ዘ.ብ.ጉ.ኦክቶበር 2018
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ምንም እንኳን የሀገራችን አጠቃላይ ሁኔታ ፈታኝና ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ህልውናዋ ሳይቀር አስጊ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረበት ሁኔታ ውስጥ ሥልጣን ቢረከቡም የሀገራችንን የተወሳሰቡና የቆዩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ፣ እንዲሁም ድንበር ነክ ጉዳዮችንና ሀይማኖታዊ ጉዳዮችንም ጭምሮ ለመፍታት ያስችላሉ ብለው ያሰቧቸውን ተከታታይ እርምጃዎችንና ውጤታቸውን በመመልከት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባይባልም አብዛኛው ሕዝብ ድጋፉንና አድናቆቱን ሲቸርዎት ቆይቷል።
ይሁንና ኢትዮጵያን ለረጅም ጊዜ ከገባችበት ከተወሳሰበና ከተንሰራፋ ዘርፈ ብዙ ችግሮቿ መንጭቆ ለማውጣት በሚደረግ ጥረት ውስጥ የተለያዩ መሰናክሎችን እንዳመጣጣቸው በዕውቀትና በጥበብ ማለፍን እንደሚጠይቅ ይታመናል። በዚህም ረገድ በየሞያ ዘርፉ ተደብቀው ያሉና ከፍተኛ ብቃት ያላቸው ባለፈው የተዛባ የፖለቲካ ስርዐት ውስጥ ምንም ዐይነት ሚና ያልነበራቸው ስለሀገሪቷ ከልብ የሚቆረቆሩ ምሁራንን አማራጭ ሃሳብ እንዲያመነጩና የመፍትሄ ሰጪው አካል ሆነው እንዲሳተፉ እያደረጉ ያሉትን ጥረት እንያደነቅኩ ጥሪውንም በመቀበል ለሀገራችን ይበጃል ብዬ ይህችን ምክር አዘል ጥቆማ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ የነበሩ የቆዩ ችግሮችን በማንሳትና ችግሮቹን ለመፍታት የሚያስችሉ ጥቂት ሃሳቦችን በቀናነት ለማቅረብ እወዳለሁ።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚያውቁትና ከታሪክ እንደምንማረው አንድን ሀገር መሪዎችዋ ሊያነሱዋትም ሆነ ሊጥሏት ይችላሉ። መሪ ስል ትልቁን የርእሰ ብሔር ስልጣን የያዙትን ብቻ ማለቴ አይደለም ። በየደረጃው የአንድን ሀገር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተቋማትን እንዲመሩ የሚሰየሙ ባለስልጣኖች ብቃትና ኢንቴንሽን አንድን ሀገር ለዘላቂ ልማት እንዲሁም ለማያባራ ጥፋት ሊዳርጓት ይችላሉ። በዚህ ረገድ በሀገራችን ላለፉት 27 ዓመታት በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዙሪያ በቅርብ ሥራቸውን የምናውቃቸው ባለስልጣናት በተለይም አሁንም በስልጣን ላይ በእርሶ ዙሪያ ቦታ ተሰጥቷቸው አንዳንዶቹ እንደውም በእርስዎ ጭምር ሲሞካሹ ያደመጥናቸውን ነገር ግን ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ በግሉ ዘርፍ ተሰማርቼ ሥሰራ በነበረበት ጊዜ የማውቀውና ባለፍኩበት የመከራና የቁጭት ዘመን ውስጥ አሌ የማይባሉ ጥፋት በሀገሪቷ ላይ ያደረሱ ቁንጮ ባለስልጣናትን ህፀፅ አንስቼ እንዲገለጥ በማድረግ በዋናነት በእርሶ መሪነት በሀገሪቷ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ሊገጥመው ከሚችለው መሰናክል ቀድሞ እንዲጠነቀቅና የማስተካከያም እርምጃ እንዲወሰድ በማሰብ ነው። በዚህም መሠረት ከዚህ በታች ዋና ዋና ጉዳዮቹን በሶስት ርዕስ በመክፈልና ፍሬ ሃሳቦችን በመዳሰስ ለግንዛቤ እንዲረዳ አቅርቤያለሁ።
