የጉምቱው የፖለቲካ ሰው የዛሬ ትችት
መርህ እና ትግል፣ ለውጥ ስንል
=====================
እንዲህ ላቅርበው። መቸውንም ቢሆን ግለሰብ ላይ ያነጣጠረ ትችት በዘመኑ አነጋገር “አይመቸኝም”። ዛሬ አንድ ጉምቱ እና ሁላችንም አይተን የማናልፈው ጽሁፍ አቅራቢ በዚሁ በማህበራዊ ሚዲያ ያቀረቡትን በማየቴ ነው መታዘቤን መደበቅ ያልቻልሁት። አስተያየቱ አዲስ እየተመረጡ የስልጣን ማማውን በመያዝ ላይ ያሉትን ተሿሚወች አስመልክቶ ሲሆን በይበልጥም የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ፕሬዜዳንት

(አዲስ የተሾሙትን የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ተብሎ ይታረምልኝ)

ሆነው የተሾሙትን እመቤት ለሦስት ጨቋኝ ስርአቶች ያገለገሉ ናቸው እናም እንዴት እኒህ ሴት ተመረጡ የሚል ቅሬታ ነው። ምናልባት በትችቱ ሁላችንም ልንስማማ እንችላለን። በበኩሌ አሮጌውን በአዲስ ብርጭቆ እንዲሉ ሁሉም ተሿሚወች ሴቶች ከመሆናቸው በቀር የስራቱ ውጤቶች ናቸው። ህወሓት መራሹ ዘረኛ ስርአት ወልዶ ያሳደጋቸው ማለት ነው።

ይህን ለማብራራት አስፈላጊ አይመስለኝም ሆኖም ትዝ ይላችኋል ደብረጺዮን በንቅናቄው ሰሞን በጥብቅ ተሀድሶ ታድሰን ወጥተናል ያለን ሰሞን ማለት ነው ህወሓት ለአንድ ወር ተቀምጣ ያማጠችው ይህን ነበር። አይቀበሉ ከባድ ፈተና ለመወጣት እና ስርአቱን ከመፍረስ ለማዳን፣ ህገመንግቱን ከመናድ ለማትረፍ የግድ አይቀበሉ ፈተና ማለፍ ነበረባቸው። ግን ያሲሆን ስርአቱን ማትረፍ ማለት ያሳደጓቸው ልጆቻቸውን ከአይን እርቀው የቆዩትን ቦታ ማሲያዝ ማለትም ነው። እንደሚመስለኝ ተደጋጋሚው የአራቱ እድምተኞች (ኢህአዴጎች) ስብሰባወች ዋና አጀንዳም ይኸው ይመስለኛል።
በንቅናቄው (በትግሉ አፍላ) ማግስት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቦታ ሲይዙ አንድ የተቃዋሚ ቲቪ ተች ለሚኒስቴርነት የተመኛቸውን ስም ዝርዝር አቅርቦ አይቸ ነበር። ሁሉም የሕዝባዊው ትግል ደጋፊወች እና የስርአቱ ተቀናቃኞች የነበሩ ምሁራንን፣ በተመክሮ እና በእውቀት የዳበሩ ግለሰቦችን ያካተተ ምኞት ነበር። ከነዚያ ውስጥ ካልተሳሳትሁ የዳኛ እና የታጋይዋ ብርቱካን ሚዲቅሳም ስም እንደነበረ አስታውሳለሁ። ባጭሩ ለዛሬ ትዝብት ያበቃኝን ይህን ስጫጭር ጉምቱው የእድሜ ባለጸጋ እና የሦስቱም ስርአቶች ተቀናቃኝ የነበሩት ተች (ከነበሩ ማለት ነው) ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንድንደግፍ አበረታተውን እንደነበር አይዘነጋም። የእኔም ትዝብት ከዚህ ጋር የተቆራኘ ነው። መቸም ልምድ እና ተመክሮ የሚባለው ይህ ነው። አስቀድሞ ማመስገን ለመውቀስ አስቸጋሪ ነው ይሏል። ምኑንም ሳናይ ኢህአዴግን እስከምናምኑ መደገፉ እና ለኔ ስትሉ ሁላችሁ ደግፉ የሚለው አድራጎት አሁን እየቆየ ሲታይ ያሉትን መልሶ በሌላ መድገም ያስገምታል ባይ ነኝ።
በኢትዮጵያ ሕዝብ ደም እና አጥንት የተገኙ ድሎች አሉ። ግን አሁንም ምሉእ አይደሉም። ድሎች ተሸራርፈዋል ባይ ነኝ። በሌላ በኩል ለወቀሳም ሆነ ለሙገሳ መቸኮሉ ተገቢ ላይሆን ይችላል።

