June 8, 2018
ከሁለት ቀን በፊት የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የአልጄርስ ስምምነትን ለመቀበል ያሳለፈውን ውሳኔ አስመልክቶ የትግራይ ልሂቃን በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰጡትን ሃሳብና አስተያየት ስመለከት በጣም ግርም ብሎኛል። ከዓረና ትግራይ እስከ የህወሓት/ኢህአዴግ ደጋፊዎች፣ እንዲሁም “ገለልተኛ” ነን የሚሉት ልሂቃን በውሳኔው ዙሪያ ተመሳሳይ አቋም በማንፀባረቅ ላይ ናቸው። በአጠቃላይ አብዛኞቹ የትግራይ ልሂቃን የአልጄርስ ስምምነትን መቀበል “የኢትዮጲያን መሬትና ሉዓላዊነት አሳልፎ መስጠት” እንደሆነ ይገልፃሉ።
ከዚህ በተጨማሪ የአማራ፥ ኦሮሞና ሌሎች ብሔር ተወላጅ የሆኑ ልሂቃን የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባሳለፈው ውሳኔ ዙሪያ ቅሬታና ተቃውሟቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ። ነገር ግን፣ ከትግራይ ተወላጆች በስተቀር አብዛኞቹ ልሂቃን በዋናነት ለችግሩ ተጠያቂ የሚያደርጉት፤ አንደኛ፡- በአልጄርስ ስምምነት ላይ ፊርማቸውን ያኖሩትን የቀደሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊን፣ ሁለተኛ፡- በወቅቱ የትግራይ ክልል ፕረዜዳንት የነበሩትና የዓረና ፓርቲ መስራች የሆኑትን አቶ ገብሩ አስራትን፣ ሦስተኛ፡- በወቅቱ የኢትዮጲያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩትና ሄግ የሚገኘው ዓለም-አቀፍ ፍርድ ቤት “ባድመን ለኢትዮጲያ ተወሰነ” የሚለውን “ነጭ ውሸት” የዋሹት አምባሳደር ስዩም መስፍን፣ አራተኛ፡- በተጠቀሱት የህወሓት ባለስልጣናት የተፈረመውን ስምምነት የተቀበሉት ጠ/ሚ አብይ አህመድን ነው።
የትግራይ ልሂቃን ግን ከሁሉም በተለየ የመለስ ዜናዊ፥ የገብሩ አስራት እና የስዩም መስፍንን ስም ሲጠሩ አይስተዋልም። በመሆኑም የአልጄርስ ስምምነትን ከፈረሙት የህወሓትና ዓረና ፓርቲ መስራቾችና መሪዎች ይልቅ ስምምነቱን የተቀበሉትን በግንባር ቀደምትነት ተጠያቂ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በዚህ መሰረት አብዛኞቹ የትግራይ ልሂቃን “ዶ/ር አብይ የኢትዮጲያን መሬትና ሉዓላዊነት ለኤርትራ አሳልፎ ሰጥቷል” በማለት ተቃውሞና ቅሬታ በማሰማት ላይ ናቸው። የአልጄርስ ስምምነትን በፊርማቸው ያፀደቁትና ባድመን ለኤርትራ አሳልፈው የሰጡት ፓርቲዎች የትግራይ፣ አመራሮቹም ትግራዋይ ሆነው ሳለ ሌሎችን የሚቃወሙበት ምክንያት ምንድነው?
አብዛኞቹ የኢትዮጲያ ልሂቃን ስለ የባድመ ሲነሳ አያይዘው የአሰብ ወደብን ያነሳሉ። ልክ እንደ ባድመ የአሰብ ወደብ የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ግዛት እንደነበርና በህወሓት መራሹ መንግስት ለኤርትራ ተላልፎ መሰጠቱን ይወሳሉ። በተመሳሳይ ስለ አሰብ ወደብ ሲነሳ ደግሞ ኤርትራና ምፅዋ ራሳቸው የኢትዮጲያ አካል እንደነበሩ ይጠቅሳሉ። ከዚህ በተቃራኒ የትግራይ ልሂቃን ግን ስለ ባድመ በተናገሩበት አንደበታቸው የአሰብ፥ ኤርትራ ሆነ ምፅዋ ጉዳይን አያነሱም። በአጠቃላይ የትግራይ ልሂቃን ስለ ባድመ ሲናገሩ ሆነ ሲከራከሩ የመለስ ዜናዊ፥ ገብሩ አስራት እና ስዩም መስፍንን ስም አያነሱም፣ አሰብ፥ ኤርትራና ምፅዋ የሚሉትን ቃላት በጭራሽ አይጠቅሱም። ለምን?
