“ነፃነት ከመንግስት ወይም ከመሪዎቻችን በስጦታ የምናገኘው ሣይሆን በየቀኑ በግልና በሕብረት በይዞታችን ስር የምናደርገው የባለቤትነት ይዞታ ነው” (“Freedom is not a gift received from the State or leader, but a possession to be won every day by the effort of each and the union of all.” (አልበርት ካሙ – Albert Camus)
ሰሞነኛው በጠ/ሚ አቢይ ላይ የተከፈተው የፌስቡክ ዘመቻ አሳስቦኛል። ይህ ባለብዙ ፈርጅ ዘመቻ በሚገርም ሁኔታ የተከፉና ወደ ሥልጣን ለመመለስ ያኮበኮቡ ወያኔዎችን፣ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተሰለፉ ኦነጋውያንና በጎሣ ፓለቲካና ብሔረተኝነት የተቃኙ “የአማራ” አክቲቪስቶችን በስፋት አሣትፎ “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” ግንባር ሥር ገዳይና ሟችን በአንድ ማዕድ አሠባስቧል። “በተደመሩ’ግለሰቦችና ሃይሎች ላይ የጣምራ ጦር ሠብቀው አካኪ ዘራፍ የሚሉ የድል አጥቢያ አርበኞች ሆነው ቀርበዋል። የወያኔን እጅ ሥራ እያየሁ ነው። ቅንስናሾች በተደመሩት ላይ የሚያናፉበት የሞራል ብቃትም የላቸውም። ጥያቄው ያለው ‘በመደመርና ባለመደመር’ ውስጥ አይደለም:: የተደመረው “ቂል” ያልተደመረው “ብልህና ዛሬን ትላንት ያየ” መሆኑ ላይ አይደለም:: መፍትሄው የመደመሩን ትርፍና ኪሣራን ከማስላት ላይ ነው:: መደመሩ የጠ/ሚ ቤተሰብ ጋር ሣይሆን ኢትዮጵያን ለማዳን ከኢትዮጵያውያን ጋር ነው። ድምሩ ውስጥ አደፍራሾች አልገቡም አላልንም። ነገር ግን ወርቅ የሚገኘው ከአፈር ጋር ነው። ገንቢ ትችትን ማቅረብ ወንጀል አለመሆኑን እረዳለሁ። ችግሩ ግን ሌላ ነው። መዘዙ የከፋ ነው።
ሎሪ ደሽን “ከመፍረዳችን፣ ከመገመታችን፣ ከማውገዛችንና በግንፍልነት ከመቧረቃችን በፊት ረጋ ማለትን እንለማመድ። ረጋ ማለት በተናገርነውና በምናደርገው ቃልና ተግባር ሁሉ በሁዋላ ከመፀፀት ያድነናል።” ትላለች።
ሀ). ችግሩ ያለው የት ላይ ነው?
ጠ/ሚ አቢይና ቡድናቸው ለኢትዮጵያዊነት ጥሪ ሲያቀርቡ አንደመርም ፤ ለእርሣቸው ማህበራዊ መሠረት አልሆንም እየተባለ ከእርሳቸው ምን እንደሚጠበቅ አልገባኝም። በየቀኑ የፌስቡክ የተከታዮችን ቀልብ ለመግዛት ከእውነትና ከምናምንበት ውጭ የባህሪ ጥቃት (character assassination or ad hominem argument) ማፋፋሙ ነው:: መሪዎቹን በማብጠልጠል ወደ አክራሪው ጎራ ጠቅለው እንዳይገቡ በዘዴና በብልሃት መያዝ አለመቻሉ ነው::
1. ጠ/ሚ አቢይን የማወግዘው የአዴፓ አባላትን ሚኒስትር አድርገው ባለመሾማቸው አይሆንም። ጠ/ሚ አቢይና ቡድናቸው ዴሞክራሲያዊ ሐገር አልሰጡኝም ብዬም አይደለም። ወይም በዴሞክራሲያዊ መንገድ ያልተመረጡ የፓርላማ አባላትን ዴሞክራሲያዊ ባለማድረጋቸውም አይደለም።
2. ጠ/ሚ አቢይንና “የጎሣ ፌደራሊዝምንና አቢዮታዊ ዴሞክራሲን” የምናወግዘው በጎሣ ፓለቲካ እንክርዳድ ሠክረንና የጎሣ ብሔረተኛ በመሆን አይደለም። ከአንድ ባህር ለተቀዱ የጎሣ ፓለቲከኞች የተለያየ መስፈርት አስቀምጠንም እይደለም።
3. ጠ/ሚ አቢይን የማወግዘው መንግስታቸውን ኦነጋዊ እያደረጉ ነው ብዬም አይሆንም። እኔ የማወግዛቸው ኢትዮጵያዊ ሕብረት የሚፈጥሩ ሃይሎችን በኦነጋውያን እንዲረቱና እንዲጠቁ መንገድ ከከፈቱ ብቻ ነው። ከዴሞክራሲያዊው ሽግግር ሲያፈነግጡ ነው።
4. ጠ/ሚ አቢይን የማወግዘው ከሁለት ዓመት በሁዋላ ይደረጋል ያሉት ምርጫና የምርጫው ተዐማኒነት ሲጣስ ብቻ ነው። እኔ የማወግዛቸው ለዚህ ምርጫ ግብዐት የሆኑ ገለልተኛ ተቁዋማትን ለማነፅ አሻፈረኝ ካሉ ነው። ዴሞክራሲያዊ ሃይሎችን መውጋት ከጀመሩ ነው።
ለ). መውጫ መንገዱ በየት ነው?
