በአገራችን ፈጣን የሆነ የፖለቲካ ለውጥ አለ፡፡ የሚታየው የፖለቲካ ለውጥ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን በመመሥረት ይቋጫል ወይስ ተንገራግጮ ይቆምና ሌላ አምባገነናዊ አገዛዝ ይቀጥላል? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡

በገዥው ግንባርና በመንግሥት ደረጃ በሚታየው ለውጥ ላይ ብናተኩር፣ በእኔ አስተያየት ኢሕአዴግ ውስጥ የመጣው ለውጥ ተጻራሪ (paradoxical) ባሕርይ ያለው ነው፡፡ በአንድ በኩል ኢሕአዴግ የሚባለው የፖለቲካ ድርጅቶች ግንባር እና ግንባሩ የሚመራው መንግሥት አሁንም በሥልጣን ላይ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም አሁን በአገራችን የሚታየውን ለውጥ ያመጡት ኢሕአዴግና ኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት ሳይሆኑ በድርጅቱ ውስጥ ይህ ነው የሚባል እውቅናና ተሰሚነት ያልነበራቸው ግን ደግሞ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ያነገሠው ፈላጭ ቆራጭ አምባገነናዊ ሥርዓት ለአገርና ለሕዝብ እንደማይበጅ የተገነዘቡ የሕዝብ ተቆርቋሪ የሆኑ ጥቂት የለውጥ መሪዎች ናቸው፡፡ የለውጥ መሪዎቹ ለሕዝብ እየቀረቡ ያሉት በኢሕአዴግ አባልነታቸው ቢሆንም ከልብ ኢሕአዴጋዊያን ያልሆኑ ኢሕአዴጎች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

በእርግጥ የለውጥ ራዕያቸውም ሆነ መንፈሳቸው እስካሁን እየናኘ ያለው ኢሕአዴግ በሚባለው አቁማዳ ውስጥ ነው፡፡ ወደፊት የለውጥ ራዕያቸውና መንፈሳቸው ተቋማዊ ሲሆን ኢሕአዴግ በሚለው አቁማዳ ይቀጥላሉ ወይስ አይቀጥሉም? የሚለውን የምናየው ይሆናል፡፡

ለውጡ እንዲቀጥልና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን በማዋለድ እንድጠናቀቅ የምንፈልግ ኢትዮጵያዊያን ከፍ ያለ ተስፋ የሰነቅን ቢሆንም ይህንን ተስፋችንን የሚያደበዝዙ አደገኛ አዝማሚዎችን ደግሞ እየታዘብን ነው፡፡

ዘውግ ተኮር ግጭቶችና መፍትሔዎቻቸው
***
በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች እየተቀሰቀሱ ብዙ ወገኖቻችን ሕይወታቸውን እያጡ እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትጵያዊያን ከቤት ንብረታቸው እየተፈናቀሉ ነው፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ኢትዮጵያ በዓለማችን ከሚገኙት ዜጎቻቸው ከሚፈናቀሉባቸው አገሮች መካከል የመጀመሪያውን ቦታ ይዛለች፡፡ ለመሆኑ የግጭቶቹ መንስኤዎች ምንድን ናቸው? መፍትሔዎቻቸውስ? ግጭቱ፣ የዜጎች ሞትና መፈናቀል ወደማንወጣው አገራዊ ቀውስ እንድንገባ ሳያደርገን አሁንኑ ሁላችንም ልንወያይበትና መፍትሔ ልንፈልግለት ይገባል፡፡
በእኔ በኩል የግጭቱን መንስኤዎች በሁለት እርከኖች ከፋፍዬ ነው የማያቸው፡፡ የመጀመሪያወቹ የግጭቱ አቀጣጣይ መንስኤዎች (immediate cause) ሲሆኑ፣ ሁለተኛዎቹ የግጭቱ መሠረታዊ ምክንያቶች (underlying causes) ናቸው፡፡

