ለአቶ ባይሳ ዋቅወያ፣
እንደምን ሰነበቱ?
ከአዲስ አበቤዎች ጋር በተያያዘ የጻፉትን ጦማር በተመለከተ አጭር አስተያየት ልሰጥዎት እሻለሁ፡፡
ቡራዩ ላይ የተፈጸመው ኢሰብአዊ ዘረፋ፣ የሰው ሕይወት ጉዳትና መፈናቀል ብዙዎችን ያሳሰበ መሆኑን በመጥቀስ “ፈተና ላይ ለወደቀው ኢትዮጵያዊነት አዲስ አበቤዎች የመታደግ ሚና እንዳላቸውና ሌሎች ደግሞ ወራሪዎችና ባዕዶች እንደሆኑ ያመለክታል…” ብለው ገልጸዋል፡፡ አክለውም “የቡራዩ ጉዳይ በብዙ ሚሊዮን የሚደርስ መፈናቀል ከደረሰበት የኦሮሞ ተፈናቃዮች እኩል ወይም ይበልጥ…እንዴት ትኩረት አገኘ” ብለው ተደንብቀዋል፡፡ አዲስ አበባ ርዕሰ ከተማ መሆኑን ዘንግተውታል ማለት ነው፤ እንዴት ጠቅላይ ሚኒስትሩና አስተዳደራቸው ካሉበት ጥቂት ኪሎሜትር ርቀት ውስጥ ይህ ጉድ ሊፈጸም ቻለ አለማለትዎ ደግሞ በአንጻሩ እንደሚያስገርም አልተገነዘቡም ማለት ነው፡፡ አልሰሙ እንደሆን እንጂ በብዙ የኢትዮጵያ ክፍሎችና በውጭ አገር ጭምር ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግና የገንዘብ አስተዏፅ ኦ ጭምር በማድረግ በደቡብ ኢትዮጵያ ከተጎዱት የኦሮሞ ወገኖቻችን ጎን መቆማቸውን በተግባር አሳይተዏል፤ በዚህ መሠረት ነው የሁሉም ር ዕሰ ከተማ ሲደፈር ብዙዎች የተሰማቸው፤ እርስዎንም ሊሰማዎት በተገባ ነበር።
አክለውም ስለአዲስ አበቤዎች መደራጀት የተነሣው ጥያቄ መብት ሳይሆን ስውር የፖሊቲካ አጀንዳ ነው ብለው ማቅረብዎ በጣም ትዝብት ውስጥ የሚጥልዎት ነው፡፡ መደራጀት በሕገመንግሥቱ ጭምር የተፈቀደ ሲሆን፤ ይልቅስ ከፍተኛ ንቃተኅሊና ያለውና በቴክኖሎጂ በታጀበ እንዲሁም በብዙ መልኩ የሥነጥበብ፣ የአካዳሚክስ፣ የብዙዎች ፖሊቲካም ሆነ ማኅበራዊ ተቋሞች ስብስብ በሆነበት ትልቅ ከተማ ውስጥ የአዲስ አበባ ወጣቶች እንዴት እስከዛሬ አልተደራጁም ብለው መደነቅ ነበረብዎት፡፡ ለመሆኑ ቄሮዎች እንዲደራጁ በሕግ ተፈቅዶላቸው ነበር ወይ? ታዲያ የአዲስ አበባ ወጣት መደራጀት እንዴት ሕገወጥ ሆኖ ታየዎት? ዲሞክራሲ ባለበት አገር ወጣቶች በሕዝብ ምክር ቤት ውስጥ ጭምር ቦታ እንዳላቸው ያውቃሉ? በመጀመሪያ የአዲስ አበባ ወጣት የሚደራጀው በጎሣ ስላልሆነ ለሁሉም ወጣት ልዕልና እንደሚቆም ቢገነዘቡ መልካም ነው፡፡ የአዲስ አበባ ወጣት መደራጀት ለፖሊቲካ ብቻ መስሎዎት የወገኖቼን ሥልጣን ይጋፋል ብለው አይስጉ፤ ወጣቱ እኮ የራሱን ማኅበራዊ መብት ራሱ በመታገል እንጂ የሚያስከብረው ማንም እንደሱ ሊቆርቆርለት አይችልም፤ ዛሬ በተለያዩ እፅዋትና በአልኮል እንዲነዝዝ የሚያደርገውን ሥርዓት እኮ ራሱ ወጣቱ ነው ተደራጅቶ ለማስወገድ የሚታገለው፡፡ የሙያ ትምህርት ተምሮ፤ ሠርቶ አገርን የማልማት ተስፋ የሚጣልበት ወጣት ካልተደራጀ እንዴት የወደፊቱን እጣ ፋንታ ይወስናል ብለው ይገምታሉ?