ነፍሱን ይማረውና መለስ ዜናዊ “ድንጋይ መፈንቀል አያስፈልግም” ይል ነበር። አዎ…የትግራይ ልሂቃን ስለ ባድመ በሚናገሩበት ወቅት የተጠቀሱትን ስሞች በመጥራት ድንጋይ መፈንቀል አይሹም። ምክንያቱም ድንጋይ ሲፈነቀል ለእይታ የማያምሩ ብዙ አይነት ነፍሳትና ትላትሎች ከድንጋዩ ስር ይወጣሉ። የትግራይ ልሂቃንም ስለ ባድመ ሲናገሩ የህወሓትና ዓረና አመራሮችን ስም ከጠቀሱ፣ የአሰብና ምፅዋን ስም ካነሱ በአሁንና በቀድሞ የትግራይ መሪዎች የተፈፀሙ አሳፋሪ ታሪካዊ ስህተቶች ብቅ ይላሉ። ለምሳሌ ከእነዚህ አሳፋሪ ታሪካዊ ስህተቶች ውስጥ የሚከተሉት በአብነት መጥቀስ ይችላል፡-
1 ኛ፡ – የአደዋ ስምምነት – ምፅዋ
የአደዋ ስምምነት (Treaty of Adwa) የሚባለው እ.አ.አ በ1884 በአፄ ዮሃንስ 4ተኛ እና በእንግሊዞች መካከል የተፈረመ ነው። በወቅቱ በሱዳን የሚገኘው የእንግሊዝ ጦር ከመሃዲስቶች በደረሰበት ጥቃት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ነበር። ጦሩ ከሱዳን ለመውጣት የነበረው አማራጭ በኢትዮጲያ በኩል ብቻ ነበር። በወቅቱ እንግሊዝ ምፅዋን፣ ኢጣሊያን አሰብን፣ ግብፅ ደግሞ ቦጎስ የሚባሉ የኢትዮጲያ መሬቶችን ይዘው ነበር። በአደዋ ስምምነት አፄ ዮሃንስ አጣብቂኝ ውስጥ የገቡትን የእንግሊዝ ወታደሮች ከሱዳን እንዲያወጣ፣ በምላሹ ግብፅ የያዘችውን ቦታ እንድትለቅ፣ ምፅዋ በእንግሊዞች ቁጥጥር ስር ሆኖ አፄ ዮሃንስ የጦር መሳሪያና የንግድ ዕቃዎችን በወደቡ እንዲያስገባ የሚጠይቅ ነበር።
በስምምነቱ መሰረት ራስ አሉላ አጣብቂኝ ውስጥ የገባውን የእንግሊዝ ጦር ምፅዋ ወደብ ድረስ አምጥቶ ለእንግሊዞች ያስረክባል። እንግሊዞች ፍላጎታቸውን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንደተሟላ ተገነዘቡ። በምስራቅ አፍሪካ የፈረንሳይን መስፋፋት በመግታት ረገድ ከአፄ ዮሃንስ በተሻለ አጋር ለምትሆነው ኢጣሊያ እንግሊዞች የምፅዋ ወደብን እንሆ በረከት አሏት። አፄ ዮሃንስ ባዶ እጁን አጨብጭቦ ቀረ። በዚህ መልኩ አፄ ዮሃንስ የምፅዋ ወደብን ያለ ምንም ጥቅም፣ ፍፁም አሳፋሪ የሆነ ታሪካዊ ስህተት በመስራት የምፅዋ ወደብን በመጀመሪያ ለእንግሊዞች፣ ቀጥሎ ለኢጣሊያኖች አሳልፎ ሰጠ።
አፄ ዮሃንስ በአደዋ ስምምነት ላይ የሰራው ስህተት ኢጣሊያን ኤርትራና ኢትዮጲያን ቅኝ ለመግዛት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላታል። ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ለብዙ አመታት ኤርትራን በኃይል ለመቆጣጠር ችላ ነበር። በዚህ መልኩ ኤርትራ በባዕድ ሀገር ቁጥጥር ስር መውደቋ ከተቀረው የኢትዮጲያ ክፍል የተለየ ብሔራዊ ማንነትና ማህበራዊ ስነ-ልቦና እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። ይህ በኤርትራ የፖለቲካ ልሂቃን ዘንድ የመገንጠልና ራስ በራስ የማስተዳደር ጥያቄ እንዲሰርፅ አድርጓል። ይህ ሁሉ የሆነው የህወሓትና ዓረና ፓርቲ መሪዎች ቅድመ አያት የሆነው አፄ ዮሃንስ በሰራው ታሪካዊ ስህተት ነው። ይህን ታሪካዊ ስህተት በአንድ የታሪክ ድረገፅ ላይ እንደሚከተለው ተከትቦ ይገኛል፦
