ነሐሴ 30 ቀን 2010 ዓም(05-09-2018)

ኢትዮጵያ አገር ናት፣ኢትዮጵያ የሚለው መጠሪያ ስሟ በተለያዬ የታሪክ ጸሃፊዎች የተለያዬ ትንተና ቀርቧል። በግሪኮች በኩል ኢትዮጵያ ማለት ፊቱ የተለበለበ(የጠዬመ ወይም የጠቆረ ሰው)ማለት ሲሆን መሬቷም በዛው ነዋሪ ሕዝብ ስያሜ መሰየሙን ያስረዳሉ።በቅርቡ በፕሮፌሶር ፍቅሬ ቶሎሳ በኩል ደግሞ የካህኑ መልከጻድቅ ልጅ የሆነው ኢትዮጲስ የተባለው ባለሥልጣን አካባቢውን ያስተዳድር ስለነበረ ከባቢውና የአሁኗ ኢትዮጵያ በስሙ ለመጠራት እንደበቃች ባቀረቡት መጽሃፍ ላይ ገልጸዋል።

የአንድ ከባቢም ሆነ የግለሰብ ስም በታሪክ አጋጣሚ በሚከሰት ክስተት ሊወጣ እንደሚችል በተለያዩ ቦታዎችና አገሮች ስያሜ ለማወቅ ይቻላል።ስም ወጥቶለት የተፈጠረ አካባቢ ወይም የሰው ልጅም ሆነ እንስሳና እጽዋት የለም።በዓለማችን ላይ ላሉት ህይወት ያላቸውንና የሌላቸውን ፍጥረታት፣አካባቢዎች፣ተራሮችና ወንዞችን ስም እያወጣ እንዲለዩና እንዲታወቁ ያደረጋቸው የሰው ልጅ ነው።

የአሁኗ አሜሪካ አሜሪካ ከመባሏ በፊት ፌስፑቺ የተባለው ጣልያናዊ አገር አሳሽ በደቡብ አሜሪካ ጉዞው እንደሰንሰለት የተያያዘውን በቀይ ህንዶች አሜሪጎ ተብሎ የሚጠራውን ተራራ መነሻ በማድረግ አሰሳውን ቀጥሎ የደረሰበትን የአሁኑን አሜሪካ በተራራው ስም እንደሰዬመውና የራሱንም ስም በዚያው አሜሪጎ ፌስፑቺ ተብሎ እንዲጠራ ማድረጉን ከታሪክ ጸሓፊዎች ለማወቅ ተችሏል።የአሁኑም ካናዳ በነዋሪዎቹ የቀይ ሕንዶች ካናታ ማለትም መንደር ከሚለው ቃል የመጣ መሆኑ ታሪክ ይመሰክራል።

ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስ ለልዩ ልዩ ቦታዎች ፣ወንዞችና ተራሮች ስያሜ በዚያው መልክ በነባሩ ሕዝብ ወይም ከጊዜ በዃላ በሰፈሩ ሰዎች ቋንቋ አጠራር መሰዬማቸውን ታሪካችን ያረጋግጣል።ለምሳሌ ያህል የወሎና በወሎ ውስጥ ያሉ አንዳንድ አውራጃዎችና ወረዳዎች ለምሳሌም ወረባቦ፣ወረኢሉ፣ወረሂመኖ፣ቦረና፣ወረባቦ…ወዘተ ከግራኝ መሃመድ ዘመቻ ጋር በተያያዘ የሕዝብ አሰፋፈር ተከትሎ የተቀዬረ ለመሆኑ ብዙ አመላካቾች አሉ።በዚሁ ወቅት ከደቡብና ከምስራቅ ተነስቶ ወደ ሰሜኑና መሃል የአገሪቱ ክፍል የፈለሰው የኦሮሞና የሶማሌ ዘማች ኑዋሪውን አሸንፎ ቦታውን በመንጠቅ የሰፈረበትን አካባቢ በራሱ ስያሜ እንደጠራና ስያሜው በሌሎቹ ተቀባይነት አግኝቶ እስከዛሬ ድረስ የቦታዎች መጠሪያ ሆኖ መቅረቱንና ሰያሚውም ከነባሩ ሕዝብ ጋር ተዋህዶ በሰላም እንደኖረ ታሪክ ይመሰክራል።በሌላዎቹም አካባቢዎች እንዲሁ በተመሳሳይ መልኩ የስም ለውጥ እንደተካሄደና ሕዝቡ በሰላም አብሮ እንደኖረ አይካድም።

