ከአመልማል አንዳርጌ ፌስቡክ ገፅ
በአቶ በረከት ላይ ብዙ አሉታዊ ትችቶች ቀርበዋል፡፡ እኔም የአቅሜን ተችቻለሁ፡፡ ሳስበው ግን ስህተት ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ በረከት የሚያስበው በራሱ ልክ ነው፡፡ ዓለምን የሚመለከተው በደደቢት መነጽር ነው፡፡ በእሱ ቤት ዓለምም—ኢትዮጵያም– የኢትዮጵያ ህዝብም ያኔ ከጫካ ሲገቡ እንደ ነበሩ ያሉ ይመስለዋል፡፡ ይኸ ደግሞ መታመም ነው –እብደት፡፡ ለሩብ ምዕተ ዓመት የገዛው በግፍ፣ በቅጥፈት፣ በማምታታ፣ በተንኮልና በሴራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያውቅ አልመሰለውም፡፡ በሽተኛ ሰለሆነ፡፡ እንኳን እኛ የገፈቱ ቀማሾች ይቅርና አና ጉሚዝ እንኳ  ጠንቅቃ ታውቃለች፡፡ በሽተኛ አእምሮ ትክክለኛ ነገር እንዲያስብ መጠበቅ የለብንም፡፡ የአእምሮ በሽተኛ ቦታው አማኑኤል ነው፡፡ ወንጀለኛም ፍርዱን አግኝቶ ቦታው ወህኒ ቤት ነው፡፡ በረከት መወሰድ ያለበት ከነዚህ ቦታዎች ነው፡፡
ከእንግዲህ የበረከት ጉዳይ አጀንዳችን ሊሆን አይገባም፡፡ ወደ አንገብጋቢው የሀገራችን ጉዳይ እንግባ፡፡ ኢትዮጵያችን እንዴት እንደምታድግ– ጸጥታዋ እንዴት እንደሚጠበቅ– የቀን ጅቦች እንዳይበሉን እንዴት በጋራ መከላከል እንዳለብን— እስከዛሬ በመለያየታችን የጅብ መጫወቻ መሆናችንን ተረድተን በመቻቻልና በመተሳሰብ እንዴት ከጅቦች ጨርሶ ነጻ እንደምንወጣ— ሕብረ ብሔር ድርጅቶችም ሆኑ የብሔር ድርጅቶች እንዴት የሕዝብ ተገዥ ሆነው ሕዝቡን ማገልገል እንዳለባቸው– የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ የአንድነታችን እንጂ የልዩነታችን ምክንያቶች ሆነው እንደፈረስ እንዳይጋልቡን እንዴት ልጓም እንደምናበጅላቸውና እንደምንቆጣጣራቸው– በአጠቃላይ አሁን ያለው መንግሥትም ሆነ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ የሕዝብ አገልጋይና ተገዥ መሆናቸውን በመወያየት፣ በመነጋገር፣ በመተባበርና በመተሳሰብ ማሳወቅ ማቻል አለብን፡፡ ሕዝብ ዝም ብሎ ለተቃውሞ የሚወጣና የአምባገነኖች የጥይት ራት የሚሆን ብቻ አይደለም፡፡ የፈለገውን የሚሾም ያልፈለገውን ከስልጣን የሚያወርድ እንጂ፡፡ ሰለሆነም ለሕዝብ ለልዕልናና ለሀገር አንድነት ስንል ባለን አቅም ሁሉ ተግተን መሥራት ያለን ጊዜው አሁን ነው!!