ መሆን አለመሆኑ ሳይሆን ኢትዮጵያዊና ፍትሀዊ መሆኑ ለራሱም አደጋ እንደሆነበት ነው የሚገባኝ፡፡ ይሄን ልጅ በየትኘው የዩኒቨርሲቲ በሉት ሌላ የአእምሮ ብክለት በሚፈጸምባቸው የዘረኝነትና የጥላቻ ተቋማት ቢያልፍም ከልጅነቱ የወጣበት አስተዳደጉ ጉልበት ሆኖት ዛሬ እውነትን፣ ኢትዮጵያዊነትን ፊት ለፊት ይዞ የወጣ እንደሆነ ብዙዎቻችን ይገባናል፡፡ ገብረ ጉራቻ መወለድና አንድ አይነት ማህበረሰብ ብቻ ከአለበት መወለድ ይለያያል፡፡  አብይ ዛሬ ወጣቶች በየክልሉ እየሄዱ በጎ ሥራ እንዲሰሩ እያልክ ነው፡፡ ጥሩ ሀሳብ ነው፡፡ እስኪ ትንሽ እንኳን ሌላውንም ማየት ቢቻል፡፡

አብይ አሁን አልናገረውም ግን ከላይ በጠቀስኩት መልክ ለአገር አስተዋጽዖ ማድረግ ያልቻልን ብዙዎች አለን፡፡ ሀሳብ ብናመጣ ማን ይቀበለናል፡፡ አሁንም የእናንተን ወደፊት መምጣት በተቻለን መጠን ሁሉ ለማጉላት እየሞከርን ነው፡፡ ይህን ችግራችን በአስቸኳ ከፈታን እኔም ሆንኩ ጓደኞቼ በሙያችን አገርን ሊቀይሩ የሚችሉ ሀሳቦች አሉን፡፡ ኢትዮጵያ እንደተባለው ነው፡፡ ለምለሚቷ አገሬ የሚለውን ዛሬ እንደሚሳለቁበት አደለም፡፡ እውነትም ነበር፡፡ እኛ ነን ሲዖል ያደረግናንት፡፡ ረሀብና ችግርን ብዙዎች አልፈውበታል ግን አልተለማመዱትም፡፡ የእኛዋ አገር ኢትዮጵያ በሚገርም ሁኔታ ብዙዎች የጻፉላት ነች፡፡ በብዝሀ ሕይወት ከአለም 7 አገሮች አንዷ መሆኗ ብቻም ሳይሆን እንደነ ቫቪሎቭን የመሳሰሉ አሳሾች እጅግ ያስደመማቸው የብዝሃነት በውሱን ቦታ ታጭቆ መኖሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአፍርካን ከፍተኛ ቦታዎች ቢያንስ ከ60 በመቶ የሚሆነውን የያዘች፣ ከዳሎል እሰክ ራስዳሽን በአለው አጭር ርቀት ላይ ዓለም ላይ ሊኖሩ የሚችሉ ስነፍጥረትን መያዝ የሚያስችል አቅም ያለው ስነምድር ነች፡፡ ይህ ለእኛ አይገባንም፡፡ የእኛ የሆነውን ሁሉ ዛሬ አለም በስነሕይወት ባንኮቻቸው ይዘው እናያለን፡፡ የእኛ የሆኑት ለብዙዎች እንዳይራቡ ዋስትና ሆነዋል፡፡ ቢያንስ የቀድሞው የአሜሪካ ምክትል ፕሬዘደንት የነበሩት አልጎር ስለ ኢትዮጵያ መናገር ነበረባቸውና እዲህ ነበር ያሉት አንዲት ከኢትዮጵያ የተወሰደች የገብስ ፍሬ ዛሬ አጠቃላይ የካሊፎረኒያን 160ሚሊየን ዶላራ የገብስ ምርትን ከቢጫው አቀንጭር ቫይረስ ታድጋለች ይላል ኧርዝ ኢን ዚ ባላንስ በተሰኘው መጻፉ፡፡  በአንድ ወቀት እኔ አንተ እንደነበርክ የዛን ጊዜ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አላውቅም ግን ከሆነ ሰው ጋር አንድ ትልቅ ሀሳብ ይዘን መጥተን ግን ልናገኝህ አልቻልንም፡፡ ዛሬ እንደውም የተሻለ ቦታ ስለሆንክ ተመልሰን እንመጣ ይሆናል፡፡ ግን ለእንደነዚህ ያሉ ሀሳቦች ከላይ በጠቀስኩት አይነት መስተንግዶ የሚቀበሉን እያሉ አይሞከርም፡፡

