የሀገርን ስሜት በሚመለከት በየቤታችን ከምንታዘበው ቤተሰባዊ በተለይም ከብዙዎች ሴቶች የግዴለሽነት ድባብ አኳያ እነ ርዕዮት ዓለሙን የመሳሰሉ ጥይት ሴቶች ስናይ በዚህ ረገድ ሌት ከቀን የምንለፋና የምንጨነቅ ወገኖች ደስታችን ወደር የለውም፡፡ እኔ ጫካ እንዳለመሆኔ የምደብቀው ምሥጢር የለኝም – ሁሌም የግምባር ሥጋ እንደሆንኩ አለሁ፡፡ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ግን በጣም ነው የምታናድደኝ፡፡ ከዚህ ቃና ከሚባል ትውልድን በራዥ ቲቪ ሥር ትደቀንና እኔ ኢሳትን ወይ ሌላ ጣቢያ ልከፍት ስል ከነልጆቿ ትንጫጫብኛለች፤ ጉዳቱ ለኔው ነው እንጂ “እግዜር ይይላት” ብዬ ለላይኛው ንጉሥ ላጋልጣት በወደድኩ ነበር፡፡ ያኔ ታዲያ እነ መስከረም አበራ፣ እነ ገሊላ መኮንን፣ እነ መታሰቢያ ቀፀላ፣ እነ ኢየሩሳሌም፣ እነብሩክታዊት፣ እነየሐረር ወርቅ ጋሻው፣ … ትዝ ይሉኝና ተስፋየ ይለመልማል፡፡ የ22 እና የ23 ዓመት ጎረምሣ ልጆችህ ምንም ብሔራዊ የሀገር ስሜት ሳይኖራቸው አርቲ ቡርቲ ፊልም ላይና ወፍ ዘራሽ የፈረንጅ ሙዚቃ ኳኳታ ላይ ሲያተኩሩ የመንግሥቶቻችን የድካም ፍሬ ቁልጭ ብሎ ይታይሃል፡፡ ነገ ይህችን ሀገር ማን እንደሚረከባት ስታስብ እኮ ይጨንቃል፡፡ ወዴት እየሄድን ነው? ሀገራችን በኳስ ዐበደች የልጆች ጨዋታ እየታመሰች ናት፡፡ መጨረሻንን አንድዬ ያሳምርልን እንጂ ማኅረሰባችን ከቤተሰብ ጀምሮ ተናግቷል፡፡ ጥሩ ትዳር የለም፤ ጥሩ ጓደኝነት የለም፤ መተማመን የለም፡፡ ተበድሮ በወቅቱ መመለስ፣ የገቡትን ቃል መጠበቅ፣ ያዋሱትን ዕቃ ለባለቤቱ መስጠት፣ የፈጣሪን ህግጋትና ትዕዛዛት ማክበር፣ የሀገርን ህግና መመርያ አለመጣስ፣ … የፋራዎች እየሆነ እኮ ነው፡፡
ርዕዮት ዓለሙና ባልደረቦቿ በትናንተናው ምሽት የኢሳት “ዕለታዊ” ፕሮግራም ዝግጅት ያቀረቡት መሰናዶ በጣም ግሩም ነበር፡፡ ይወያዩበት የነበረው ጉዳይ የተለያዬ ቢሆንም ስለጠ/ሚኒስትራችን የቅርብ ጊዜ አሻሚ ንግግር ግልጽ ዴሞክራሲያዊ ውይይት ሲያደርጉ ለተመለከተ ሀገራችን በዴሞክራሲ ግንባታ ጥሩ እመርታ ላይ እንደምትገኝ ያመላክታል – ምንም እንኳን ኢሳት ገና በሁለት እግሩ ወደ ሀገር ባይገባም፡፡ ይህን መሰል ነፃ የሃሳብ ልውውጥ በኢቲቪና በሌሎችም ሀገራዊ የሚዲያ ተቋማት ቢለመድ ለሁለንተናዊ ዕድገታችን ጉልኅ ሚና በተጫወተ፡፡ በኛ ሀገር የተለመደው ነገር “እንትናን” ወይም “እነንትናን እንዳይከፋቸው” በሚል አጉል ይሉኝታ ታጥሮ ነገሮችን እየሸፋፈኑ ወይም እያድበሰበሱና ከፍ ሲልም እየዋሹ ሰውን ለማስደሰት በመሞከር ዴሞክራሲን ማቀጨጭ ነው፡፡ አሁን ላለንበት ዝብርቅርቅ ያለ ሁኔታ ከዳረጉን መሠረታዊ ምክንያቶች አንዱ ይሄው ሃሳብን በነፃነት መግለጽ ያለመቻል ባህላዊና ምናልባትም ሃይማኖታዊ ተፅዕኖ ይመስለኛል፡፡ አስተዳደጋችንም ችግር አለበት – ከመነሻው “ትልቅ ሲጫወት ልጅና ሴት ወደማጀት” እየተባለ በሚነገርበት ኅብረተሰብ ውስጥ የአውሮፓና አሜሪካን ዓይነት ነፃነት መመኘት ከንቱ መቀናጣት ነው፡፡ ግን እግዜሩን ምን በድዬው ይሆን – ምናለ ፊጂ ወይም ማልታ ውስጥ እንኳን ፈጥሮኝ ቢሆን?
