October 10, 2018
መንግስት በኦነግ “ትጥቅ አልፈታም” ሀሳብ ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል፤
“ኦነግ ወደ ሀገር የገባው ትጥቅ ፈትቶ ነው፤ የቀረውን ትጥቅ መፍታት አለበት”
“የማይፈታ ከሆነም መንግስት ትጥቅ የማስፈታቱን ስራ ይሰራል” ሲልም አስታውቋል
‘‘ኦነግ ወደ ሀገር የገባው ትጥቅ ፈትቶ ነው አሁንም ቢሆን የቀረውን ትጥቅ መፍታት አለበት፤ ካልሆነ ግን መንግስት የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅና ህገመንግስታዊ ስርዐቱን ለማስጠበቅ ሲል ትጥቅ የማስፈታቱን ስራ ይሰራል’’ አቶ ካሳሁን ጎፌ
ከሰሞኑ የኦነግ አመራር አቶ ዳውድ ኢብሴ ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ከመንግስት ጋር ትጥቅ ለመፍታት አልተደራደርንም፤ ትጥቅ የሚፈታም የሚያስፈታም የለም ማለታቸውን ተከትሎ ዛሬ የኢፌዲሪ መ/ኮ/ጉ/ፅ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ በጉዳዩ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ባደረገው የሰላም ጥሪ መሰረት በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶችና የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ ሀይሎች ወደ ሀገር መግባታቸውን ያስታወሱት አቶ ካሳሁን ኦነግም ወደ ሀገር ሲገባ 1300 ያህል ጦሩን ትጥቅ አስፈትቶ መግባቱንና ጦሩም በአሁኑ ሰአት በጦላይ ማሰልጠኛ ስልጠና እየተከታተለ ነው ብለዋል፡፡
ኦነግ በአስመራ በተደረጉ ሶስት ድርድሮች በሰላማዊ መንገድ ወደ ሀገር ገብቶ ለመፎካከር መስማማቱ የሚታወቅ ነው፤ ለዚህም ወደ ሀገር ሲገባ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል ያሉት አቶ ካሳሁን በድርድሩ ወቅት ትጥቅ የመፍታት ጉዳይ ያልተነሳው የመደራደሪያ ጉዳይ ስላልሆነ ነው ብለዋል፡፡
ሰላማዊ ትግል የሚደረገው በሀሳብ እንጅ በአፈሙዝ ስላልሆነ ትጥቅ የመፍታትን ጉዳይ ለድርድር የማናቀርበውና ቀይ መስመር ነው ሲሉ አቶ ካሳሁን በመግለቻቸው ተናግረዋል፡፡ስለሆነም ኦነግ አቋሙን እንደገና በመፈተሽ ትጥቁን እንዲፈታ መንግስት ጥሪውና ያስተላልፋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ካልሆነ ግን የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅና ህገመንግስታዊ ስርዐቱን ለማስጠበቅ ሲል መንግስት ትጥቅ የማስፈታቱን ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡
መንግስት ህግን የማስከበር ስራውን በቆራጥነት ስለሚሰራ መላው ህዝብ የደህንነት ችግር ይገጥመኛል በማለት ስጋት ላይ እንዳይወድቅና እንዳይደናገር አቶ ካሳሁን መልእክታቸውን ማስተላለፋቸውን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ገልጻል ፡፡