ከምሣ ስመለስ ከፊት ለፊቴ አንድ ሰው በሞባይል ስልክ ያወራል፡፡ እንደአጋጣሚ ሆኖ በዚያኛው ጫፍ ያለው ግለሰብ ድምጽ በደምብ ይሰማል – “ላውድ ስፒከር” ላይ ነበር፡፡ የዚህን ወሬ እውነትነት ለማስረገጥ “እውነቱን እውነት፣ ሀሰቱንም ሀሰት” ከማለት ውጪ መሃላ በሃይማኖቴ አይፈቀድም እንጂ በልጆቼ ብምል ደስ ባለኝ፡፡ ከዚያላችሁ እኔም ወሬያቸውን በጉጉት እያዳመጥኩ ጠጋ ብዬ መከተሌን ቀጠልኩ፡፡ የሰውን የግል ወሬ ማዳመጥ ብልግና ቢሆንም መረጃው ጠቃሚ ነበርና ምንም ማድረግ አልቻልኩም፡፡ የሚነጋገሩትን ልቅም አድርጌ ሰማሁ፡፡ ስልኩ ሲዘጋ ለመጻፍ ወደ ቢሮየ በሩጫ አመራሁ፡፡ ግን የሀገራችን ዕድል እጅግ አሳዘነኝ፤ ከአንዱ የመከራ ጫፍ ወደሌላው የመከራ ጫፍ እንደ ቅሪላ ስትለጋ ምንም ነገር ላደርግ ባለመቻሌም ክፉኛ አዘንኩ፡፡ እንደውነቱ ከሆነ የአበራሽን ጠባሳ ያዬ በእሳት ለመጫወት መጣደፍ አልነበረበትም፡፡ እነዚህ ማመዛዘን ያቃታቸው አዲሶቹ ባለጊዜዎች ይህችን አገር ወደ ለዬለት መቀመቅ እንዳይከቷት ፈራሁ፡፡ ባሏን የጎዳች መስሏት ሰውነቷን በእንጨት እንደወጋችው ጅል ሚስት ወያኔም አማራንና ኢትዮጵያን የጎዳ መስሎት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተጋሩ የሚኖሩባትንና (አብዛኞቹ በዘረፋና በሙስና ያከማቹት ቢሆንም) ሀብት ንብረታቸውን ያፈሰሱባትን ሀገር እንጦርጦስ ለማውረድ ባዘጋጀው ወጥመድ ማን ተጎጂ ማን ተጠቃሚ እንደሚሆን በጣም በቅርቡ የምናየው መራር እውነታ ነው፡፡ ማንንም ለማስፈራራት አይደለም፡፡ የበሰበሰ ዝናብ እንደማይፈራ ታውቃላችሁ፡፡ አማራ ከሀብትም ከሥልጣንም ስለሌለበት ዋና ተጎጂዎቹ ይህችን የዘረኝነት ቁማር የቆመሩና በኢትዮጵያ ላይ ሌላና ከእስካሁኑ ዘረኝነት በባሰ የሚጠነባ የጎሠኝት ወጥመድ የዘረጉ ወገኖች ናቸው፡፡ አማራውማ አህያም የለው ከጅብም አይጣላ፡፡ ጉድጓድ ለሰው መቆፈር የማይመከረው ለዚህ ነው – ቀድሞ የሚገባበት ስለማይታወቅ፡፡ ሌባ ጣትን በሰው ላይ መቀሰር የማይመከረው ለዚህ ነው – ሦስቱ ጣቶች ወደራስ ስለሚቀሰሩ፡፡ ተንጋሎ መትፋት እንደማያዋጣ የሚነገረውም ለዚህ ነው – ትፋቱ ተመልሶ ለራስ ስለሚተርፍ፡፡ … ጆሮ ያለው ይስማ፡፡ ይህን ወልጋዳ አካሄድ ሃይ ማለት ያለበት ወገን ካለ ኢትዮጵያ ውስጥ እሳተ ገሞራ ሳይፈነዳ ከአሁኑ አንድ ነገር ይደረግ፡፡ “በጊዜ የጮኸ ጅብ አያሳድረኝም” እንዲሉ ገና ለገና ጊዜው ለኦሮሞ አዘንብሏል ተብሎ እንዲያ ያለ ማፈሪያ ነገር ከአሁኑ ማሳየቱ ሲያንስ ችኩልነት ሲበዛ ደግሞ ንቀት ነው፡፡ ማንኛውም ቢሆን ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አንጎል የሚባል ነገር ከናካቴው መጥፋቱ ግን በእጅጉ ያሳዝናል፤ ያሳስባልም፡፡ መጨረሻችን ምን እንደሚሆን ለማወቅ ጓጓሁ፡፡