በውይይታቸው ወቅት ከተነሱ ነጥቦች አንደኛው ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሁን ያመኑት በፊት ግን የካዱት ወታደራዊ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው፡፡ በዚህ ነጥብ ዙሪያ ብዙ ነገሮች ተነስተዋል፡፡ ርዕዮት ያስተላለፈቻቸው ቁም ነገሮች ግን እኔንም ከበፊት ጀምሮ ያሳሰቡኝ ስለነበሩ ይህችን ማስታወሻ ለራሴ የሰነዶች ስብስብ ስል ከትቤ ማኖርን ወደድኩ፡፡ ደግሞም ቀን ላይ ከአለቃየ ጋር አንስተን ተመሳሳይ ነገር ተጫውተናል፡፡
በፊት ሰዎች መፈንቅለ መንግሥት እንደተደረገ ሲናገሩ ጠ/ሚኒስትሩ “ውሸት ነው” ማለታቸውና ካለፈ በኋላ ደግሞ ለሥልት እንጂ እንደዚያ ያሉት ነገሩ መፈንቅለ መንግሥት እንደነበር አሁን ማመናቸው እርሳቸውን ለወደፊቱ ለማመን እንደምንቸገር፣ በርሳቸው ምክንያት አመኔታ እንዳያገኙ የተደረጉ በወቅቱ እውነቱን የዘገቡ ሚዲያዎችና ግለሰቦች ደግሞ በሌላ በኩል ትልቅ በደል እንደተፈጸመባቸውና ለወደፊቱ በተከታታዮቻቸው ያለመታመን ችግር ቢደርስባቸው ተጠያቂው ጠ/ሚኒስትሩ እንደሚሆኑ በግልጽ ይሁን በአንድምታ ትርጉም ገብቶኛል፡፡ ይህንን ነጥብ አስረግጣ የገለጸችው ርዕዮት በመሆኗ ነው ይህችን መጣጥፍ በዚህች ግሩም ዜጋ ስም ለማውጣት የፈለግሁት፡፡ በነገራን ላይ ይህን ሰውን ይቅርታ የማስጠየቅ ባህል ወያዎች አለቦታው እየደነቀሩ ዋጋ አሳጡት እንጂ ጠ/ሚኒስትራን በሰሞኑ ንግግራው ምክንያት ተዓማኒነት ለማሳጣት የሞከሯቸውን የዜና መዕከላትና ብሎገሮች ይቅርታ ቢጠይቁ ታላቅታቸውን ያስመሰክራሉ – የፈጠሩት ቀውስ (mess) ቀላል አይደለምና፡፡
ከዚሁ ነጥብ ጋር ወደተያያዘ አንድ ነጥብ ላምራና ጅምሬን ልቋጭ፡፡ ርዕዮትም በሚገባ አብራርተዋለች፡፡
“መንግሥታችን ተነካ ብለው የቡራዩ፣ የሰበታና የለገጣፎ ወጣቶች …” ወደ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት እየተመሙ በመምጣታቸው ወይም ሊመጡ በዝግጅት ላይ በመሆናቸው እነዚያን የመፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎች በዘዴ ማብረድ እንደነበረባቸው ጠ/ሚኒስትሩ ቆይተውም ቢሆን ጠቅሰዋል – “በላይ እየሳቅሁ በውስጤ ግን እርር ድብን እያኩ” ሲሉ፡፡ ይህ ነገር ፈጽሞ ሊዋጥ የሚችል አይደለም፤ ለገበያ የሚቀርብና ሊሸጥ ወይ ሊገዛ የሚችልም አይደለም፡፡ ቅሽም ያለ የቧልታይና ድንቃይ ድራማ ሆኖ ሰውን ከማዝናናት ባለፈ አንዲትም ጠብታ ውኃ አያነሳም፡፡ አንድምታዊ ትርጉም ግን አለው፡፡ ይህን ዓይነት ንግግር ከጠቅላይ ሚኒስትራችን ባንሰማው የወደድን ብዙዎች ሳንሆን የምንቀር አይመስለኝም፡፡ ከዚህ ንግግር በኋላ ዶ/ር ዐቢይን ማወቅ አለማወቄን ለመረዳት ራሴን ደጋግሜ ጠየቅሁ፡፡ መልስ ላገኝ ግን አልቻልኩም፡፡ የጠ/ ሚኒስትሬን የጦርነት አቅጣጫ ላለማብዛት ስልም ይህን ማስታወሻ ላለመጻፍ አመንትቼ ነበር – ግን እውነትን በወቅቱ መግለጽ ከኋለኛ ጠጠት ይታደጋልና መጻፌ አልቀረም፡፡
