October 10, 2018

ቀን 30/01/2011 ዓም

ጉዳዩ:_ ማብራሪያ መስጠትን ይመለከታል

የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ በውጭ ሀገር የሚኖር ከኮሚቴው ጋር አብሮ ለመስራት የውክልና ስምምነት ላይ የደረሰ ወይንም በጋራ ለመስራት ውክልና የሰጠው አካል እንደሌለ መስከረም 29/2011 ዓም በተፃፈ ደብዳቤ ማሳወቃችን ይታወሳል።
የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ “ልሳነ ግፉአን” የሚባል አካል “የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ብቸኛ ወኪል እኛ ነን፣ ማንኛውም ድጋፍ ሰጭ መደገፍ ያለበት በእኛ በኩል ነው” በሚል በኮሚቴው ስም እየተንቀሳቀሰ መሆኑን እና በቪዲዮ ኮንፈረንስም “እኛን አገዛችሁ ማለት ኮሚቴውን አገዛችሁ ማለት ነው፣ አብረን ቢሮ ከፍተን እየሰራን ነው” በሚል ቅስቀሳ እያደረገ መሆኑን ማወቅ ችለናል። በትናንትናው ደብዳቤ ይሁን አካል በግልፅ “ልሳነ ግፉአን” ብለን ስሙን ጠቅሰን ባለመግለፃችን በውጭ ሀገር የሚኖሩ ደጋፊዎቻችን ግራ መጋባታቸውን ገልፀውልናል። ለተፈጠረው ብዥታም ይቅርታ እንጠይቃለን።
ይሁንና የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ “ልሳነ ግፉአን” የሚባል አካል የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴን የሚወክል ስራ እንዲሰራ ውክልና እንዳልሰጠነው አስረግጠን መግለፅ እንወዳለን። በዚሁ አጋጣሚ ይህ አካል በወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ስም እንደተወከለ አድርጎ ከመንቀሳቀስ እንዲቆጠብ እንጠይቃለን።
የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ በውጭ በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ድጋፍ የሚያደርጉልን የአማራ ተወላጆች፣ ኢትዮጵውያን፣ የሌሎችም ዜጎችም ደጋፊዎች እንዳሉት ይታወቃል። ለወልቃይትጠገዴ ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ መደገፍ ለሚፈልግ አካል በራችን ክፍት ሲሆን ኮሚቴው ለሚደረግለት የትኛውም ድጋፍ ሁሉ ሕጋዊ ደረሰኝ ይሰጣል። ልሳነ ግፉአንም እንደማንኛውም ደጋፊ መደገፍ ይችላል።
ነገር ግን “ልሳነ ግፉአን” የተባለ አካል ምንም አይነት የውክልና ስምምነትም ሳይኖረው እና ውክልና ሳይሰጠው፣ “በኮሚቴው ስም ውክልና ተሰጥቶኝ እየተንቀሳቀስኩ ነው፣ ከኮሚቴው ጋር ለመስራት ስምምነት ደርሻለሁ፣ የጋራ ቢሮ ከፍተን እየሰራን ነው” በሚል የሚገለፀው ከእውነት የራቀ መሆኑን ደጋፊዎቻችን እና ሕዝብ እንዲያውቁልን እና “ልሳነ ግፉአንም” ከዚህ ተግባሩ እንዲቆጠብ በድጋሚ እናሳውቃለን።

ከሰላምታ ጋር