Friday, October 19, 2018
ታዋቂው የሥነ ልቡና ምሁር ሮልፍ ዶብሊ ‹አጥርቶ የማሰብ ጥበብ› በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ይላሉ፡፡ እንበልና አንተ የመድኃኒት አስተዳደር ኃላፊ ነህ፡፡ ለረዥም ግዜ ታምሞ የአልጋ ቁራኛ ለሆነ ሰው የሚሰጥን መድኃኒት በተመለከተ እንድትወስን ቀረበልህ፡፡ መድኃኒቱ ከባድ የሆነ የጎንዮሽ ችግር አለው፡፡ ከሚወስዱት መካከል 20 በመቶዎቹ ሊሞቱ ይችላሉ፡፡ 80 በመቶዎቹን ደግሞ የማዳን ዕድል አለው፡፡ ይህን መድኃኒት ሰውዬው ይውሰድ ወይስ አይውሰድ? የሚለውን ጉዳይ እንድትወስንበት ፊትህ ላይ ቀረበ፡፡
ብዙዎች ይላሉ ሊቁ ከአምስት ሰዎች አንዱን የሚነጥቀውን ይህንን መድኃኒት ሰውዬው ይውሰድ ብለው ለመፈረምን ይፈራሉ፡፡ በሰው ሞት ላይ መፈረም ወይም በሰው ሕይወት ላይ መፍረድ አድርገው ይቆጥሩታልና፡፡ በቶሎ የሚታያቸውም 20 በመቶ ሰዎችን ይጎዳል የሚለው እንጂ 80 መቶ ሰዎችን ይጠቅማል የሚለው አይደለም፡፡ ምናልባትም ከመድኃኒቱ በኋላ ሰውዬው ቢሞት ሚዲያውም ሆነ ሰዎች የሚያወሩት ወሬ የሚገድል መድኃኒት ወስዶ መሞቱን የሚገልጥ ሊሆን ይችላል፡፡ ምናልባትም ባንተ ውሳኔ መድኃኒቱን የወሰዱ ተከታታይ ሦስት ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ በአንተም፣ በሆስፒታሉም፣ በታካሚዎቹም ሆነ በኅብረተሰቡ ዘንድ ‹ለምን ወሰነ? ለምን አይተወዉም ነበር? ለምን አይቀርበትም?› የሚሉ ጥያቄዎችን ሊያስነሣ ይችላል፡፡ እነዚያ በተከታታይ ሞትን የቀመሱት ወገኖች ከጠቅላላው ውጤት 20 በመቶው ውስጥ መሆናቸውን የሚመለከት አይኖርም፡፡
ይህ ነው ሰዎችን ከዝምታ ይልቅ ተግባርን እንዲፈሩ የሚያደርጋቸው፡፡ ሮልፍ ዶብሊ ይህን ሁኔታ በኛ ብሂል ‹መተው ነገሬን ከተተው› ወይም በእርሳቸው ቋንቋ ‹the omission bias› ይሉታል፡፡ የማይወስንና የማይሠራ ከሚወስንና ከሚሠራ ሰው ይልቅ የተሻለ ነገር እንዳደረገ የሚቆጠርበት አዝማሚያ ነው፡፡ ከሚመጡ ሚሊዮን መልካም ውጤቶች ይልቅ የሚከሠቱ አንድ ሺ ስሕተቶችንና ጥፋቶችን አጉልቶ በመመልከት ‹ቢቀርስ› የሚል ውሳኔ፡፡
ሊቁ፡-
እመ ተናገርኩ ጽድቀ ሰብአ ዛቲ ዓለም ይጸልዑኒ፣
(እውነትን ብናገር የዚህ ዓለም ሰዎች ይጠሉኛል)
ወከመ ኢይንብብ ሐሰተ ኩነኔ ዚአከ ያፈርሀኒ፣
(ሐሰትንም እንዳልናገር የአንተ ፍርድ ያስፈራኛል)
እም ኩሉሰ አርምሞ ይኄይስ ወይሤኒ…
