ሸገር ኤፍ ኤም
በአሁኑ ጊዜ 2.8 ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎች በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉባት ኢትዮጵያ በሐገር ውስጥ ተፈናቃዮች ብዛት ከአለም ቀዳሚ ሆናለች…
የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያዎች ማህበር ከመኖሪያቸው የሚፈናቀሉ ዜጎችን ሁኔታና መወሰድ ያለበትን እርምጃ አስመልክቶ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡
የማህበሩ ፕሬዝደንት አቶ ደበበ ሐ/ገብረዔል፣ በእርስ በርስ ጦርነቶች ውስጥ ካሉ ደቡብ ሱዳንና ሶርያን ከመሰሉ ሐገራት ኢትዮጵያ በሐገር ውስጥ ተፈናቃዮች ብዛት መብለጧ ጉዳዩ ምን ያህል ትኩረት የሚያሻው እንደሆነ ያሳያል ብለዋል፡፡
በመንግሥት በኩል ለዜጎች መፈናቀል ምክንያት የሆኑ ችግሮችን ለመቅረፍ ሕገመንግሥቱንና ሌሎች ሕጎችን ማስከበር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
የፀጥታና የደህንነት ተቋማትም በገለልተኝነትና በሐቅ የህገ መንግሥቱን ድንጋጌዎች ሊያስከብሩ ይገባል ብለዋል፡፡
መመሪያ አልተሰጠኝም በሚል ዜጎች ላይ የሕይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት መውደም ሲደርስ ቆሞ የሚያይ የፖሊስ አባል ወይም ተቋም መኖር የለበትም ሲሉም አቶ ደበበ ተናግረዋል፡፡
ማህበሩ የሐገር ውስጥ መፈናቀልን አስመልክቶ የሌሎች ሐገራትን ልምድ በመውሰድ ለችግሩ መላ መፈለግ ስለሚቻልበት ሁኔታም እየተወያየ ነው፡፡
(ማህሌት ታደለ)