1ኛ. አዲስ አበባ መስተዳድርንና የከተሞች ልማትን በተመለከተ
• አርከበ እቁባይ ከመቀሌ ወደ አዲስ አባባ መስተዳድር በከንቲባነት ተመድቦ ወደ አዲስ አበባ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ የሚፈልጋቸውን ባለሞያ ተብዬዎች በተለይም የአንድ የቋንቋ ትስስር ያላቸውን በዙሪያው አሰባስቦ ከተማዋን ለነዋሪዋ ሳይሆን ለጥቂት ቡድኖች ፍላጎት ማርኪያ እንድትሆን አድርጓታል። አማረ አስገዶምንና የመሳሰሉትን ቁልፍ ቦታ ላይ በማስቀመጥ በተለይ ከምርጫ 97 ማግስት የከተማዋን ክፍለ ከተሞች ሥራ አስፈጻሚዎችን ሙሉ በሙሉ አዲሳባን ረግጠው በማያውቁ የአንድ ብሔር ተወላጆች በመቀየር ወደ 20ሺ የሚገመቱ ካርታዎችን በአንድ ለሊት በማዘጋጀት በከተማዋና በከተማዋ ዙሪያ የሚገኙ ቦታዎችን ባለቤትነት ወደ አንድ ብሔር ተወላጆች እንዲተላለፍ አድርገዋል። ይህን ህገ ወጥ ሥራ ከተሰራባቸው ቦታዎች ሲኤምሲና ጀሞ አካባቢዎች ዋነኞቹ ናቸው። በነዚህ ቦታዎች የተሰሩ ህንጻዎችንንና የመኖሪያ ቤቶችን ባለቤትነት ፋይል በቀላሉ በማገላበጥ እውነቱን ለመረዳት ይቻላል።
• ከንቲባው አቶ አማረ አስገዶምን የቤቶች ቢሮ ሃላፊ አድርጎ በመመደብ ዲክቴት እያደረ ከነ ዶ/ር መሰለ ጋር በመተባበር የቦርድ አባል እነሱ ዲዛይነርና አማካሪ እነሱ በመሆን ከተማይቱን በእጅጉ ተመሳጥረው ጎድተዋታል። የተመጣጠነና ፈር የያዘ እድገት እንዳይኖራት ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ አድርሰውባታል። ለአብነት ያህል low cost የመኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክት / ኮንዶሚኒየሞች/ የዲዛይን አማራጮችን መሰረት ያደረገ መሆን ሲገባው የነዋሪውን ባህልና ስነልቦና ባላገናዘበ መልኩ ለምሳሌ ያኽል ሶስት እጅ ልስን ሲባል ሁለት እጅ እንዲሁም በአንድ እጅ በተጨማሪ ብሎኬትን በመተኮስ የደረጃ መወጣጫን በብረትና በኮንክሪት በማይጣጣም መልኩ ከስታንዳርድ በታች በመስራት ወዘተ ለደህንነትና ለህልውና አመቺ ባልሆነ ያሰራር ሁኔታ በአንድና በሁለት በሶስት ሰዎች ውሳኔ አመቺ ያልሆኑ መኖሪያ ቤቶች ተሰርተው ህብረተሰቡን ለችግርና ለአደጋ አጋልጠውታል። እነዚህ አገልግሎት ላይ ያሉ ኮንደሚኒየሞች በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ አደጋ ላይ እንደሚወድቁ በአካል እያየናቸው ያሉና ወደፊትም አስጊ የሆኑ ናቸው። ይህ ሁሉ የሆነው ብዙ አዋቂ ባለሞያዎች በሀገራቸው ተወዳድረው የመስራት መብታቸውና ፍላጎታቸው ተገድቦ የሚሰሩበትም ምህዳር እነዲጠብ ተደርጎ ነው። እነዚህ ሥራውን ሁሉ በሞኖፖል የያዙት ባለስልጣናትና ድርጅቶቻቸው ከተማዋን እንዳይሆን እንዳይሆን አድርገው ሕዝብ እስካሁን ድረስ ለከፍተኛ የቤት እጦትና ምቹ ባለሆኑ አካባቢዎች በስጋት እንዲኖር ተገዷል።
