አማራ ሆይ! አብንን በመማረክ የራስህ አድርግ!!!

ትናንትና አብኖች ሥራ ላይ ነን ስንላቹህ ሥራ ላይ ነን ማለታችን ነው!” ምንትስ በማለት ጉራ እየቸረቸሩ ይሄንን ከታች የምታዩትን ሕንፃ በማሳየት አብን በፕሮ. (በሊጠ.) ዐሥራት ወልደ ኢየሱስ ስም የስትራቴጂክ (ሥነ ስልት) ጥናትና ሥልጠና ማዕከል አስመረቀ!” የሚል ዜና ለቀው ተመልክቸ ነበረ፡፡

ዜናውን ስሰማ በጣም ተደንቄ ከመቸው ገነቡት?” ብየ እራሴን ጠይቄ ነበር፡፡ ምክንያቱም ከተመሠረቱ ወዲህ ያለው ዕድሜያቸው ይሄንን ሕንፃ ለመገንባት በቂ አይደለም፣ የገንዘብ አቅምም የላቸውምና ነው፡፡ እንዲሁም የሕንፃው ግንባታ የተገባደደው ከአብን መመሥረት በፊት በመሆኑ ነው፡፡

ለካ ነገርየው ሌላ ነው፡፡ ይሄንን የመኝታ ክፍሎች፣ የሥልጠና አዳራሽ፣ መለስተኛ መወያያያ ክፍሎች፣ የምሥልና ድምፅ ክምችት ክፍልና ስቱዲዮ (መከወኛ ክፍል) እንዲሁም ቤተመጻሕፍት ያለውን ትልቅ ሕንፃ የገነባውና ለአብን ያበረከተው አንድ ስሙ ያልተገለጠ ተቆርቋሪ አማራ ኖሯል ለካ፡፡

እንግዲህ ይመስለኛል ሰውየው ሕንፃውን ሲገነባ አብን ገና ስላልተመሠረተ ሕንፃውን ገንብቶ ለሕዝብ ለማበርከት አስቦ ይመስለኛል ገንብቶት የነበረው፡፡ አሁን ላይ ሲያስበው ሕንፃውን ለሕዝብ ቢያበረክተው እንዳሰበው ሕንፃው ለሕዝብ አገልግሎት መዋሉ ቀርቶ የብአዴን የቀበሌ መዋቅር መጠቀሚያ ሊሆን እንደሚችል በመገመቱ ፕሮ. (ሊጠ.) ዐሥራት ወልደ ኢየሱስ የሚዘከሩበት ሆኖ ለአብን ባስረክበው ነው የአማራ ሕዝብ ተጠቀሚ ሊሆን የሚችለው!” ብሎ በማሰቡ ለአብን ያስረከበው ይመስለኛል፡፡

እነሱ ግን ልክ እነሱ የገነቡት አስመስለው አብን ሥራ ላይ ነው ስንላቹህ ሥራ ላይ ነው ማለታችን ነው…. !” እያሉ ጉራቸውን በመቸርቸር የሚከተለውን መግለጫ አወጡ፦

“””የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ–አብን የአማራ ሕዝብን የህልውና ጥያቄዎች በመመለስ በአስተማማኝ መልኩ የሕዝባችን ዘላቂ ጥቅሞች፣ መብቶችና ፍላጎቶችን ለመፍታት የሚያስችሉ የፖለቲካና ማኅበረ–ኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ስትራቴጂዎችንና ፕሮግራሞችን ነድፎ ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያግዝና ተተኪ አመራሮችን በልዩ ልዩ ሥልጠናዎች ለማብቃት እና ለማፍራት የሚያስችል የስትራቴጂክ ጥናትና ሥልጠና ማዕከል ዛሬ ጥቅምት 25/2011 /ም በባሕርዳር ከተማ በይፋ መርቆ ከፍቷል። ማዕከሉ በታላቁ የአማራ ሰማዕት ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ስም የተሰየመ ሲሆን ይፋዊ መጠሪያውም «አስራት ወልደየስ የስትራቴጂክ ጥናትና ሥልጠና ማዕከል» ተብሏል! ማዕከሉ ከአንድ ወጣት አማራ በተሰጠ የነፃ ውለታ የተከፈተ ነው። በዚህ አጋጣሚ ለስትራቴጂክ ጥናትና ሥልጠና ማዕከልነት እንድንጠቀምበት ቤታቸውን ላልተወሰነ የጊዜ ገደብ ላበረከቱልን ድንቅ የአማራ ባለውለታ ወጣት አማራ በንቅናቄያችን አባላት፣ ደጋፊዎችና በመላው አማራ ሕዝብ ስም አክብሮትና ምስጋናችንን እንገልፃለን። ሌሎች ባለሐብቶችና ግለሰቦችም የአማራ ሕዝብ የተደቀነበትን የኅልውና አደጋ ለመቀልበስ አብን እያደረገ ያለውን ጥረት እንዲደግፉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፥ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!