ወደሰማሁት ወሬ ልመለስና በምናብ ወደ ስፖርት ኮሚሽን ላስገባችሁ ነው፤ ወሬው በዚያ መሥሪያ ቤት ላይ የተመረኮዘ ነውና፡፡ ስፖርት ኮሚሽን ከሚኒስትር መሥሪያ ቤትነት ወደ ቀድሞው የኮሚሽን መሥሪያ ቤትነት ተመልሷል፡፡ በዚህ መሥሪያ ቤት የሚሠራ አንድ ታታሪ ሠራተኛ በብሔሩ ምክንያት ከ“ካቢኔ ሹም-ሽር” ወዲህ (ወግ አይቀር መቼም “ሹም-ሽር” ልበለው እንጂ) በቅርቡ በተዘጋጀው አዲሱ የመ/ቤቱ አወቃቀር አልተመደበም፤ “ስትጠራ ትመጣለህ” ተብሎ እቤቱ ተቀምጧል፡፡ እርሱ ብቻ ሣይሆን የጊዜውን የዘር መሥፈርት የማያሟሉ ሌሎች ትጉሃን ሠራተኞችም እቤታቸው ውለዋል – በግልጽ ለማስቀመጥ ኦሮሞ ያልሆኑ ማለት ነው፡፡ በዚህ የዘረኝነት ወረርሽኝ ሰለባ ሰው ምትክ የተመደበው የአዲሱ ገዢ ዘር ግለሰብ የሥራ ልምድም ሆነ የትምህርት ደረጃ ዝቅተኛ ነው፡፡ ምደባው ከላይ እስከታች ዘርን መሠረት ያደረገና ኦሮሞዎችን እየለዬ የሚሾምና ወደ ልዩ ልዩ የሥራ ክፍሎች የሚመድብ ነው፡፡ ምን አለፋችሁ – ኦሮሞ በሌሎችም የአዲስ አበባና የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ሌሎችን እያባረረ እንደትግሬው የገዢ መደብ ሁሉንም ራሱ ሊቆጣጠር በመራወጥ ላይ የሚገኝ ይመስላል፡፡ ይህንን ስል ሰፊውን የኦሮሞ ሕዝብ ማጣቀሴ ሳይሆን በስሙ ሊነግዱ የተነሡ ጥቂት ቢሮክራቶችን ማለቴ ነው፡፡ በወያኔ ጊዜም ቢሆን የአዲጉዶምና የአጋሜ ገበሬዎች አልነበሩም ኢትዮጵያን መቅ የከተቷት – ብልጣብልጦቹ ግን ጥቂት የማይባሉት የመለስ ደቀ መዛሙርት እንጂ፡፡ ልብ አናድርግ – አንዲት ክብሪት አንድን ጫካ እንደምታወድም ሁሉ አንድ ትንሽዬ እረኛም ሽህ ከብት ሊነዳ እንደሚችል ሁሉ በተመሳሳይ ሁኔታ ጥቂት ወሮበሎች ብዙ ሕዝብ በማታለልና በዘረኝት መርዝ በመበከል ከሥራቸው አሰልፈው ብዙ ጥፋትና ውድመት ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ በነገራችን ላይ እነግንቦት ሰባትን የመሰሉ የዜግነት መርህ አቀንቃኞች ቀን ሊወጣላቸው መሰለኝ፡፡ የሚያዋጡን እነሱ ብቻ ናቸው ወንድሜ፡፡ እርግጥ ነው – ችግር ካለባቸው ለመታረም ዝግጁ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ምድራውያንን ደግሞ ካለችግር ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ ምድር የችግር ሥፍራ ናት፡፡ ዋናው ካለፈ ተሞክሮ ተምሮ በልምድ በካበተ ዕውቀትና ግንዛቤ የወደፊቱን ማስዋብ ነው፡፡ ይህም ይቻላል፡፡