ማየት የተሳነን ነን እኛ፡፡ ዛሬ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከአብዲ ኢሌ ጋር በተያያዘ በሩ ላይ ያለውን ጽሁፍ ሳይ ድሮም ይገርመኝ የነበረውን እንደገና አስታወሰኝ፡፡ ፅሑፉ በሰማያዊ መደብ ላይ በነጭ የተጻፈ ነው፡፡ ከላይ መስታወት አለው በማታ እንዲታይ የፈሎረሰነት መብራት ተገጥሞለት ነበር፡፡ ግን መስታወቱ ተሰብሯል ፈሎረሰንቱም የሚሰራ አልመሰለኝም፡፡ አስቂኙ ነገር ይሄ የሆነው ከዓመታት በፊት ነው፡፡ አንድ የፌደራል መስሪያ ቤት ሊያውም የፍትህ መስሪያ ቤት ይችን የምታክል ቀላል ነገር እንኳን ኃላፊነት ተሰምቶት ቢያስ ለአይን እይታ ሲባል ማስተካከል እንኳን አለመቻሉ እንደው እንደመሳሌ ልጠቁምህ ነው፡፡ የእኛ ነገር እንዲህ ነው፡፡ አብይ ሆይ እስኪ ዱባይም አሜሪካም ሌሎች አገሮችም ሄደሃል እንዲህ ባለ ዝርክርክነት ለመሆኑ አገር አገር ሆና ትቀጥላለች፡፡ በሆነ ወቅት የሆነ የሚዘረፍ ብር ሲገኝ የማይሰራው ሁሉ ይሰራል ከዛ በቃ አይደለም የማስታወቂያ ጽሁፍ ሕንጻ ቢፈርስ እዛው ፍርስራሹ ውስጥ እንደተለመደው ይቀጥላል እንጂ ልጠግን አይባልም፡፡ ይቺ ለምሳሌ ያነሳኋትና በጣም ቀላሏ ነች፡፡ ከዛ ያለፈውማ ….! የምናገረውን አንተ ትረዳዋለህ ብዬ ነው፡፡ ለሌሎች የሥራፈትና የአጉል ዘመናዊ ልበል ባይነት ሲለሚመስላቸው አይገባቸውም፡፡ አጥሩን እስከዘማይ እጥሮ ከግቢ ሲወጣ ደጁ ላይ ያለ ቆሻሻ የማያስጠይፈው ዘመናዊ ነኝ ባይ ሀብታም በዘመነባት አገር ማለቴ ነው፡፡ ስለ ሀሳቤ እድሉን ከአገኘው አንድ ቀን እንነጋገር ይሆናል፡፡ ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያን ከአደጉት አገሮች ተርታ ለማሰለፍ 20 የተሳኩ ዓመታት በቂ ናቸው! እውነት ነው! ትንሽ በትክክል ብንጀመረው ይገባናል!  ግን የተለክፍንበትን ልክፍት መድሀኒት እንፈልጋል! የምንጸልዮ አባቶችና እናቶች ከአላችሁ እባካችሁ ለትላልቅ ሀሳብ ላላቸው ጸልዩ፡፡

ልዑል አምላክ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ! አሜን!

ሰርፀ ደስታ