ከአቀጣጣይ ምክንያቶቹ ስንጀምር፣ በአብዛኛው ግጭት ተቀሰቀሰባቸው ወይም ሊቀሰቀስ ታስቦ የነበረባቸው ቦታዎች ጠረፋማ የክልል አካባቢዎች (ሶማሊና ቤንሻንጉል ጉሙዝ -የተቀሰቀሰባቸው፣ ጋምቤላና አፋር – ሊቀሰቀስ የታቀደባቸው) ናቸው፡፡ ይህም የሆነበት መሠረታዊ ምክንያት ፀረ-ለውጥ ኀይሉ ለውጡን ለማደናቀፍና ተቀባይነት ለማሳጣት እንደ ትልቅ ስትራቴጂ የያዘው በእነኝህ ጠረፋማ አካባቢዎች ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ዘውጌ ማኅበረሰቦች መካከል ግጭት በመቀስቀስ አገሪቱ ወደ ሥርዓት አልበኝነትና ብጥብጥ እንድትገባ ማድረግን ነው፡፡ የፀረ-ለውጥ ኀይሉ ጥረት ፍሬ አፍርቶም ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ባይተዋር ሆነው ከያለበት ሲፈናቀሉና ሕይወታቸውን ሲያጡ ታዝበናል፡፡ የዜጎች ሞትና ስደት አሁንም እንደቀጠለ ነው፤ ፀረ-ለውጥ ኀይሉ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ በተጠቀሱት ክልሎች ውስጥ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ካልተገታና አደብ እንዲገዛ ካልተደረገ ወደፊትም አይቆመም፡፡

ሁለተኛውና ዋነኛው የግጭት ምክንያት ዘውጋዊ ማንነትን መሠረት ያደረገው ፌደራላዊ አወቃቀር ነው ብየ አምናለሁ፡፡ በአገራችን ላለፉት 27 ዓመታት በሥራ ላይ የቆየውና ለአያሌ ዜጎች ሞትና መፈናቀል ምክንያት የሆነው ፌደራላዊ ሥርዓት ኢትዮጵያዊያንን “የክልል” እና “ከክልል ውጭ የመጡ” ብሎ ይመድባቸዋል፡፡ በዚህ ክፍፍል መሠረት በአንድ ክልል ውስጥ ከሚኖሩት ኢትዮጵያዊያን መካከል የክልሉ ባለቤቶችና ባለሙሉ መብት የሚሆኑት “የክልሉ ሰዎች” ሲሆኑ፣ “ክልል ውጭ የመጡት” በክልሉ ባለቤቶች መልካም ፈቃድና ችሮታ ላይ ተመሥርተው በጥገኝነተ መልክ የሚኖሩ ናቸው፡፡ የክልሉ ባለቤት ነን የሚሉት ወገኖች ከክልሉ ውጭ የመጡ ተብለው የተመደቡትን ዜጎች በሚፈልጉበት ጊዜ ሁሉ “ከክልላችን ውጡልን” የማለት መብት እንዳላቸው ይሰማቸዋል፡፡ እየሆነ ያለውም ይኸው ነው፡፡ በዚህ ጠንቀኛ አስተሳሰብ ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው እንደ ባይተዋር እየተቆጠሩ በገፍ ሲፈናቀሉና በርካቶች ሲገደሉ ታዝበናል፤ እየታዘብንም ነው፡፡

የአገራችን ሕገ መንግሥት ዜጎች በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ እንደፈለገ ተዘዋውሮ ሠርቶ የመኖር መብት አለው እየተባለ ተደጋግሞ ሲነገር እንሰማለን፡፡ ሆኖም ይኸው ሕገ መንግሥት የአገሪቱ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤቶች “ብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች” ናቸው ብሎ በማያሻማ ሁኔታ እንደሚደነግግና ክልሎች፣ የብሔረሰብ ዞኖችና ወረዳዎች የተዋቀሩትም ይህንኑ የሕገ መንግሥቱን መርህ መነሻ በማድረግ በዘውጋዊ ማንነት ላይ ተመሥርተው በመሆኑ ይህ ሥርዓት በሥራ ላይ እስካለ ድረስ ዜጎች አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተብለው መከፈላቸውና በማንነታቸው ምክንያት መበደላቸው እንደሚቀጥል ጥርጥር የለውም፡፡

የዘረኝነት እና ዘውጋዊነት ፈተና
***
“ዘረኝነት” (racism) እና ዘውጌያዊነት (ethnocentrism) የተሰኙት ሁለት ጽንሰ-ሐሳቦች “እኛ” እና “እነሱ” በሚል አገላለጽ የተቀነበቡ ቢሆንም ለክፍፍላቸው እንደመሣሪያ የሚጠቀሙት የተለያዩ መነሻዎችን ነው፡፡ ዘረኞች (racists) የሚባሉት “እኛ” እና “እነሱ” የሚለውን ክፍፍል ሲያካሂዱ በአብዛኛው የቆዳ ቀለምን ወይም አካላዊ ገጽታን መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ዘውገኞች ደግሞ ብዙውን ጊዜ የመከፋፈያ መሠረታቸውን የሚጥሉት በዘር ሐረግ፣ በባህል፣ በአካባቢ ወይም በቋንቋ ላይ ነው፡፡

