የድምር ፖለቲካችን፤ የስድስት ወር ልጅ ወይስ የተጨናገፈ ሽል? (ያሬድ ኃይለማርያም)
ጥቅምት 21 ቀን 2018 እ.አ.አ
ከሚያዚያ ወር ጀምሮ በለውጥ ማዕበል ስትናጥ የቆየችው አገራችን ዛሬ ምን አፈራች፣ ምንስ አጣች፣ ምን ተስፋ ሰነቀችስ፣ ምንስ አደጋዎች ተጋረጡባት የሚለውን ለመገምገም ስድስት ወር በቂ ጊዜ ባይሆነም የተወሰኑ ነገሮችን ለማየት ግን ያስችላል። ለውጡም የስድስት ወር ጤናማ ልጅ ሆኗል ወይስ የተጨናገፈ ሽል የሚለውን ለማየት ግን በቂ ጊዜ ይመስለኛል።
እስቲ ሥርዓቱንም ሆነ እራሳችንን በሃቅ እንሞግት። አሁንም አገራችን ከስድስት ወር በፊት በነበረችበት ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ነው ወይ ያለችው? አሁንም አንባገነናዊ ሥርዓት ነው የተሸክምነው? አሁንም የአፈና መዋቅሩ እንዳለ ነው? ኢትዮጵያስ በመበታተን ዋዜማ ላይ ነች? ወይስ እነዚህ ስጋቶቻችን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊት ተወግደዋል? የፈነጠቀ የብርሃን ጭላንጭል አለ ወይ? ዛሬም መስቀለኛ መንገድ ላይ ነን ወይስ አንዱ አቅጣጫ ተከትለን ወዲፊት ፈቅ ብለናል? የመጣንበት መንገድስ የህግ ልዕልንና የተረጋገጠባት፣ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚበለጽግባት እና ሰብአዊ መብቶች የተከበሩባት ኢትዮጵያን ለማየት የሚያስችለን ወይስ የመንሸራተት ኋልዮሽ ጉዞ? እነዚህን እና መሰል ጥያቄዎችን እያነሳን ልንወያይ እና እራሳችንንም ሆነ መንግስት ለመፈተሽ የምንችልበት ጊዜ ይመስለኛል።
እኔን ጨምሮ ብዙዎች ተስፋ መሰነቃቸውን፣ ብርሃን ማየታቸውን፣ በለውጡ ላይ እምነት ማሳደራቸውን እና እንደ ሕዝብ እና እንደ አገር በተቀናጀ መልኩ አስበን እና ተጨንቀን በጥናት እና በጥንቃቄ ከተራመድን ከፊት ለፊት የተጋረጡትን በዙ አደጋዎችም ማለፍ እንችላለን፤ ካሰብነውም እንደርሳለን የሚሉ እንዳሉ አቃላሁ። የዛኑ ያህልም ቁጥሩ ቀላል የማይባል የህብረተሰብ ክፍልም ገሚሱ ከመነሻውም፤ አብዛኛው ደግሞ እለት ተዕለት ከሚያያቸው አስደንጋጭ እና ተስፋ አስቆራጭ ከሆኑ ክስተቶች የተነሳ ከመነሻው በለውጡ ላይ የነበርው ተስፋ እየተመናመነ እና እምነት እያጣ ምነው ባልተደመርኩ ወይም አለመደመሬ በጀኝ ማለት ጀምሯል። ባጭሩ በማህበረሰባችን ውስጥ ግራ መጋባት በግልጽ እየታየ መጥቷል።
ከለውጡ ምን ጠብቀን ነበር? የጠበቅናቸውንስ ነገሮች በምን ያህል ጊዜ ውስጥ እውን ሆነው እናያቸዋለን ብለን ተስፋ አደረግን? ምንስ አገኘን? ምንስ አጣን? ወደፊትስ የምንጠብቀው ነገር አለ? ወይስ ተስፋችን በጊዜ ተንጣፎ አልቋል? ወይስ መመነሻውም ለውጥ የሚባል ነገር የለም የጥቂቶቻችን ቅዠት እና ያልተጨበተ ምኞት ነው? መገናኛ ብዙሃን እነዚህን ነገሮች እያነሱ ምሁራንን፣ ሕዝቡን እና የለውጥ ኃይሉን ቢያወያዩ መልካም ነው።
በመጣንበት ስድስ ወራት ውስጥ እጅግ በጎ የሆኑ እና መጥፎ የሚባሉም በርካታ ነገሮች በአገራችን ውስጥ ተከስተዋል። ከሁለቱም ክስተቶች አንኳር አንኳር የሚሆኑትን መጠቋቆም ይቻላል።