አማራ በልጆቹ ትግል ታሪኩን ያድሳል!””” የሚል መግለጫ በመልቀቅ የአበርካቹን ክሬዲት (ዋጋ) ለራሳቸው ለመውሰድ ጥረት አደረጉ፡፡ በጣም አሳፋሪ ነገር ነው፡፡

እርግጥ ነው አበርካቹ ሕንፃውን ለአብን ለአንድያው አልሰጡትም፡፡ ምክንያቱም ነገ አብን ያልጠበቁትን ነገር ሲፈጽም ቢያገኙት ወይም በአማራ ሕዝብ ላይ ክህደት ሲፈጽም ቢገኝ ለእነዚህ ነው ወይ ንብረቴን የሰጠሁን?” ብለው ከፍተኛ ቁጭት ውስጥ መግባት አልፈለጉም፡፡ ስለሆነም እኒህ ብልህ ሰው ምን አደረጉ አብን ያልሆነ ነገር ቢፈጽም ልቀቁልኝ!” ብለው ማስለቀቅ የሚችሉበትን ሁኔታ አመቻችተው ላልተወሰነ ጊዜ በነጻ እንዲገለገሉበት ሰጧቸው፡፡ በዚህ መልኩ በነጻ እንዲገለገሉበት መስጠትም ራሱ ታላቅ አበርክቶ ነው፡፡ ኪራይ ይከፈልበት ቢባል በየወሩ ከመቶ ሽህ ብር በላይ የሚጠይቅ ሕንፃ ነውና፡፡

ከዚህ ከለጋሹ አበርክቶ መረዳት የምንችለው ቁምነገር ቢኖር አማራ የራሴ ነው!” የሚለውን ድርጅት ቢያገኝ የት ድረስ አበርክቶና አስተውጽኦ ለማድረግ፣ ዋጋ ለመክፈል የተዘጋጀ፣ ፈቃደኛና ቁርጠኛ የሆነ መሆኑን ነው፡፡

ከዚህ ቀደም እንደምታውቁት አብንን የመሠረቱ ሰዎች አብዛኞቹ የብአዴን አባላት በመሆናቸው ምክንያት አብንን እንደማላምነውና ከብአዴን ንክኪ ነጻ የሆነ፣ በአማራ ሥነልቡናና ማንነት ላይ የተመሠረተ ማለትም ኢትዮጵያዊነትን መሠረቱ ያደረገና አካታች ትክክለኛ የአማራ ድርጅት መመሥረት እንዳለብን በማሳሰብ እንቅስቃሴ እንደምጀምር መግለጤ ይታወሳል፡፡

ብየም አልቀረሁ ይሄው ከዚያ ጊዜ ጀምሬ እንቅስቃሴ በማድረግም ይገዳቸዋል ብየ የገመትኳቸውን አካላትና ግለሰቦችንም አነጋግሬ ነበር፡፡ በእጅጉ አደከሙኝ! ወይ እሽ አይሉ ወይ እምብኝ አይሉ እንዲሁ አደከሙኝ፡፡ እንደተረዳሁት ሲሰለቸው ይተወናል!” ዓይነት ነገር ነው አኪያሔዳቸው፡፡ እምብኝ!” ብለው ፈሪ እንዲባሉ አይፈልጉም፡፡ እሽ!” እንዳይሉ ደግሞ ይፈራሉ፡፡ ለውጥ የተባለው የወያኔ ድራማ (ትውንተ ሁነት) እንደሆነ ያውቃሉና፡፡

