October 20, 2018

 

“በአዲሱ ካቢኔ ዐብይ አሕመድ አማራውን ከወሳኝ የፌደራል መንግሥት የሥልጣን ቦታዎች እንዲገለል እያደረገ እንደሆነ ነው የምረዳው።” የሚለውን ፁህፍ በፌስቡክ ገፆች ላይ ሲንከባለል ሣይ ይህን ለማለት ደፈርኩኝ

ድፍን ኢትዮጵያውያን ከወሳኝ የፌደራል መንግሥት የሥልጣን እርከን የተገለሉት ዛሬ አይደለም። ዘመናትን አስቆጥረዋል። የአማራም ይሁን የኦሮሞ ወይም ሎሎች ኢትዮጵያውያን በኢፌዲሪ ፓርላማ ውስጥ ውክልና የላቸውም:: ምክንያቱም ሥርዐቱም ይሁን ፓርላማው በሕዝብ፣ ለሕዝብና ከሕዝብ በዴሞክራሲያዊ አግባብና ምርጫ ባለመመረጣቸው:: በዚህ ፓርላማም ይሁን መንግስት ውስጥ ይሄኛው ወይም ያኛው ሕዝብ ተገቢ ውክልና የለውም፣ ተገለለ፣ የሚሉን “እየታገልንለት ነው” በሚል ጆሯችንን የሚያደነቁሩን የጎሣና የጎጥ ፊታውራሪዎች ሕዝብን “ለድል” የሚያበቁት በዚህ ፓርላማና መንግስት ውስጥ የጎሣ እባላቸውን በማስመደብ ሥልጣንና ወሣኝ መንግስታዊ ዙፋን ሲያገኙ ይሆን? ይህ ግብዝነት ነው:: ሕዝብን እንደ መሠላል በመጠቀም የሥልጣን ጥማቸውን ለማርካት እንደቋመጡ ማስረጃው ይሄው ነው::

ሕዝብ ተገቢውን ውክልና የሚያገኘውና የሥልጣን ባለቤትንቱ የሚረጋገጠው እንዲሁም መብትና ነፃነቱ የሚከበረው በዴሞክራሲያዊ መንገድና ሥርዐት ብቻ ነው:: የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው መብትና ነፃነት እንጂ ለጎሣ አባሉ ሹመትና የኢህአዴግ ፓርላማ ወንበር አይደለም:: የጎጥ ባላባቶችን ማንገስ ሣይሆን ዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት መኖር ነው:: ይህን ሁሉ የምንለው በሥርዐቱ ጉያ ውስጥ የመሸጉ በርካታ መሰናክልና እንቅፋቶች መኖራቸውን በመዘንጋት አይደለም። መብትና ነፃነትን ማስከበር የሚቻለው መብትና ነፃነት በቅድሚያ ሲኖሩ ነው። መብትና ነፃነትም መጎናፀፍ የሚቻለው በፌስቡክ አድማ፣ ጫጫታ፣ ስድብና ዋልጌነት ሳይሆን በትግል ነው።

ሕዝብን የሥልጣን ባለቤት ለማድረግ:-

1. በእልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ በመሳተፍና ሕዝብን በማሳተፍ ለሥርዐቱ ለውጥ በመፋለምና በዕውቀትና ልምድ ላይ የተገነባ የበሰለ ፓለቲካ በማራመድ

2. የአላማ እንጂ የመርህ ልዩነት ከሌላቸው ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ጋር በጋራ ግንባር ተጣምሮ ሕብረት መመስረት

3. የጎሣና የጎጥ ፓለቲካን በመጠየፍና “የጎሣ ፌደራሊዝምንና አብዮታዊ ዴሞክራሲን” የሕግ የበላይነት በሚከበርበት የዴሞክራሲ ሥርዐት በመተካት ብቻ ነው::