ይህን የተፈጠረውን ጠባብ ዕድል ተጠቅሞ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር የሚከሰትበትን መንገድ ማሣየትና መላ ማዘጋጀት ላይ ነው::
መፍትሄው ያለው “የጎሣ ፌደራሊዝም” በዴሞክራሲያዊ ሥርዐት ለመተካት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማድረጉና ይህም እንዳይኮላሽ መስራቱ ላይ ነው:: በታየው የለውጥ ጭላንጭል ውስጥ ገብቶ ዴሞክራስያዊ ፉክክር በማድረግ ዴሞክራሲያዊ ሐገርን መገንባቱ ላይ ነው። ይህን የተፈጠረውን ጠባብ ዕድል ተጠቅሞ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር የሚከሰትበትን መንገድ ማሣየትና መላ ማዘጋጀት ላይ ነው:: መቃወምና የሠላ ትችት ማቅረብ የሚቻለው ይህ ቃል ሲታጠፍ ነው።
ሐ). ያልገባኝ ጉዳይ ይህ ነው!
ጠ/ሚ አቢይና መንግስታቸው በርካታ ስህተቶችን ሠርቷል። ይህን ተችተናል። ውግዘቱን በማፋፋም መንግስታቸው ቢፈርስ ሐገሪቷን ከመበታተንና የኦነግ መጨፈሪያና የወያኔን ህልም ከማሳካት የዘለለና ይህ ገቢር እንዳይሆን የተችዎቹ መውጫ እስትራቴጂ ምንድነው?
ሕብረት ጠልተን፣ ሕብረ-ብሔራዊ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን አብጠልትለንና የባለብዙ ጠላትና የጦር ግንባር በመክፈት ውጊያን መምረጥ ጦርነቱ ሣይጀመር መሸነፍ ነው። ብቸኛ መፍትሄውም በኢትዮጵያዊነት ፀንተን በመቆምና ሐገራዊ ሕብረት በመፍጠር አደጋውን መቀልበሱ ላይ ነው::
መገንዘብ ያለብን ሁላችንም የውዲቷ ሐገራችንን መቃብር ከገዳዮቿ ጋር ሳናውቀው ወይም በማወቅ አብረን ጉርጉዋድ እየቆፈርን ነው።
Face the following:-
I can see a strong accord among anti-Ethiopian tribal centrifugal political forces merging together to bring about disintegration of Ethiopia. Bear in mind that we are slowly sleep waking in to an all round ethnic war. Act responsibly & do the right thing before it’s too late. Waging a smear campaign is not the answer. If not, we are paving way for the fulfillment of the long awaited dream of tribal politicians. Knowingly or unknowingly we are currently facilitating their cause by serving them as enzyme.
መፍትሄ አልባ ነቆራ እንኳን መላ መላምት አይደለም።
እንደ ሐገር ብቻ ሣይሆን እንደ ሕዝብ የምንጠፋበትን ቦይ እየቆፈርን ነው!
ሞት “ለጎሣ ፌደራሊዝምና አብዮታዊ ዴሞክራሲ”!
@@××@@
Reminder!
I rather have no likes than writing lies, unverified gossip & hogwash just to secure more thumbs.
Faith & principle matter most to me.