የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ኢትዮጵያ አቀፍ የዜግነት የፖለቲካ በሚል በደምሳሳው ተጠቅሞበታል:: ጽሁፉ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት በቲም ለማ ፖለቲካዊ የለውጥ ጉዞ ከየት ተነስቶ ወደየት እነደደረሰ በአጭሩ ይመለከታል:: ጽሁፉ ከወያኔ የአንድ ብሄር የበላይነት የአፈና ስርአት ለመላቀቅ በተደረገው  የለውጥ ሂደት የትግል ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት የተጫወታቸውን ሚና: አሁን የደረሰበትን የእድገት ደረጃና ለሀገሪቱ መጽአዊ የሉአላዊነትና ዲሞክራሲያዊ ጉዞ ያበረከተውን  ለወደፊትም ሊያበረክት የሚችለውን ሚና ይመለከታል::

ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት በቲም ለማ  የለውጥ ጉዞ ያለበትን ደረጃና የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ   ለመመልከት ይረዳን ዘንድ ይህንን የለውጥ ጉዞ በሶስት ከፈለን እንመልከት

1-ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት በህዝቡ ብሶትና ምሬት የተካሔደውን ብዡ ዋጋ ያስከፈለ የተናጥል ትግል ወደውጤታማ ሀገር አቀፍ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ያሳተፈ ተሰፋ ሰጪ የቲም ለማ የለውጥ ጉዞ ቅርጽ እንዲይዝ አድርጕል::

የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ኢትዮጵያዊ አንድነትን “ማንነትን የጨፈለቀ መሰረት ያለው አሐዳዊ ስርአት ግንባታ ሂደት ነው” በማለትና  ፌደራል ስርአትም በጎሳ ላይ የተመሰረት ስርአት ብቻ ነው በሚል ድንግዝግዝ መነጽር የሚመለከቱትን ቡድንች በአጽኖት ይቃወማል:: እነዚህ ቢድኖች ሆን ብለው የልዩነት ዘር ፍሬ እንዲያፈራ የሚሰሩ “ኢትዮጵያ ያለብሔር አደረጃጀት መቀጠል አትችልም” በሚል ጭፍን ሐሳብ ለይ ተመርኩዘው  የሚጋዙትን በተጻራሪነት ይመለከታል ሃሳባቸውንም ይሞግታል::

በወያኔ የዘር አደረጃጀት ተከፋፍለው የለውጥ ትግል ጉዞውን ከራሳቸው ህዝብ ብሶት አንጻር በተናጥል ትግል ውስጥ የነበሩትን ወጣት ጸረ ወያኔ ታጋዮች ለተሻለ ሐገር አቀፍ ተስፋ ሰጪ ጠንካራ  የለውጥ ጉዞ የመድረሳቸውና ወያኔን የመፈረክረካቸው ምስጢር የቲም ለማ ምስረታ ነው:: ቲም ለማ ደግሞ ኦቦ ለማና ዶ/ር አብይን ከኦፒዲኦ እነአቶ ገዱን ከብአዴን እነወ/ሮ ሙፈርያትን ከደህዴን ብስለት ባለው ኢትዮጵያዊነት ባያጣምር ኖሮ የዶ/ር አብይ ጠቅላያችን የመሆን ስኬት መና ሆኖ ይቀር ነበር:: የእነዚህን ትንታግ የለውጥ መሪዎች ህዝብን የማዳመጥ ብቃትና የወያኔን ዘረኝነት ከህዝቡ ጋር አብሮ በመጥየፍ  “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው”  “ኢትይጵያዊያን ታላቅ ህዝቦች ነበርን ታላቅም እንሆናለን” በሚል ጉዞ የባህርዳር ውጣቶችን“ የኦሮሞ ደም ደሜ ነው”ን የትግል አርማ የኦሮሞ ወጣቶችን የእምቦጭ ለቀማ የጣና ጉዞ በማዳመጥ ኢትዮጵያዊ ዜግነትን ያማከለ ጉዞን ባይከተሉ  ኖሮ  ይህን ሁሉ ኢትዮጵያ አቀፍ ተቀባይነት ባለገኙም ህዝቡንም ታላቅ ኢትዮጵያዊ ተስፋ ወዳለውጥ ባልመሩትም ነበር:: ይህን  ስንመለከት ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት በቲም ለማ የለውጥ ጉዞ የለውጥ ጉዞ ውስጥ የነበረውን ጉልህ ድርሻ እናያለን:: የዶ/ር አብይ ተወዳጅ የለውጥ መሪነት ትልቁ ምስጢር ኢትዮጵያ አቀፍ የዜግነት ጉዞ ለመሆኑ መረጃ ማሰባሰብ የማይሻ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚያውቀው ሀቅ ነው