• በወቅቱ ከነበሩ የስርአቱ ባለስልጣናት በተለይ የግል ጥቅማቸውን ከህዝብ ጥቅም ከሚያስበልጡት ጋር እጅ ለእጅ ተጠላልፎ የሚሰራው ዶ/ር መሰለ በሞያው የሚከበር ሰው ቢሆንም ካለ አግባብ በገፍ የወሰዳቸውን ፕሮጀክቶች አንዱን ሳይጨርስ ሌላውን በላይ በላዩ እየወሰደ በርካታ ፕሮጀክቶች ላይ የጥራት ጉድለትና ግድፈት እንዲከሰቱ ምክንያት ሆኗል።
ለምሳሌ ዶ/ር መሰለ ያለጨረታ የወሰዳቸው የ13 ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ የታየው የከፋ የጥራት ጉድለት አንዱ ሲሆን በተለይ ከዲዛይን ጋር ተያይዞ ዋጋን ለመቀነስ በሚል ምክንያት ህንፃዎቹን ከተፈጥሮ ወለል በታች /below natural ground level/ ተቀብረው እነዲሰሩ በመደረጉ ሕንፃዎቹን ለአጠቃቀም አስቸጋሪ ከማድረጉም በላይ ለፍሳሽ እንዲጋለጡ በመደረጋቸው ዩኒቨርስቲዎቹ ይህንን ችግር ለማስተካካል ተጨማሪ ከፍተኛ ወጪን በማውጣት መቆሚያ የሌለው ተከታታይ የዲዛይንና የግንባታ ሥራዎች እንዲያከናውኑ ተገደዋል። ይህ የሚያሳየው ወጪን እቀንሳለሁ በሚል ምክንያት በዘርፉ ብቃት ካላቸው ባለሞያዎች ጋር ምክክር እንኳን ሳይደረግ ባልተጠኑና ባልተረጋገጡ ጥናቶችና ዲዛይኖች የተወሰኑ ግለሰቦችን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲፈፀሙ ከነበሩ የረቀቁ ሴራዎች መሃከል ለአብነት የሚጠቀስ ነው።
• በቀድሞው የደርግ የፖለቲካ ስርአት አብዛኛው የግንባታና የዲዛይን ሥራ በመንግስት ድርጅቶች ብቻ ሞኖፖሊ የተያዘ መሆኑ ይታወቃል። ነገር ግን የኢህአዴግ መንግሥት ወደስልጣን ሲመጣ የመወዳደሪያ ሜዳው ችሎታና እውቀትን ያማከለ የሁሉንም ተሳታፊዎች እድገት ማዕከል ያደረገ እንደሚሆን ይገመት ነበር። ይሁን እንጂ በተለይ በትልልቅ ግንባታዎች ላይ ተቋራጮችም ሆኑ አማካሪዎች ተመጣጣኝ የእውቀትም ሆነ የሪሶርስ አቅም እንደነበራቸው እየታወቀ ለባለሥልጣናት ቅርበት ያላቸው ተቋራጮችና አማካሪዎች ሥራውን በሞኖፖል ከአምባገነኑ አገዛዝ ባልተለየ መልኩ ሲቆጣጠሩት ቆይተዋል። ለአብነት በአዲስ አበባ የሀገሪቷን ብሔራዊ ስታዲየም ለመገንባት በወጣው ዓለምአቀፍ ጨረታ ከገቡት የዲዛይን ተወዳዳሪ ፕሮጀክቶች መካከል ጀዳው አማካሪ አርክቴክቶችና ኢንጅነሮች በዳኝነት አሸናፊ ሆነው በሴክተሩ የመንግስት ሚኒስትር መስሪያ ቤት እውቅና ተሰጥቷቸው ሽልማት ካገኙ በኋላ በማናለብኝነት ሌላው አቅም የለውም በማለት በቀድሞው የሀገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ወደሚዲያ በመውጣት ጉዳዩ የፍርድ ቤት ጉዳይ ነው ብለው ሲገልፁ በማይታወቅ ሁኔታ አስፈፃሚ አካላት ላያ ጫና ተፈጥሮ ያለአግባብ ለዶ/ር መሰለ ድርጅት ፕሮጀክቱ ተሰጥቷል። እዚህ ላይ ከግንዛቤ ሊወሰድ የሚገባው ጉዳይ የባለሞያዎች ስብስብ ጁሪ( ዳኞች) የተመረጠው ዲዛይን በገላጋይ ዳኝነት ( arbitration) ሳይታይ በአንድ የግለሰብ ዳኛ ከስልጠኑ ውጪ እንዴት ለሌላው ድርጅት ተላልፎ መሰጠቱ ነው።