ሌላ ትዝብት ልጨምር፦ የስርአቱ ተቃዋሚ ነን ብለው ለአመታት ሲውተረተሩ የነበሩት ባለፈው ብዙ ጉድለት ስለነበራቸው ተጠናክረው ትግሉን መምራት ይቅር እና ብዙወች የዚህ ወይንም የዚያ ጥገኛ ነበሩ። ከመተባበር እና በራስ መተማመንን ከማጠናከር ይልቅ ጥገኝነት የመረጡም ነበሩበት። እንዴውም የእኔ እበልጥ የእኔ እበልጥ የአዳራሽ ቅድድሞሹ ቦታ የያዘባቸውም ይመስለኝል ድፍረት ካልሆነብኝ። የስርአቱ ባለቤቶች ይህን ክፍት ቦታ መውሰዳቸው ፍጥነት እና ችሎታቸው ገላጭ ነበር። የሰሜን ጎንደር ትግል ሲግም እና ዜጎች በመትረጌስ ሲቆሉ የት ነበር ታጋይ እና አታጋይ የተቃዋሚ ድርጅቶች እከሌ ከእከሌ ሳንል ብንወቅስ መብቻችንም የሆነ ተግባርም ስለሆነ ሊቀበሉ ይገባል። ባጭሩ ሕዝባዊው ትግል መሪ አልባ ስለነበር (ከተቃዋሚው ማለት ነው) ከገዥው ፓርቲ የወጡት የአሁኑ ጠ.ሚ እና መሰል አቻወቻቸው ክፍቱን ቦታ ሞሉት። ለዚህም ይመስለኛል ለመውቀስ የሞራል እና የልብ ድፍረቱን ብዙ ዜጋ ያጣው። ይህ ከሆነ ያንኑ የስርአት አገልጋይ የነበሩት ቢመረጡ ችግሩ ምንድን ነው? ብለው የሚጠይቁ ብዙወች ናቸው።

አንዳንድ ነገርም አለ፦ በበኩሌ ስርአቱ ማለት ሀገ መንግስቱ ማለት ነው። ሌላው ቢቀር ሀገመንግስቱ እንኳን ሙሉ ይወገድ ባይባል በጣም ብዙ ለትግሉ መነሳሳት ምክንያት የሆኑ አሉበት። ለምሳሌ ክልል ምንም ግዜ ቢሆን እስካለ ዘረኝነት ይኖራል። ፌደራሊዝምን ከክልል ማያያዝ ማደናቆር ካልሆነ ፌደራሊዝም እና ኮንፌደሬሽን የተለያዩ ናቸው። በአሁኑ ሰአት ያለው የፌደራል አወቃቀር ከኮንፌደረሽንም የበዛ እንደሆነ ግልጽ ነው።
ለምሳሌ ያህል አሜሪካኖች እና የሊንከእን መንግስት 1860-65 ዋና ጥያቄው እና ለትልቅ የእርስ በእርስ ውጊያ የዳረጋቸው ደቡባዊ የአሜሪካ ግዛት ባሪያ ፈንጋይ ስለነበር እና ዴሞክራሲን በጭልፍታ የሚቀበል በመሆኑ ያነን ለማስወገድ ሲነሳሱ የመገንጠል እና ኮንፌደሬሽን የማቋቋም አላማ በነ ጃፈርሰን ዲቪስ እና በመላ የደቡብ ግዛት ተቀነቀነ። ወደ መሀል የሚያመጣ አስታራቂ ሀሳብ ባለመኖሩ ከባዱ የእርስ በእርስ ጦርነት ተነስቶ ፌደራሊዝምን የሚደግፈው ያንኪወች የኋላ ኋላ አሸንፈው የአሜሪካ አንድነት እና ስርአት ሊተርፍ ችሏል። በሀገራችን ያለው ስርአት እና ህገመንግስት ይወገድ ስንል እና ሕዝብ የታገለውም ህገመንግስቱ ይህን ችግር ያመጣብን፣ ሐገራችንን ለአደጋ የዳረገብን ይወገድ ማለት ነው። በአንጻሩ ተቃዋሚነን የሚሉት ከህወሓት መራሹ አፋኝ ስርአት ጋር ምንም ተቃውሞ ያልነበራቸው፣ ልዩነታቸው የስልጣን ድርሻ ማነስ እና አለመመጣጠን ብቻ ከሀገር እንዲወጡ፣ ከፊሎች ለእስር እንዲዳረጉ የሆኑት አምስት የኦሮሞ ድርጅቶች በአደባባይ ወጥተው የነገሩን የሚታወስ ነው። ሕገመንግስቱን አትንኩብን በአላማ ለ27 አመት ከተንሰራፋው ስርአት ጋር እንመሳሰላለን ማለታቸው መሆኑ ግልጽ ሊሆን ይገባል። ባጭሩ ያለንበት ሁኔታ ሚና የለሽ እና ዝብርቅርቅ ነው። በእርግጥ አሁን መታሰር፣ መገረፍ፣ ጥፍር መነቀል የለም። ሰው ያሻውን መናገር ችሏል። መደራጀትም እንዲሁ ከልካይ ያለ አይመስልም። እንዴውም አንዳንዴ እድሜ ደጉ 1967 እስከ 1968 አጋማሽ – ያኔ “ጎሕ የተባለች የተቃዋሚ መጽሄት ስትታተም” እና አዲስ ዘመን ጋዜጣ እና ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አዲስ አምድ (አብዮታዊ መድረክ) የሚል አዘጋጅተው የነጻ ክርክር ከፍተው እንደነበር አስታውሳለሁ። በአሁን ላይ ያለው ግዜም ያንን የሚመስል ሆኖ ይታየኛል። ያች አንድ አመት ያልሞላች የነጻነት ዘመን ወዲያው በነጻ እርምጃ እና በቀዩ ሽብር ተተካች ሀገራችንም ማቅ ለበሰች። ለአለፉት አምስት እና ስድስት ወራት የምናየው ያልለየለት ግን የነጻነት አየር የሚነፍስበት ግዜ ነው። በአንጻሩ ያኔ 1967 ጥንታዊው ዘውዳዊው ስርአት በወታደራዊ የተተካበት እና ፍጹም ለውጥ የታየበት የከተማ እና የገጠር ትርፍ መሬት እና ቤት ወደመንግስት ካዝና የተዛወረበት ነበር። ዛሬ ግን ህገመንግስቱም፣ ገዥው ፓርቲም እንዳሉ ናቸው። ለውጡ ገዥው ፓርቲ ከተቃዋሚው በፊት ተለውጫለሁ ብሎ እያሳየን ያለው የተለሳለሰ ሁኔታ ነው። ይህ ሁኔታ ይቀጥላል አይቀጥልም ካለፈው እስከተማርን እና አሁን ተወዳዳሪ የተባሉት ጠንክረው እስከታገሉ። አዲስ ስትራቴጅ ነድፈው በአንድ እስከቆሙ። እና ሁኔታወችን አብረው መለወጥ እስከቻሉ ወይንም ያሉ ሁኔታወችን አስቀጥሎ ለለውጥ ግፊት ማድረግ አቅም እስከቋጠሩ ለውጥ ፍጹም ሊሆን ይችላል። ሀገራችንም ከአደጋ ተርፋ ለ 50 አመታት ብዙ መስዋ’እትነት የተከፈለለት የዴሞክራሲ ስርአት ሊጀመር ይችላል።

