31 ኦገስት 2018

ጎረቤት ሃገር ኬንያ መዲና ናይሮቢ ነዋሪነቱን ያደረገው ሄኖክ አበራ ዘመድ ጥየቃ ወደ ተወለደባት አዲስ አበባ ከማምራቱ በፊት የሚያደርገው አንድ ነገር አለ፤ የኬንያ ሽንግልን ወደ ዶላር መቀየር።
«ናይሮቢ ውስጥ ዶላር መግዛትም ሆነ መሸጥ እጀግ በጣም የቀለለ ነው፤ ሊያውም በሕጋዊ መንገድ። እኔ አዲሳ’ባ ላይ ዶላሩን ሞቅ ባለ ዋጋ ስለምሸጠው አዋጭ ነው» ይላል ሄኖክ።
«ማድረግ ያለብህ መታወቂያህን ወይም ፓስፖርትህን ይዘህ ለውጭ ምንዛሪ ወደተዘጋጁ ወርደ ጠባብ ሱቆች መሄድ ብቻ ነው።»
በእርግጥም ናይሮቢ ውስጥ በሕጋዊ መንገድ በፍጥነት ከሚከናወኑ ተግባራት አንዱ ዶላር መግዛት እና መሸጥ ነው፤ ከአዲስ አበባ እጅጉን በተለየ መልኩ።
• ”የጫት ንግድና የዶላር ጥቁር ገበያ. . .ለግጭቶች ምክንያት ሆነዋል”
በኢትዮጵያ ሕጋዊ ባልሆነው የውጭ ምንዛሬ ገበያ ወይም ጥቁር ገበያ የዶላር ዋጋ ማሽቆልቆላ ማሳየት ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል።
ከሰሞኑ ደግሞ መንግሥት ጥቁር ገበያ ላይ ሲያገበያዩ የተገኙ ሱቆችን እንዲሁም ሲያሻሽጡ ነበሩ ያላቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ተያይዞታል።
ኢትዮጵያ ሆቴል አካባቢ በሰፊው ይንቀሳቀሱ የነበሩ የጥቁር ገበያ የደራባቸው አልባሳት መሸጫ ሱቆችም ‘ታሽጓል’ በሚል ምክልት ዝምት ለብሰው ታይተዋል።

እውን ጥቁር ገበያውን ማሸግ ዘለቄታዊ መፍሄ ነው?
የምጣኔ ሃብት ባለሙያ የሆኑት ዶክተር አየለ ገላን «ጥቁር ገበያ ሊሠራ የማይችል ነገር እንዲሠራ ያደርጋል፤ ወደ ሃገር ቤት የሚገቡ የካፒታልም ሆነ የጥሬ ዕቃ አቅርቦቶች የተሳኩ እንዲሆኑ ያደርጋል፤ ግለሰቦች ኢኮኖሚያዊ ችግራቸውን እንዲቀርፉ ያደርጋል። ለዚህ ነው ጥቁር ገበያው የሚጫወተው ሚና ቀላል አይደለም የምንለው» ሲሉ ባለሙያው ያስረዳሉ።
«መንግሥት ጥቁር ገበያውን ሲዘጋ ሰዎች አማራጭ በማጣት ወደ ባንክ በመሄድ በኦፌሴላዊ መንገድ ይገበያያሉ የሚል እምነት አለው። ነገር ግን ጥቁር ገበያውን በእንዲህ ዓይነት መልኩ መግታት ይቻላል የሚል እምነት የለኝም።»
«ዞሮ ዞሮ. . .» ይላሉ ዶክተር አየለ «ዞሮ ዞሮ ዶላሩ የሚመጣው ከውጭ ሃገር ነው። ሰዎች ካስፈለጋቸው ሕጋዊ መንገድ ሳይጠቀሙ ዶላሩን ብሩን በሰው በሰው ማዘዋወር ይችላሉ። ወጣም ወረደ በእንዲህ ዓይነት መልኩ ጥቁር ገበያውን ማሸነፍ አይቻልም።»
ዶ/ር አየለ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችም መንግሥት ጥቁር ገበያውን በመሰል መልኩ ማሸነፍ እንደማይችል ሃሰብ እየሰነዘሩ ነው።
የማክሮ እና ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚክስ ባለሙያ የሆኑት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ ጥቁር ገበያው የሚሸፍነውን ክፍተት መደበኛው ገበያ ሊሸፍነው አይችልም ሲሉ በትዊተር ገፃቸው ፅፈዋል።

ወደ መፍትሄው. . .
አሁን ትልቁን ጥያቄ ማንሳት ይቻላል። መንግሥት ጥቁር ገበያውን እንዴት ማሸነፍ ይችላል።
«የመንግሥት ፖሊሲ አውጭዎች ማሸነፍ የማይችሉትን ጦርነት ከመጀመር እንዴት ባለ ፖሊሲ ነው ጥቁር ገበያውን ማስወገድ የሚቻለው የሚለው ላይ ማተኮር አለባቸው» በላመት ዶክተር አየለ ይተንትናሉ።
«ይህ የሮኬት ሳይንስ አይደለም፤ ሌሎች ሃገራት አድርገውታል። ኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ ዶላር ያስፈልጋታል፤ የዶላር እጥረት አለ። እንዲህ ባለ አስቸጋሪ ወቅት ከበድ ያለ እርምጃ መውሰድ ሊያስፈልግ ግድ ይላል።»
ዶክተር አየለ እንደ መፍትሄ የሚያቀርቡት ‘መልቲፕል ኤክስጄንጅ ሬት’ የተሰኘውን ሃሳብ ነው።
«’መልቲፕል ኤክስጄንጅ ሬት’ ማለት ለተወሰነ ጉዳዮች ቋሚ የሆኑ የውጭ ምንዛሪ ዋጋን መጠቀም፤ ለምሳሌ ዕቃ ከውጭ ለሚያስመጡ እና ለሚልኩ። ጥሬ ገንዘብ ወደ ሃገር ቤት በሚገባበት ጊዜ ደግሞ ለእሱ የተለየ ምንዛሬ መጠቀም ይቻላል።»
ሁለት የተለያዩ የውጭ ምንዛሬ ዋጋዎችን መጠቀም አስቸጋሪ አይሆንም ወይ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ባለሙያው ሲመልሱ፤
«ይሄ እኮ አዲስ ነገር አይደለም» ይላሉ። «እንዲህ ባለ አስቸጋሪ ጊዜ ‘መልቲፕል ኤክስጄንጅ ሬት’ን መጠቀም ይፈቀዳል፤ ሌሎች ሃገራትም አድርገውታል፤ ነገር ግን ይህ ለተወሰነ ጊዜ የሚሆን እንጂ ለዘለቄታው አይደለም።»
ዶክተር አየለ ትንታኔያቸውን ሲቀጥሉ «በፍላጎት እና አቅርቦት ላይ የተመረኮዘ የገንዘብ ፍሰት ከተከናወነ ጥቁር ገበያው ቢያንስ እንዲህ እንደ አሁኑ አይንሰራፋም።»
ዶክተር አየለም ሆነ ፕሮፌሰር አለማየሁ በአንድ ጉዳይ የተስማሙ ይመስላል፤ መንግሥት የተሻለ የምጣኔ ፖሊሲ እንደሚያስፈልገው።
ዶክተር አየለ «መንግሥት ፈጠራ የተሞላቸው የምጣኔ ሃብት ፖሊሲዎችን በመቅረፅ ሊጠመድ እንጂ ከጥቁር ገበያው ጋር ትንቅንቅ ውስጥ ሊገባ አይገባም» በማለት ሃሳባቸውን ይቋጫሉ።