• አማረ አስገዶም የመንግስት ሰራተኛ ሆኖ በከተማዋ ቁጥሩ የማይታወቅ በዶላር የሚከራዩ ቤቶች እንዳሉት የአደባባይ ምስጢር ነው። በተጨማሪም አርከበ እቁባይ በተዘዋዋሪ ከቻይኖች ጋር በመመሳጠርና ቻይና ልኮ ያስተማረውን ልጁን ዋና ተቆጣጣሪ በማድረግ ሲኤምሲ አደባባይ የሚገኘውን የፀሐይ ሪል ስቴት ማስገንባቱ የሀገሪቷ ሃብት ወዴት እየሄደ እንደሆነ አመላካች ነው።
• ካዛንቺስ አካባቢን ተፋፍኖ የተገጠገጠው ሕንፃ ሞያተኞች ማስተካከያ እንዳይሰጡና እንዳይተነፍሱ ታፍነው የሚናገሩትን አንሰማም ብሎ በሞያ ጉድለት በግልጽ ለመንገደኛም በሚታይ ሁኔታ /Concrete Jungle/የኮንክሪት ጃንግል ፈጥረዋል። በዚሁ ምክንያት በዛው አካባቢ ያሉ ጥሩ ጥሩ ሕንፃዎች ተፋፍገው እንዲሰሩ በመገደዳቸው ለከተማዋ ሊሰጡ የሚችሉትን ውበት ተነፍገዋል።
• አንድ ሕንፃ ሲሰራ ለሃምሳ ዓመት ያህል እንዲቆይ ታስቦ ቢሆንም እነ አቶ አርከበና በስራቸው የተደራጁት ቡድኖች በመሪ ፕላኑ መሰረት መንገድ እንደሚወጣባቸው የሚታወቁ ቦታዎችን ጭምር ለሚፈልጉት ሰው ፈቃድ እየሰጡ ግንባታዎችን አካሂደዋል።
• አቶ አርከበ የማፍያ ሥራቸውን አላሰራ ብሎ የያዛቸውን የቀድሞ ብሔራዊ የከተማ ፕላን ኢንስቲቱትን(ብከፕኢ) አፍርሰዋል። የብከፕኢ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ግለሰብ ለአቶ አርከበ ብከፕኢን ማፍረስ አይችሉም ፣ ኢንስቲትይቱ የተቋቋመው በአዋጅ ነው “ከመሬት ተነስቶ ማፍረስ አይቻልም” ብለው ባለሞያዎች በተገኙበት ስብሰባ ላይ ሲከራከሯቸው “አሳይሃለው ነገ አፈርሰዋለሁ” በማለት እንዳሉትም በማግስቱ አዋጅ አስወጥተው ያፈረሱ ባለሥልጣን
ናቸው። በዚህም ምክንያት ነባራዊው አሉታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ካስከተለው መዘዝ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ላሉ ከተሞች ያልተመጣጠነና የተዛባ ዕድገት እንዲሁም የከተማና ገጠር ሀገራዊ ንፅፅር በመቶኛ ከፍተኛ ልዩነት መንስኤ ሊሆን ችሏል።
2ኛ. የምድር ባቡርን በተመለከተ
• የሰበታ ጅቡቲን በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ወጪ የወጣበትን ፕሮጀክት ካለአገልግሎት መና የቀረበት ሁኔታ ላይ ነው ያለው። ፕሮጀክቱ ቢያልቅም ጥቅም እየሰጠ አይደለም። በቢሊየን ዶላር የሚቆጠር በብድር የተገኘን የሃገር ሀብትን ካለጨረታ ለአንድ ሥራ ተቋራጭ መስጠት ምን ይባላል? እንደዚህ ዓይንት ሜጋ ፕሮጀክቶች ለአንድ ተቋራጭ ሲሰጥ ያለ አንድ ነገር ሊሰጥ እንደማይችል ግልጽ ነው። በተጨማሪም የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት የሀገሪቷ ከፍተኛ ባለሞያዎች ሳይሳተፉበትና ሳይተቹበት በተወሰኑ ግለሰቦች ውሳኔ ብዙ ቶን