ቲም ለማም ቢሆን ይህንኑ የቀን ጅቦችን ቅስም የሰበረ ሐገር አቀፍ እውነታ ለአፍታ ሊዝዘነጋውም ሆነ በምንም ጊዜ አመጣሽ ሀይል ጫና ሊለውጠው  የማይገባ እውነታና  ለምንወዳት ሐገራኝችን ብቸኛና ዘላቂ መፍትሔ ነው::

2-ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት አሁን ባላአንበት የለውጥ የእድገት ደረጃ ያለው ወቅታዊ አቍዋም::

ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ባለንበት ጊዜ እስካሁን ያበረከተውንም ሆነ ወደፊትም ሊያበረክት የሚችለውን ወሳኝ ድርሻ የሚመጥን ትኩረት ያላገኘበት ወቅት ላይ ይገኛል::

ኢሀድጋውያን ሳይቀር የደሰኮሩትን በወያኔ 27 አመት “የልዩነት ፖለቲካ ትኩረት  መሰጠት ህዝቡን ከፋአሎታል” ያሉትን መሰረታዊ ሀሳብ ወደጎን በመተው የኦሮሞ አክራሪ ብሔርተኞችን  በኢትዮጵያ ብሔርተኞች ላይ እንዲጎለብቱ የተደረገበት ጊዜ ውስጥ መገኘታችንን የሚጠቁሙ ብዙ ምልክቶችን በምናይበት ጊዜ ውስጥ እንገኛለን::  ለዚህም ማሳያ የሚሆነን  የኢትዮጵያን ባንድራ ይዘው የሀገራዊ አንድነትን ባቀነቀኑ የአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ እስርና እንግልት እንዲያደርሱ  በአዲስ አበባ ላይ የተሾሙት የጊዜው ሹመኞችን ስራ መመልከት ነው:: እነዚህ በዘረኝነት የሰከሩ ሹማምንት ቡራዩ ላይ ጭፍጨፋ የፈጽሙትን ወንጀለኞች በተቻላቸው መጠን ብዙ አሉታዊ በሆነ መልኩ ሲተነትኑ አይሰሙም:: የአንድነትና የአብሮ መኖር ተምሳሌቱን አዲስ አበቤ በጅምላ ወደጦላይ ያጋዙ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ዋና ከተማ ዘረኛ መሪወችን እኩይ ስራ  የምናይበት  የቆየው አንድነትና አብሮ የመኖር እሴት “ተረኛ ነን” የሚሉ  ስግብግብ ዘረኞች  የሚፉዋልሉበት ጊዜ ላይ እንገኛለን:: እነዚህ እኩይ የዘር ፖለቲካ አራማጆች የቲም ለማን ኢትዮጵያዊ የለውጥ ጉዞ እጅ ጥምዝዘው  ለመጣል ተግተው ይሰራሉ:: የቀረው ህዝብም በነዚህ ሀይሎች  ግርግር ብዥታ ውስጥ የሚገኝ መሆኑ እሙን ነው :: እውንትና ንጋት እያደረ ይጠራል እንዲሉ ዘር እንደወይንጠጅ ያሰከራቸው ዘመዶቻችን ስካር እስኪላቃቸውና የለውጡም ጉዞ ሳይደናቀፍ በታላመለት መሰመር እንዲቀጥል መትጋት አማራጭ የሌለው  ጉዳይ ነው::

የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ  ይህ የኢትይዮጵያዊ ብሔርተኝነት ጉዞ በብዙ ደንቃራ ቢተበተም ጉዞው ሩቅ ግብ ያለው ሰላማዊና ሀገር አቀፋዊ መሰረትን ይዞ መቀጠሉ በጥላቻ ስሜት ትኩሳት የነደደውን የዘር ጉዞ የሚያሰክን ብቸኛ የሐገር ሉአላዊነት ማስተማመኛ መንገድነቱን በመረዳት ትግሉን በተቀላጠፈ መልኩ መቀጠሉ ወሳኝ ነው  ይላል  ::

