ዘረኛ የምለው ዘረኞቹን ነው፡፡ ሌላው ኦሮሞ ሆነ አማራ ወይም ሌላ አይመለከተውም፡፡ እንደእውነቱ ምን እየሆነ እንደሆነ ሊገባኝ አልቻልም፡፡ ሰሞኑን አንድ ቤቲ የተባለች ጋዜጠኛ አብን የተባለውን ቡድን ዋና ቃለ ምልልስ ከአደረገች በኋላ  ነገሮችን ስመለከት የፈራንው ነገር ሥር እየሰደደ ይመስላል፡፡ እኔ በአጠቃላይ በዘር ሥም የሚደራጁ በሕዝብ ሥም ለመነገድ እንጂ ለሕዝብ ሠላምና ብልጽግና ይሰራሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ አገራችንን አሁን የደረሰችበት አጣብቂኝ የከተታት ይሄው በተንኮለኞች ተወጥኖ የተንሰራፋ የዘር ፖለቲካ ነው፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት በየትኛውም መስፈርት ሌላ የዘር ቡድን በመጨመር መፍትሄ አይመጣም፡፡ ከመሠረቱ የዘር ፖለቲካን ሙጥኝ ያሉትን በሕዝብ ሥም ተደብቀው የራሳቸውን ኑሮና ሴራ ለመገንባት የተነሱ ጸረ-ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት የዚሁ ሴራቸው ግፍ እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ደርሶታል፡፡ አዚም ተደርጎብን ከአልሆነ ኢትዮጵያዊ የሆን ሁሉ ዳግም ወደዚህ እርግማን እንዳንመለስ እስከዛሬም የመረዘንን መርዝ ከሰውነታችን እንድናወጣ ይገባናል፡፡ የሆነብንን ሁሉ በራሳችን አይተን ከአልተማርን ሌሎች ሆነዋል ብንባልማ እንዴት እንቀበለዋለን፡፡ አንድን ችግር ችግሩ በተፈጠረበት መንገድ መፍታት አይቻልም ያለው ፈላስፋው ነው፡፡

በጠዋቱ በኦሮሞ ላይ ለመነገድ በኦሮሞ ነጻነት ሥም የተነሱት ይሄው ነጻነት የተባለውን ሕዝብ እውነት እየመሰለው 50 ዓመት ሲጠብቅ በጎን ነገሩ የገባቸው ኢትዮጵያውያን(ቲም-ለማ) በአጭር ጊዜ ውስጥ ነጻነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ በተግባር አሳይተው አገርንና ሕዝብን ወደ ሠላምና ብልጽግና ለመምራት ቁርጠኝነታቸውን ማየት ስንጀምር አሁንም ሕዝቡንያን ኦነጋው ከእነሱ የባርነት ቀንበር እንዳይወጣባቸው ከፍተኛ ፍልሚያ እያካሄዱ ነው፡፡ ኦነግ የኦሮሞን ሕዝብ ሲነግድበት ኖሮ አሁንም የግል ንብረቴ ነው ነጻ ልታወጡት አትችሉም ይለናል፡፡ ይህ ይፋዊ የኦነግ አቋም ነው፡፡ ኦሮሞም ሆነ ሌላው እንግዲህ እድል ቀርቦለታል፡፡ ቀጥሎም በባርነት መቆየት የፈለገ ምርጫው ነው፡፡ ይህ እየሆነ ነው፡፡