በበጎ የለውጥ እርምጃ ሊጠቀሱ ከሚችሉት ውስጥ፤
– በዙ ሥራዎች ቢቀሩትም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመንግስት ጋር ተቀራርበው መወያየት መጀመራቸው፣ (የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት)
– አሁንም ጥፋቶችና የመብት ጥሰቶች ቢኖሩም ሕዝብን አድማጭ መንግስት እና ባለሥልጣናት እየታዩ መምጣታቸው፣ (መንግስታዊ ተጠያቂነት መኖር)
– የመገናኛ ብዙሃን በተወሰነ ጫናም ውስጥ ሆነው በፈለጉዋቸው ጉዳዮች ላይ ሕዝብን ማወያየት እና ዘገባዎችን መሥራት መቻላቸው፣ (ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ላይ የታየ መሻሻል)
– የአፈናው መዋቅር ዋና መሳሪያ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩ ሕጎችን ለማሻሻል በግልጽ የሚታዩ እርምጃዎች መወሰዳቸው፤ (የሕግ ማዕቀፉን ለማስተካከል የታየ ጭላንጭል)
– የፓርቲውን ሳይሆን የመንግስትን አስተዳደራዊ መዋቅርን ለማስተካከል የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች እና ጥናቶች (መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የተደረጉ ውጥኖች)፣
– የቀጠናውን ሰላም ለማስጠበቅና ግጭቶችን ለመቀነስ ከጎረቤት አገሮች ጋር የተጀመሩት በጎ ግንኙነቶች (የመንግስት የውጪ ፖሊሲ ላይ የታዩ እምርታዎች)፣
– በሕዝብ ንብረት ላይ የሚደረጉ ዝርፊያዎችን እና አይን ያወጣ ሙስናን ለማስቆም የተጀመሩ አበረታች ሁኔታዎች (የአገሪቱን ሃብት አጠቃቀም ፍትሃዊነት ለማረጋገጥ እየተወሰዱ ያሉ ለውጦች) እና ሌሎች ዋና ዋና የሚባሉ እና የዘለልኳቸው በጎ የለውጥ ማሳያዎችን ልታክሉበት ትችላላችሁ።
አወንታዊ የሆኑ እና ለውጥ አደናቃፊ ሊሆኑ ከሚችሉ ክስተቶች መካከል፤
– ለውጡኑ የሚመራው ኃይል ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት የከፋ ወንጀል በፈጸሙ፣ ከፍተና የአገር ሃብት በዘረፉ እና አሁንም ከተመሳሳይ አድራጎታቸው ባልታቀቡ ነገር ግን በጉያው ያቀፋቸው፤ መገለጫቸው ብዙ (የቅን ጅብ፣ ለውጥ አደናቃፊ፣ አክራሪ ብሄረተኛ፣ ሌቦች፣ ወዘተ … ) የሆኑ ግለሰቦች እና ቡድኖች ላይ በጅምላ ይቅርታ ስም መሸሸጊያ ሆኖ መቀጠሉ እና የተረጋጋ ለውጥ ለማምጣት ሲባል ወንጀል ሲፈጽሙ ለኖሩ ሰዎች የተደረገው ያለመጠየቅ ከለላ የተፈራውን አደጋ ማስቀረት አለመቻሉ፣
– ኢህአዴግ እራሱን ጠንካራ የለውጡ መሪ ለማድረግ በውስጡ ያደረጋቸው ትግሎች ትግሎች በአዋሳው ጉባዔ የተቋጨ ቢመስልም አሁንም በክልሎች መካከል ያለው ውጥረት እና መገፋፋት መቀጠሉ፣
– ወደታች ያለው የድርጅቱ ሰፊ መዋቅር ገና ያልተነካ፣ ለውጥ ያልጎበኘው እና በአስተሳሰብም ሆነ በአሰራር እረገድ ከህውሃት ዘመን የተለየ መሻሻል አለማሳየቱ፣