ታሪክ ላይ ያተኮረው ስለብሔር በደል በማውራት ነገን የዘነጋ ትርክት አራማጆች ጊዜ ያስገኘላችውን አጋጣሚ ከመከተል  ባለፈ ድልድዮን የመስራት ጥበብ ያልተሰጣቸው  መሆኑን በመገንዘብ ኢትዮጵያዊ ዜግነትን  መሰረት  ያደረገ ጉዞ ዞሮ ዞሮ ህዝባችንን ከጥፋትና ከተጨማሪ ደም መፋሰስ የመታደጊያ ብችኛ መፍትሄ መሆኑን ማጤን በሁሉም ጎራ ለተሰለፉት ትኩረትን ያሚያሻ ጉዳይ ነው::

3- የኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት መርህ ለሐገራችን መጽአዊ ሰላማዊ የመደመርና የአንድነት ብሎም በዜግነት መብትና ግዴታ ላይ የተመሰረተ የህዝቦች ተቻችሎና ተፋቅሮ የመኖርን: ዜጎች በያትኛውም የሐገሪቱ ክፍል የመኖርና በዘረኞች ያለመፈናቀልን ነጻነት የህግ ከለላ ለማረጋገጥ መተኪያ የሌለው ወሳኝ ድርሻን ይጫውታል::

በዚህ መሰረታዊ ሐሳብ ስር ሊሰመረበት የሚገባው ነገር አሁን ሰፋሰፋ ያሉት የዘር አቀንቃኞች ስኬት ማለት ወርዶ ወርዶ ዶ/ር መራራ ማታማታ አማራ ሚስቱን አቅፎ ኦሮሞ ኦሮሞ ይላል እንዳሉ:  ይህ መርዛም ጉዞ ነገ  ወደታች  ሲወርድ  በግል ህይወታችን እንደሚመጣ ማሰቢያ ጊዜ አሁን ነው:: በየክልሉ በዘራቸው ምክንያት ለተፈናቅሉትም ሆነ በቀጣይ በቀን ጅቦችም ሆነ በሌሎች አክራሪ ዘር ተኮር አቀንቃኞች ውጥን ተጨማሪ የዘር ማጽዳት ክልላዊ እንቅስቃሴዎች መቆም ብችኛው መፍትሔ ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነት ላይ የተመረኮዘ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩል የሚያስተዳድር ስርአት ምስረታ ነው:: ይህም የአስተዳደር ስርአት ዘርን መሰረት ያላደረገ ፌደራላዊ ስርአት ሆኖ  እንዲቀጥል መስራት የሐገሪቱ ምሰሶ እንደጠላት ምኞት ሳይወድቅ በፊት ከወዲሁ ተግባራዊ የለውጥ ጉዞ ለማድረግ ይበጃል::

ቲም ለማም ሳይውል ሳያድር ህዝብ በተገነዘባችሁ የሞራል ደረጃ ለኢትዮጵያዊነት ባደባባይ የገባችሁትን ቃል በማክበር የታለመውን የለውጥ ጉዞ በታቀደው ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት መስመር እንደምታራምዱት ተስፋ በማድረግ የህዝባችሁ የአደራ ቃል ደጋግሞ ማስታወሱ ወቅቱ የሚጠይቀው ተገቢ አበይት ጉዳይ ነው::

እንደማጠቃለያ: ኢትዮጵያ በብዙ ነጹሃን ጀግኖች ዜጎች ደም የተገነባች መሆኑዋን ለወዳጅም ለጠላትም ደጋግሞ ማሳሰቡ ተገቢ ነው:: የብዙ አንጽባራቂ እድሜ ጠገብ ታሪክ ባለቤት ኢትዮጵያ በታሪክ ብዙ የአንድነትና የህልውና ፈተናወችን ያሳለፈችው በልጆችዋ ህብረትና ጠንካራ መተሳሰር ነው:: የኢትዮጵያን ታሪክ ደካማ ጎኖች አጉልቶ አእላፍ አለምን ያስደመሙ እንቁ ታሪኮችዋን ጥላሸት በመቀባት የህዝቦችዋን ዘመናት ያስቆጥረ አንድነት ፈቶ ለመግጠም መሞከር ለሁሉም ኢትዮጵያዊ አደጋ ያለው ጅልነት ነው::

በዘመናችን ያለብንንም የዘርና መከፋፈል ችግር የምንወጣው በጽናትና በህብረት በመቆም የዘር ግንድ ካለያያችው ቀደምት አባቶቻችን የተጋድሎ ታሪክ ኢትዮጵያዊ  ኩራትን “ከድር ቢያብር አንበሳ ያስር” አስተምሮአቸው አንድነትና ህብረትን ተምረን የተፋጠጥነውን የፍቅርና አንድነት ፈተና ለልዩነታችን ከአንድነታችን የበለጠ ትኩረት ሳንሰጥ በመታገል ነው::