የብዙ አገሮችን አመሰራረት ስንመረምር የትኛውም አገር በሰላም የተመሰረተ ሳይሆን በብዙ ውጣውረድና ግጭት ብሎም የእርስበርስ ጦርነት ተካሂዶበት ነው።በክልል ተነጣጥሎ የኖረ ሕዝብን አሰባስቦ በአንድ ትልቅ አገራዊ ዜግነት ለማስተሳሰር ቆራጥነትን፣ብልህነትንና አርቆ አሳቢነትን ይጠይቃል።ከዚያ አንሶ መገኘትና ከሌላው ተነጥሎ ለመኖር መጣር የድክመትና የአውሬነት ጸባይ ነው።ሁሉም የተዋደቀለትን ኢትዮጵያዊነትን መካድና መቃወም የራስን ማንነት መካድና ዝቅተኝነትን ማስተናገድ ይሆናል።እንደሰው የሚያስብ ፍጡር እንኳንስ ለዘመናት አብሮ ለኖረው ወገኑ ቀርቶ ለማያውቀው ለሩቁ የሰው ልጆች ሁሉ ሰላምና መልካም ኑሮ ይጨነቃል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሁሉም ዜጋ ሁሉም ዜጋ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ማሰብና መጨነቅ ይገባዋል።

አንድ አገር ለሚጠራበት ስያሜ ምክንያቱን በትንሹ ለመግለጽ የተሞከረው በአሁኑ ጊዜ አገራችን ኢትዮጵያ የአንድ ጎሳ ማለትም አማራው ብቻውን የፈጠራት አገር እንዳልሆነችና ኢትዮጵያዊ ማለትም አማራ ጎሳ ማለት እንዳልሆነ ለማሳዬት ነው።በሌሎቹ አገሮች የተለያዩ ጎሳዎች እንደሚኖሩ ሁሉ በኢትዮጵያም የተለያዩ ጎሳዎች ኖረዋል፣ ይኖራሉም።የሚያስተሳስራቸውና አንድ የሚያደርጋቸው የሚኖሩበት አገር የወል መሆኑና የጋራ የሆነ የዜግነት ማንነታቸው ነው።አሜሪካ ወይም በሌሎቹ አገሮች የሚኖሩ የተለያዬ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች በቋንቋቸው አንጻር የተለዬ ዜግነት የላቸውም። በኖሩበት የጊዜ መጠን በሕግ የሚኖሩበት አገር ዜጎች የመሆን መብት አላቸው። በሚናገሩት ቋንቋ ተዋረድ አገር መስርተው ሊኖሩበት የሚያስችላቸው መብት የላቸውም።ሕጉ ያገሪቱን አንድነት የሚያስከብር ነው።ያንን የተቀበለ ሁሉ ተከብሮ ይኖራል።በቋንቋ ተዋረድ አገር ይመስረት ቢባልማ ኖሮ የተባበሩት መንግሥታት ሳይቀር ለቁጥር የሚያዳግቱ አገሮች ስብስብ ይሆንና ለግንኙነት ከማዳገቱም በላይ የግጭት መድረክ ይሆን ነበር።አሁንም ቢሆን የጥቅም ግጭት ከሚካሄድበት መድረክነት አልወጣም።

ኢትዮጵያዊነት የጋራ የሆነ የወል መጠሪያ ነው።ኢትዮጵያም የምትባለዋ አገር ከየትም ይምጣ ከዬትም ፣መቼም ይሁን መቼም ስሟ ከመውጣቱ በፊትና በዃላ የሰው ልጅ የሚኖርባት በአፍሪካ ክፍለዓለም ውስጥ የምትገኝ ፣ በሂደት አንድ ጊዜ ሲሰፋ ሌላ ጊዜ ሲጠብ የኖረ የራሷ ድንበር ያላት አንድ ነጻ አገር ናት።ይህች አገር የተለያዬ ቋንቋ የሚናገሩ፣የተለያዬ እምነት የሚከተሉና የተለያዬ ባህልና ልማድ ያላቸው ሰዎች በጋራ የኖሩባትና የሚኖሩባት አገር ናት።