– በአብዛኛዎቹ ክልሎች ውስጥ ከመቼው ጊዜ በከፋ ሁኔታ አክራሪ ብሔርተኝነት እየታየ እና አንዳንድ ሥፍራዎችም ደም አፋሳሽ ወደ ሆኑ ግጭቶች ተለውጦ መታየቱ እና በርካቶችን ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጉ፣
– አዲስ አበባን የመጨረሻው የፍልሚያ ቦታ ለማድረግ በከተማዋ ላይ የባለቤትነት ጥያቄ በሚያነሱ የኦሮሞ ፖለቲከኞች እና አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ እና የነዋሪዎቿ ነግ በሚሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ የታየው መፋጠጥ እና ውጥረት አስፈሪ አቅጣጫ እየያዘ መምጣቱ እና መንግስትም በዚህ ጉዳይ ላይ እያሳየ ያለው ሚዛን ያጣ እና ለአንድ ወገን ያደላ የሚመስል አቋም፤ (አዲስ አበቤዎች ብለው የሚደራጁ ሰዎችን ከማሸማቀቅ እስከ አስሮ ማጉላላት፤ በተቃራኒው ደግሞ ፊንፊኔ ኬኛ የሚለውን ኃይል ደግሞ እንዲደራጁ እና ጥያቄያቸው እንዲደመጥ ሁኔታዎች ማመቻቸት)፤ እዚህ ላይ ለምን መንግስት ሁለቱንም አብሮ አልጨፈለቀም ወይም ለምን በፊንፊኔ ላይ የባለቤትነት ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎችን የመደራጀት መብት አከበረ የሚል ጥያቄ እያነሳሁ አለመሆኑ ለመግለጽ እወዳለሁ። ሁሉም ሰው በመሰለው መልኩ የሌሎችን ሰዎች መብት ሳይነካ እና ሕግን ሳይጥስ የመደራጀት እና ሃሳቡን የመግለጽ መብቱ በእኩል እየተከበረ አይደለም ከሚል አንግል ነው፤
– በተደጋጋሚ ሲገለጽ የቆየውን የፖለቲካ ኃይሎችን ሁሉ ያሳተፈ አፈራዊ ጉባዔ እና የምክክር መድረክ ችላ በማለት ይሁን ቅድሚያ ባለመስጠጥት የፍኖተ ዲሞክራሲ መቅረጽ ሂደቱ እንዲጓተት እና በተቃራኒውም በድርጅቶች መካከል ውጥረት እና መቃቃር እንዲፈጠር የሚያደርጉ ሁኔታዎች በመንግስት ባለስልጣናት ሳይቀር በየሚዲያው መንጸባረቃቸው፣
– እየታየ ያለውን የፖለቲካ ለውጥ ከወዲሁ በዘር ፖለቲካ ለመጥለፍ እና ለአንድ ወገን የመጣ ክስተት ለማስመሰል በመንግስት ኃላፊነት ደረጃ ከተሾሙ የኦሮሞ ባለስልጣናት አንስቶ ታዋዊቂ ለሂቃን ጊዜው የኛ ነው፣ የኢትዮጵያን ቀጣይ እጣ ፈንታ የምንወስነው እኛ ነን፣ ሥልጣን በእኛ ቁጥጥር ስር ነው፣ ያሻንን ለማድረግ ብንፈልክ ሊያስቆመን የሚችል ኃይል የለም የሚሉ ፉከራዎች እና ዛቻዎች በተደጋጋሚ በመገናኛ ብዙሃን ሲነገሩ ምመደመጣቸው እና በመሬት ላይም ይህንን ምልከታ የሚደግፉ አንዳንድ እርምጃዎች መታየታቸው፣ እና ሌሎች ያልጠቀስኳቸው ተመሳሳይ ችግሮች ጎልተው እና ተደጋግመው መታየታቸውን መጥቀስ ይቻላል።
ትልቁ ቁምነገር አሁን ካለንበት ውጥንቅጥ ሁኔታ ውስጥ ተነስተን ነገ ምን ሊሆን ይችላል? ለውጡ እንዳይቀለበስ እና የሰመረ እንዲሆን ምን ማድረግ ይገባል? ከእያንዳንዳችንስ ምን ይጠበቃል? የሚለው ይመስለኛል። እርግጥ ነው ለውጡ ተጨናግፏል ወይም ለውጥ ከመጀመሪያውም የለም፣ አለነበረም ለሚል ሰው ከላይ ያሉት ጥያቄዎችም ሆነ ውይይቱ ፋይዳ አይኖረውም። ጨለማው አንድም በውስጣችን ካለው የጨለምተኝነት አስተሳሰብ በመነጨ የተፈጠረ የእይታ ግርዶሽ ሊሆን ይችላል አለያም ጨለማውን የሚያሸንፍ ብርሃን እሲታይ ድረስ ጨለማ ነው ብሎ ማሰብ ይቀላል። ወይም ለብዙዎች የሚታየው ብርሃን አልታየን ይሆናል። ይህ ከሆነ የሚያዋጣው ሌላ አቢዮት እና ትግል ነው።