በመሠረቱ አንድ ሰው እንደሚሳሳት እረዳለሁ፤ ለመሳሳት ደግሞ ሰው መሆን እንጂ ጠ/ሚንስትር ወይም ዶክተርና ጳጳስ መሆንን አይጠይቅም፡፡ በማንኛውም የዕድም ሆነ የሥልጣንና የትምህርት ደረጃ ላይ የምንገኝ ሰዎች አውቀን ወይም ሳናውቅ እንሳሳታለን፤ እናጠፋለን፡፡ የሆነው ቢሆን ግን ይህ የጠ/ሚኒስትሩ ስህተት “የምላስ ወለምታ” ወይም “Freudian Slip” ተብሎ በቀላል ሊታለፍ የሚችል አይደለም፡፡ ስንሳሳት ደግሞ ቀይ መስመር ላለማለፍ መሞከር ይኖርብናል – ፈረንጆቹ “If you err, err on the safe side.”እንዲሉ፡፡ አለበለዚያ የሠራነው መልካም ነገር ሁሉ ሊተረተርና ለተጨማሪ ልፋት ልንዳረግ እንችላለን – ሊያውም የተተረተረውን መመለስ ከቻልን፡፡ ዕድል አንድ ናት፡፡
ይህ ንግግር በማን አንጀት ላይ ለመጎዝጎዝ ወይም ማንን ለማማለል እንደሆነ ለመረዳት ብዙ ምርምርን አይጠይቅም፡፡ ጥያቄው እንደዚያ ማድረጉ ተገቢ ነበረ ወይ? ነው፡፡ አንዱን አቅራቢ ሌላውን አግላይ፣ አንዱን የቤት ልጅ ሌላውን የውጪ አያደርግም ወይ? ነው ጥያቄው፡፡ “ለምን ይዋሻል?” ይላሉ ተስፋየ ካሣን መሰል ኮሜዲያኖች፡፡
ለመሆኑ የመፈንቅለ መንግሥቱን ሙከራ እንኳንስ የሰንዳፋና የቡራዩ ወጣት የአራት ኪሎ ወጣቶችስ ያውቁ ነበር ወይ? እንኳንስ የሰበታ ወጣቶች ቤተ መንግሥት ሥር የተወተፍኩት እኔ ነፃነት ዘለቀ ማታ በቲቪ የዜና ዕወጃ ከመስማቴ ውጭ ግርግሩ ድግስ ይሁን የቀብር ሥነ ሥርዓት ይሁን መቼ አወቅሁና? እነዚህ በጠ/ሚኒስትሩ የተጠቀሱት የኦሮሞ ወጣቶች በየት በኩልና ዜናውንስ ማን ነግሯቸው ነው ጦር ሰብቀው፣ ስንቅና ጥይት በአጋሰስ ጭነውና በአምባላይ ፈረስ ሽምጥ ጋልበው ወደ ቤተ መንግሥት የመጡት? ትልቁ ዳቦ ሊጥ ከሆነ ከእንግዲህ ማንን እንመን? ለምን ይዋሻል? ለምን ዓይነት የፖለቲካ ትርፍ? ኪሣራው ሊበልጥ እንደሚችልስ እንዴት ግልጽ ሊሆን አልቻለም?
ይህ ለውጥ የአዲስ አበባን ወጣት ገሸሽ ያደረገ መሆኑን ለመረዳት ይህን የጠ/ሚኒስትሩን ንግግር እየበለቱ ማጤን ይገባል፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች በጥልቀት ቢያዩት ንግግሩ ከባድ አንድምታዊ ይዘት ያለው ሽል መንጣሪና ውለታቢስነትን ገላጭ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ወጣት የአሁኑን አያድርገውና “ከሳቸው በፊት የኔን ደረት በጦር በጣጥሱት!” ብሎ ቀድሞ የሞተላቸው ነው፡፡ ዘረኝነትን የሚፀየፈው የሸገር ወጣት የጠ/ሚኒስትሩን ዘር ማንዘር ለማወቅ አንድም ፍላጎት ሳይኖረውና ለዚያ ርካሽ አስተሳሰብ ዋጋ ሳይሰጥ ያን የመሰለ ድጋፍ ያሳየው በጠ/ሚኒስትሩ ርቱዕ አንደበትና ኢትዮጵያዊ የንግግራቸው ቃና ተማርኮ ነው፡፡ አሁን ያን ሁኔታ ወደ ኋላ የሚያንሸራትትና ወደ ዘር ማዕቀፍ የሚያሸጉጥ ምን አዲስ ነገር ተከሰተ? ይህን ጥያቄየን የሚመልስልኝ ባገኝ ጠ/ሚኒስትሬን እንደወደድኩ ለመቀጠል ቃል እገባለሁ፡፡ ለነገሩ እኔ ወደድኳቸው አልወደድኳቸው ምን አመጣለሁ – አፌ ለምዶበት እንጂ፡፡