27 ዓመታቱ የወያኔ አገዛዝ ዘመን ለመሠረተ ልማትና ለተጓዳኝ የልማት ሥራዎች በሚል ክልሎች ለሚላቸው የሀገሪቱ ክፍሎች ባጀት ሲመድብ የአማራ ክልል ለሚለው የሀገራችን ክፍልም ይደርሰዋል የሚለውን ባጀት ሲመድብና የመሠረት ድንጋይ በየቦታው ሲጥል መቆየቱ ይታወቃል፡፡

እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ግን ለክልሉ ተመደበ በሚባለው ባጀት የአማራ ክልል በሚለው አንድም የልማት ሥራ ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቃ የለም፡፡ አብዛኞቹ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባልታወቀበት ሁኔታ ባጀቱ ታጥፏል!” እየተባለ በመሠረት ድንጋይ ደረጃ እንዲቀሩ ተደርጓል፡፡

በለጋሽ ሀገራት ወጪ የተሠሩ ሥራዎችንም በአገዛዙ ወጪ የተገነቡ በማስመሰል ባጀት እንዲጣጣ የተደረገበት አጋጣሚም አለ፡፡ ለምሳሌ ጎሐ ጽዮን ደጀን ያለው መንገድና መንገዱ ላይ ያለው የዓባይ ድልድይ፡፡ ይሄንን መንገድ የገነባው በራሱ ተነሣሽነት የጃፓን መንግሥት ነው፡፡ ሥራው ሲጠናቀቅና ለአገልግሎት ሲበቃ ግን አገዛዙ በራሱ ባጀት እንደሠራው አስመስሎ ነበር ያወራው፡፡

አስቂኙ ነገር ደግሞ የክልሉ ሕዝብ በመሠረተ ልማት እጦት እየተሰቃየ ባለበት ሁኔታ የተሰጣቹህን ባጀት መጠቀም ስላልቻላቹህ!” እየተባለ በተደጋጋሚ ባጀቱን ትግራይ ክልል የሚለው እንዲጠቀምበት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ይሄንን የሚያደርጉት የብአዴንን ሥልጣን ተቆጣጥረው የያዙት እንደነ በረከት ስምኦን ያሉ ትግሬ የብአዴን ባለሥልጣናት ናቸው፡፡ እነበረከት ይሄንን ግፍ ሲሠሩ የሚቃወም አንድም የብአዴን አመራር አልነበረም፡፡ ጭራሽ እንዲያውም ባለፈው ገዱን እንደሰማቹህት ነባር የብአዴን አመራሮች የአማራ ክልልን ሕዝብ ለማገልገል ሲደክሙ የኖሩ ምስጋና የሚገባቸው ወገኖች ናቸው!” እያሉ ነው የሚሳለቁብን፡፡

ወያኔ የአማራ ክልል የሚለውን የሀገራችንን ክፍል ባለው አማራን የማጥፋት፣ የማደህየት፣ የማቆርቆዝ አጋንንታዊ ዓላማ ምክንያት በዚህ መልኩ ሲያቆረቁዘው፣ ሲዘርፈው፣ ሲያጠፋው፣ ግፍ ሲሠራበት ቆየ፡፡ በዚህ ምክንያት ክልሉ እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ በልማት ወደኋላ ሊቀርና በተባበሩት መንግሥታት ግምገማ መሠረትም ጨለማው ክልል!” ለመባል በቅቷል፡፡

በዚህ የወያኔ ሸፍጥ ምክንያት ተጀምረው ያለተጠናቀቁና ታቅደውም ከነአካቴው የቀሩ በርካታ የልማት ሥራዎች በዚሁ የአማራ ክልል በሚለው አሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ሁለቱ ማለትም ቢዘገይ በአራት ዓመት ውስጥ መጠናቀቅ ሲኖርበት በዘጠኝ ዓመቱ በስንት መከራና በስንት ፈተና ከቀናት በፊት ያውም ሥራው ሳይጠናቀቅና አገለግሎት ለመስጠት ዝግጁ ሳይሆን ተመረቀ የተባለው የርብ ግድብ እና ዛሬ ከሃያ ዓመት በኋላ ምንም ዓይነት የሕክምና መሣሪያ ሳይገባለት ተመረቀ የተባለው የባሕር ዳሩ ጥበበ ግዮን ሆስፒታል ነው፡፡

በሌሎች የወያኔ ክልሎች አዳዲስ የልማት ሥራዎች ይመረቃሉ እዚህ ግን በሃያ ምናምን ዓመቱና በዘጠኝ ዓመቱ መረቅነው የሚሉት የልማት ሥራዎች ግን በአግባቡ የተጠናቀቀና አገልግሎት መስጠት የሚችል አይደለም፡፡ አያሳዝንም???

በሆስፒታሉ የምረቃ ሥነሥርዓት ወቅት የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ዲን ሆስፒታሉ የሕክምና መሣሪያዎችና ተጓዳኝ ግብአቶች ተሟልተውለት በሙሉ አቅሙ ወደአገልግሎት እንዲገባ የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት እንዲሰጠው!” በማለት ለጠየቁት ጥያቄም ነውረኛው ዐቢይ የጎንደር ሕዝብ በዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የጎንደር ሆስፒታልን ሲገነባ በራሱ አቅም መዋጮ ሰብስቦ ገነባ እንጅ በባጀት አልተገነባም!” በማለት በሕዝብ መዋጮ አጠናቁት!” የሚል አሳፋሪ ኢፍትሐዊና አድሏዊ ምላሽ እዚያው ላይ ሳያፍር ሕዝብ ፊት ቆሞ መልሷል፡፡

እንግዲህ ይታያቹህ በድኑ ብአዴን ሲያቆስለን ሲያሳርረን የኖረው ሳይበቃው በአግባቡ ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ያልሆኑ ግድብና ለአገልግሎት ብቁና ዝግጁ ለመሆን ገና ከፍተኛ ወጭ የሚጠይቁ ግድብና ሆስፒታል ለባዶ የፕሮፓጋንዳ (የልፈፋ) ፍጆታ ሲል መረኩ እያለ በቁስላችን ላይ እንጨት እየሰደደ እያፌዘብን ይገኛል፡፡

ይሄንን የበድኑን የብአዴንንና የደላላውን የዐቢይን ሕዝባችንን አለቅጥ የናቀ ነውረኛ ተግባር ሕዝባችን በዝምታ መመልከት የለበትምና አጥብቆ ማውገዝና ተቃውሞውን ማሰማት ይኖሩበታል፡፡

ድል ለአማራ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com