ጎሳና አገር በእኩል ደረጃ የሚታዩ ሳይሆን፣ አገር ለሚኖሩባት ለተለያዩ የጎሳ ተወላጆች ሁሉ የጋራ ቤቱና ንብረቱ ናት።አብሮ ከመኖር ሂደት በሚያደርገው መቀራረብና መስተጋብር በራሱ ፈቃድ ሳይገደድ አንዱ የሌላውን ቋንቋ እንዲለምደውና እንዲናገረው ኑሮው ያስገድደዋል። ባህልና እምነቱንም ይጋራል።በታሪክ አጋጣሚ የአንዱ ጎሳ ቋንቋ የበላይነቱን አግኝቶ የሁሉም መነጋገሪያ መሆኑ የጭቆና፣ የበታችነትና የበላይነት ያመጣው ጣጣ ተደርጎ መታዬት አይኖርበትም።ሰው በሄደበት ቦታ መስሎ ለማደርና ለመግባባት ሲል የከባቢውን ቋንቋ መልመዱ የኑሮ ግዴታ ነው።በፈረንጅ አገር ፣በአረብ አገር በሌላውም አገር ስንኖር የዚያኑ አገር ሕዝብ ቋንቋ መቻሉ ይጠቅማል እንጂ ጉዳት የለውም፣ጉዳቱ አለማወቁ ነው።ዓለም እየጠበበች ስትመጣና የሕዝብ መቀራረብ ድንበር የለሽ ሲሆን የሚግባባበት አንድ ቋንቋ የበላይነት እንደሚኖረው አያጠራጥርም።አሁን በማንኛውም የዓለም ክፍል እንግሊዝኛ ቋንቋ የበላይነቱን እንደያዘ አይካድም።ምንም እንኳን በእንግሊዞች የቅኝ አገዛዝ የተስፋፋ መሆኑ ባይካድም አሁን ያ ዘመን በሌለበት ዓለም ውስጥ እየኖሩ ቋንቋውን ፈርጆ ላለመናገርና ምንም የማያውቀውን የአሁኑን እንግሊዛዊ ትውልድ ከቀድሞው የእንግሊዞች ታሪክ ጋር እያያያዙ መጥላት ትልቅ ጥፋት ከመሆኑም በላይ ዃላ ቀርነት ነው። መታዬት ያለበት የቋንቋው ጥቅምና የሰው ልጆች ወይም የትውልዱ አስተሳሰብ ነው።

በአገራችን የሌላው ጎሳ ተወላጅ የአማርኛን ቋንቋ መናገሩ የጎሳ ማንነቱን ጥሎ የቋንቋው ባለቤት የሆነውን የአማራ ጎሳ መሆን አይደለም። ለጉዳትና ለጭቆናም መጋለጥ አይደለም፤የተለያዩ ቋንቋዎች ተናጋሪ መሆን ይበልጥ በሌላውም ቦታ እንደልብ ተንቀሳቅሶ ለመኖርና ለመስራት የሚረዳ ችሎታ ነው።ከሁሉም በላይ አማርኛን መናገር የሚያኮራው ኢትዮጵያዊ የሆነ የራሱ ፊደል መኖሩ ነው።ሌሎቹ ያፍሪካ አገሮች በነጮች የላቲን ፊደል ሲጠቀሙ ኢትዮጵያውያን ለዚያ የበታችነት አለመጋለጣችን ሊያኮራን ይገባል።የመፍጠር ችሎታችንንም ያረጋግጣል።

በሌላውም ቦታ የሚኖረው የተለያዬ ጎሳ ተወላጅ የሚኖርበትን አካባቢ ቋንቋ መናገሩ ይበልጥ ይጠቅመዋል እንጂ አይጎዳውም።ሁሉም ተገዶ ሳይሆን ወዶ የሚመርጠውን ቋንቋ ቢማር ይጠቀማል እንጂ አይጎዳም።ኢትዮጵያዊነት ትልቅነትን፣የወልነትን፣የብዛትን፣ የአንድነትን የሚያሳይ ክቡርና መከበሪያ ማንነት፣የመደመራችን ውጤት እንጂ የሚያሳፍር የቅኝ ግዛት ስያሜ አይደለም።የሚያሳፍረው በጎሰኝነት አስተሳሰብ ተቀፍድዶና ቀጭጮ መቅረት ነው።

ለተለያዩ ጎሳዎች ጋሻና መከታ፣መኖሪያና መታፈሪያ የሆነችው፣የሁሉም ጎሳ ተወላጅ በከፈለው ድርሻ የተመሰረተችው ኢትዮጵያና የሁላችንም መታወቂያችን የሆነው ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም ይኑር!

አገሬ አዲስ