ኮንክሪት ከመሬት በላይ ካስት/cast/ ሲደረግና ከተማዋን ለሶስት ላራት ሲከፋፍል ነዋሪው ህብረተሰብ ላይ የፈጠረው ጫና እና ከተማዋ ላይ ያስቀረው አሉታዊ ገጽታ ይሄ ነው አይባልም። የከተማዋ የመሬት አቀማማጥ ለባቡር ሀዲድ ሥራ አመቺ ቢሆንም የውስጥ ለውስጥ መንገድ /tunnel/ መጠቀም ሲቻል ያለአግባብ ለአንድ ሥራ ተቋራጭ በቋንቋ ግንኙነት ለሀገር በቀሉ/aser construction/ ያለውድድር ተሰጥቶ ሀብት ማካበቻ ሆኗል። ይህ ሁሉ በደል ሳያንስ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ዋና መስሪያቤት የግንባታ ሥራ ለቻይናው ስቴት ኮንስትራክሽን ቢሰጥም በሰብ ኮንትራት/sub construct/ ስም አሁንም ለአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ሥራ ተቋራጭ ተሰጥቶ የሀብት ማካበቻ እየሆነ ይገኛል። ይህም የሚያሳየው ያለው የነፃ ውድድር ሜዳ አለመሆኑንና በትውውቅ ጋብቻና በአንድ አካባቢ ተወላጆች ሜጋ ሥራዎች በሞኖፖል ተይዘው ሃገሪቷ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ መሆናቸውን ነው። በዚህም ምክንያት ሁኔታው ተስፋ ያስቆረጣቸው ሌሎች የሥራ ተቋራጮችና አማካሪዎች ሥራ በማጣት ፈቃዳቸውን እየመለሱ ሲገኙ ለእስር የተዳረጉና ከሀገር የተሰደዱም ይገኙበታል።
• አዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ሥራ ላይ ከዋለ የቆየ ቢሆንም ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የፈሰሰባቸው በሁሉም ከመሬት በላይ ላሉ ጣቢያዎች የተገጠሙት ተንቀሳቃሽ ደረጃዎችና አሳንሰሮች (escalators &elevators ) አንዳቸውም አገልግሎት እየሰጡ አይደሉም።
3ኛ. የኢንዱስትሪመንደርንበተመለከተ
• በከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር የቤቶች ኃላፊ የነበረውን አማረ አስገዶምን ወደ ኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች ኮርፖሬሽን ምክትል ሥራ አስፈፃሚ አድርጎ በማምጣት አርከበ እቁባይ የቦርድ ሰብሳቢ፣ አማራ አስገዶም ምክትል ሥራ አስፈፃሚ ፣ ዋና ሥራ አስፈፃሚን ለይስሙላ ከኦሮሞ ተወላጅ በማድረግ እንደ ዕቃ በማስቀመጥ ሁለቱ ያለ ምንም ተቀናቃኝ በሀገሪቷ የተሰሩ የኢንዱስትሪ መንደሮች ግንባታንና የማማከር ሥራን በሙሉ ለሚፈልጉት ሥራ ተቋራጭ አመቻችተው ያደሉ ሲሆን አሁንም እየሰጡ ይገኛሉ። ለምሳሌ ያህል ከነሱ ጋር በቅርበት ከአዲስ አበባ መስተዳድር ጀምሮ አብሮ ሲሰራ ለነበረው ለዶ/ር መሰለ አብዛኛዎቹን ሥራዎች በመስጠት ያለ ምንም ተቀናቃኝ እንደፍላጎታቸው የሀገሪቷን ሀብት በመበዝበር ላይ ቆይተዋል። አሁንም እየመዘበሩ ይገኛሉ። እንደዛም ሆኖ ሥራው መሰራቱ እሰየው ሊያስብል የሚችል ቢሆንም ለሀገር በቀል አቻ ኩባንያዎች ሊተላለፍ የሚገባው ምርጥ ተመክሮና እውቀት ሳይተላለፍ ቀርቷል።