ሰሞኑን የአማራን ሕዝብ ነጻነት አስከበራለሁ በሚል የተነሳው አብን የተባለው ቡድን በእኔ አተያይ የኦሮሞው ኦነግ በአማራ ቢባል ይቀላል፡፡ ሕዝብ በምንም መልኩ መሸወድ የለበትም፡፡ ነገሮችን እነፕሮፌሰር አስራት ከመሰረቱት መዐድ ጋር እያመሳሰለ ሊያምታታ የሚሞክር ይመስላል፡፡ አስራት አሁን በኢትዮጵያ እየመጣ ያውን የተስፋ ጭላንጭል አይተው ቢሆን ከኢትዮጵያዊ ያነሰ መዐድን አያቋቁሙም ነበር፡፡ መዐድ የተቋቋመበት በቂ ምክነያት አለ፡፡ ይሰራም የነበረው ዓላማውን ተንተርሶ እንጂ የአማራ ዘረኝነትን ለማስፋፋት፣ ሌሎችን ለመጥላትና አማራትን የግል የንግድ እቃ ለማረግ አደለም፡፡ አብን የሚባለው አካሄድ ግን ጭርሱንም ከሕዝብ ነጻነት ጋር የሚቃረነው ሥራው በዝቶ ይታያል፡፡ እሺ አብንም ምክነያት አለው እንበል፡፡ የአማራን ሕዝ ነጻነትና ሠላም አስጠብቃለሁ የሚለው ይህ ቡድን አማራ በሌሎች ላይ ጥላቻ እንዲኖረው ከፍተኛ የዘረኝነትና የጥላቻ መርዝ እየዘራ ነው፡፡ ይህ ራሱ ነበር በኦነግና ኦነጋውያን ለዘመናት በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ሲፈጸም የነበረው፡፡  እንደነ አብንና ኦነግ እንዲሁም ወያኔ አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር በሕዝብ ነጻነት ሥም ተደራጅተው ነጻ እናወጣዋለን የሚሉትን ሕዝብ ጥላቻና ዘረኝነት በማስተማር ከኢትዮጵያዊ ማንነቱና ከእምነትና፣ ባሕላዊ እሴቶቹ ከአመከኑት በኋላ የእነሱ የንግድ እቃ ለማድረግ ነው፡፡ አስተውሉ አብን ገና ከጅምሩ አማራ ከሌሎች ጋር እንዳይኖርና የግል (የአብን) ገንዘቡ ሊያደርገው የሕዝብ ማንነት ማመከኛውን በሰፊው እያሰራጨ ነው፡፡ እወክለዋለሁ ለሚለው ሕዝብ ነጻነትም ይሁን ጥበቃ የሚሆን ነገሮችን አናይበትም፡፡ በአለፈው በጋዜጠኛዋ ከተነሱት ሌላ አንድ እኔ ያየሁትን እንደምሳሌ ልጥቀስ፡፡  የእነዚህ ጥላቻና ዘረኝነትን የሚያስተላልፉ መርዞችን እያሰራጨ ያለ ተብሎ በዋናነት የሚጠቀሰው ደግሞ በአማራ ክልል የወጣቶች ሊክ ሰብሳቢ በሚል ለወያኔ ሲያገለግል የኖረ ዛሬ ደግሞ በአዲስ መልክ የአብን ቡድን ሕዝብ ግንኙነት የተባለ ሰው ነው፡፡  አስተውሉ፡፡ ይህ ሰው የጎንደሩን አመጽ አስነስተሀል በሚል መታሰሩን እንደ አማራ ሕዝብ ታጋይነት ማሰብ የወያኔን ሴራ አለመረዳት ነው፡፡ ግለሰቡ እስር ቤት እንዲገባ የተደረገበት በዋናነት ለስለላ ሥራ እንጂ እውን እንደሌላው መከራ ለመቀበል ነው ብሎ ማሰብ በራሱ ሞኝነት ነው፡፡ ሲጀምር በምን መስፈርት የወያኔ በአማራ የወጣቶች ሊግ ሰብሳቢ ሊሆን እንሚችል ማስተዋል ብልህነት ነው፡፡ ወያኔ የወጣት ሊግ እያለች ያሰማራቻቸው በብዙ ቦታዎች ሴራዋን ያጠመቀቻቸውን ታማኞቿን እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ ከወጣቱ ሊግ ይልቅ በክልል የፓርቲ አባልነት ውስጥ ሆነው ሌሎች ከወያኔ ሀሳብ የቆሙ እንደነበሩ እናውቃለን፡፡ የወጣት ሊግ የሚባለው ግን ወሳኝ የወያኔ ታማኝ ነበር፡፡ ይበልጠውንም በሰብሳቢነት መመረጥ የሚችለው በታማኝነቱ የተረጋገጠለት ነው፡፡ እናም ምን አልባትም አሁን ደግሞ በሌላ መልክ የአማራን ሕዝብ ከኢትዮጵያዊነቱና ከመሠረታዊ ሐይማኖታዊና ባሕላዊ እሴቶቹ ለማምከን በወያኔ ተመርጦ የሚሰራ እንደሆነ አለማስተዋል ስህት ብቻም ሳይሆን አደገኛም ነው፡፡ ወያኔ ኦሮሞን ከኢትዮጵያዊነትና ከመሰረታዊ የእምነትና ባሕላዊ እሴቶቹ አውጥታ ምን ያህል እንደተጠቀመች ስለምታውቅ አማራንም በማያዋጣው ፊት ለፊተ ከመጋተር ከማንነቱ ከአወጣችው በኋላ እንደፈለገች መዘወር አቅዳ ነበር፡፡ አሁን ይሄ ለወያኔ ብዙም ባይጠቅማት ግን የወጠነቸው ውጥን የሴራዋ አስፈጻሚ በሆኑት እየተካሄደ እንደሆን እናስብ፡፡ አሁን ላይ የምናየው የአብን ደጋፊ ነን የሚሉት በቀጥታ የኦነጋውያን ባሕሪን በአማራነት የወረሱ ነው የሚመስለው፡፡

