የተከበራችሁ ወገኖቺ ሆይ
በቅድሚያ የከበረ ሰላምታዮን አቀርባለሁ።
ክፍል አንድ
በመጀመሪያ ይህ ድብዳቢ ስፋ ያለ ውይይት ተደርጎበት ወደፊት ነፃ ለምትሆነው አገራችን በምን ዓይነት አስተዳደርና ሕገ መንግሥት እንደምንተዳደር ተወያይተንና ሃሳብና መላ ምቶች ተንሽራሽረው በስምምነት የሕግ በላይንትን ተቀብለን፤ የፍርድ ቢቱንና የምርጫ ቦርዱን ነፃነት አስተካክለን የሕዝብ መንግሥት በሕዝብ ለሕዝብ አዋቅረን የሚያስፈልገውን ለውጥ እንደአስፈላጊነቱ በቅደም ተከተል እንድንሰራ ለመወያየት ታስቦ የቀረብ የውውይት ሰነድ ነው።
ይህም ሰነድ እጅግ በጣም ሳይሰፋ ደግሞም ሳይጥብ ወጣ ውረድ ሳይኖርበት ያስፈልጋሉ በምንለው አጀንዳ ላይ መሆን ይኖርበታል። ጊዛዌ አጀንዳ አሁን ለጊዜው እዚህ ላይ ይቀርባል። ሆኖም በውይይት አጀንዳው ሊሻሻል ይችላል።
በተጨማሪ ለውይይት እንዲረዳ በማለት የሊሎች አገሮች የፖለቲካ ሂደትና የፖለቲካ ሥራዓታቸዉን በአጭሩ ይጠቀሳል።
በአለፈው 27 ዓመታት ውስጥ ተሰሩ የተባሉትን ወንጀሎች ከሕግ ውጭ የተሰሩትን ሕገ ወጥ ስራዎች እንደዘር ማጥፋት፤ የአንድ አናሳ ጎሳን የበላይነትን ጌዜው በአለፈበት ሥራዓትና በአፈታሪክ ወሬ ሕዝብን አስገድዶ እንዲቀበል ማድረግ፤ ሕዝብን ከሚኖርበት ማፈናቀል፤ የአገር ንብረትን ለዉጭ ሃይል መሸጥ መለወጥ፤ የአገርን ገንዘብ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ወደ ውጭ ማውጣት፤ የብሕራዊ ባንኩን ገንዘብ ሕገ ወጥ በሆነ በብድር በመወሰድና “የተበላሸ ብድር” እያሉ ወደ ግል ባንክ ማስገባትና፤ የግል ንብረቶችን እየነጠቀ ሕገ ወጥ በሆነ መንግድ መወሰድ፤ የተለያዩ የኢኮነሚና የመንግሥት ድርጆችን በአድላዌነት ለአንድ ጎሳ ብቻ እንዲሆን ማድረግ፤ ሙስና ቅጥ ያጣ ዝርፊያ ሌብነቱን በይፋ ለማሳወቅ፤ በስምምነት የተመረጠዉን ጠቅላይ ሚንስትርና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያቀረበዉን የለውጥ ታሪካዊ ሂደት ግቡ እንዳይደርስ ጎሳ ጽንፈኞችና ተላላኪ ቅጥረኞችን በገንዘብ እየገዛ በአገር ውስጥ ሽብርን በመፍጠር የኢትዮጳያ ሕዝብ በደሙ ያመጣዉን ለውጥ ለማስቆምና ወደ ነበረበት ሥልጣን ለመመልስ የሚያደርገዉን ሕገ ወጥ ስራ ለዓለም ሕዝብ ለማሳወቅና አሸባሪነቱን ለማስቆም፤ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በውጭ አገሮች የአስቀመጠውን ገንዘብ በሕግ እንዲመልስ ማድረግ፤ በአሚሪካ የሕዝብ ምክር ቤት የተጀመረዉን የኢኮነሚና የፖለቲካ ዕቀባ ሕጋዊነት አግኝቶ በስራ ላይ እንዲውል ማድረግ፤ በኢትዮጵያ አካባቢ የሚገኝቱን አገሮች ሰላምና አንድነት ለማሳጣት የሽብር ስራዎችን እንዲያቆም ለማድረግ፤ በአሚሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያን በሰላም ስም ወደ አገር በመግባት የሚያካሕዱትን ሽብር በአሚሪክ ሕግ መሰረት እንዲያቆሙ ለማደረግ፤ እነኝህን የሚመስሉ ሕገ ወጥ ስራዎች ሁሉ ዓለም አቀፍ በሆነው ሕግ መሰረት የወዲፌታን ኢትዮጵያን እንዴት እንደምንመሰርታት ተወያየትን በአንድነትና በስምምነት የምናጸድቀው ሰነድ ይሆናል።
ይህ ደብዳቤ በዙ ክፍሎችን ይዝዋል፤
በከፍል አንድ ላይ ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ አሚሬካ በመጡ ግዜ የተጻፈላቸዉን ደብዳቤ በከፌል በዚህ ሰነድ ውስጥ እንዴካተት በማለት በአባሬነት ከተጨማሪ አስተያየት ጋር ይቀርባል።
ክፍል ሁለት በኢትዮጵያ ውስጥ በአለፉት ሶወስት ትውልደ ዘመን የተደረገዉን የመንግሥት ለውጥና “ታሪካዌ ሂደቱን” ትውልዱ ያደረጋቸዉን ታሪካዌ ስህተቾችን በዝርዝር ይተነትናል።
በክፍል ሶስት ላይ ዓለም አቀፍ በሆነው “ዲሞክራሲና” ስለ ሕገ መንግሥት ታሪካዌ ሂደት ሰፋ ያለ ውይይት ይደረጋል።
በክፍል አራት ላይ ስለሰነዱ የሚሰጡትን አስተያየት ከግንዛቤ በማስገባት በሚያስማሙ አሳቦች ላይ ተመርኩዘን እንዲት አብረን መስራት እንደምንችል የስምምነት ውል እንደ መስሪያ ሰነድ ሆኖ ይቀርባል።
ግልጽ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ፊደራል መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስተር
ለተከበሩ የኢትዮጵያ ፊደራል መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አቢይ አህመድ
ክቡር ሆይ፡
ይህንን ደብዳቤ ስጽፍ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አቢይ አህመድ ያለኝን ከፍተኛ አክብሮትና ድጋፍ እየሰጠሁ ነው። ባለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያዊነታችን ተገፎ፣ ማንነታችንን ጠፍቶ፣ ክብራችን ተወስዶ ለሰው ልጆች የተሰጠዉ ሰብአዊ መብታችን ተወግዶ፣ በማንነታችን ብቻ በመታሰር፣ በመገደል፣ በመሰደድ፣ ያሳለፍነው ስቃይ ተነግሮም ተጽፎም አያልቅም። ምናልባት ታሪክ ጸሐፊዎች ዘግበው ይህንን በሰው ታሪክ ዘመን ውስጥ ተሰርቶ የማያልቅ ግፍ ለልጅ ልጆቻችን ያስተላሉፉናል በማለት ተስፋ አደርጋለሁ። ይህም ተስፋ ለበቀል ሳይሆን እንዲህ ዓይነቱ ጭካኔ እንዳይደገም ትምህርት እንዲሆን ተብሎ ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ ፈላስፋ ዘርዓያቆብ እንዳለው “ንፉጎች ምንም እንኳ የሃብት ባለጸጋዎች ቢሆኑ ጠገብኩን ስለማያውቁ” የሰዉን ልጅ ከመብላት አይመለሱም ይላል። እናትን ልጇዋን ገድለው እሬሳው ላይ አንድትቀመጥ አድርገዋል፤ ጉድጓድ ቆፍረው በቁማቸው ብዙ ሰዎችን ቀብረዋል፤ የአማራ ሴቶችን እንዳይወልዱ መካን የሚያደርጋቸውን መድኃኒት እንዲወስዱ ተደርገዋል፤ ቦሌ አካባቢ የምትኖር እመጫት ቤቷ ውስጥ ሆና ልጇን ስታጠባ ቤቷን በቡልዶዘር ደምስስው ከነልጇ ገድለው ቦታዉን ወስደው ቤታቸውን ሰርተዋል፤ የቀድሞው የትግራይ ነፃ አውጭ አባል የነበሩት አቶ ገብረመድሕን አርያ በማስረጃ እንዳረጋገጡት አራት ሚሊዮን አማራ በጅምላ ተገድሏል፣ የወያኔ መንግሥትም 3.5 ሚሊዮን አማራ የደረሰበት አይታወቅም በማለት አምኗል፤ በመረጃ የተረጋገጠ በበዙ ሺህ የሚቆጠር ኦሮሞ በጅምላ ገድለዋል፤ በብዙ ሺህ የሚቆጠር የፖላቲካ እስረኞች እስር ቤት ይገኛሉ። ይህንን ሁሉ ሲያደርጉ ድርጊቱን ያዩት እንደጀግንነት ነበር። ግን የእነሱ ጀግንነት በአገር ያሉ ሆዳሞችና ደላላዎች ከዚያም በውጭ ኃይል መረዳታቸውን ዘንግተው ለ27 ዓመታት ሲደነፉ እንደነበር ለሁላችንም ግልጽ ነው። ግን አምስት ሚሊዮን የማይሞሉ ዘጠና አምስት ሚሊዮን የሚሆነውን ሕዝብ እንደከብት እንነዳዋለን ሲሉ ያሳዩት ትዕቢተኝነትና ትምክህተኛነትን እንጂ ጀግንነትን አይደለም። ጀግንነት ማለት እንደ ኦሮሞው ፈረስኛ፣ እንደ አማራው አርበኛና እንደ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተባብሮ ጣሊያንን ድል አድርጎ ትግራይን ነጻ አውጥቶ ለትግራይ ሕዝብ አስረክቦ ወደ አገሩ የተመለሰው ነው ጀግና ማለት። ባንዳና የቀን ጅብ ከሆዱ በስተቀር አገር የለውም፤ ለባንዳና ለቀን ጅብ አገር ሕዝብ ለሚለው ስሜት የለዉም። አንድ የአሜሪካ ፈላስፋ እንደጻፈው ከአለፈው ታሪክ የማይማር ሕብረተሰብ እጣ ፋንታው ሞት ነው ይላል። ለ27 ዓመታት መልሰው መላልስው የኢትዮጵያን ሕዝብ አጭበርብረዋል። አሁን ግን ሕዝብ ነቅቷል። እርስዎ የዚህ ሕዝብ ንቃት ትግልና ደም ውጤት ኖት። እርስዎ ትከሻ ላይ ያረፈው ሸክም ከባድ ነው። ከሕዝቡ ጋር ሆነው “ሁኔታውን” እየተቆጣጠሩ በቅደም ተከተል ከባለሞያዎች ጋር በተረጋጋ መንፈስ በመወያየት ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ክቡርነትዎ በሰጡት መመሪያ መሰረት እንደሚከናወን ተስፋዬ ነው። ይህንን አጭር መግቢያ ከአደረኩ በኋላ የሚከተሉትን የለውጥ ታሪክዊ ሂደት ለክቡርነትዎ ሳቀርብ በታላቅ አክብሮት ነው።
