ቢቢሲ
የኤርትራ ነፃነቷን ካወጀች በኋላ የሁለቱን ሃገራት የንግድ ግንኙነት ምን መልክ ሊኖረው እንደሚገባ በውል ውይይት ተደርጎበት መልክ እንዲይዝ አልተደረገም።
ሁለቱም ራሳቸውን የቻሉ ሃገራት ከሆኑ ከዓመታት በኋላም የሚኖራቸው የገንዘብ ልውውጥ በምን መልኩ መካሄድ እንደለበት ምንም ዓይነት ስምምነት ላይ አልተደረሰም ነበር።
በወቅቱ የሁለቱ ሃገራት ምጣኔ ኃብታዊና የንግድ ግንኙነት በተጠናና ግልጽ በሆነ መንገድ አለመመራቱ ደግሞ ለደም አፋሳሹ ግጭት አንድ መንስኤ መሆኑን በርካታ ጉዳዩ በቅርበት የተከታተሉ ምሁራን ይገልፃሉ። በዚሁም ሳቢያ በተቀሰቀሰው ጦርነት በአስር ሺዎች የሚቆጠር ህይወት ሲጠፋ ሃገራቱ ከ20 ዓመታት በላይ በፍጥጫ ውስጥ ቆይተዋል።
ዛሬስ ሃገራቱ ሰላም አውርደው ድንበራቸውን ክፍት ካደረጉ በኋላ ጠባሳውን ለማሻርና ይበልጥኑም ግንኙነታቸውን ለማደስ በያሚደርጉት ጥረት ውስጥ የምጣኔ ሃብት ግንኙነቱ እንዴት እየተከናወነ ነው?
ድንበሩ በይፋ መከፈቱን ከታወጀበት ደቂቃ ጀምሮ በድንበር አካባቢ ከሚኖረው ህዝብ አልፎ የንግድ ግንኙነት በርካቶችን እየሳበ ነው። ነገር ግን ይህ ንግድ በምን መልኩ ነው እየተካሄደ ነው ያለው የሚለው ጥያቄ አሁን ማነጋገር ጀምሯል።
ማን ምን ይፈልጋል
ኤርትራዊው ገብረመስቀል መኪናውን መቐለ ከተማ መሃል መንገድ ላይ አቁሞ የተለያዩ ጫማዎች ይሸጣል። ጫማዎቹ ከዱባይ የመጡ መሆናቸውንና በምትኩም እሱና መሰሎቹ ደግሞ ጤፍ፣ ብሎኬትና ጣውላ ይዘው ወደ ኤርትራ እንደሚመለሱ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ገብረመስቀል እንደሚለው ድንበር ተከፍቶ የንግድ ልውውጡ እነደተጀመረ የዋጋ ጭማሪ ታይቶ እንደነበርና በአሁኑ ሰዓት ግን እየተረጋጋ እንደሆነ ምሳሌዎችን ጠቅሶ ይናገራል።
“ለምሳሌ አንደኛ ደረጃ ጤፍ እስከ 3300 ናቕፋ ይሸጥ እንደነበር አስታውሶ በአሁኑ ሰዓት ግን 2500 በመሸጥ ላይ ይገኛል። 33 ናቕፋ ይሸጥ የነበረው አንድ ብሎኬት በአሁኑ ሰዓት 25 ናቕፋ ሆኗል፤ ስለዚህ ዋጋው እየቀነሰና እየተረጋጋ ነው” ብሏል።
አቶ ሳምሶን አብርሃ በበኩሉ ከኤርትራ የታሸገ የወተት ዱቄት፣ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች፣ በጎች፣ ጫማዎችና አልባሳት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ፤ በአንፃሩ ደግሞ ጤፍ፣ ፍርኖ ዱቄት፣ ብስኩት፣ ስሚንቶና ሌሎች የግንባታ ቁሶችኘን ወደ ኤርትራ በመጓጓዝ ላይ እንደሚገኙ ያስረዳል።
አቶ ፋሲል መንገሻ የተባሉ ሌላው ኤርትራዊ ደግሞ “የድንበሩ መከፈት ሁለቱንም ህዝቦች አስደስቷል፤ ይህም ሁለቱም ህዝቦች እንደ ልባቸው እንዲገበያዩ አስችሏል። ድንበሩ እንደማይዘጋና የንግድ ግንኙነቱ በምን መልኩ እንደሚቀጥል በቂ ማብራሪያ መሰጠት አለበት” ብሏል።