ይሄ ፍርሐት እንዳለባቸው ስለሚገባኝም ሞት ካልቀረልን ዝም ብሎ እንደመሥዋዕት በግ እየተነዱ ከማለቅ ታግሎ መሞት በእጅጉ የተሻለና ወንድነቱም ይሄ መሆኑን፣ አማራ ያለበትን የህልውና አደጋ መቀልበስ የምንፈልግ ከሆነ መንገዱ ይሄና ይሄ ብቻ መሆኑን ለማስረዳት በመጣር ብዙ ደከምኩ፡፡ ይሁንና ከመጡት ይልቅ የቀሩት ናቸው የሚበዙት፡፡ ባጭሩ ስምና ከፍ ከፍ ያለ ደረጃ ያላቸው ሰዎች ቀርተዋል ሊሳተፉ አልፈለጉም፡፡ በዚህ ምክንያት ትቸዋለሁ፡፡ የራሴን ትግል በግል ማድረጌን ግን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እግዚአብሔር ባስቻለኝ መጠን በሕይዎት እስካለሁ ድረስ እቀጥላለሁ፡፡

አሁን ግን ማለት የፈለኩት ዐቢይ ቁምነገር ቢኖር ከዚህ ቀደም አብን ብአዴን የአማራን ሕዝብ ትግል ለመቀልበስ፣ ለመያዝ፣ ለመቆጣጠር፣ ለመማረክ ያቋቋመው ብአዴን ቁ. 2 ነውና እንዳትቀላቀሉት ተጠንቀቁ!” ብያቹህ የነበራቹህ ወገኖች ከላይ በገለጽኩላቹህ ችግር ምክንያት ከወያኔ/ብአዴን ንክኪ ነጻ የሆነ ትክክለኛና ጠንካራ ድርጅት የመመሥረቱ ነገር ሊሳካ ስላልቻለና ከሀገራችን ፖለቲካ (እምነተ አሥተዳደር) ተሞክሮ መማር እንደምንችለው አንድን የፖለቲካ ድርጅት ከወያኔ ሰርጎ ገቦች መጠበቅ መከላከል ፈጽሞ የማይቻል በመሆኑ አብንን ተቀላቅላቹህ አብንን የአማራ ሕዝብ ድርጅት እንድታደርጉት መልእክቴን ማስተላለፍ እወዳለሁ፡፡

የአማራ ልኂቃንና ባለሃብቶች ከዚህ ውጭ አማራጭ ያለን አይመስለኝም፡፡ የወያኔ/ብአዴን ሰርጎ ገቦች አሉና በሚል እራስን ማግለሉና መቆጠቡ የአማራን የነጻነት ጉዞ በእጅጉ የሚያራዝም እንጅ ሕዝባችንን የሚጠቅም አቋም ሆኖ እየታየኝ አይደለም፡፡ ያሰብነውን ድርጅት መመሥረት ችለን ቢሆንም እንኳ ጅርጅቱን ሙሉበሙሉ ከሰርጎገብ መጠበቁና መከላከሉ የሚቻል ነገር ባለመሆኑ፤ እንዲህ መሆኑ የሚቀር ካልሆነም ሌላ ድርጅት መመሥረት ሳያስፈልግ እዚሁ አብን ውስጥ ግቡና አብንን ከብአዴን ካድሬዎች (ወስዋሾች) እጅ ነጥቃቹህ የአማራ ጅርጅት እንዲሆን ታገሉ፣ አስተዋጽኦ አበርክቱ፣ ለግሱ፣ አጠናክሩ፣ አደራጁ ማለትን እወዳለሁ!!!

ድል ለአማራ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com