የመተዳደሪያ ደንብ ወይም “ሕገ መንግሥት” እና የማሻሻያ ኮሚሽነር
1. ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት መምሪያ መሰረት ለመደምርም ሆነ ለመቀነስ ለውጥ ያስፈልጋል። በቅደም ተከተል ደረጃ ስንመለከተው “የሕግ የበላይነት” የዲሞክራሲ መስፈረት ነው እንላለን። ስለዚህ የለውጡ መጀመሪያ የአገራችን መተዳደሪያ ደንብ ነው፤ ይህም ማለት “ሕገ መንግሥቱ” ማለት ነው። ይህ የዲሞክራሲ መሰረቱ ወይም ምሶሶ ነው ማለት እንችላለን። የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግር የሚፈታው አንድ ጎሳ ሌላዉን አሽንፎ ሳይሆን በዲሞክራሲ ነው፤ የግልሰቡ ሰብአዊ መብት ከተጠበቀ የሁላችንም ተጠበቀ ማለት ነው። ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሁኔታው” በፈቀደ ጊዜ የሕገ መንግሥቱን “ማሻሻያ ደንብ” አርቃቂ ኮሚሽነር መስየም አስፈላጊ ነው እላለሁ። ይህ በቅደም ተከተል ክምንም በፊት መደረግ አለብት።
2. ሕገ መንግሥቱ የኢትዮጵያን ልዑላዊነት ማንጸባረቅ አለበት፤
3. ሕገመንግሥቱ በጎሳ የተከፋፈለዉን ክልል አሻሽሎ የዜጎችን እፈለጉበት ክፈለ አገር የመኖር መብት ማስከበር አለበት፤
4. ሕገ መንግሥቱ ከተሻሻለ ነጻ የሆነ “ፍርድ ቤት” ይኖረናል ማለት ነው፤
5. ሕገ መንግሥቱ ከትሻሻለ ነጻ የሆነ “የምርጫ ቦርድ” ይኖረናል ማለት ነው፤
6. ሕገ መንግሥቱ ከተሻሻለ የዜጋ “ሰብአዊ መብት” ተከበረ ማለት ነው፤
7. ሕገ መንግሥቱ ከተሻሻለ “የሕግ በላይነት” ተከበረ ማለት ነው። ማንም ሰው ቢሆን ከሕግ በላይ ሊሆን አይችልም
8. ሕገ መንግሥቱ ከተሻሻለ “የአገልግሎት ዘመን” ተገደበ ማለት ነው
9. ሕገ መንግሥቱ ከተሻሻለ መንግሥት በማንኛዉም ኃይማኖት ውስጥ ጣልቃ አይገባም ማለት ነው፤
10. ሕገ መንግሥቱ ከተሻሻለ ሁሉም ሃይማኖት ከፖለቲካ ፍጹም ነጻ ይሆናል ማለት ነው፤
የእርቅ የፍቅር የሰላምና የእኩልነት ስምምነት
የአገራችን ችግር ከደቡብ አፍሪቃ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ስለዚህ አፍሪካውያንና አውሮፖውያኖችን እንዲት እንደተስማሙ ክግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ የስምምነት ውል መዋዋል አስፈላጊ ነው። ደቡብ አፍሪካ የቤሔራዌ ስምምነት ቀን ብለው በየዓመቱ ይከበራል፤ ይህም ቀን የተመረጠው ሁሉም ወገን ተስማምትው ነው፤ እዚህም ስምምነት ላይ የተደረሰው ያለፈዉን ችግር በሚገባ ተወያይተውና የተሰራዉን በደልና ጥፋት አምነው ነው፤ይህ ከአልሆነ የአለፉት ጥፋቶች ሊታረሙ አይችልም፤ጥፋት የሚታረመው ጥፋት መሆኑን አጥፊው ጥፋቱን ሲያምን ነው፤ ይህ እንደሚሳሌ ተወስዶ እትዮጵያም ውስጥ ይህንን ጉዳይ የሚያጠና ኮሚቴ ተሰይሞ በሚከተሉት ነገሮች መወያየት ይኖርበታል [መላ ኢትዮጵያዉያን የሚያስማማ ቀን “የአድዋ ድል ቀን” ይመስልኛል}፤
1. የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጭ ግንባር አማራ የትግራይ ሕዝብ ጠላትና የቅኝ ገዥው ስለሆነ መጥፋት አለበት የሚለዉን “አዋጅ” [Manifesto] ትክክል ያለመሆኑን ከይቅርታ ጋር ለትግራይ ሕዝብ ሲያሳውቅ፤
2. እትዮጵያ የምትባል አገር ከዚህ በፈት አልኒበረችም፤ የተፈጠረጭው የዛሬ መቶ ዓመት በምኒልክ ዘመነ መንግሥት ነው የሚለዉን ፕሮፓጋንዳ ስህተት መሆኑን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሲያሳውቅ፤
3. በግፍ በጎሳቸው ማንነት ብቻ ለተገደሉትና ለዚህ ሁሉ እልቂት በሃላፊነት ተጠያቂዎችን ለፍርድ ሲያቀርብ፤
4. በዝርፍያ የተወሰዱትን ንብረቶች መልሶ ለባለቤቱ ሲያስረክብ፤
5. በስርቅት የተወሰዱትንና በውጭ አገር ባንኮች የተቀመጡትን የአገር ገንዘብ ሲመልስ፤
6. በተዘረፈ የአገር ገንዘብ ለትግራይ ልማት ተብሎ የተከማችውን ሃብት ለመንግሥት ሲመለስ፤
ይህን ደብዳቤ በተጻፈበት ግዜ የነበረው ጥያቄ ጠቅላይ ሚንስትሩ ያበሰሩን ለውጥ “እንዴት ሊሆን ይችላል?” በማለት ነበር። ጥያቄው አንድ መንግሥት ከላይ እታች ድረስ በአንድ ብሔር የበላይነት ሙሉ በሙሉ ተይዞ በምን አይነት “ሁኔታ” ሊለወጥ ይችላል ነው። እንግዲህ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንክሮ መመልክት ያለበት ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር ያደረገዉን ስምምነት ነው። ለ27 ዓመታት ያደረገው ትግል መራራና አስከፊ ከመሆኑም በላይ ቅጥሩ ይህ ነው መባል ከማይችል በላይ ሕዝብ አልቆ፤ አገሩ ለውጭ ሀብታሞች ተሸንሽኖ ተሽጦ፤ ንበረቱ ተዘርፎ፤
የአገሩ ጠቅላላ ገንዘብ ወደ ውጭ አገር ባንክ በገለሰብ ስም ተዛውሮ፤ የመከላኪያው ጦር፤ የመንግሥትና የግል የሆኑ የንግድ አቃውሞች በነሱ ቁጥጥር ሆኖ እንዴት ሊለወጥ ይችላል ነው ጥያቄው? በዚህ ክፍል ሁለት አበይት በሆኑ ነገሮች ላይ እንወያያለን። በመጀመሪያ በምን አይነት “ሁኔታ” ነው የትግራይ ነፃ አውጭ ነኝ የሚል የኢትዮጵያን ሕዝብ ሊቆጥጠር የቻለው? ነው። በብሔር ነፃነት ስም የአገር መከፋፈል “ሁኔታ” ስለተፈጠረ ወያኔ ተለጣፊ ድርጅቶችን በሽግግር መንግሥት ስም ሰይሞ የይስሙላ የሕዝብ ምክር ቤትን በተለጥፊ ድርጅቶቹ አስመርጦ የመሰረተው በሱ በላይነትና ጠቅላይ ሚንስተርነት ያዋቀረው መንግሥት ነው። ይህ መንግሥት የኢትዮጵያን ሕዝብ አይወክልም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለ 27 ዓመታት ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ የተዋጋው ሕገ ወጥ መንግሥት ነው። እዚህ ላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ወያኔ ያዋቀረው መንግሥት በደቡብ አፍሪቃ ሞዴል መሆኑን ነው። ደቡብ አፍሪቃ የአፍሪቃን የተለያዩ ጎሳዎችን በመከፋፈልና የክልል መንግሥት በመመስረት እርስ በርሳቸው እንዳይነጋገሩና አንድነት እንዳይፈጠሩ በማድረግ የአፓራታያድ ስርዓት በመፍጠር ነው። ይህንንም እዉን ስለአደረገ ለብዙ ዘመናት የአፍሪቃን ሕዝብ በመጨቆን ሊገዛ ችልዋል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለው “ሁኔታ” ይህ ስለሆነ በቀላሉ ሊስተካከል አይችልም። ስለዚህ ይህንን “ሁኔታ” ከግንዛቤ አስገብቶ ሕዝብ በተረጋጋ መንፈስ ተወያይቶ የአገር ለዑላዊነትን የሚያመጣ “ሁኔታን” ፈጥሮ በውይይትና በዲሞክራሴ ያለውን ችግር መፍታት ታሪካዌ ግዲታ ነው። ኢትዮጵያ በክልል ተከፋፍላ በባህል በቃንቃ የማይተዋወቅ ሕዝብ ስለተደረገ ማንነቱን የሚገልጽበትን “ኢትዮጵያ” የምትባልዋን አገር ምን እንደሆነ ማስተዋወቅ አስፈላጊ ነው። “ኢትዮጵያ” የሁሉም መታወቂያ መጠሪያ ስሙ ነው። አድዋ ላይ የተዋደቀው ሕዝብ ከኢትዮጳ አልፎ ለአፍረኢቃ ክብር ሆኖ ሕያውነቱን አግኝታል። ይህ ለባንዳዎቹና ለተላላኬ አሽከሮቹ ራስ ምታት ነው።
