የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቀጣዩ ሳምንት በአውሮፓ ይፋዊ የስራ ጉበኝት ያደርጋሉ ሲል ፋና ብሮደካስቲንግ ዘግቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአውሮፓ ጉብኝታቸውን ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በመቀጠልም ከጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዘገባዉ ያስረዳል።

ከዚህም በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓ.ም ከተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ከሚውጣጡ 25 ሺህ ኢትዮጵያውያን ጋር በፍራንክፈርት ዉይይት እንደሚያደርጉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ በሰጠዉ መግለጫ አስታዉቋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአውሮፓ ጉብኝት “አንድ ሆነን እንነሳ ነገን በጋራ እንገንባ” በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ እንደሆነ ተነግሯል።

መግለጫውን የሰጡት የ ሚኒስቴሩ ቃል አቃባይ አቶ መለስ ዓለም ኢትዮጵያ በአዲስ የለውጥ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች ያሉት ሲሆን፥ ዳያስፖራውን የማያሳትፍ የሀገር ግንባታ ጎዶሎ ነዉ ማለታቸዉን ዘገባዉ አስፍሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝቱን የሚያደርጉት በሀገራቱ መሪዎች በቀረበላቸው ግብዣ መሰረት ነው።

ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሰሜን አሜሪካ በማቅናት በዚያ ከሚኖሩ ኢትዮጲያዉያን ጋር ዉይይት ማድረጋቸዉ ይታወቃል፡፡