የጎሳ አወቃቀር ለጉዳት ለመከፋፈል ዳርጎናል እየተባለ ባለበት ወቅት በወ/ሮ ሙፈሪያት የሚመራው ደሃዴን፣ የደቡብ ክልልን እንደገና በዘር ለመከፋፈል ሲጣደፍ እያየን ነው። በደሃዴን የሚመራው የደቡብ ክልል ምክር ቤት የሲዳማዎች ብቻ የሆነን አዲስ አፓርታይዳዊ ክልል ለመሸንሸን ዉሳኔ አሳልፏል።
ይህ ዉሳኔ ምን አልባት ለጊዜው ኢጄቶ የተባሉ የሲዳማ አክራሪዎችንና ከነኦነግና ኦብነግ ጋር ለዘመናት ሲሰሩ የነበሩ ራስቸውን የሲዳማ ነጻ አውጭ ግንባር ብለው የሚጠሩትን ጠባቦ ዘረኞች ሊያስደስት ይችል ይሆናል። ግን የሲዳማ ማህበረሰብን በእጅጉ የሚጎዳ ዉሳኔ ነው። የሲዳማ ማህበረሰብ የሚጊዳ ብቻ ሳይሆን በዚያ የሚኖሩ ሌሎች ማህበረሰባት ለከፍተኛ አደጋ ማጋለጡ የማይቀር ነው። በቅርቡ አክራሪ የሲዳማ ቡድኖች በወላይታዎች ላይ ያደረሱት ሰቆቃና እልቂት ሁላችንም የምናስታወሰው ነው። አሁን ደግሞ ጭራሽ ይሄ የናንተ ክልል ነው ብለን ከሰጠናቸው ፣ ሌላውን መጤ እያላችሁ ማባረራችሁ ቀጥሉበት ማለታችን ነው።
የደቡብ ክልል አነስ ወዳሉ ሕብረብሄራዊ አስተዳደርኖች መቀየሩ ችግር የለውም። ለምሳሌ የሲዳማ፣ የጌዴዎ ዞኖች አንድ ላይ ሆነው ሲዳማዎች የበላይ የሆኑበት ክልል ሳይሆን በዚያ የሚኖሩ ሁሉም ዜጎች እኩል የሚታዩበት የዘር ልዩነት የማይደረገበት ሕብረ ብሄራዊ መስተዳደር ቢሆን የበለጠ ሊጠቅም ይችላል። መስተዳደሩም እንደ ድሮ የሲዳማ መስተዳደር ቢባልም ችግር የለውም። ግን የሲዳማዎች ክልል ተብሎ ራሳቸው ሲዳማዎችን ነን ብለው የሚጠሩ የበላይ የሆኑበት ክልል መፍጠር ግን ከእሳት ወደ ረመጥ መሄድ ነው።
ይህ ዉሳኔ ከሕግ፣ ከፍትሃዊነት አንጻር ሶስት መሰረታዊ ችግርቾ አሉት።
አንደኛ – የሲዳማ ክልል ሲመሰረት በስተሰሜን በኩል አዋሳ አለች። የደቡብ ክልል ዋና ከተማ ሆና በመላው የደቡብ ክልል ሕዝብ ያደገች ከተማ ናት። በክልሉ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በፌዴራል ደረጃ ብዙ ወጭ አዋሳ ላይ ፈሷል። ይችን ዉብ ሕብረ ብሄራዊ ከአዲስ አበባና ከባህር ዳር ቀጥሎ፣ ምን አልባት ከባህር ዳር በላይ፣ ትልቅና ዘመናዊ የሆነች ከተማን ለአንድ ጎሳ ብቻ መስጠት ኢፍትሃዊነት ነው። በመሆኑም ሲዳማዎች ክልል ካልተሰጠ ብለው ድርቅ ካሉ ያለ አዋሳ መሆን ይኖርበታል። አዋሳ ከተማ ራሱና የቻለን ቻርተር ከተማ ሆና መቀጠል ይኖርባታል።
ሁለተኛ – ከሲዳማ ክልል በስተደቡብ የሚገኝ ሌላ ትልቅ ዞን አለ። የጌዴዎ ዞን። የሲዳማ ዞን የሲዳማ ክልል ይሁን ከተባላ የጌዴዎ ዞን ከደቡብ ክልል ይለያል ማለት ነው። ኩታ ገጥምነቱ ስለሚቀር። የጌዴዎ ዞን ከደቡብ ክልል ተለይቶ የራሱ ክልል ሊሆን ነው ? ወይስ በሲዳማ ክልል ውስጥ ሊጠቃለል ነው ? ስለዚህ የሲዳማ ክልል የመሆን ጉዳይን በተመለከተ ሲዳማዎችን ብቻ ሳይሆን የጌዴዎ ዞን ነዋሪዎችን የሚመለከት ነው የሚሆነው።
ሶስተኛ – ይሄን ዉሳኔ ያሳለፉ የክልል ምክር ቤት አባላት በመቶ በሞቶ ምርጫ አሸነፉ የተባሉ ናቸው። በመሆኑን ይሄንን ዉሳኔ ለመወሰን ሕጋዊ መሰረት የላቸውም። ስለዚህ በሕግ አንጻር ዉሳኔያቸው ተቀባይነት ሊኖር አይችልም።
በዞኢህ ጉዳይ ላይ የዶ/ር አብይ አስተዳደርም ያለውን አቋም ምን እንደሆነ ብናውቀው ጥሩ ነው። ይሄ ዉሳኔ የነ ዶር አብይን አዎንታ ሳያገኝ የደቡብ ክልል ምክር ቤት በራሱ ይሄን ይወስናል ብዪ አላስብም። የሲዳማ ተወካዮች እንኳ ሲዳማ ዞን ወደ ክልል ይዙር ቢሉ፣ የጉራጌ፣ የጋሞ፣ የወላይታ … የተቀረው የክልሉ ምክር ቤት አባላት ከአዲስ አበባ ውስጣዊ መመሪያ ካልተሰጣቸው በቀር እሺ ይላሉ ብዬ አላስብም። በዚህ ጉዳይ ላይ ጋዜጠኞች የዶ/ር አብይን አስተዳደር መጠየቅና እውነታዉን ለማወራ መስራት ያለባቸው ይመስለኛል።
