አቶ ሲሳይ አጌና ቀንደኛ የዐቢይ አስተዳደር ደጋፊ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በተለይም ዐቢይ አሜሪካንን በጎበኘበት ወቅት ስሙን ጠርቶ ካመሰገነውና ካደነቀው ወዲህ ብሶበታል፡፡

ሚዛናዊ የሆነ ዕይታውን ጨርሶ ትቶታል፡፡ የማገናዘብና የማሰብ ብቃቱ ከድቶታል፡፡ ባልደረቦቹና ለውይይት የሚጋብዛቸው ሰዎች ዐቢይን የተቹ እንደሆነ ለንቦጩን መጣልና ሐሳባቸውን እንዳይገልጹ ለማቀብ መጣር የዕለት ተዕለት ተግባሩ አድርጎታል፡፡

ከዚህ ትዝብት ላይ ከሚጥለው፣ ታሪኩን ከሚያበላሸውና ስሙን ከሚያጎድፈው ጭፍን ድጋፉ ጀርባ ሌላ የጥቅም ትስስር ስለፈጠረ ይሁን አይሁን ግን የማውቀው ነገር የለም፡፡ ዐቢይ ስላደነቀው ወይም ስላመሰገነው ብቻ አቶ ሲሳይ እንዲህ ይሆናል ብሎ ማሰብ ግን በጣም የሚከብድ ይመስለኛል፡፡

አቶ ሲሳይ የዐቢይ አሥተዳደር ወንጀልና የማይጠበቅ ነገር ሲፈጽም ምንም ዓይነት ማስረጃ ሳያቀርብ በደፈናው በውስጣቸው ያሉ ከሕወሓት ጋር ትስስር ያላቸው ናቸው ይሄንን የሚያደርጉት እንጅ በዐቢይ እውቅናና ትዕዛዝ ይሄ ሊፈጸም አይችልም!” እያለ ሲያስተባብልና የነዐቢይን ወንጀል ሲከላከል ቆይቷል፡፡

አሁን ወደ መጨረሻ በግልጽ ዕየታዩ ያሉ የነዐቢይን ወንጀል፣ ማንነትና አስተሳሰብ ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ አንባገነናዊ ተግባራትን ማስተባበል ሲሳነው ደግሞ ምንም ይሁን ምን የዐቢይን አሥተዳደር ከመደገፍ ውጭ አማራጭ የለንም!” ማለት አምጥቷል፡፡ ለምን ሲባል ሀገር ይፈርሳል!” ይላል፡፡

ልብ በሉ እንዲህ እያሉ በማስፈራራት ሀገር የመግዛት ፈሊጥ የማን እንደሆነ ታውቃላቹህ፡፡ ወያኔ እሱ ከሌለ ሀገር ትፈርሳለች!” እያለ እያስፈራራ ነው ሲገዛን የኖረው፡፡ ስለዚህ የሀገር መፍረስ ሥጋት የህልውና ዋስትናው ስላደረገው እንዲህ እየፈራን ሰጥለበጥ ብለን እንድንገዛለት የሀገርን መፍረስ ሥጋትን ሆን ብሎ እንዲኖር አድርጎታል፡፡ ሥጋቱ እንዲጠፋ ወይም እንዲወገድ አይፈልግም፡፡ ጭራሽ እንዲያውም እንክብካቤ ያደርግለታል፡፡ ሕዝቡ ካልሠጋ በስተቀር እንደማይገዛለት ያውቃልና፡፡

ዐቢይም ይሄንን ቁማር እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ዐቢይን ከወያኔ ነጥየ ዐቢይም ማለቴ ዐቢይ በራሱ የቆመና ነጻ መስሎ ለሚታያቸው ለነ ሲሳይ ዓይነቶቹ ዘገምተኞች ነው እንጅ የኔ እምነት ዐቢይ የወያኔ ተቀጣሪና ትዕዛዝ ፈጻሚ፣ የድርሰቱ መሪ ተዋናይ እንጅ በራሱ የቆመ ነጻ አካል አይደለም!” የሚል እንደሆነ ታውቃላቹህ፡፡ ከስር ከስርም በርካታ ማሳያዎችን እያቀረብኩ ተቀጣሪ ወይም ተዋናይ መሆኑን ሳሳይ መቆየቴን ታውቃላቹህ፡፡

ሲሳይ ሊያውቀው የሚገባ አንድ ቁምነገር ቢኖር ወያኔ የኢትዮጵያን ህልውና መቆመሪያ ማድረጉን ሲቃወም ከቆየ ያንኑ ቁማር ዐቢይ ሲጫወተው ሊደግፍ የማይገባ መሆኑን ነው፡፡ የገረመኝ ነገር ሲሳይ ትናንትና ወያኔ የኢትዮጵያን ህልውና መቆመሪያ ሲያደርገው ሀገር ትፈርሳለችና እንዳትፈርስ ከፈለግን አርፈን ከመገዛት ውጭ አማራጭ የለንም!” ሳይልና ሳይሠጋ ሲቃወም ቆይቶ አሁን ዐቢይ ላይ ሲሆን አማራጭ የለንም ካልሆነ ሀገር ትፈርሳለች!” ማለቱ ነው፡፡