ሁለተኛው አብየት ስለልውጥ የተደረገውን ስምምነት ነው፤ ይህ “ሁኔታ” የተፈጠረው በኢትዮጵያ ሕዝብ ደም ነው፤ የወያኔ መንግሥት ተገዶ አዲስ ጠቅላይ ሚንስተር መርጦ “በሁለት” ዓመት ግዜ ውስጥ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስረክባለህ በማለት የተዋዋለዉን ውል መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለለውጡ ሂደት ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር መደራደር
አለበት፤ የታሰበው ለውጥ የሚከናወነው “ሕዝብ በሕዘብ ለሕዝብ” መርጦ መንግሥትን ሲረከብ ነው። ከዚህ አጅንዳ ውጭ ሊላ ጉዳይ መኖር የለበትም። ለውጥ ማለት ያለፈዉን መጠገን ወይም ማሻሻል አይደለም። ለውጥ ማለት ሕዝብየመረጠው መንግሥት ሕገ መንግሥቱን ጽፎና ተወያያቶ ሲያጸድቅ፤ ነፃ የሆነ ፍርድ ቤትን አዋቅሮ በስራ ላይ ሲውል፤ ነፃ የሆነ የአስመራጭ ቦርድን አስተካክሎ ምርጫው ያለምንም ችግር ሲከናወን ነው። ይህ ነው ለውጥ ማለት።
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የፖለቲካ ተኝታኞችና ጋዜጠኞች ከሕዝብ ጋር የመወያየት ግዲታ አለባቸው። አሁን ግን በለውጡ ሂደት ላይ ያለው በእርቅና በሰላም መንግሥት ለሕዝብ ይተላለፋል የተባልውን ውል ሙሉ ሙሉ የጣሰ ይመስላላ፤ የጠቅላይ ሚንስትሩ ዋና ሃላፊነት ፀጥታን ማስከበርና የሚደረገው ለውጥ በሰላም እንዲሆን ከማድረግ ሌላ ስልጣን አልተሰጣቸውም፤ ሕዝብ በደስታ እልል ብሎ የተቀበላቸው አሽባሪው መንግሥት ተወግዶ ራሱ ለመረጠው መንግሥት እንዲያስረክቡ ነው። ነገር ግን የኢትዮጵያን ሕዝብ ለ27 ዓመታት ሲያሽብር የነበረው ሃይል እንደገና ወደስልጣን ለመመለስ በማሰብ “አሸጋግሪ መንግሥትን አስረክባለሁ” ያሉትን ጠቅላይ ሚንስትር በግድም ሆነ በውድ አስገድደው የሚያደርጉት ጥረት የሚያመጣው ጥፋት ታላቅ መሆኑን የትግራይ ሕዝብ አስቦ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ታሪካዌ ግዲታ ነው። ይህ ከአልሆነ መለስ ዚና ሲመኝው የነበረውን “የሮንዳን ዓይነት እልቂት” በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ማምጣት እንዳይሆን የሁላችንም ሃላፊነት ነው። ወያኒ ከአልገዛ አገር ትበጣጠሳለች ማለት ቅጀት ነው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አይበጣጠስም፤ ለብዙ ዘመን አብሮ በሰላም በፍቅር የኖረ ጨዋ ሕዝብ ነው። ክፍል ሁለት ይቀጥላል።
ግልጽ ደብዳቤ ለመላ የኢትዮጵያ ሕዝብ በያላችሁበት
ወሰኔ ይፍሩ [ፕሮፌሰር]
ክፍል ሁለት
የከተበራችሁ ወገኖቺ ሆይ በቅድሚያ የከበረ ሰላምታዮን አቀርባለሁ።
በክፍል አንድ ላይ እንደተጠቀሰው በክፍል ሁለት ላይ የሚቀርበው በተከታታይ የአለፉት ሶወስት ትውለደ ዘመናት ያደረጉትን ታሪካዊ ፖለቲካ ለውጥ ነው። ይህም በግዜ ብዛት 90 ዓመት የፖለቲካ ሂደት ይሆናል። ሂደቱም ሙሉ በሙሉ ስለ ተጠናቀቀ እንደ ታሪክ መወሰድ ይቻላል። ግዚውም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1930 እስክ 2020 ያለው የፖለቲካ ሂደት ይሆናል። እንግዲህ ውድ ወገኖቼ ይህንን የፖለቲካ ሂደት በምን አይነት “ሁኔታ” ላይ ሆነን ነው መወያየት የምንችለው? ለውይይቱስ ምን አይነት ቅድመ “ሁኔታ” ያስፈልጋል? በማለት ነው። በአጭሩ የሚያስፈልገው ቅድመ “ሁኔታ” የመናገር፤ የመጻፍ፤ በአጠቃላይ ፍጹም ነፃ የሆነ የብዙሐን መገናኛ፤ ከምንም ነገር ገለልተኛ የሆኑ ጋዚጠኞች ተደራጅተው[institutionalized] ሲገኙ ነው። ጋዚጠኞች ከፖለቲካ፤ ከጎሳ፤ ከሃይማኖትና ከግል ጥቅም ጋር የተያያዘ ነገር ሁሉ ፍጹም ነፃ መሆን ግዴታቸው ነው። የጋዚጢኛ ዋናው ተግባሩ የአገርን ጉዳይ በተመለከት ሁለ ገብ በሆነ መንገድ ተመልክቶ ለሕዝብ ማሳወቅና ጥቅሙንና ጉዳቱን ለይቶ ማመልከት ነው። ከሁሉ በላይ የሕገ መንግሥቱን መከበር፤ የሕግ በላይነትን አስፈላጊነት፤ የግለ ሰቡን ሰብአዊ መብት መከበሩን፤ የፍትሕ ሥርዓት መጠበቁን፤ መንግሥት በሕዝብ ስም የሚሰራዉን በጥብቅ እየተከታተለ ማሳውቅ ነው።
በተጨማሪ ጋዚጠኛ የውጭ አገርን ግንኙነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለዉን የፖለቲካ ሂደትንና “ሁኔታ” እየተነተነ ለሕዝብ ማሳወቅ ዋነኛ ከሚባሉት ተግባራት አንዱ ነው። እንግዲህ እዚህ ላይ የሚደረገው ጥረት ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት የመልካም አስተዳደር “ቅድመ ሁኔታ” እንዲት መፈጠር እንዲሚችሉ መላ ለመምታት ነው። ምክናያቱም ይህ “ሁኔታ” ከአልተፈጠረ መልካም አስተዳደር በራሱ ወይም በተአምር ሊፈጠር የሚችል ርዕተ ዓለም አይደለም። ዶክተር አቢይ የኢህደግን አሽባሪነትና የሰራቸውን ወንጀል ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሳውቆ ይቅርታ ጠይቆ በሁለት ዓመት ግዚ ውስጥ ሕዝብ ለሚመርጠው መንግሥትን እናስረክባለን ብሎ ቃል ሲገባ የነፃነት “ሁኔታ” ተፈጠረ ብለን ነበር። እዚህ ላይ በጥንቃቂ ማስተዋል ያለብን የጠቅላይ ሚንስትሩን ያለበትን “ሁኔታ” ነው። ለለውጥ ተዘጋጁ ብሎ መልክቱን ከማድረስ በላይ ሊላ ስልጣን የለውም። ይህም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፍኩት ደብዳቤ ላይ በግልጽ ተቀምጧል፤ ሕዝብ በትግል ያመጣዉን ለውጥ አንድ ሰው ሊቀለበሰው አይችልም። የጠቅላይ ሚኒስትሩም ስራ ከዚህ ሊያልፍ አይችልም። ሆኖም አሸጋግራለህ ባለው መሰረት የአገሩን ሰላምና የሕዝቡን ደህንነት ማስጠበቅ ግዲታ ነው። ወገኖቺ እዚህ ላይ በቅጡ ማስተዋል ያለብን ተፈጠረ የተባለው “ሁኔታ” በአንድ ሰው ችሮታ የተሰጠ አይደለም፤ በዙ ሰው በአደረገው ከፍተኛ መስዋዕትነት ነው። እኛ ግን ልክ እንዳለፈው ትውልድ ሳንጠቀምበት ከእጃችን ሊያመለጠን ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለውጥ ሊያመጣልን ነው ብሎ መጠበቅ ቀበሮዋን መሆን ነው፤ ቀበሮዋ በሪ ስታይ ብልቱ ድብ ብሎ የምትበላው እየመሰላት ትከተላላች ይባላል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢሃደግ ጠቅላይ ሚንስትር ነው። ተጠሪነቱም ለድርጅቱ እንጂ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አይደለም። እኛም በሕዝብ ደም የተገኝዉን “ሁኔታ” ከአልተጠቀምንበት ጠቅላይ ሚንስትሩ በደስታ ኢሃደግን በድል አድራጊነት መልሶ ስልጣን እንዲወጣ ለማድረግ መሆኑን ማወቅ ይገባናል። ይህም ሊሆን የሚችለው ከአለፈው ጥፋት ስለአልተማርን ነው። ስለዚህ ምን አልባት ትምህርት እንዲሆን በማለት ያለፈዉን ትውልድ የፖለቲካ ሂደት አጠር በአለ መልኩ ይቀርባል። መልካም ንባብ።