የሁለቱ ጽንሰ-ሐሳቦች በቅርጽ እንጅ በይዘት ደረጃ ያን ያህል የጎላ ልዩነት የላቸውም፡፡ የሁለቱም ከፋፋይ አስተሳሰቦች መሠረታዊ መገለጫ የደምና ርስት ቀጥተኛ ግኙነት ነው ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ እሳቤ መሠረት “የእኛ” የሚሉት ዘር ወይም ዘውጌ ማኅበረሰብ በስፋት የሚኖርበት አካባቢ ከፈጣሪ ተሰጣቸው ርስት አድርገው ይገምታሉ፡፡ የዚያ አካባቢ ብቸኛ ባለቤቶች እነሱና እነሱ ብቻ መሆናቸውን የሚገልጹ የተለያዩ የፈጠራ ትርክቶችን በማቅረብ የማኅበረሰቡን አባላት በማሳመን የዚህ የፈጠራ ትርክት ጭፍን ደጋፊዎች ያደርጓቸዋል፡፡

የፖለቲካ ልሂቃኑ የተለያዩ የፈጠራ ትርክቶችን በማድራት የእነሱን ግለሰባዊ ራስ ወዳድነት ወደ ቡድናዊና ማኅበረሰባዊ ራስ ወዳድነት ከፍ በማድረግ እንወክለዋለን የሚሉት ኅብረተሰብ በስግብግብነትና ጥላቻ የተጠቃ ማኅበራዊ-ሥነልቦና እንዲገነባ ያደርጉታል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ የተገነባ ማኅበረሰብ ሌሎችን ማኅበረሰቦች በጥርጣሬና ጥላቻ ይመለከታቸዋል፤ ስለሆነም ከሌሎች ጋር በሰላምና በመግባባት አብሮ ለመኖር ሲቸገር ይስተዋላል፡፡ በነገራችን ላይ ይህ የከፋፋይነት ሥነ-ልቦና የተለያየ ተዋረድ ያለውና ማቆሚያ የሌለው፣ ልክ እንደ ቀይ ሽንኩርት የላይኛው ሽፋን ሲላጥ ሌላ ሽፋን ይዞ ብቅ የሚል ነገር ነው፡፡ ብሔር ብሎ የሚቆም አይደለም፡፡ ዘውግ፣ ጎሳ፣ ንዑስ ጎሳ እያለ ከክልል፣እስከ ዞን፣ ወረዳ፣ ቀበሌላ ጎጥ እያለ ይወርዳል፡፡

ዘውጌያዊነት በጥንቃቄ ካልተያዘ በስተቀር መዘዙ የከፋ ይሆናል፡፡ በተለይም ኀላፊነት የጎደላቸውና ሥልጣን አምላኪ የፖለቲካ ልሂቃል ዘውጋዊ ማንነትን እንደ ዋና ማደራጃ መሣሪያ በመጠቀም “ተጠቃህ”፣ “ተዋረድህ”፣ “ጠላቶችህ ሊመጡብህ ነው” ወዘተ. የሚሉ ከሆነ አገር ሰላም አታገኝም፡፡