የገንዘብ ምንዛሬ
ድንበሩ እንደተከፈተና የንግድ ልውውጡ እንደተጀመረ ዛላምበሳ ከተማ ውስጥ ብርና ናቕፋ እኩል አንድ ለአንድ ይመነዘር እንደነበር በወቅቱ በንግድ ልውውጡ ተሳታፊ የነበሩ ሰዎች ይናገራሉ።
በአሁን ግን በተለያዩ የትግራይ ከተሞች የተለያየ የምንዛሬ መጠን እንዳለ ለማረጋገጥ የጠየቅናቸው ነዋሪዎች አረጋግጠውልናል። ለምሳሌም በዓዲግራት ከተማ አንድ መቶ ናቕፋ በአንድ መቶ ሰማንያ ብር ይመነዘራል። ከዓዲግራት ወደ አስመራ በሚወስደው መንገድ ላይ በምትገኘው ቀርሰበር በተባለችው አነስተኛ ከተማ ደግሞ አንድ መቶ ናቕፋ በአንድ መቶ ስድሳ ብር፣ መቐለ ከተማ ውስጥ አንድ መቶ ናቕፋ ሁለት መቶ ብር መድረሱን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሰዎች ገልፀዋል።

የነዳጅ እጥረትና ወረፋ
ድንበሩ ከተከፈተ በኋላ ባለመኪኖች ወደ ሁለቱም ሃገሮች ለመንቀሳቀስ ግማሽ ቀን ብቻ ነው የሚፈጅባቸው። አሁን ላይ አዲስ አበባን ጨምሮ ኢአር የሚል የሰሌዳ ቁጥር መለያ ያላቸው መኪኖች በተለያዩ የትግራይ ከተሞች ማየት የተለመደ ሆኗል።
በተለይም ከኤርትራ የሚመጡ የመኪና ባለቤቶች በነዳጅ እጥረት ምክንያት አብዛኛዎቹ መኪኖቻቸው ቆመው እንደነበረ ይናገራሉ። ይህም ድሮም እጥረት ተለይቶት የማያውቀውን የነዳጅ ገበያ አጨናንቆታል ይላሉ ነዋሪዎች።
በጣም ብዙ ሰዎች ነዳጅ ለመሙላት ሦስት ቀናትን ወረፋ ላይ እንደሚያሳልፉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። በተለይ ባለ ባጃጆች ክፉኛ ተማረዋል። በዚህም ሰርተው የቤትና የባጃጅ ኪራይ ለመክፈል እንደተቸገሩም ይናገራሉ።
ድንበሩ እንደተከፈተ በጣም ብዙ ሰዎች በበርሜልና በጀሪካን ነዳጅ ሞልተው በመኪና በመጫን ወደ ኤርትራ ሲያጓጉዙ እንደነበር አንዳንዶች ያስታውሳሉ። ይህ ደግሞ በነበረው እጥረት ተጨማሪ ጫና መፍጠሩን ያመለክታሉ።
ከምጣኔ ኃብት አንፃር እንዴት ይታያል?
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የምጣኔ ኃብት ምሁር ዶ/ር ተስፋማርያም መሓሪ “አሁን ላይ እየታየ ያለው ግኑኝነት ጊዜያዊ ነው፤ መደበኛም አይደለም። ቢሆንም የንግድ ግንኙነቱ ሕጋዊ አሰራር ካልተከተለ አለመስማማትን ይፈጥራል” ሲሉ ያላቸውን ስጋት ይናገራሉ።
ዶ/ር ተስፋማርያም የቀደመው ጦርነት መነሻን አሁኑ ካለው ሁኔታ ጋር ያመሳስሉታል። “በወቅቱ ሁለቱ ሃገራት አዲስ የገንዘብ ኖቶችን ማሳተማቸው፣ የገንዘብ ምንዛሬ መጠንና የሚገበያዩበት ገንዘብ ለግጭቱ መንስኤ እንደነበረ መታወቅ አለበት” ሲሉ እምነታቸውን ይገልፃሉ።
ስለዚህ ከዚህ በኋላ ተመሳሳይ አለመግባባትና ግጭት እንዳይፈጠር ከወዲሁ ሕጋዊና መደበኛ አሰራር ላይ አጽንኦት ተሰጥቶ መስራት ይኖርበታል ሲሉ ይመክራሉ ዶ/ር ተስፋማሪያም።