ያለፈው ትውልድ ያደረጋቸው የፖለቲካ ለውጥና ታሪካዊ ሂደት የሚጀምረው በንግርት መልክ ተጽፎ እንደ ምሳሌ ሆኖ ለአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ግብረ ገብ እንዲማሩበት በግዕዝ ብራና ላይ የተጻፈ ጽሑፍ ነው። ይህ ጸሐፊ ደበረ ሲና በሚገኝው አብዮ ትምህርት ቤት በሚባለው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በነበረበት ግዚ በግብረገብ ክፍል በቄስ ታደሰ እየተተሮጎመ የተማረው ትምህርት ነው። አስተማሪያችን እንደነገሩን ከሆነ ደራሲው መሪጌታ አጥናፍ ሰገድ ዋቄ ይባላሉ። እሳቸውም የዶባው ባላባት የአቦ ዋቄ ልጅ እንደሆኑና አሉ ከሚባሉት የዋዚማ ሊቃውንት አንዱ እንደነበሩ ይነገርላችዋል። በተጨማሪ መሪጊታ አጥናፍ ሰገድ ዋቄ ተጉለት በሚገኝው አጃና ሚካኢል በሚባለው ደብር የዋዚማ መምሕር እንደነበሩ አስተማሪያችን ይነግሩን ነበር። ተጉለትም በዋዚማ ታዋቂ እንደሆነ ይታወቃል። የሳቸዉንም ጽሁፍ በምንማረበት ግዚ እሳቸዉን በሃላፊ ግዚያት ስለሚጠራቸው በዚያን ግዚ በሕይወት እንደሊሉ ያስታውቃል። የግብረ ገብ መምሕራችን ድምጻዊ ስለነበሩ ግዕዙን ወደ አማርኛ እየተረጎሙ ጣዕም በሚሰጥ ዋዚማ ሲያነቡልን ተመስጠን ነበር እምናዳምጥው። ምንም እንኳ ከ60 ዓመት በፊት ቢሆነውም የመሪጊታውን ትንቢት በሚገባ ላስታውሰው እችል ይሆናል ብዮ እገምታለሁ። ምንአልባት ቋንቋው እንደሊቃኑ ላይሆን ይችላል። ታላቁ ሊቅ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ እንዳለው የአማርኛ ቃንቋ እጅግ የላቀ የኢትዮጵያ ብሒራዊ ቃንቋ ስለሆነ ታላቅ ሊቅ ሲጽፈው ጣዕሙ የተለየ ይሆናል፤ ለማንበብም ሆነ ለመስማት የሚያስቸግር በክፍተኛ ደረጃ የዳበረ ቃንቋ ነው ይላል። ስለዚህ እዚህ በትውስታ የሚቀርበው ቃንቋ እንደ ዋዚማው መምህር ሊሆን አይችልም። ሆኖም በተቻለ መጠን የመመህሩን አጻጻፍ ችሎታ ለማንጸባረቅ እምክራለሁ። ጽሑፉ በነጠላ ዓረፍተ ነገር፤ በመስተዋድድ፤ በአንቀፅና በኑዕስ አንቀጽ ታጅቦ ተጽፏል፤ የመሪጊታው ትንቢት እንዲህ ይላል፤
የደጉ እምዮ ምኒልክና የደጓ ንግሥት ዘውዲቱ ዘመን ሲያበቃ ኢትዮጵያ ለሶወስት ትውልድ በመከራና በስቃይ ውስጥ ታልፋለች፤ ከቀዳማዊ ምኒልክ እስክ ዳግማዊ ምኒልክ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የነገሥታት ዘመን እዚህ ላይ ያበቃል። በመጨረሻው ዙፋን ላይ የሚቀመጠውም ንጉሥ ራሱን ወዳድ አገሩን አሳልፎ ለባዕድ የሚስጥ፤ ሃብትና ንብረት በቃኝ የማይል ንፉግ፤ ስለስሙ ታላቅነት ሊት ተቀን ሳይታክት የሚሰራ በግለሰባዊነት መንፈስ የተሞላ ሰው ይሆናል። ሰውነቱንም እንደሰው ሳይሆን እንደ ጣኦት እንዲመለክ አድርጎ ለግዛት ዘመኑ ዘለዓልም እንዲሆን የሚመኝ ጣኦት አምላኪ ይሆናል። በግዛት ዘመኑም ረሃብ፤ ድርቀት፤ ጎድፍ፤ ማዕበል፤ ሰብሉን ጠራርጎ የሚበላ አንበጣ ይመጣበታል፤ በውጭ ጦርም ተሽነፎ ይሰደዳል። እንደገናም ተመልሶ አገሩን ይገዛል፤ የግዛት ዘመኑም 44 ዓመት ይሆናል፤ በዘመኑም አገሪቷ የምትታወቀው በረሃብና በችግር ይሆናል። ከሱ በኋላ የዘውድ አገዛዝ ስራዓት በጉግ ማንጉግ ስራዓት ይተካል፤ የጉግ ማንጉግ ትውልድ ሁሉን አውቃለህ የሚል ይሆናል፤ ሁሉም አዋቂ፤ ሁሉም መሪ ሆኖ እኔ በልጥ እኔ በልጥ በማለት ይገዳደላል፤ እሱ ያለው ከአልሆነ አባቱን፤እናቱን፤ወንድሙን፤እህቱን የሚገድል ትውልድ ነውና፤ መግደልም ጅግንነት ስለሚመስለው ይመጻደቃል፤ መጎደኛም ስለሆነ ግብረ ገብነት የለውም፤ ከጥፋቱም መማር አይፈልግም፤ ስህተትን ስለማያቅ ምንጊዜም ቢሆን የሚሳሳት አይመስለውም፤ ፍጹም አዋቂ ነኝ ብሎ ያምናል፤ አዋቂነቱንም በግድ እንዲታወቅለት ያደርጋል፤ ራሱን ማወደስ ትልቀኛው ተግባሩ ይሆናል። ግን በራሱ ኅይል እንደ ንፋስ ብን ብሎ ይጠፋል። ከሱም ቀጥሎ የወንበዴ መንግሥት ይመጣል። ውንብድናውም በአገሩ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ይሆናል፤ ሴትን ልጅ እባልዋ ፊት ይደፍራል፤ ልጅም እናዳተፈራ መካን ያደርጋትል። የሰውን ንብረት ያለምንም ሃፍረት ይቀማል፤ ይሉኝታ የሚል ቃል በቃንቃው ውስጥ ያለ አይመስልም፤ አገሩን ለውጭ ሃብታሞች ይሽጣል፤ የአገሩን ሃብት ወደ ውጭ አገር ያሸሻል፤ የኢትዮጵያን የተለያዩ ጎሳዎች ለያይቶና በድንበር ከልሎ ነፃ ብሒረሰቦች ናችሁ በማለት ራሱን የብሒር በሒርሰቦች የበላይ ጠባቂ በማድረግ በሚቃወሙት ላይ የዘር ማጥፋት ያካሂዳል። የብሒር ብሒረሰቦች ጽንፈኞችን አሰልጥኖ እሳትና መርዝ አጉርሶ እርስ በእርሳቸው እንዲፋጁ ያደርጋል። ኢትዮጵያ የምትባል አገር አልነበረችም እያለ ሕዝቡን እንዳይግባቡ ያደርጋል። ይህም ፍጅትና መከራ የበዛበት ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ይነሳበታል፤ አናሳም ስለሆነ መግቢያ ቀዳዳ ያጣል፤ ያም መከራና ፍጅት የበዛበት መልካሙን ትውልድ ይወልዳል፤ መልካሙ ትውልድ መላ ኢትዮጵያን ይሞላታል፤ ሆኖም ወንበዲው ተኩላ ሆኖ የበግ ለምድ ለብሶ መልካሙን ትውልድ ሊበላ ይመጣል፤ ግን በመከራ የተፈተነው መልካሙ ትውልድ እራሱን አሳልፎ ለተኩላዎቹ አልሰጥም በማለት በአሽናፊነት አገሩን ኢትዮጵያን ያድናል:: በመጨረሻም መልካሙ ትውልድ ጥንታዊት የሆነዉን የኢትዮጵያን ክብርና ግርማ ሞገስ ይመልሳል፤ የጎሳ እኩልነት፤ የሚያልቅ ፅጋ፤ ማርና ወተት እንደ ውሀ የሚፈስበት አገር ትሆናለች፤ እንደገና ኢትዮጵያ በነፃነታ ለዘለዓለም ተክብራ ትኖራለች።