ከኔ እኩል ለኢትዮጵያዊነት የሚቆረቆር የለም በማለት ትምክህት የሚያሳይ ወገን አለ በማለት የገለጹት በቀጥታ በአማራ ላይ ያተኮረና የቆየ ወያኔዎች የዋሆችን ጠባብ ለማድረግ ያስተማበሩት ዛሬ ግን የእኩልነትንና የፍትሕን መበልጸግ በሚናፍቀው ሰፊ ሕዝብና ዲሞክራቲክ አመለካከት ባለው የተማረ ወገን ሁሉ ዘንድ ያፈጀበት የፖሊቲካ ቋንቋ ነው፡፡ ዛሬ ወደዱም ጠሉም አማራና ኦሮሞ ግምባር ከመፍጠር በስተቀር የድሮ ታሪክ ማውራት ጠቃሚ እንዳልሆነ የተረዱበት ዘመን ነው፡፡ አንዱ ወገን የኔ ብሔር ለኢትዮጵያ ሕልውና የታገለና ለአንድነት የጣረ ነው ሲል ሌላው ደግሞ ያንተ ብሔር ለዘመናት ጨቁኖኝ ስለነበር ከሐጢአቱ እስካልፀዳ ድረስ ካንተ ጋር በቅንነት ስለአገራችን እጣ ፋንታ ማውራት አልችልም ይለዋል በማለት የገለጹት ይልቁንስ ለሰላም እየተፈላለገ ያለውን ወገን የሚያራርቅ እርሾ እንዳይደርቅ እያቋቱ መሆንዎን ይረዱት ይሆን? ከዚህ በፊት አንድ ምሁር ናቸው ተብለው የሚገመቱ ሰው በጻፉት ጦማር ላይ ኦሮሞ እንዲህ… እንዲህ… ተብሎ ተሰድቧል ብለው በገለጹት ላይ በሰጠሁት ምላሽ፣ ኣላዋቁ ሰው ሰድቦ ለተሳዳቢ ይሰጣል፤ ላላወቀውም ስድብ ያስተምራል፤ በሚል ምላሽ ሰጥቼ ነበር፡፡ የሚገርመኝ እና ከርስዎ አገላለጽ ጋር ተመሣሣይ ሆኖ አገኘሁት። እንደዚሁ “ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ፤ መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ” ተብሎ ጀግኖቹ ሲወደሱ የገበየሁ አያት አልተገለጸም በማለት ቅሬታውን የገለጸ ፀሐፊ ነው፡፡ ሁለቱም ጀግኖች ታዋቂ ስለሆኑ በየመጀመሪያው ስማቸው አየተወደሱ እና ሁላችንም የኢትዮጵያ ጀግኖች በመሆናቸው እየኮራንባቸው እያለን የዘር ሐረግ ከመፈልገ በላይ ምን ጠባብነት አለ?
