
በቅርቡ ኤልቲቪ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀ መንበር ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ከቤተልሄም ታፈሰ ጋር ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ለቴሌቭዥን ጣቢያው ማስጠንቀቂያ እንደሰጠ በማህበራዊ ሚዲያ እየተነገረ ነው።
የኤልቲቪ የሰው ኃይል አስተዳደር አዲስ ብርሃኑ ግን ማስጠንቀቂያ እንዳልተሰጣቸው ለቢቢሲ በመግለፅ፤ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ከሚዲያዎች ጋር ተደርጎ በነበረው የመገማገሚያ ውይይት ቃለ መጠይቁ ተነስቶ “ካለው የፖለቲካ ሁኔታ ጋር የማይጣጣምና ሁኔታውንም የሚያጋግል ስለሆነ ትክክል አይደለም” የሚል አስተያየት እንደተሰጣቸው ገልፀዋል።
ስብሰባው ላይ ተገኝተው እንደነበር የሚናገሩት አዲስ ኤልቲቪን ለብቻ ጠርቶ ማስጠንቀቂያ የሰጠ አካል እንደሌለ ገልፀዋል።
ጉዳዩን እንደ ማስጠንቀቂያ እንደማይወስዱት የተናገሩት አዲስ ቃለ-መጠይቁ ከማህበራዊ ሚዲያ ላይ የወረደበት ምክንያት ከብሮድካስት ባለስልጣን አስተያየት ጋር የተገናኘ አይደለም ብለዋል።
“ከማህበራዊ ሚዲያ ላይ ቃለመጠይቁን ያወረድነው በራሳችን ፈቃድ ነው። ጋዜጠኛዋን የግል ህይወት የሚነካና ስድብ ስለበዛ ጉዳዩን ለማቀዝቀዝ አውርደነዋል።” ብለዋል።
በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ስራ እንደለቀቀች ተደርጎ የሚነገረውም ፍፁም እውነት እንዳልሆነ ተናግረዋል።
ምንጭ:- BBC/Amharic