ለውጥ መጥቷል፣ አለተጨናገፈም፣ ተስፋም አለው፣ ከጨለማም ወጥተን ብርሃን እያየን ነው ብሎ የሚያስብ ግን እነዚህን ጥያቄዎች አንስቶ መወያየቱ እና የመፍትሔ ለታጋረጡትም ችግሮች አቅጣጫ መፈለግ ግድ ይላል። ጨለማ ነው ማለት ብርሃን የለም ማለት አይደለም። ብርሃኑ እንዲያሸንፍ ማድረግ ግን የሁላችንም ድርሻ ነው።
መፍትሔ
– መንግስት የጀመረውን የለውጥ ጉዜ ዘላቂ እና የማይቀለበስ እንዲሁን ሕዝብን በየሰልፉ ማንጋጋት ብቻውን በቂ ስላልሆነ የተደራጁትን የፖለቲካ ኃይሎች ያሳተፈ አገራዊ ጉባዔ በአፋጣኝ ሊያካሂድ ይገባል። አገሪቱ ሊትከተል ያሰበችውንም የለውጥ ጉዞ እና ፍኖተ ዲሞክራሲ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ መቅረጽ እና ለሕዝብ ይፋ ማድረግ አላበት፤
– የተቃዋሚ ፓርቲዎችም በምርጫ ጊዜ ሊያካሂዷቸው ከሚችሉ ፉክክሮች እና ግፊያ ለጊዜው ታቅበው በጋራ በመቀመጥ እና መንግስትንም አስጨንቀው በመያዝ የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳውን በማደላደሉ ሥራ ላይ ቢያተኩሩ እና አብረው በአገራዊ መግባቢያ ሰነድ ላይ እየሰሩ በማሳየት ሕዝቡን ሊያረጋጉ ይገባል፤
– በጎጥ የተደራጁ የፖለቲካ ኃይሎችም ሆነ ቡድኖች በሚዲያ ላይ ከሚጠቀሙዋቸው ቃላቶች እና አገላለጾች አንስቶ በሚያደራጁት እና በሚቀሰቅሱት ሕዝብ መካከል የሚያደርጉትን ልዩነትን፣ ጥላቻን፣ በቀልን እና ቁርሾን የሚያሰፉ ንግግሮች ሊታቀቡ ይገባል። በዚህ እረገድ መንግስትም እነዚህን ኃይሎች ሊገስጽ እና እንደ አግባብነቱም ሕጋዊ እርምጃ ሊወስድ ይገባል።
– ጋዜጠኞች እና የማህበረ ድረ ገጽ ተሳታፊዎችም የዘር ጥላቻን ከሚያነግሱ ቅስቀሳዎች ታቅበው ነገር ግን በማንማውም አገራዊ ጉዳይ ላይ በምክንያታዊነት ላይ የተመሰረተ ትችት እና ዘገባ በማቅረብ መንግስትንም ሆነ ሌሎች በአገር ጉዳይ እጃቸውን ያስገቡ አካላትን መንቀፍ፣ መተቸት፣ የሚደነቀውን ማድነቅ፣ የሚወገዘውንም እያወገዙ ማህበረሰቡ የማንቃት ሥራዎቻቸው ሊተጉበት ይገባል።
ባጭሩ አገራችን ትልቅ የለውጥ እድል አግኝታለች፤ ይህን እድል በአግባቡ ተጠቅመን አገሪቱን ከገባችበት ቅርቃር እንድትወጣ መርዳት ከሁሉም ኃይል ይጠበቃል። ይህ ለውጥ ተደናቅፎ አቅጣጫውን ቢስት በትውልድ ሆነ በታሪክ ተጠያቂዎቹ ዶ/ር አብይ እና ቲም ለማ ሳይሆኑ በዚህ ሁላችንም፤ የተደመረውም ያልተደመረውም ነው። እኔ ስላልተደመርኩ በለውጡ የሚመጣው ኪሳራ አይመለከተኝም ማለት አይቻልም። ሁላችንንም ደምሮ ወደፊት ሊጓዝ የሚችል የፖለቲካ ቀመር እንዲመጣ መታገል የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ይመስለኛል።
በቸር እንሰንብት!