ዋናው የዚህ ትዝብት መነሻ ድጋፍም ሆነ ተቃውሟችን በአቋም እና በመርህ ቢሆን ለመደራደርም ሆነ ሲያስፈልግ ጠንክሮ ለመታገል ይመቻል። አለበለዚያ እንደሚያለቅስ ልጅ ትንሽ ሲያሳዩን ዝም፣ ሲነፍጉን ማልቀስ እንዳይሆንብን መጠንቀቅ ይኖርብናል። ቀድሞ መደገፍ ለመውቀስ ያስቸግራል በመሆኑም ይህ ሙሉ ድጋፍ እና ልክ የሌለው ተቃርኖ በልክ ቢሆን ተመልካችን፣ በተለይም ሕዝብን ግራ አያጋባም ባይ ነኝ። ስንደግፍ እስከምናምኑ ይሆን እና ሳይመቸን ሲቀር ደግሞ 360 ዲግሪ ተሽከርክረን አይንህ ላፈር የሚል ባህል ሊወገድ ይገባል። ሁሉም በልክ ይሁን!ግን በእርግጠኝነት ለመናገር አሁንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ የስርአት ለውጥ ነው። ሕገመንግስቱ ሕዝብን አይወክልም። ገዥ ፓርቲወችም እንዲሁ። በስርአቱ ውስጥ ያሉ ለውጥ ፈላጊወች ከስርአቱ ወንጀለኞች ሊለዩ፣ እራሳቸውን ለይተው ሊያሳዩን ግድ ይላል። እኛም አንዴ መውቀስ ለኢላ ግዜ መደመር ሳይሆን ቋሚ በአህርይ ኖሮን አላማ ለይተን ትግሉ ግቡን እንዲመታ እና ሀገራችን ከተደቀኑባት አደጋወች አሸንፋ እንድትወጣ የየበኩላችንን ማድረግ እንጅ ደግፉልኝ ወይንም የንቀፉልኝ ስራ አይበጀንም።