ዛሬ የኦነጉን ዳውድን የልብ ልብ የሰጠው ከማንነቱ የወጣ ብዙ በእኔ አስተሳሰብ ባርነት የወደቀ ተከታይ አለኝ በሚል ነው፡፡ ሲጀምር ኦነግ ይህ ነው የሚባል ወታደርም የለውም፡፡ አሁን እየሆነ ያለው በኦነግ አስተሳሰብ የተመረዙ ወጣቶችን ትጥቅ እያቀበሉ በየቦታው ሽብር መፍጠር ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሊነቁ ይገባቸዋል፡፡ ብዙዎቻችን በአልገባን ነገር የጠላቶቻችን ባሮች ሆነን ኖረናል፡፡ ከዚህ በኋላ እያንዳንዳችን የግል መብታችንን እንጂ የቡድን መብት በሚል እያሳከሩ የቡድኑ ቀርቶብን እንደሰው የመኖር መብታችንን ሁሉ ነግገው እነሱ የሚኖሩብንን ልንነቃባቸው ይገባል፡፡

መንግስት እንደመንግስት የዜጎች ደህንነትና መብት መጠበቅ ግዴታው ነው፡፡ ማንም እየተነሳ የሚያናፋበት እድል ሊሰጠው አይገባም፡፡ ብዙዎች በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እየነገዱ ያሉት ከእነጭርሱም ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ መግባት የሌለባቸው ናቸው፡፡ በትውልድ ኢትዮጵያዊ መሆናቸው በበጎ እንጂ በሴራ የሚሄዱበትን አካሄድ ዜግነት ከአገኙበት መንግስትም ጋር በመነጋገር ሕጋዊ እርምጃ ማስወሰድ ይገባል፡፡ ሰሞኑን ጂጂ የተባለች በጀርመን በምትኖር የጥላቻና ዘረኝነት መልዕክቶችን በማስተላለፍ የምትታወቀው ላይ ኢትዮጵያውያንና በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ጀርመናውያን የጀርመን መንግስት ይህችን ግለሰብ ከእኩይ ድርጊቷ እንድትቆጠብ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ እየጠየቁ ነው፡፡ ይህ አይነቱ አካሄድ በሁሉም አገራት ሊተገበር ይገባል፡፡ ብዙዎች በሰሜን አሜሪካ ዜግነት ነው የኢትዮጵያን ደሀ ሕዝብ ሠላም እያወኩ እነሱ መኖሪያ ያደረጉት፡፡ የጥላቻና ዘረኝነት መልዕክቶችን በማሕበራዊ ሚዲያ ማሰራጨት በተባበሩት መንግስታት ጨምሮ የብዙ አገራት ሕግ ያወግዘዋል፡፡ ብዙ የዘር ተኮር እልቂቶች በእንደዚህ አይነት መርዛማ መልዕክቶች እንደተከሰቱ ከሆሊኮስትና ከሩዋንዳው እልቂት በላይ ምስክር የሚሆን የለም፡፡ ስለዚህ ይህን ኢትዮጵያውያን ሁሉ በያሉበት በሕዝብና አገር ላይ የጥላቻና ዘረኝነትን መልዕክት በሚያስተላልፉ ግለሰቦችም ይሁን ቡድኖች ላይ በየአገራቱ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ጠንክሮ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ማስረጃዎቹ ቀላል ናቸው፡፡ ብዙዎች በይፋ በቪዲዮ ቀርጸው በፌስቡክና ዩ ቲዩብ ነው የለቀቋቸው፡፡ በተጨማሪ ፌስቡክም ሆነ ዮ-ቲዮብ ወይም ሌላ ለዚህ ነገር እየተጠቀሙባቸው ያሉትን ቢጠቆሙ እርምጃ ይወስዳሉ፡፡