“YOHANNES THEN TURNED HIS ATTENTION TO NEGOTIATING WITH THE BRITISH AND EGYPTIANS TO RECOGNISE ETHIOPIA AS A SOVEREIGN STATE AND INDEPENDENT COUNTRY. YOHANNES AMBITIONS WERE HELPED WHEN THE MAHDIST WAR BROKE OUT IN SUDAN IN 1882. BRITAIN HAD TROOPS STATIONED THERE AND BRITAIN NEEDED ETHIOPIA’S ASSISTANCE TO RESCUE ITS TROOPS. IN 1884 THE TREATY OF ADWA WAS SIGNED BETWEEN ETHIOPIA AND BRITAIN, WHICH FULFILLED YOHANNES DEMANDS SUCH AS THE RETURN OF BOGOS WHICH WAS OCCUPIED BY THE EGYPTIANS AND THE RIGHT TO IMPORT WEAPONS AND GOODS. IN RETURN BRITAIN WOULD CONTROL THE PORT OF MASSAWA. AFTER A YEAR, BRITAIN TORE UP THE TREATY AND HANDED THE PORT OF MASSAWA TO ITALY, WHICH BECAME A MAJOR THREAT TO ETHIOPIAN SOVEREIGNTY.”
2 ኛ፡ – የኤርትራ መገንጠል – አሰ ብ
እ.አ.አ. በ1884 የተሰራው ታሪካዊ ስህተት በ1993 ፍሬ አፍርቶ ኤርትራ ከኢትዮጲያ ለመገንጠል ሕዝበ ምርጫ አደረገች። ህወሓት መራሹ የሽግግር መንግስት ኤርትራ ከኢትዮጲያ እንድትገነጠል ድጋፍና ትብብር ከማድረጉ በተጨማሪ የአዳል አውራጃ (በአሁኑ አጠራር የአፋር ክልል) አካል የነበረውን የአሰብ ወደብ አሳልፎ ሰጥቷል። በመሆኑም የህወሓትና ዓረና መሪዎች ከመቶ አመት በፊት በቅድመ አያታቸው የተሰራውን ታሪካዊ ስህተት መልሰው ደገሙት። የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ግዛት አካል የነበረችውን ኤርትራ እንድትገነጠል ከማድግ በተጨማሪ የአሰብ ወደብ በነፃ አሳልፈው በመስጠት ሀገሪቱን ወደብ አልባ አደረጓት።
3 ኛ፡ – የአልጄርስ ስምምነት – ባድ መ