የመሪጌታው ንግርት አፈ ታሪክ ነው ተብሎ መወሰድ አይኖርብትም፤ ንግርት የሊለው ሕብረተሰብ የለም፤ በሁሉም ባሕል አለ። ንግርቱም እንደ ትንቢት ተወስዶ ከሃይማኖት ጋር ከተያያዘ የሕብረተስብ ችግር ሊፈታ አይችልም፤ በአገራችን በየግዚው ባሕታውያን እንደዚህም የሊላ ሃይማኖት ተከታዮች “ሁኔታን” አይተው የሚያስከትለውን በማስታዋል ይናገራሉ፤ መሪጌታው የሁለቱን ነገሥታት “ሁኔታ” በአንክሮ ተመልክተው በቀጣዩ ሶወስት ትውልድ የሚመጣውን መከራ በትክክል ሊያውቁ ችልዋል፤ የመጥፎ “ሁኔታ” ውጢት ጥሩ ሊሆን አይችልም፤ ሊላ ጥሩ “ሁኔታ” ከአልተፈጠረ ታሪካዌ ሂደቱ በተከታታይ መጥፎ ስለሚሆን፤ ስለዚህ የትንቢት ጉዳይ ሳይሆን “ሁኔታ” እየተከሰት የሚያመጣው መከራ ነው። እንግዲህ እዚህ ላይ የሚደረገው ጥረት የመሪጌታውን ንግርት መተንተን ይሆናል። የመጀመሪያው “ሁኔታ” የተፈጠረው በኢጣልያን ፋሺስት ጦርነት ምክንያት ንጉሡ ወደ እንጊሊዝ አገር ተሰደው ለአምስት ዓመት ኖረዋል፤ በዚህ አጋጣሚ የእንግሊዘን አገር የአስተዳደር ስራዓትና የንጐሠ ነገሥቱን በአጠቃላይ በአገር ውስጥ ያለውን ተግባር ሳይመለከቱ ከግንዛቤ ያስገቡት የንጉሠ ነገሥቱንኑሮውንና ክብሩን ብቻ ነበር። የእንግሊዝ ንጉሥ በማግና ካርታ [Magana Carta-Liberation] 1215 የፃነት ሰነድ ላይ በተፈረመው ውል መሰረት ንጉሡ እንደማንኛውም ሰው የሕግ በላይነትን ተቀብሎ በአገሩ ሕገ መንግሥት ደንብ ለመተዳደር የተስማማመብት ነው። በሕዝብ ምክር ቤትና በጠቅላይ ሚንስተር የሚመራ መንግሥት መመስረቱንና ንጉሠ ነገሥቱ ምንም ዓይነት ስልጣን እንደሊለው አስተውለው ወደ አገራቸው ሲመለሱ ተመሳሳይ “ሁኔታን” ፈጥረው ሕዝባቸዉን ነፃ ሊያወጡ ሲችሉ ስለአልተጠቀሙበት ሕያዉነት የሚያስግኝላቸውን እድል አልፈው ለጥፋት ተዳርገዋል። ታሪካዌ “ሁኔታን” ያለመገንዘብ የሚያስከትለው ጥፋት ከባድ ነው። ንጉሡ ከስልጣን ሲወርዱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የተከሰትዉን”ሁኔታ” ተመልክተው አገሩን መሪጌታው እንዳሉት ከጉግ ማንጉግ ስር እንዳትወድቅ ማዳን ሲችሉ በቸልተኛነት አገሩን ጥፋት ላይ እንድትወቅ አድርገዋል። ጉግ ማንጉግ በኖ ሲጠፋ የተፈጠረው “ሁኔታ” አገርን መከፋፈልና እንዳልነብረ ማድረግ ስለነበር ለወንበዲዎቹ ጥሩ “ሁኔታ” ስለሆነ ዛሬ አገራችንና ሕዝቡን በክልል የተከለለ የ80 ብሒረ ሰቦች አገር ሆኖ አክራሪ ጽንፈኞች እያሽበሩ በስርዓት አልባነት የምትገኝ አገር ሆናለች።
በእርግጥ አንድ ሰው “ሁኔታን” ፈጥሮ አምባገነንተን ሊያመጣ ይችላል፤ ምክናያቱም የአምባ ገነንት ባሌቤት ምንም ግዜ ቢሆን አንድ ሰው ነው። የእንግሊዙ ንጉሠ ነገሥት በማግና ካርታ ላይ የሕዝቡን ነፃነት የተቀበለው ተገዶ ነው፤ በኢትዮጵያ ያ “ሁኔታ” ስለአልነበረ ነገሠ ነገሥቱ በፈቃደኝነት ለሕዝብ ስልጣንን መሰጠት ፈቃደኛ አልነበሩም፤ አሁንም ቢሆን ለሕዝብ አምባ ገነኖች ስልጣንን አይሰጡም፤ ዲሞክራሲን የሚያመጣ ሕዝብ እንጂ ጠላይ ሚንስትሩ አይደለም፤ ዲሞክራሲ በአንድ ሰው ፈቃድ የሚከሰት አይደለም፤ ይህንንም በክፍል ሶወስት በዝርዝር ይጻፋል፤ ከዚህ ሊላ ውድ ወገኖቼ በጥንቃቄ መመልከት ያለብን እውጭ አገር ያለን ኢትዮጵያውያን በእነዚህ የለውጦች ዘመናት ምን አይነት ሚና እንደተጫውትን ነው። የምንፈልገዉን ዲሞክራሲ ማምጣት የምንችለው አንድ ሆነን በውውይት ነው፤ የሃሳብም ልዩነት ቢኖር የሚፈታው ዲሞክራሳዌ ቦሆነ ውይይት ነው። የንጉሠ ነገሥት አገዛዝ አበቃ ሲባል ተሰባስበን ወደ አገር የገባነው ለመወያየትና አገራችንን በዲሞክራሲ እንድትመራ ለማድረግ ሳይሆን እያንዳዳችን ስልጣን ለማግኝት ስለሆነ “ቀይ ሽብር ነጭ ሽብር” ብለን ተላለቅን፤ ይህ መሪጌታ እንዳሉት “የጉግ ማንጉግ ዘመን ሆነ.”በወንበዴዎቹ ዘመን ደግሞ ተሰባስበው የገቡት “ካሪ ሜትር ቦታ ተመርተው” ኢትዮጵያን ሊከፋፍል ለመጣ ጠላት ሃይል ድጋፍ በመስጠት የጥፋቱ ተካፍይ ሆነዋል። ይህ መጻፍ አለበት፤ ስለዚህ ይህ ጸሐፊ የዚያ “አጥፍቶ ለጠፋው ትውልድ” ወገን ስለሆነ ያደረግነውን ስህተት ለመጭው ትውልድ መጠቆም አስፈላጊ መስሎ ስለታዮው ነው፤ እንግዲህ “እኒን ያየህ ተቀጣ” ብሎ የሚቀጥለው ትውልድ የቀድሞው ትውልድ የሰራዉን ጥፋት አርሞ ደሙንና አጥንቱን ከስክሶ ለመጣው “መልካም ትውልድ” ማስረከብ ታሪካዌ ግዲታ ነው።
ክፍል ሁለትን ለማጠቃለል ያህል አሁን የተፈጠርውን “ሁኔታ” በአጭሩ መግልጽ አፈላጊ ነው። ኢሃደግ በጠቅላይ ሚንስትሩ አማካይነት በሁለት ዓመት ውስጥ ሕዝብ ለመረጠው መንግሥት ሥልጣን አስረክባለሁ ያለው ተገዶ ነው። ሕዝብ ከእንግዲህ ወዲህ በክልል ለከፋፈለን፤ ለአሰረን፤ ለገደለን፤ ከሞኖሪያችን ለአፈናቀለን፤ ዘርን ላጠፋ፤ አገርን ሽንሽኖ ለውጭ ሃይል ለሽጠ መንግሥት ሁለተኛ አንገዛም ብሎ ነው። ይህንን ለውጥ እዉን ለማደረግ የኢትዮጵያ ሕዝብ መነጋገር ያለበት በለውጡ ሂደት መሆን አለበት እንጂ ጠቅላይ ሚንስትሩ ስለሚሾመውና ስለ ሚሽረው፤ ኢሃደግ ለ27 ዓመታት አደርኩት ብሎ ስለሚሰራው ድራማ፤ ቤተመንግሥት ዉስጥ ወታደሮች ስለአደረጉት ጨወታ አይደለም፤ የኢሃደግ ጉዳይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳዩ መሆን የለበትም፤ ነፃ የሆኑና ገለልተኛ የሆኑ ጋዜጠኞች ከአሉ ውይይታቸው ስለ ሚጻፈው ሕገ መንግሥት፤ ስለ ነፃ ምርጫ ቦርድ፤ ስለ ነፃ ፍርድ ቤት፤ ለኢትዮጵያ ምን አይነት ሕገ መንግሥት ያስፈልግታል፤ ሕዝብ በሕዝብ ለሕዝብ ተብሎ ለሚመሰርተው መንግሥት የሚያስፈልገው አመራር ምን አይነት ቢሆን ጥሩ ነው? በፕሪዝዳንትና በጠቅላይ ሚንስትር ያለዉን ልዩነት፤ የፖለቲካ ፓርቲ በምን አይነት መደራጀት እንዳለበት? በጎሳና በብሒር ያለዉን ልዩነት? ታሪካዌ አመጣጡንና ሂደቱን፤ በሕገ መንግሥቱ እንዲት መካተት እንደሚችል? እነዚህ ሁሉ በአዋቂዎች አስተባባሪነት ከሕዝቡ ጋር መወያየት አስፈላጊ ነው።
ከሁሉ በላይ ለውጡን ምክንያት በማድረግ የገቡት ኢትዮጵያን ከአለፈው ትውልድ ምን መማር እንዳለባቸው ከግንዛቤ አስገብቶ ምን አይነት ሚና እንደሚጫወቱ በዝርዝር መታወቅ ይኖርበታል። ይህ ከአልሆነ ከአለፈው ጥፋት መማር ስለማይቻል አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባችዋል። እስከ አሁን ድረስ ለለውጡ ሂደት የፖለቲካ ፕሮግራም አዘጋጅተው ለሕዝቡ ያቀረቡት ነገር የለም፤ ጥቂት አክራሪ የጎሳ ጽንፈኞች በቁርስና በምሳ ተገዝተው በሕዝቡ ላይ ሽብር እየፈጠሩ ነው፤ አንዳዶቹም ድርጎ እየተቀበሉ በምርጫ ግዜ ሽብር ለመፍጠር መዘጋጅታቸውን የአደባባይ ሚስጥር ነው። አንድ መቶ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ የተለያዩ የጎስ ድርጅቶች የየራሳቻውን ፕሮግራም በማውጣት ተደራጅተዋል። በጎሳ ተደራጅተው የሕዝቡን ደህንነት መጠበቅ ተገቤ ነው። ግን በሃይማኖትና በዘር የፖለቲካ ፓርቲ መመስረት የሚያመጣው የኢሃደግን ክልል መንግሥት ስለሆነ ይህንን ከግንዛቤ አስገብተው ከሕዝባቸው ጋር ተነጋግረው የሕዝብ መንግሥት የሚመሰርበትን “ሁኔታ” መፍጠር ታሪካዌ ግዲታቸው ነው። መልካሙ ትውልድ ደሙን አፍሶና አጠንቱን ከስክሶ ያመጣዉን ነፃነት ማደናቀፍ መሆኑን ተረድተው ያለዉን ልዩነት በውይይትና በዲሞክራሲ አጥብቦ የሕዝብ መንግሥት የሚመጣብትን “ሁኔታ” መፍጠር ታሪካዌ ግዲታ ነው። ይህ ከአልሆነ ተመልሶ ያለፈው ትውልድ ያጠፋዉን መድገም ይሆናል። በክፍል ሶወስት ላይ “ዲሞክራሲ እንዲት እንደተመሰረተ ከዓለም አቀፍ ታሪካዊ ሂደት ጋር እያመሳከርን እንማማራለን።
አገራችን ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ተክብራ ትኑር!