• ከኢንዱስትሪ መንደሮች ግንባታ መካከል አንዱ የሆነው የአግሮ ኢንዱስትሪ መንደሮችን በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች ውስጥ ለመገንባት ከታቀደው ውስጥ አንዱ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኘው አግሮ ኢንዱስትሪ መንደር ነው። ምንም እንኳን ለኦሮሞ ክልል የኢኮኖሚ አብዮት ያመጣሉ ከሚባሉት አንዱ ቢሆንም ግንባታውን የሚያከናውነው የወላቡ ኮንስትራክሽን የቦርድ ሊቀመንበር ዶ/ር መሰለ ሆኖ ሳለ ግንባታውን የመቆጣጠርና የማማከር ሥራውንም እራሱ እየሰራው መሆኑ ሌላው ባለድርሻ
አካልና የኢትዮጵያ ህዝብ በዝምታ እየተመለከተው ይገኛል። የሀገሪቷ ህግ እርስ በእርስ የጥቅም ግጭት የሚያስከትልን ሥራ መስራት የሚከለክል ቢሆንም ይኽው ፕሮጀክት በማናለኝብነት ያለምንም ሶስተኛ ወገን ቁጥጥር እየተሰራ ይገኛል። ይሄንንና ከላይ የተጠቀሱትን ጉዳዮች የሚመለከተው የመንግስት አካል ጉዳዩን መርምሮ እውነቱን አውጥቶ ለሕዝብ ማሳወቅ ይጠበቅበታል።
•ከዚሁ ጋር በተያያዘ እግረመንገድ ቆም ተብሎ ግንዛቤ ሊወሰድባቸው የሚገቡ ፦ ይህ መጠነ ሠፊ ግንባታ ከፍተኛ በሆነ የውጪ ብድር የሚሰራ ከመሆኑ አንፃር ካለበቂ ካሣ ከሚፈናቀለው አርሶ አደርና ከሚቃወሰው ተፈጥሮአዊ ሥነ-ምህዳር አኳያ ሊፈጠር የሚችለው ተመጣጣኝ ያልሆነ የሥራ እድል እንዲሁም ሌላው ዓለም እየደረሰበት ካለው ሰው አልባ (robotized ) ሥልተ – ምርት ጋር ሲወዳደር የዚህ አሰራር ስርአት አዋጪነቱና ዘላቂነቱ ከዚሁም በላይ ከመንግስት ጣልቃ ገብነትና ” ና እዚህ ግባና ሥራ” ከሚለው መርህ በተጓዳኝ ሀገርን በተለይ የሚለውጡት ፈጠራ አከል ችሎታ ያላቸው ግለሰቦች መሆናቸውን አምኖ “ነፃ ሜዳ እንካ” የሚለውን ፍትሃዊ መሪ ቃል በመንግሥት ደረጃ መተግበርን የመሳሰሉት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ናቸው።
በመጨረሻም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እርስዎ እነዚህን አንኳር ጉዳዮች በጥልቀት ሳያጤኑ የጥፋት ተዋናይዎቹን የኢትዮጵያ ብርቅዬ ልጅና ሰባት ቀን የሚሰራ ፣ ሠርቶ የሚያሳይ ብለው በአደባባይ ሲያሞኳሿቸው ይህ የተራበ፣የተቸገረ፣የታሰረና ሞራሉ የተነካ የሀገሪቷ ባለሙያም ሆነ ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በምን ህሊና ይቀበሎታል? ከዚህም በተጨማሪ ከላይ የተጠቀሱት አሉታዊ የዝቅጠት ምሳሌዎች እንደ መልካም ማሳያ የአብነት ሚዛን ሲጠቀሱ ለአዲሱ ትውልድ እንደ አሳሳች የስነ ምግባር መለኪያ ሊወሰዱ ስለሚችሉ ጉዳዩን እንደገና በአጽንኦት እንዲመረምሩትና አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃም እንዲወስዱ ስጠይቅ ከታላቅ አክብሮት ጋር ነው።
ዘሪሁን ብርሃኑ ጉተማ /ከአትላንታ ጆርጂያ/ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ በግሉ ዘርፍ ተሰማርቶ ሲሠራ የነበረ።