በዘር ሐረግ ፖሊቲካውንም፣ ማህበራዊ ጉዳዮችንም ምጣኔ ሀብቱንም ከመተንተን ይልቅ እንዲህ ያሉ የሚያለያዩንን ነገሮች በመተው አንድ በሚያደርጉን በጋራ በሚያኮሩንና ወደፊትም በአንድነት ልናገኛቸው የምንችላቸው ግቦች ላይ መድረስ እንድንችል እንደሠለጠነ የ፳፩ኛው ክፍለዘመን ሰው ለልጆችዎና ለወገኖችዎ ሁሉ ቢያስተምሩ ይሻል ይመስለኛል። የጥላቻ ባህል እንዲቀርና ፍቅር እንዲጎለብት በአኖሌ ላይ የተሠራው የጥላቻ ሐውልት ፈርሶ በምትኩ ለአገራቻን ነፃነትና ለሰው ልጅ ክብር ታግለው ታላላቅ ድሎችን ያስመዘገቡ እንደ ኮሎኔል አብዲሳ አጋ ያሉ ታላላቅ የኦሮሞ ጀግኖች ሐውልት ቢሠራላቸው ሁላችንንም የሚያኮራን ይሆን ነበር።
በመጨረሻ በኔ ዕድሜ ሰላም ዲሞክራሲ፣ ፍትሕና እኩልነት የሰፈነበት አገር አላይም ማለትዎ አንድም ተስፋ አለማስተማር ሲሆን፤ ሁለተኛም ከሃያ ሰባት ዓመታት በላይ በየአደባባዩ፣ በትምህርት ቤትና በየቤቱ ጭምር ጥላቻ ሲማር ያደገን ግማሹን የአገራችን ሕዝብ የማያንሰውን ትውልድ በአንድ ሰሞን መለወጥ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ የተረዱት አይመስልም፡፡ የሚያውቋቸው እነለታ ሌንጮ ቀደም ሲል አስተሳሰባቸውን ከተጨባጩ የአገራችን ሁኔታ ጋር የማስተካከል ተሰጥኦ ሲካኑ እንደነ ዳውድ ኢብሳ ያሉት አዋቂ ሰዎች እንኳ ይኸው እውነታን መቀበል አቅቷቸው ዲፕሎማሲው ወደ ምሬት ቢለወጥ ነገሩ ሁሉ የእሳት እራት ሊያደርጋቸው እንደሚችል ባለመገንዘብ ለመንፈራገጥ ሲዳዱ ታይተዋል፡፡ አሜሪካኖች ለመገነጣጠል የእርስበርስ ጦርነት አድርገው ከጦርነት ጉዳቱ ትምህርት በመውሰድ ዛሬ ያንን እንደትዝታ እንጂ በቀል የሚባል ነገር ጭርሶ ስለማያስቡ ከዓለም ኣንደኛ አገር አደረጋቸው እንጂ አልጎዳቸውም፡፡ እንግሊዞች, “The sun never sets in the British isles” የሚሉት በጦር ተሽንፎ ከመክሰርና ከመዋረድ ይልቅ በድርድር መልቀቅን የሚመርጡት የወዲፊቱን ጥቅም በመረዳት ነው፡፡ ብልኅነት ሐሳብን መለወጥ ነው፤ ብልኅነት አርቆ ማስተዋል ነው፡፡ ታዲያ ብልኅነታቸውን እያደነቅን እኛ ግን እስከመቼ ድረስ አየተሳሳትን እንኖራለን? ጥሩ ነገር እንዲያዩ የጥሩ አርዓያ መሆን ነው እንጂ ጥላቻን ማራገብ አይደለም የሚጠቅመው፡፡ መቻቻል ለሰላም መሠረት መሆኑን በመዘንጋት፣ ለጋራ በጎ የአገር ዓላማ በመደጋገፍ ፋንታ በቂምበቀል ያደፈ አእምሯችንን ካላፀዳን እንዴትስ ዲሞክራሲያዊ ባህል መገንባት እንችላለን?