ጥላቻ ወደ ቂም፣ ቂም ወደ በቀልና በቀልም ወደ ስቃይ እንደሚወስድ ማጤን ብልህነት ነው:: ከሁሉም በላይ ከለውጥ ሃይሎች ጎን በመቆም፣ ስኬታቸውን በማወደስና ግድፈታቸው ላይ በምክንያታዊነት፣ በመረጃና ማስረጃ ገንቢ ትችት በማቅረብ የዴሞክራሲው ሂደት እንዳይጨናገፍ በማገዝ ነው:: ለሂደቱም ማህበራዊ መሠረት (social base) በመሄን ነው። ከማይረባ ንትርክና መጨቃጨቅ ወደ ውይይትና መግባባት በማቅናት ነው። (As it’s said “argument is an exchange of stupidity but discussion is an exchange of ideas”)። በአንድ በኩል ተገቢ ውክልና የወያኔ ሠራሹ ፓርላማ አባላት “ተገቢ ውክልና አልሰጡንም” የሚሉን ቂሎች በሌላ ጎኑ የዶ/ር አቢይ መንግስት ላይ የጥላቻና የወረደ የሥም ማጥፋት ዘመቻ እያደረጉ “ከአንድ ራስ ሁለት ምላስ” (Doublethink) ይመዙልናል::

የኢትዮጵያን ትንሣኤ ያበስሩልናል፤ ህልውናዋን ይጠብቃሉ፤ ያስጠብቃሉ ብለን ያሰብናቸው ሁሉ ኢትዮጵያን በበዳይነት ስለውና ክደው የጎጥ ወንበር ሊቀራመቱ ቤተ መንግስቱን እንደ አሞራ በምናባቸው ሲዞሩ ማየት ያሣፍራል:: በፌስቡክ ላይ ተጥደው ሃሣብን ሳይሆን አሉባልታን፣ አግቦና ስድብን እያራገቡ ወጣቱን ደንቁረው በማደንቆር የሚያገኙት ትርፍ ምን እንደሆነም አይገባንም። ይቀጥፋሉ። ይዋሻሉ። ይህን ምክር ሊኦ ቶልስቶይ ‘አና ክረኒና’ በተስፕኘው መፅሃፉ (” መጥፎ መሆን ትችላለህ። ነገር ግን ውሸታምና አጭበርባሪ አትሁን” ይላል። “Be bad, but at least don’t be a liar, a deceiver” (Leo Tolstoy, ‘Anna Karenina’ )

አሁንም የዴሞክራሲው ሂደት ተጨናግፎ የሐገር መበታተን እንዳይከሠት የለውጥ ሃይሉን መቀላቀልና መመከት እንጂ መስንቆ ይዞ የዝናብ መርገምት ማዝነብ እራስን ከማበስበስ ውጭ ትርፍ የለውም:: የነፃነት መንገድ ካለ፤ የነፃነት መንገድ ሁሉ ወደ ነፃነት የሚወስደው በኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው:: የጎጥና የጎሣ ፓለቲከኞች ከወያኔ ቫይረስ እራሣችሁን ነፃ አውጡ:: በጎጥና በጎሣ ፓለቲካችሁ የሚያብድ ኢትዮጵያዊ አይኖርም:: የችግራችን መፍትሄ የመንግስትና የፓርላማ ወንበር ሣይሄን ነፃነትና ዴሞክራሲ ነው። ታላቁ ጆርጅ ኦርዌል “ነፃነት ማለት ሁለት ሲደመር ሁለት አራት ይሆናል ማለት መቻል ነው። ይህ ከተተገበረ ሌላው ይከተላል” ይለናል።

ይህን የቻይናውያን ብሂል ልጨምር::

“ጥሬ ያላቀረብክላት ዶሮን ብዙ እንቁላል እንድትጥል መጠበቅና ግጦሽ የከለከልከውን ፈረሥ ፊጥኖ እንዲጋልብ መመኘት ምን የሚሉት ስነአመክንድ ይሆን?” [“You want the hen to lay more eggs but you don’t give her grains. You want the horse to ride fast but you don’t allow it for grazing. What kind of logic is it?” (Chinese Adage)]

ሞት “የጎሣ ፌደራሊዝምንና አብዮታዊ ዴሞክራሲ”!

ኢትዮጵያና እትዮጵያውያን ያሸንፋሉ!

ኢትዮጵያዊነት የነፃነትና የአሸናፊነት አርማና ሊሻን ነው!