ክፍል ሶስት ይቀጥላል።
ግልጽ ደብዳቤ ለመላ የኢትዮጵያ ሕዝብ በያላችሁበት
ወሰኔ ይፍሩ [ፕሮፌሰር]
ክፍል ሶስት
(ክፍል አንድ እና ሁለትን ለማንበብ ከዚህ ላይ ይጫኑ)
የተከበራችሁ ወገኖቼ ሆይ በቅድሚያ የከበረ ሰላምታዬን አቀርባለሁ፤
በሶስተኛው ክፍል የሚደረገው ውይይት እጅግ ጠቃሚ ከመሆኑም በላይ መከራ ፈትኖ ለወለደው “መልካሙ ትውልድ” ለሚመሰረተው መንግሥት ምሶሶና ግድግዳ ሆኖ አዲስቷን ኢትዮጵያ በምን ዓይነት “ሥርዓትና” “ሁኔታ” ሊሰራ ይችላል ብለን በተረጋጋ መንፈስ ሆነን የምንወያይበት መድረክ ይሆናል። ውይይቱ በበለጠ እንዲዳብር በማለት ሕዝብ ለሚመሰርተው መንግሥት አስፈላጊ ናቸው በምንላቸው ዝክረ ነገሮች ላይ እናተኩራለን። ከዚህ ውጪ ኢሃዴግ በአወጣው አጀንዳ ላይ ሆነን መዋለል አስፈላጊ ያለመሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ማወቅ ግዴታው ነው። በብዙሃን መገናኛና በአብዛኛው ድህረ ገጾች ላይ የሚደረገው ውይይት ኢሃዴግ በአወጣው አጀንዳ ስለሆነ የለውጡን ሂደት ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል ማለት ይቻላል። ስለዚህ እዚህ ላይ የሚቀርቡት ውይይቶች ስለ ዓለም አቀፍ “ዲሞክራሲ” ስለ “ሕገ መንግሥት” ስለ “ነፃ ፍርድ ቤት” ስለ “ነፃ ምርጫ ቦርድ” ስለ “ሕዝብ መንግሥት አወቃቀር” ይሆንና በተጨማሪ አገራችን ውስጥ ለብዙ ጊዜ ሲያወዛግብ የነበረዉን “ሁኔታ” የሚገልጽ እንደ “ብሔር” “ብሔር ብሔረሰቦች” እና በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩትን “ጎሳዎች” “በአብዮታዌ ዲሞክራሲ” ስም እንዴት ወደ “ብሔር ብሔረሰቦች” ተለውጠው እንደተከፋፈሉ በሰፊው መወያየት አስፈላጊ ነው። ለውይይታችን ግልጽ እንዲሆን በማለት የእነዚህን “ቃላት” አመጣጥ፣ ትርጉምና አጠቃላይ ይዘታቸውን እንመለከታለን። ለምሳሌ “ዲሞክራሲ” ምን ማለት እንደሆነ እንዴትስ እንደመጣ፣ “ብሔር” ወይም “የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት” እንዴት እንደመጣ ከእነ ትርጉሙ፣ “ጎሳ” ምን ማለት ነው? “በጎሳና” “በብሔር ብሔረሰቦች” ያለውን ልዩነት ዓለም አቀፍ በተስማማበት ትርጉም መሰረት እንወያያለን። እንግዲህ እዚህ ላይ የሚደረገው ጥረት ለመልካም አስተዳደር “ዲሞክራሲ” በዋናነት “ቅድመ ሁኔታ” ሆኖ ሲቀርብ ደግሞ በአንጻሩ “ብሔር ብሔረሰቦች” “ጎሳ” “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” የሚባሉት ዝክረ ነገሮች በአንድ አገር ፖለቲካ ሂደት ላይ ምን አይነት ሚና እንደሚጫወቱ በዝርዝር ማየቱ አስፈላጊ ይሆናል። በክፍል ሁለት ላይ በዝርዝር እንደቀረበው “ዲሞከራሲ” ሊመሰረት የሚችለው ከዚህ የሚከተሉት “ቅድመ ሁኔታዎች” ሲቀነባበሩ ነው።
በአጭሩ [ለመልካም አስተዳደር] የሚያስፈልገው ቅድመ “ሁኔታ” የመናገር፣ የመጻፍ፣ በአጠቃላይ ፍጹም ነፃ የሆነ የብዙሃን መገናኛ፣ ከምንም ነገር ገለልተኛ የሆኑ ጋዚጠኞች ተደራጅተው [institutionalized] ሲገኙ ነው። ጋዜጠኞች ከፖለቲካ፣ ከጎሳ፣ ከሃይማኖትና ከግል ጥቅም ጋር የተያያዘ ነገር ሁሉ ፍጹም ነፃ መሆን ግዴታቸው ነው። የጋዜጠኛ ዋናው ተግባሩ የአገርን ጉዳይ በተመለከት ሁለ ገብ በሆነ መንገድ ተመልክቶ ለሕዝብ ማሳወቅና ጥቅሙንና ጉዳቱን ለይቶ ማመልከት ነው። ከሁሉ በላይ የሕገ መንግሥቱን መከበር፣ የሕግ በላይነትን አስፈላጊነት፣ የግለ ሰቡን ሰብአዊ መብት መከበሩን፣ የፍትሕ ሥርዓት መጠበቁን፣ መንግሥት በሕዝብ ስም የሚሰራዉን በጥብቅ እየተከታተለ ማሳውቅ ነው። በተጨማሪ ጋዜጠኛ የውጭ አገርን ግንኙነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለዉን የፖለቲካ ሂደትንና “ሁኔታ” እየተነተነ ለሕዝብ ማሳወቅ ዋነኛ ከሚባሉት ተግባራት አንዱ ነው። እንግዲህ እዚህ ላይ የሚደረገው ጥረት ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት የመልካም አስተዳደር “ቅድመ ሁኔታ” እንዴት መፈጠር እንዲሚችሉ መላ ለመምታት ነው። ምክንያቱም ይህ “ሁኔታ” ካልተፈጠረ መልካም አስተዳደር በራሱ ወይም በተአምር ሊፈጠር የሚችል ርዕተ ዓለም አይደለም። ዶክተር አቢይ የኢሃዲግን አሽባሪነትና የሰራቸውን ወንጀል ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሳውቆ ይቅርታ ጠይቆ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሕዝብ ለሚመርጠው መንግሥትን እናስረክባለን ብሎ ቃል ሲገባ የነፃነት “ሁኔታ” ተፈጠረ ብለን ነበር። እዚህ ላይ በጥንቃቄ ማስተዋል ያለብን ጠቅላይ ሚንስትሩ ያለበትን “ሁኔታ” ነው። ለለውጥ ተዘጋጁ ብሎ መልዕክቱን ከማድረስ በላይ ሌላ ስልጣን የለውም። [ከክፍል ሁለት የተወሰደ.]
እነዚህ ከዚህ በላይ የተጠቀሱት “ቅድመ ሁኔታዎች” የሉም። እነዚህ “ቅደመ ሁኔታዎች” ከሌሉ መልካም አስተዳደር ሊኖር አይችልም። በአለፉት ሶስት ትውልደ ዘመናት እነዚህ “ቅድመ ሁኔታዎች” አልነበሩም። አሁንም የሉም። “ቅድመ ሁኔታ” በተአምር የሚከሰት ርዕዮተ ዓለም አይደለም። በታሪካዌ ሂደት ቀስ በቀስ የሚዳብርና እንደልምድ ሆኖ [norm] በስራ ላይ የሚዉል ያልተደነገገ ሕግ ነው። ማለትም ሕዝብ በዘልማድ የሚገለገልበት ማለት ነው። ለምሳሌ ያህል የልጆችን ጨዋታዎች ብንመለከት ለጨዋታቸው ሁሉ ያልተደነገገ [ያልተጻፈ] ሕግ አሉት። ያን ሕግ የሚያከብር ልጅ ከጨዋታ ውጭ ይሆናል፤ “አፋራም ተብሎ” ማንም ልጅ ከሱ ጋር አይጫወትም፤ ከባድ ቅጣት ነው። ደግሞ ወደ ተደነገገ ሕግ ስንመጣ ቀስ በቀስ በዓለም አቀፍ አዋቂዎች የዳበረ ነው። “ሕግ” ፍጥረትንና የሰዉን ልጅ ባሕርያት አጥንተው ለሰው ልጅ መተዳደሪያ ይሆናል ተብሎ በውውይትና በስምምነት የተደነገገ የሰው ልጅ መተዳደሪያ ደንብ ነው። እንግዲህ ከልጆች ጨዋታዎች ሕግ ወደ “ሕብረተሰብ መተዳደሪያ ሕግ” ተሻግረን እንወያያለን። መልካም ንባብ።
የአእምሮቻንን ጅማት ለማጠንቀርና የሕሊና ንቃታችን ከፍ እንዲል በማለት ይህንን ውይይት የምንጀምረው አገር በቀል በሆነው ዘርዓ ያዕቆብ በተባለው ፈላስፋ ላይ ይሆናል። ዘርዓ ያዕቆብ የንቧን ስራ በትኩረት ተመልክቶ እንዲህ ይላል፦
ንብ ስራዋ እፅብ ድንቅ ነው። የማትቀስመው ዕፅዋት የለም። ከእነዚህ ሁሉ ዕፅዋት የቀሰመችዉን ሰብስባ እጅግ ጣፋጭ የሆነዉን ማር ትሰራለች። ማሩም ለመጠጥ የሚሆን ጠጅ ይወጣዋል። የጠጁም ቅሪት ጧፍ ሆኖ በጭለማ ጊዜ ብርሃንን ይሰጣል። ዕውቀት በተለያየ ስፍራ ይገኛል። የሰውም ልጅ እንደንቧ ሆኖ የተለያዩ ቦታ የሚገኝዉን ዕውቅት ቢቀስም ብዙ ዕውቀቶችን ይሰበስባል። እንደ ንቧም ባለሙያ ይሆናል። ግን አንድ ሰው ሁሉን አውቃለሁ ካለ ምንም ነገር የማያውቅ መሃይም ሆኖ ይቀራል። ለመሃይምነቱም ፍጹም ተወዳዳሪ አይኖረውም። ግብዝና ሞጎደኛም ስለሆነ ሂደቱም ታሪካዊ አይሆንም። ስርዓት አልባም ስለሆነ ኑሮው ሁሉ በመከራ ይሆናል። ስህተቱን መልሶ መላልሶ ስለሚሰራው ከመከራው ምንም ጊዜ ቢሆን አይወጣም። መከራም አይመክረዉም። [ዘርዓ ያዕቆብ]