በተረፈ የአማራም ሆነ የኦሮሞ ሕዝብ እስከዛሬ የተሸወዳችሁት ይበቃል፡፡ ሴረኞች ቁልፍ አድርገው የሚያሴሩት አማራና ኦሮሞን ማጋጨት ነው፡፡ አማራ፣ ኦሮሞ እያለ የሚያገንህን አትከትል፡፡ ወደንንም ጠላንም የተዋረድን ሆነናል፡፡ እንደአገር በአለቤትነት እንኳን እንዳንኮራ ከማንነታችን እያመከኑን ነው፡፡ በእኛ ውርደት ሴረኞች ይከብራሉ፡፡  አስተውል፡፡ ባሕልምና እሴቶችህ ሁሉ የሚከበሩት መጀመሪያ የግል መብትህ ሲከበር ነው፡፡ በጅማላ በማንነት ስም እያጨቁ ሲነግዱብህ ዘመናት አልፈዋል፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በማንነቱ ምክነያት ኢላማ ተደርጎ ብዙ ግፍ ያልደረሰብት የለም፡፡ ይህ ኋላ ቀር በተባለው ዘምን አልሆንም፡፡ ዛሬ በሚሊያን የሚቆጠር ሕዝብ በማንነቱ ምክነያት ማንም ተነስቶ ያፈናቅለዋል፣ ያሰቃየዋል፣ ይገድለዋል፡፡ በዘር ማንነት ቁማር አራሳቸውን ያከበሩ የንግዳቸው መሠረት እዚህ ውስጥ ነው፡፡ አስተውሉ፡፡ አሁን እየታየ ያለውን ተስፋ በምንም መልኩ አሳልፎ ዳግም ጨካኝ ሴረኞች መስጠት በራስ ላይ ዳግም ግፍን መመለስ ነው፡፡

በዚህ አጋጣሚ የሚዲያ ባለቤት የሆናችሁ ለአገራችን ሕዝብ በጎ ተጽኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ የተባበሩት መንግስታትን ኤጀንሲዎች ጨምሮ በትልልቅ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ሳይቀር በኃላፊነት ጭምር ያገለገሉ ምሁራንን በሚዲያዎች በመጋበዝ ለትውልዱ የበጎ አስተሳሰብን በመሰራጨት ብትተባበሩ፡፡ እኔ በግሌ የማውቃቸውን ምሁራን አድራሻ ልሰጥ እችላሁ፡፡