(ከዚህ ሁሉስ ዝምታ ይበልጥብኛል፣ ይሻለኛል)
ያለው ቅኔ ይህን በሚገባ ይገልጠዋል፡፡
አንዳንድ እናቶች ልጆቻቸውን ለምን እንደማያስከትቡ ሲጠየቁ ‹ልጄ ሲከተብ ይታመምብኛል፤ የእገሌም ልጅ ታምሟል› ይላሉ፡፡ ክትባት ልጆች በበሽታ የመያዝ ዐቅማቸው የሚጨምርላቸው ቢሆንም አነስተኛ በመሆነ መጠን ግን በክትባት ምክንያት የሚታመሙ ልጆች አሉ፡፡ ልጆቻቸው በክትባት ምክንያት ከሚጠቀሙት ሚሊዮን ሕጻናት ወገን ከሚሰለፉ ይልቅ ከሚታተሙት መቶ ሕጻናት ጋር ሊሰለፉ ይችላሉ ብለው ይፈራሉ፡፡ ከዚህ ሁሉ ጭቅጭቅ መተው የተሻለ ምርጫቸው ነው፡፡ አጠቃላዩን ነገር አያዩትም፡፡ ውሳኔያቸው ሊያስከትል ከሚችለው መልካም ውጤት ይልቅ ሊያመጣ የሚችለውን ፈተና ይፈሩታል፡፡ ክትባት ልጆችን ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰብንም ከበሽታ የሚጠብቅ ነው፡፡ በክትባት ምክንያት በሽታን የመቋቋም ዐቅም ያዳበረ ልጅ ሌሎችን በሽታ አይበክልም፡፡ ነገር ግን ይላሉ፡፡
ተግባር ከዝምታ በላይ ይጮኻል፡፡ ለዚህም ነው ምንም የማያደርጉ ሰዎችን እንደ ጨዋዎች የምንቆጥራቸው፡፡ እየሠሩ ከሚሳሳቱ ሰዎች ይልቅ ተቀምጠው ምንም ያልተሳሳቱ ሰዎችን እንመርጣለን፡፡ ስሕተት በራሱ የመጮህ ኃይል አለው፡፡ የዜና ሰዎች ‹መጥፎ ዜና ምርጥ ዜና ነው – bad news is good news› የሚሉት ለዚህ ነው፡፡ ሰዎች መጥፎ ዜናዎችን ጆሯቸው ቀስረው ስለሚሰሙ፡፡ ጥቂት ስሕተቶችም ሚሊዮን በጎ ሥራዎችን የመሸፈን ኃይል አላቸው፡፡ በመጠኑ ካንተ የሚያንስ አቧራ አንተን ሊሸፍንህ ይችላል፡፡ በውሳኔያቸውና በተግባራቸው ምክንያት ስሕተት የሠሩ ሰዎች ባለማድረጋቸውና ባለመወሰናቸው ምክንያት ስሕተት ከሠሩ ሰዎች በላይ ይወቀሳሉ፡፡ ተግባር አሰምቶ ይጮኻል እንዲሉ፡፡ 80 በመቶዎቹን ያዳነው መድኃኒት በሞቱት 20 በመቶዎች ምክንያት ይወቀሳል፡፡
ዛሬም በሀገራችን ውስጥ የማንፈልጋቸው፣ የምንቃወማቸው፣ የምንተቻቸውና የምንታገላቸው ድርጊቶች ይደረጋሉ፡፡ ከትናንቱ እንዲሻሉ የምንጠብቃቸው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የፍትሕና የአስተዳደር ውሳኔዎችና ተግባራት ሳይሻሻሉ እናያቸዋለን፡፡ እነዚህ ግን የተሠሩትን በጎ ነገሮች እንደ አቧራው ሊሸፍኑብን አይገባም፡፡ የመድኃኒት ሞያተኞች ምንም ዓይነት የጎንዮሽ ችግር የሌለበት መድኃኒት ሊፈለስፉልን አይችሉም፡፡ ይህንን ማድረግ የሚችለው ራሱ መድኃኒት የሆነው ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡ የጎንዮሽ አደጋውን ግን ከጊዜ ወደጊዜ እየቀነሰ እንዲሄድ ይመራመራሉ፡፡ መሪዎችም ለማድረግ የሚችሉት ይሄንኑ ነው፡፡ ምንም ዓይነት ስሕተት የሌለበት፤ ሁሉን ሊያስማማ የሚችል፤ ሁሉን በሽታዎች የሚያክም ነገር ሊሰጡን አይችሉም፡፡ በየጊዜው ግን ይህንን የጎንዮሽ ችግር እየቀረፉ መሄድ አለባቸው፡፡
የአንዳንድ መድኃኒቶችን የጎንዮሽ ችግር ለመቅረፍ የታካሚው ዝግጅትና ትብብርም ወሳኝ ነው፡፡ ከሕክምናው በፊት በስፖርት የዳበረ፣ በምግብ የጠነከረ፣ ከሱስ የጸዳ፣ ከክፉ ልማድ የታቀበ ከሆነ የመድኃኒቱን የማዳን ኃይል ይጨምረዋል፡፡ ከሕክምናውም በኋላ ተገቢውን ምግብ ከተመገበ፣ መመገብ ከሌለበት ከታቀበ፤ መድኃኒቱ አዎንታዊ እንዲሆንና አሉታዊ ተጽዕኖው እንዲቀንስ ለማድረግ ይችላል፡፡ የመሪዎች ውሳኔ የጎንዮሽ ችግሩ እየቀነሰ እንዲሄድ መድኃኒቱ ይበልጥ እንዲሠራ የሚያግዝ ሕዝብ ይፈልጋል፡፡ ጊዜያችን፣ ጉልበታችንና ዕውቀታችን መሠዋት ያለበት መድኃኒቱን ይበልጥ እንዲሠራ በሚያስችለው ላይ ነው፡፡ በቀዶ ጥገና የተገኘው ጤና ምክልት የለውም፡፡ በቀዶ ጥገናው ጊዜ የተቀደደው ሆድ ግን የቁስሉ ምልክት ብዙ ዘመን ይኖራል፡፡ ከመልካሙ ነገር ይልቅ ሕመሙ ምልክት የመተውና የመታወስ ዐቅም አለው፡፡ በሀገራችንም ከተፈጠረው አዎንታዊ ነገር ይልቅ አሉታዊው የመታወስ ዕድሉን እየተጠቀመ ነው፡፡
መሪዎች የሚወስኑት ውሳኔና የሚፈጽሙት ተግባር የሚያስከትለውን ችግር ብቻ ሳይሆን ያመጣውንም ውጤት መመዘን አለብን፡፡ ለመልካሙ ውጤት የምንሰጠው ዋጋም ሆነ ለስሕተቱ የሚኖረን ቅሬታ በልኩ መሆንም አለበት፡፡ ለሰዎች የመሳሳት መብት የማንሰጥ ከሆነ ‹መተው ነገሬን ከተተው› ወደተባለው ዋሻ ይገባሉ፡፡ ይህ ደግሞ ከሁሉም በላይ አደገኛ ነው፡፡ በዝምታና በመተው የተፈጠረን ችግር ማንም አያየውምና፡፡ ዝምታና መተው ዜና የመሆን ዕድላቸው እጅግ አነስተኛ ስለሆነ፡፡ በሌላውም በኩል የዕቃ ዕቃ ጨዋታ ይመስል ‹ወጥቼበታለሁ› ዓይነት ‹ነገርን የመክተት አባዜም አዋጭ አይደለም፡፡ በርግጥ ማድረጋችን ከዝምታችን በላይ ወጭ ያስከትልብናል፡፡ ድርጊት የሚያመጣውን ውጤት ያህል ግን ዝምታ እና መተው አያመጡልንም፡፡ ስሕተቱንም እየነቀስን በጎውን እያበረታን እንቀጥላለን እንጂ ነፋሱ ሻማዋን ሲያጠፋት በዝምታ ማየት የለብንም፡፡ ወይ እንደፋኖሱ ነፋሱን እንከልላለን ወይ እንደ ብልኋ ሴት ዘይትና ፈትል እንጨምራለን፡፡