የኢትዮጵያን ህልውና መቆመሪያ እንዳደረጉት እያወቅን የፈጠሩልንን ማሰሪያ ምክንያት ተቀብለን አማራጭ የለንም!” ብለን አርፈን ከተቀመጥን እኛ ተሸናፊዎች ነን፡፡ ትግል ማለት ጠላት በፈጠረው ችግር፣ አደጋ፣ መሰናክልና ሥጋት ሳይበገሩና እጅ ሳይሰጡ ሪስክ ወስደው (አደጋን ተጋፍጠው) በመታገል ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ወይም አደጋ ለማስቀረት ለመከላከል የሚደረግ ፍልሚያ ነው እንጅ ጠላት የሚለውን ነገር እየተቀበሉ፣ የፈጠረውን እንቅፋት ላለመሻገር እየወሰኑ፣ በመሰናክሉ ተደናቅፈው እየወደቁ ትግል ብሎ ነገር የለም፡፡

በግልጽ አማርኛ ሲሳይ ያለው ነገር ምንድን ነው ኦሮሚያ ውስጥ የአንድነት ኃይል ተቀባይነት ስለሌለው የኢትዮጵያን ህልውና ለማስቀጠል ከተፈለገ እነ ዐቢይን ወይም ኦሕዴድን መጠቀም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው!” የሚል ነው፡፡

በየትኛው ጥናቱ መላው የኦሮሞ ሕዝብ የአንድነት ኃይልን እንደማይቀበል እንዳረጋገጠ ግን አላውቅም፡፡ ከኦሮሞ ሕዝብ ከፊሉ እንኳ ፀረ የአንድነት ኃይል አይመስለኝም፡፡ እሱ እንደሚለው የኦሮሞ ሕዝብ የአንድነት ኃይልን ያለመቀበል ደረጃ ደርሶ ከሆነ በኢትዮጵያ የግዛት አንድነት ላይ የተቃጣን አደጋ ለመቀልበስ የተወሰደውን የራስ ጎበና ዳጬን ዘመቻ በዚህ በዘመናችንም አስፈላጊ መሆኑን መናገር፣ ማስተጋባት፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ማዘጋጀት አለበት እንጅ አማራጭ የለንም!” በሚል ሽፋን ሥጋቱን መቆመሪያ አድርገው የሚጠቀሙበትን እነዐቢይ ሳይነኩ እንዲኖሩ ጭራሽም እንድንደግፋቸው መስበክ ማስተጋባት ለዘብተኛ ኦነግነት እንጅ የአንድነት ኃይልነትን ወይም አንድነት አቀንቃኝነትን ፈጽሞ አያሳይም፡፡

ነባራዊ ሁኔታዎች ግድ ካሉና ፀረ ኢትዮጵያ የጥፋት ኃይሎች ከጥፋት ዓላማቸው የማይመለሱ ከሆነ ከዘመቻ ራስ ጎበና ዓይነት ዘመቻ ውጭ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ ለአንድ ሀገር ሕዝብ ሀገርን የመገንባትና የመጠበቅ ተልዕኮ ዘለዓለማዊ ተልዕኮ ነው፡፡ በአንድ ዘመን ተከውኖ የሚጠናቀቅ ተልዕኮ አይደለም፡፡ ይህች ሀገር ነጻነቷን ጠብቃ ለዚህን ያህል ዘመን የቆየችው በዚህ መንገድ ነው በዕድል አይደለም፡፡

ለአቶ ሲሳይ አጌና ያለኝ ጥያቄ ወያኔን ስትቃወም የኖርከው የትግሬ ቡድን ስለሆነ ነበር ወይ??? ችግርህ የሰዎቹ ማንነት ላይ ነው እንጅ ተግባራቸው አልነበረም ማለት ነው ወይ??? ካልሆነ ወያኔ በሕዝብ ላይ ሲፈጽመው የኖረውን ሁሉ ዓይነት ግፍ ዐቢይም ያለክስ የጅምላ እስር በመፈጸም፣ በሐሰተኛ ክስ ዜጎችን አስሮ ማንገላታት፣ በጠራራ ፀሐይ ላይ በአደባባይ ዜጎችን በማስረሸን፣ የአዲስ አበባን መሬት በሕገወጥ መንገድ በማስወረር፣ የዜጎችን የተለያዩ መብቶች በመንፈግ ወዘተረፈ. እየፈጸመ እንዲሁም የወያኔን ከፋፋይና ጠንቀኛ የጎሳ ፌዴራሊዝም (የራስ ገዝ) ሥርዓትን የበለጠ በማጠናከር አዲስ አበባን ለመጠቅለል ሸፍጠኛ ጥረት እያደረገ እየታየ እንዴት ነው ከመደገፍ ውጭ አማራጭ የለም!” ልትል የምትችለው??? ለምን ታዲያ ወያኔንም ከመደገፍ ውጭ አማራጭ የለም!” ብለህ አርፈህ አትቀመጥም ነበር ታዲያ???

አቶ ሲሳይ እነኝህን ጥያቄዎች መመለስ ካልቻልክ እራስህን የአንድነት አቀንቃኝ አድርገህ ባትቆጥር ደስ ይለኛል እዛው ኦነግህ ውስጥ ጠቅልለህ ግባ! የጊዜ ጉዳይ ነው እንጅ መግባትህ የሚቀር አይመስለኝም፡፡ ፈጣሪ ከዚህ አሳዛኝ ውድቀት ይታደግሃ ሌላ ምን እላለሁ?

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com