በኢትዮጲያና ኤርትራ መካከል ጦርነት የተቀሰቀሰው በሌላ ሳይሆን ህወሓትና ሻዕቢያ የኢትዮጲያን ሃብትና ንብረት ለመቀራመት በሚያደርጉት ጥረት በተፈጠረ ግጭት ነው። በህወሓትና ሻዕቢያ ስግብግብነትና ዘረፋ የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ ሰባ ሺህ የሚገመቱ የሀገራችን ወጣቶችን ለህልፈት ዳርጓል። ምንም እንኳን ጦርነቱ አላስፈላጊና ስህተት ቢሆንም በኢትዮጲያ ሉዓላዊነት ላይ የተጋረጠ አደጋ መሆኑ አልቀረም። ለጦርነቱ መቀስቀስ የሁለቱም ሀገራት መንግስታት ተጠያቂ ቢሆኑም ቀድሞ ወረራና ጥቃት የፈፀመው የኤርትራ መንግስት ነው። በመሆኑም የኢትዮጲያ ልጆች ነፍሳቸውን ሰውተው የኤርትራን ጦር ድባቅ በመምታት የሀገራቸውን ዳር ድንበር አስከብረዋል። ወራሪውን ጦር ከመመከት በተጨማሪ ለአስመራ ጥቂት ኪሎ ሜትር እስኪቀር ድረስ ኤርትራን ለመቆጣጠር ችለዋል።
የዕብሪት ወረራ ለፈፀመ ሀገር በመልሶ ማጥቃት የተያዘው ቦታ በቀጣይ ለሚደረገው የሰላም ስምምነት ዋና የመደራደሪያ ኃይል (Bargaining Power) ሆኖ ያገለግላል። ሆኖም ግን፣ በወቅቱ የኢትዮጲያ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የኢትዮጲያ ጦር የያዘውን የኤርትራ መሬት ለቅቆ ወደ ድንበር እንዲመለስ ትዕዛዝ ሰጡ። በዚህም የኢትዮጲያ ጦር በስንት መስዕዋት ያገኘውን የመደራደሪያ ኃይል በከንቱ ገፍፎ ጣለው። ከዚህ ቀጥሎ አልጄርስ ላይ በተደረገው የሰላም ስምምነት ባድመን ለኤርትራ አሳልፎ በመስጠት ሌላ ታሪካዊ ስህተት ሰራ።
የትግራይ ልሂቃን ስለ ባድመ ሲናገሩ ተሳስተው የሀወሓትና ዓረና መሪዎችን ስም ካነሱ ወይም ምፅዋ፥ አሰብና ኤርትራ የሚሉትን ቃላት ከጠሩ የትግራይ መሪዎች በዚህች ሀገር ሉዓላዊነትና አንድነት ላይ የፈፀሙት ታሪካዊ ስህተት ይታወሳቸዋል፥ ይነገራቸዋል፥ ያሳፍራቸዋል። ከአደዋ እስከ አልጄርስ ስምምነት፣ ከምፅዋ እስከ አሰብና ባድመ የኢትዮጲያን መሬትና ሉዓላዊነት አሳልፈው የሰጡት የትግራይ ልሂቃንና መሪዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች በኢትዮጲያ አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ የፈፀሙት ስህተት ታሪካዊ ብቻ ሳይሆን በቀላሉ የማይስተካከል፣ ለዘመናት የማይድን ጠባሳ ነው።
ኤርትራ የተገነጠለችው አፄ ዮሃንስ ለእንግሊዞች በነፃ አሳልፈው የሰጧት ዕለት ነው። ኢትዮጲያ ወደብ አልባ የሆነችው አቶ መለስ ዜናዊ አሰብን በነፃ አሳልፎ የሰጠ ዕለት ነው። ባድመ ለኤርትራ የተሰጠችው መለስ ዜናዊ የኢትዮጲያን ጦር በቁጥጥሩ ስር ያለውን የኤርትራ መሬት ለቅቆ እንዲወጣ ያዘዘ ዕለት ነው። በዘመናዊ ታሪክ የኢትዮጲያ መሬት ለሌላ ሀገር ተላልፎ የተሰጠው፣ በዚህም የሀገራችን ሉዓላዊነት የተደፈረው የትግራይ ልሂቃንና መሪዎች በሰሩት ታሪካዊ ስህተት ነው። ዛሬ የትግራይ ልሂቃን ስል ባድመ ሲናገሩ የትግራይ መሪዎችን ስም ወይም ኤርትራ፥ ምፅዋና አሰብ የሚሉትን ቃላት የማይጠሩት በኢትዮጲያ ሉዓላዊነት ላይ የፈፀሙትን ታሪካዊ ግፍና በደል ስለሚያስታውሳቸው ብቻ ነው