ለማንኛውም መፍራት አሁን ነው፡፡ ይህ ዘመን እጅግ ያስፈራል፡፡ ከወያኔም ዘመን በእጅጉ እንደሚያስፈራ መገንዘብ አይከብድም፡፡ ወያኔ ትነስም ትብዛም አንዳች ሰበብ እየፈለገች ነበር ከሥራም ሆነ ከጥቅም የምታባርረው፡፡ አሁን ግን ጭልጥ ያለ የዘረኝነት አረንቋ ውስጥ ገብተናል፡፡ ንግግር ሌላ ተግባር ሌላ እየሆነ ነው፡፡ ይህ አካሄድ ወዴት እንደሚያደርሰን ቆይተን ማየት ነው፡፡ መጨረሻው መጥፎ እንደሚሆን መገመት ግን ቀላል ነው፡፡
በአዲስ አበባ ፖሊስና የፌዴራል መ/ቤቶች እየተሾሙ ያሉት ሰዎች በአብዛኛው ኦሮሞ መሆናቸው የማያስከፋ ሆኖ ሳለ ለኢትዮጵዊነትና ከርሱ ጋር ለተያያዙ ሰብኣዊና ታሪካዊ ተጋምዶዎች ያላቸው ሸውራራ አመለካከት ግን አብሮ የሚያኗኑር አይደለም፡፡ አንድን በጥላቻ የተመረዘ ሥርዓት አስወግደህ ሌላ ተመሳሳይ በጥላቻ የተመረዘ ሥርዓት ማቆም “አልሸሹም ዘወር አሉ” እንዲሉ እንጂ የተለወጠ ነገር የለም፡፡ ጄኔራል ደግፌ በዲ በወጣት ብርሃኑ ተ/ያሬድ ላይ አሳዬ የተባለው ዛቻና ድንፋታ ለምሣሌ አግባብ አይደለም፤ ያን ያህል መውረድም የጤና አይደለም – ህግ አለ፤ ሥርዓት አለ፤ ህግና ሥርዓት አስፈጻሚ አካላትና አባላትም አሉ፡፡ ይህን ሁሉ ተላልፎና ደረማምሶ በእልህ አንድ ትልቅ ባለሥልጣን ከአንድ ተራ በ“ህግ ጥላ ሥር” የሚገኝ ዜጋ ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ መግባት ህክምና በሚያሻው ልክፍት መያዝን አመላካች ነው፡፡ “ፍየል ከመድረሷ ቅጠል መበጠሷ” ይባላል፡፡ መረገም ነው ፡፡ ያ ወጣት እንኳንስ ለአዲስ አበባ ወጣቶች የሚዘራው ገንዘብ ሊኖረው ወይም ከሌላ አካል ሊቀበል ይቅርና የራሱንም የዕለት ከለት ኑሮ በቅጡ በመራ፡፡ አንድ ወገን ላይ እንዲህ የመሰለ ጥላቻ ያላቸው ወገኖች ወደ ሥልጣን መምጣት አልነበረባቸውም፤ ከመጡ ደግሞ የተሹዋሚውን ብቻ ሳይሆን የሹዋሚውንም እምነትና አስተሳሰብ ጠቋሚ ነው – የነገሮችን ትስስር በማጤን የግለሰቦችን ግንኙነትና የፍልስፍና መመርያ ማወቅ ከባድ አይደለም፡፡ ሰሞኑን የታሰሩት ጠበቃና አክቲቪስትም ለምን እንደታሰሩ በግልጽ ይታወቃልና በቶሎ ካልታረመ ታጥቦ ጭቃ መሆናችንን የሚያሳይ ነው፡፡ ብዙ ነገሮች አቅጣጫ እየሳቱ ነውና ሀገሪቱን እየመራ የሚመስለው አካል ካለ በአፋጣኝ ለማስተካከል ይሞክር፡፡ ጥዶ ዘለልነት ለማንም አላዋጣም፤ አያዋጣምም፡፡
አንድ መሠረታዊ እውነት ተናግሬ ላብቃ – ከአሁን በኋላ ማንም ቢሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ ማታለል አይቻለውም፤ የኢትዮጵያና ሕዝቧን ነፃነትም ማዘግየት ይቻል እንደሆነ እንጂ ማንም ምድራዊ ኃይል ሊያስቀረው አይችልም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ናትና፡፡ እንኳን የኢትዮጵያ ጠላቶች ሂትለርና ሙሶሊኒም ከሕዝብ የመጨረሻ ፍርድ አላመለጡም፡፡ …
ብዙ መናገር ጥቅም የለውምና የሰማነውን በልቦናችን ያሳድርልን፡፡ ቻው፡፡