የመንግስት ሚዲያዎች የክልሎቹም የፌደራልም በተለያየ ቋንቋ የሕዝብን አብሮነትና ታሪካዊ አመጣጥን በስፋት ዘጋቢ ፊልም በማዘጋጀት ሕዝብ ስላለው ታሪካዊ ትስስርና አብቶነት ያለው ግንዛቤ እንዲጎለብት፣ እንዲሁም ስለሰላምና ፍቅር በስፋት መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል መንግስት የሆነው ኦቢኤን የተወሰኑ መልካም ጅማሮ አሳይቶናል ግን በስፋትና በተለያዩ ቋንቋዎች ተመሳሳይ ዶኪመንተሪዎች ሊሰሩ ይገባል፡፡ የአማራ መገናኛ ብዙሀን ምን ያህል እየሰራ እንደሆነ አላውቅም፡፡ ዋናው በፌደራል መንግስ ቁጥጥር ስር የሆኑ ሚዲያዎች ከዜና ማሰራጨት በአለፍ ብዙም መሠረታዊ ግንዛቤን በሕዝብ ዘንድ በሚያሰርጽ ታቅዶ የሚሰሩ ሥራዎች አላይም፡፡ በኦሮምኛ ቋንቋ ይጀምራል ተብሎ እስካሁን አላየሁም፡፡ የወያኔ እየተባለ ሲታማ የነበረው ፋና በተሻለ መልካም የሚባሉ ሥራዎችን እየሰራ ይመስላል፡፡ ግን የበለጠ መጠናከር እንዳለበት አስባለሁ፡፡  በአጠቃላይ ሕዝብን በመሠረታዊ ሠላማዊ የአብሮነት አኗኗር ከፍተኛ ግንዛቤ ፈጣሪ ዝግጅቶችን በማሰራጨት ዘረኝነትንና ጥላቻን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ባይቻልም ከአብዛኛው ሕዝብ ማጥፋትና ቀጥሎም መልካም በሥርዓትና ሕግ ላይ መሠረት ያደረገ በፍቅር አብሮ የሚኖር ማሕበረሰብን መገንባት ይቻላል፡፡ ይህ ሲሆን የተባለው ዲሞክራሲ በራሱ ጊዜ መሬት ይይዛል፡፡ ለዚህ ደግሞ በራሱ በሕዝቡ የአሉ የእምነትና ማሕበራዊ እሴቶች በጥሩ አጋዥነት ይውላሉ፡፡ መንግስት እንደመንግስት የዜጎች ደህንነትና ፍትህን ማስጠበቅ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል፡፡ በዚህ መልክ በአጭር ጊዜ ልዩ ፍቅር የተላበሰ ሠላማዊ አስተሳሰብ በሕዝብ ዘንድ ማስረጽ ይቻላል፡፡ እንደ አስፈላጊነቱ መንግስት የጥላቻና ዘረኝነት መልዕክት የሚያስተላልፉ ማሕበራዊ ገጾችንና ሚዲያዎችን ሕጋዊ እርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡ በአሁን ዘመን ብዙ አገራት የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሕግ አላቸው፡፡ ከሁሉም ግን ሕዝብን ከሕዝብ ሊያጋጭ የሚችል የጥላቻና ዘረኝነት መልዕክት ማስተላለፍ የጠበቀ የሕግ ቅጣት ያስከትላል፡፡  ስለዚህ የእነዚህ ሚዲያ ተጠቃሚ የሆኑ ግለሰቦችም ይሁን ቡድኖች በመናገር መብት በሚል ዘረኝነትንና ጥላቻን ቢያስተላልፉ በሕግ ሊቀጡ ይገባል፡፡ በአካል ሁለት ሰዎች ተገናኝተው ቢሰዳደቡ በራሱ ቅጣት አለው፡፡ በሚዲያ ብዙ ሕዝብ ጋር የሚደርስ የጥላቻና ዘረኝነት መልዕክት ማሰራጨት የበለጠ ቅጣት ሊኖረው ይገባል፡፡ ዛሬ ላይ ይህ በሠለጠኑትና ዲሞክራሳዊ በሚባ አገራት የተለመደ ነው፡፡ የመናገር መብት ማለት የሌላውን መብት መጋፋት እንዳልሆነ ዜጎች ግልፅ ሊሆንላቸው ይገባል፡፡

አመሰግናለሁ

ሰርፀ ደስታ