በእኔ አስተያየት በአገራችን ትልቅ አደጋ የደቀነው ይህ ፈተና ይህ ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈንና ለሁላችንም የምትሆን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት በዘውጋዊ ማንነትን መሠረት አድርጎ የተገነባው ፌደራላዊ ሥርዓት እና ለዚህ ሥርዓት መሠረት የሆነው ሕገ መንግሥት እንደገና መፈተሽ ይኖርባቸዋል፡፡ በዘውግ ላይ የተመሠረተው ፌደራላዊ ሥርዓት በአገራችን ሰላምና ዲሞክራሲያዊ አንድነት አምጥቷል የሚሉ አላካት እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ግን ይህ አስተያየት ምን ይህል ውኃ ይቋጥራል? ምን ያህል በሐቅ ላይ የተመሠረተ ነው? እውን በአገራችን ሰላም አለ? እውን ዲሞክራሲያዊ አንድነት አለ?
በበኩሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ የሆነ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣትና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የዜጎችን ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነት ገፍፎ ለቡድኖች ብቻ ሰጠውን ሕገ መንግሥት መፈተሽና ማሻሻል የግድ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህን ሕገ መንግሥት እንደጣኦት እንድናመልከው ነጋ ጠባ የሚወተውቱ ኀይሎች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ሆኖም ሰነዱ በሰብአዊ ፍጡራን የተዘጋጀ እንደመሆኑ መጠን በርካታ እንከኖች ሊኖሩት እንደሚችሉ መቀበል ያስፈልጋል፤ አሉትም፡፡ ከመነሻው ሰነዱ ከተረቀቀበትና ከፀደቀበት ሒደት ጀምሮ ግጭት ቀፍቃፊና የአገር ህልውና ጠንቅ እስከሆኑ ድንጋጌዎቹ ድረስ በርካታ ጉድለቶች ያሉበት ሕገ መንግሥት መሆኑ የሚያከራክር አይደለም፡፡ ስለሆነም ከፍ ብየ እንደገለጽሁት ሕገ መንግሥቱ የዜጎችን ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነት ባረጋገጠ መልኩ መሻሻል ይኖርበታል፡፡
ይህን ለማድረግ በነዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የሚመራውን መንግሥት እንደ ኢሕአዴግ መንግሥት ሳይሆን እንደ ልክ እንደ ሽግግር መንግሥት ተቀብለነውና ሙሉ እምነት ሰጥተነው፣ በለውጥ መሪዎች በኩል የሚታየውን ኢትዮጵያን ወደ እውነተኛ ፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማሸጋገር እየቀረበ ያለውን ሐሳብ ወደ ተቋማትና ሕግ/ሥርዓት ለመለወጥ ተገቢውን ጊዜና ትዕግስት ልንቸራቸው ይገባል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆንም ኢትዮጵያዊያንም እንደ ዜጋ በጥቂት የአገራችን ጉዳይ ለጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች አሳልፈን ሳንሰጥ በሒደቱ ላይ ንቁ ተሳትፎ ልናደርግ ይገባል፡፡ አሁን ጊዜው ለምርጫ የምንዘጋጅበት ሳይሆን ተቋማትን የምንገነባበት ነው መሆን ያለበት፡፡ ስለሆነም የለውጥ መሪዎችም ሆኑ ሕዝቡ ገለልተኛ የሆኑ ጠንካራ አገራዊ ተቋማትን በመገንባት ላይ እንዲያተኩሩ ያስፈልጋል፡፡

ኅብረታችን ይጠናከር
***

ማኅበረሰብ ስንል የተለያዩ ግለሰቦች በመቻቻልና መግባባት የመሠረቱት ማኅበረሰባዊ ተቋም ማለታችን ነው፡፡ የአገሮች ህልውና የተመሠረተው በማኅበረሰቦች መካከል የሚኖር የአብሮነትና የመቻቻል እሴት ላይ ነው፡፡ አብሮነቱንና መቻቻሉን በወግ፣ በደንብ፣ በማኅበራዊ እሴቶችና በሕግ ማዕቀፎች መቋጠርና ማዳበር ይቻላል፡፡

በአገራችን በማኅበረሰቦች መካከል መቻቻል እንዲጠፋ፣ መግባባት አደጋ ላይ እንዲወድቅ የሚያደርገው ዋናው ምክንያት የፖለቲካ ልሂቃኑ ሥልጣን ለመያዝ ወይም በሥልጣን ላይ ለመቆየት ኀላፊነት የጎደለው ስሜት ቀስቃሽ የቂምና ጥላቻ ትርክት ውስጥ ስለሚገቡ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት በሕዝብ መካከል አላስፈላጊ ጥርጣሬና ግጭት የሚፈጥሩ ቅስቀሳዎች ውለው አደረው ምን እንደሚፈጥሩ በሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ደቡብ ሱዳንና በሌሎች አገሮች በሚገባ አይተናል፡፡ የእኛም አካሄድ እንዲያ እንዳይሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል፡፡

በተለይ የአገር ሽምግሌዎች፣ ምሁራንና ሲቪክ ማኅበራት በማኅበረሰቦች መካከል መቻቻልና መግባባት እንዲኖር እና በፈጠራ ትርክት አማካይነት የተገነቡ የጥርጣሬና ጥላቻ ግንቦች እንዲፈርሱ ከፍተኛ ኀላፊነት አለባቸው፡፡