እንግዲህ እንደ ዘርዓ ያዕቆብ ትኩረት ሰጥተን ከተመለከትን “ሕግ” እንደማሩ ከተለያዩ ሃሳቦች የመነጨ መሆኑን መረዳት እንችላለን። ዲሞክራሲ እንደወርቅ ተፈልቅቆ የወጣው እንደማር ተሰርቶ በወጣው “ሕግ” ነው። “ሕግን” አንድ ግለሰብ አንድ ቀን ተነስቶ ያወጣው ነገር አይደለም። ወይም የአንድ ግለሰብ ስራ አይደለም። እንደ ዘርዓ ያዕቆብ ፍጥረትን በትኩረት ከተመለከቱ ግለሰቦች ተሰባስቦ ነው “ሕግ” የሆነው። ዲሞክራሲም በአንድ ግለሰብ በጎ ፈቃድ የተሰጠ የመልካም አስተዳደር “ሁኔታ” አይደለም። ግለሰብ “ያዘው” “እሰረው” “ግረፈው” “ግደለው” የሚል ባሕርይ ስለአለው ብቻዉን የሚያመጣው “አምባገነንነት” እንጂ ዲሞክራሲን አይደለም። በታሪክ ውስጥ ዲሞክራሲ በግለሰብ ችሮታ ወይም “በአብዮታዌ ዲሞክራሲ” መጥቶ አያቅም። “የአብዮታዌ ዲሞክራሲ” ዋና ስራው የግለሰቡን አምባገነንት መብት ማስጠበቅ ነው። በአብዮታዌ ዲሞክራሲ ጎሳውን ብሔር ነው፤ብሔሩን ክልል ነው፤ ክልሉን መንግሥት ነው፤ እያለ “ብሔር ብሔረሰቦች” ብሎ የፈጠራቸውን ማዋጋት፣ ማፋጀት፣ በቋንቋ እንዳይግባቡ ማገት፣ ማሰር፣ ያልተባበሩትን መግደል፣ መዝረፍ፣ መሰረቅ ነው። አብዮታዌ ዲሞክራሲ ለኢትዮጵያ አንድነትም ሆነ መልካም አስተዳደር አላመጣም። ያመጣው ፍጅትና ከሚኖርበት መፈናቀል ነው። አሁን ያለው “ሁኔታ” በቂ ምስክር ነው።
ይህንን “የሕግ” አመጣጥ ከግንዛቤ አስገብተን “ሕግና” “ሕገ መንግሥት” እንዴት ሊዳብሩ እንደቻሉ እንመለከታለን። ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ እንዳለው “ሕግና” “ሕገ መንግሥት” የዳበሩት በየቦታው ከሚገኙ ፈላስፋዎች ነው። እዚህ ላይ ሳልል የማላልፈው አንድ ግንዛቤ አለኝ። ይኸውም አገር በቀል የሆነዉን ብቸኛ ፈላስፋ ዘርዓ ያዕቆብን እንደ ፈላስፋ አንመለከተዉም። በተለይ ምሁር ነን የምንለዉ ዘርዓ ያዕቆብን የምናየው እንደ ተራ “ደብተራ” ነው፤ የደብተራ ትርጉሙንም ምን እንደሆነ አናውቀውም። በዚህ ጸሐፊ እይታ እኛ ኢትዮጵያኖች ያለመጠን “ጥገኛነት” እንደሚያጠቃን ነው። ራሳችንን ችለን እንዳንመራመር ታላቅ የሆነ ተጽኖና እገታ አለብን። እንግዲህ ስለ ዘርዓ ያዕቆብ የተባለዉን በአትኩረት እንመልከት።
“ዘርዓ ያዕቆብ ኢትዮጵያዊ ስለሆነ ፈላስፋ ሊሆን አይችልም፤ ወይም ከሌሎች ሰምቶ የጻፈው እንጂ እሱ ይህንን የመሰለ ፍልስፍና ሊጽፍ አይችልም።” በማለት እናጣጥለዋለን። ይህም ማለት ፍጡራዊ የሆነዉን ችሎታችንን ትኩረት ሰጥተን ዘርዓ ያዕቆብ የተመለከተዉን ፍጡራዊ ንብ ማየት አለመቻላችን ነው። ጥራት የሌለው ፍልስፍናችንም ጎጠኛ፣ ዘውገኛ፣ ጽንፈኛ፣ ጎሰኛ አድርጎናል። ከዚህ ሁሉ በላይ የሚያሳዝነው የቤተክርስቲያንችን ሊቃውንት እንደ ዘርዓ ያዕቆብ ፍጥረትንና የሰው ልጅ “ሁኔታ” ማየት ስላልቻሉ ዘርዓ ያቆዕብን ሃይማኖተ ቢስ እያሉ እነሱ የአምባገነን “አወዳሽ” ሆነው ቀርተዋል። ስለዚህ የተወለደው መልካሙ ትውልድ ያለፈዉን ትውልድ ስህተት ተመልክቶ አገሩን ኢትዮጵያን በመልካም አስተዳደር እንዲመሰርታት ተስፋ እናደርጋለን።
የሕግና ዲሞክራሲ ታሪካዊ ሂደት
ብላቴን ጌታ ሲራክ ሕሩይ ወልደ ሥላሴ “ራሴ ላስ” ተብሎ በእንግሊዛዊ ደራሴ በሳሙኢል ጆንሰን የተጻፈዉን መጽሐፍ ሲተረጉሙ እንዲህ ይላሉ፤ “መጽሐፉ ስለ ስነ ፍጥረት ሲመራመር ወደር የለዉም። ከፍጥረት ሁሉ የሰው ልጅ ፈጽሞ እርካታ የሌለው ፍጥረት ነው።” ይሉና ትንተናቸዉን ይጀምራሉ፦
ራሴ ላስ የተባለው አልጋ ወራሽ [መስፍን] በዚያ በተራራ በተከበበችው ሸለቆ ዉስጥ ሲኖር ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉት ነገሮች ሁሉ ተደራጅቶ የአባቱ ዙፋን ላይ ዘውዱን ጭኖ እንዲቀመጥ እስኪጠራ ድረስ ይጠብቃል። ግን ጊዜው እስኪደርስ ድረስ በልዑላን ቤተሰቦች ታጅቦ፤ በእምቢልታ፣ በመለከት፣ በበገና፣ በተለያዩ ሙዚቃ እየተደሰተ ማርና ወተት እንደዉሀ እየፈሰሰለት ይኖራል። ግን እነዚህ ደስታ ይሰጡታል የተባሉ ነገሮች ሁሉ እያሉ ምንም ነገር ያስደሰተው የለም። በመጨረሻም በሸሎቆው ያሉትን እንስሳት ተመልክቶ መስፍኑ እንዲህ አለ ይባላል። “እነዚህ ሁሉ እንስሳት እንደእኔ እርቧቸው ይበላሉ። ዉሀ ጠምቷቸው ይጠጣሉ፤ እኔም እንደነሱ እበላለሁ፤እጠጣለሁ፤ ግን እንደነሱ እርካታ አድርጌ አላርፍም፤ ለፍላጎቴ መጠን የለውም፤ ስለዚህ ከዚህ ሸለቆ ውስጥ ወጥቼ የምፈልገዉን ነገር ማግኝት አለብኝ።” ብሎ ከእህቱና ከጠባቂው ጋር ወደ ግብፅ አገር ሄደ። እዚያም ሲደርስ የፈለገዉንና እርካታ የሚሰጠዉን ነገር ስላላገኘ ወደ አገሩ ተመለሰ። የአልጋ ወራሹም ፍላጎት ፍጻሜ የሌለው ፍጻሜ ሆነ። ከፍጡራን ሁሉ የሰው ልጅ ፍላጎት ወሰን የለውም። [ራሴ ላስ]
የሕግና ዲሞክራሲ አመጣጥ የሚጀምረው ታላላቅ ናቸው ከሚባሉት “ታሪክ” አምድ ላይ ነው። ከላይ የተጠቀሰው “ራሴ ላስ” ልብ ወለድ ስለሆነ “ታሪክ” ነው ብለን አንወስደዉም። ግን ሥነ ጽሑፉ ላይ ስለ ሰው ልጅ በምሳሌ የተነገረው እውነት ነው። ሰውንና እንስሳትን አነጻጽሮ አንዱ ፍጡራዊ በሆነ ገደብ እርካታ ሲያገኝ ሌላኛው ደግሞ ፍጡራዊ በሆነ ገደብ የለሽ ፍላጎት ይኖራል። እንግዲህ ይህ እንዲት ሊሆን ይችላል ብለን ብንመለከት እንስሳና ሰው የተለያየ ባሕርይ እንዳላቸው ያሳየናል። የሰው ልጅ እንስሳትን በተለያየ ዘዴ እንደሚቆጣጠርው ሁሉ ራሱንም ገደብ አስይዞ መቆጣጠር ችሏል። ለምሳሌ የኢንግሊዝና የአሜሪካን ሕገ መንግሥትና ዲሞክራሲ እንዴት እንደተመሰረተ ብንመለከት የመልካም አስተዳደር “ታሪካዊ” ሂደትን በሚገባ ልናውቅ እንችላለን። ይህም ማለት አምባገነን በየጊዜው እየመጣ የራሱን ፍላጎት ሊጭንብን አይችልም። እኛም እንደከብት መንጋ ለውጥ ሳይኖር ሊመጣልህ ነው እየተባልን በወሬ አንነዳም። ለውጥ ታሪካዊ ሂደት አለው። ይህውም የኢንግሊዝ ሕዝብ የንጉሠ ነገሥቱን ገደብ የለሽ ስልጣን “እምቢ ብሎ” በ 1215 በማግና ካርታ [Magna Carta] ላይ በተፈረመው ስምምነት መሰረት የንጉሡን ስልጣን ገድቧል። ይህም ማለት ንጉሠ ነገሥቱ ምንም ዓይነት ስልጣን ሳይኖረው በዙፋኑ ላይ እንዳለ ሆኖ የመልካም አስተዳደር የበላይ ጠባቂ ሆኗል። ከዚህም በላይ “ታሪካዊ” ሆኖ በዓለም ሕዝብ የሚታወቀው “የእንግሊዝ ሕዝብ ሰብአዊ መብት” [English Bill of Rights, 1689] ተብሎ የሚታወቀውና ለብዙ አገሮች ተምሳሊት የሆነው “የሕዝብ ሰብአዊ መበት” ነው። ይህም መብት የሕዝብን “የመናገር” “የመጻፍ” “የመሰብሰብ” “የመምረጥ” “ራሱን ለመከላከል መሳሪያ የመያዝና” “ያለሕዝብ ፈቃድ መንግሥት ምንም ነገር ማድረግ እንደማይችል” የተደነገገበት የሕዝብ መተዳደሪያ ደንብ ነው። እንግዲህ በአትኩረት መመልከት ያለብን “ዲሞክራሲ” የሚመሰረተው በሕግ የበላይነት ነው እንጂ “በአብዮታዊ ግርግር” አይደለም፤ ዲሞክራሲ የሚመሰረተው በሕዝብ ነው። የመለሰ ዜናዊ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሕዝብን ለመዝረፍ የተደረገ ግርግር ነው።” “ግርግር ለሌባ ያመቻል” እንደተባለው ከብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ ከሕዝብ ተዘርፏል፤ የትግሬ ወያኔ “አብዮታዊ ዲሞከራሲ” ማለት ይህ ነው። ይህ ካልሆነ ደግሞ ጫካ እንገባለን ስለሚሉና ጫካ የሽፍታ መኖሪያ ስለሆነ ይህንን ውንብድናቸውን የሚያስቆም ኃይል ማሰማራት አያስፈልግም። ከጫካ ውጭ ሆነው እንደሰው መኖር ስለማይችሉ እርካታቸውን የሚያገኙት ጫካ ውስጥ ስለሆነ ይህ መብታቸው መጠበቅ ይኖርበታል።
የአሜሪካ ሕገ መንግሥትና ዲሞክራሲ ምንጭ
የአሜሪካ ሕገ መንግሥት “አባቶች” እየተባሉ የሚታወቁት ሕግ አርቃቂዎች ሕገ መንግሥታቸዉን ያረቀቁት ከተለያዩ አገሮች በተሰባሰቡ ስነ ፍጥረትን በአትኩረት ከሚያጠኑ የፍልስፍና ተመራማሪዎች ነው። የሴኔጋሊስ ስነ ፍጥረትና ታሪክ ምሁር ሼክ አንታ ዲዮፕ በጥናት እንደደረሰበት ፍልስፍናን ፍልስፍና የሚያደርጉት ሁለት ባሕርይ ሲኖሩት ነው ይላል። አንደኛው ተፈላሳፊው “እሱ ራሱን መሆኑን ሲያቅ፣” ሁለተኛው ደግሞ ተፈላሳፊው “እውነት የሆነውንና እውነት ያልሆነውን ለይቶ ሲያቅ” ነው ይላል። እንስሳትና ሰው የሚለዩት በዚህ መስፈርት ነው። እንስሳት ራሳቸውን ያውቃሉ ግን “እውነትንና እውነት ያልሆነዉን” ነገር ያውቃሉ ማለት ያስቸግራል:: “እውነትንና እውነት ያልሆነዉን” ለይቶ ማወቅ ትኩረትን ይጠይቃል:: ስለዚህ ሰው ስለሆነ ብቻ ትኩረት ይኖረዋል ማለት አይቻልም። ትኩረት ከሌለ “እውነትንና እውነት ያልሆነዉን ነገር ማወቅ ያስቸግራል።” ስለ ፍልስፍና ጥራት ሁለት “ሐተታዎችን” የጻፈ የምዕራብ አፍሪቃው አሞ የሚባል ፈላስፋ ደግሞ [Amo, West African Philosopher 1703/1759] “ፍልስፍና ጥራት ሊኖረው የሚችለው ተፈላሳፊው ቅን በሆነ ልቦና እና ትክክል የሆነ የስነ ፍጥረትን መመርመሪያ ሲከተል ነው” ይላል። እንግዲህ እዚህ ላይ በአትኩረት መመልከት ያለብን የአሜሪካ ሕገ መንግሥትና ዲሞክራሲ በምን አይነት “ሁኔታ” እንደተፈጠረ ነው። የሕገ መንግሥታቸዉን መግቢያ እንመልከት፦
Preamble
We the People of the United States, in Order to form a more perfect Union, establish Justice, insure domestic tranquility, provide for the common defense, promote the general welfare, and secure the Blessings of Liberty to ourselves and our posterity, do ordain and establish this Constitution for the United States of America.
እንግዲህ ይህንን የሕግ መግቢያ ስንመለከተው የሚያሳየው የሕዝቡን አንድነት ነው። “እኛ በአሜሪካ ውስጥ የምንኖር ሕዝብ ሕብረታችን ከምንጊዜም በፊት እንዲዳብር፣ ፍትህና ሰላም እንዲኖረን፣ ዳር ድንበራችን እንዲጠበቅ፣ ለሁላችንም መልካም አስተዳደር እንዲኖረን፣ ተባርኮ የተሰጠነን ነፃነት ለእኛና ለመጭው ትውልድ እንዲተላለፍ በማሰብ ይህንን ሕገ መንግሥት ለተባበረችው አሜሪካ የመተዳደሪያ ደንብ እንዲሆን አጽድቀናል።” ይህ ከተባለ በኋላ ለአገራቸውና መለያ ለሆነው ባንዲራቸው ያላችውን ክብርና እምነት ለመጠበቅ ቃል ኪዳን ይገባሉ። “I pledge allegiance to the Flag of the United States of America and to the Republic for which it stands, one nation, indivisible, with liberty and justice for all.”
እዚህ በአትኩረት የምንመረምረው በመግቢያው ላይ የተጻፈበትን ቃላት ነው፤ “የአገር ሰላም” “የአገር መከላኪያ ጦር” “የአገር መልካም አስተዳደር” “ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፈው ነፃነት” ሲሆን “ጎሳ” “ብሔር” “የብሔር ብሔር እኩልነት” “አብዮታዌ ዲሞክራሲ” የሚል ነገር የለበትም ። ቃል ኪዳናቸውም ለባንዲራቸው፣ ለማይከፋፈለው ሕዝብ፣ ለነፃነታቸውና በፍትሕ ለተመሰረተችው ለተባበረችው አሜሪካ መቆማቸዉን ያስታውቃሉ። መንግሥታቸውም የተዋቀረው “መንግሥት በሕዝብ ለሕዝብ” በሚለው ወሳኝ በሆነው መርሐ ግብር ነው። መንግሥትን የሚያቋቁመው ሕዝብ ነው።
የአሜሪካ ሕዝብ ከመላ ዓለም የተሰባሰበ ነው። የሌለ አይነት ጎሳ የለም። ምንአልባትም ከማንም አገር የበለጠ የጎሳ ዓይነት ያለበት አገር ነው ማለት ይቻላል። ግን ልዕላዊነትን መርጦ አንድ ሕዝብ በመሆን የማይከፋፈል አገር በሕገ መንግሥቱና በዲሞክራሲ የሚመራ ስርዓት መስርተዋል። ሕጉም የተረቀቀው ከተለያዩ ፈላስፋዎች በተወሰደ ጽንሰ ሃሳብ ነው። ለምሳሌ የአንድ አገርን መንግሥት አስተዳደር ለሶስት ከፍሎ የጻፈውን የፖለቲካ ስርዓት ተመራማሪዉን ፍልስፍና የወሰዱት ሞንቴስኪው [Montesquieu 1689/1755] ከሚባለው የፈረንሳይ ፈላስፋ ላይ ነው። በሶስት የተከፈሉት የአስተዳደር ስልጣን ክፍሎች ሚዛናዊ ስለሆኑ በእኩልነት የአገሩን ዲሞክራሲ ይጠብቃሉ። ሕዝብ ወኪሉን ይመርጣል[ምክር ቢቱን] የሕዝብ ምክር ቤት ሕጉን ያወጣል፤ ፍርድ ቤቱ ሕጉን ይተረጉማል፤ የአገሩ መሪ ሕጉን ያስከብራል፤ አንዱ ከአንዱ አይበልጥም። ሶስቱም መንግሥት በእኩልነት እየተጠባበቁ ሕዝቡን በዲሞክራሲ እንዲተዳደር በአንድነት ሆነው ይመራሉ። ያለመግባባት ሲፈጠር በዲሞክራሲ ይፈታል። የአገሩ መሪ ሕግን ሲተላለፍ ፍርድ ቤቱ ያግተዋል። የሕግ በላይነትን አልቀበልም ሲል ደግሞ የሕዝብ ምክር ቤቱ ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጋር በመተባበር ከአመራር ስራው ላይ ያነሰዋል።
የአሜሪካንን ሕገ መንግሥት ታሪካዊ ከአደረጋቸው አንዱ የሰብአዊ መብት ነው። [The Bill of Rights] ይህም ጽንሰ ሃሳብ የመጣው ከእንግሊዛዊ ፈላስፋ ጆን ስተዋርት ሚል [John Stuart Mill 1806/73] ነው። የግለሰብ መብት ሊታገት የሚችለው የሕብረተሰቡን መብት ሲነካ ብቻ ነው። ይህ እስካልሆነ ድረስ የግለሰቡ መብት መነካት የለበትም። ብዙኃኑ የአናሳዉን መብት እንደራሱ አድርጎ መጠብቅ አለበት ይላል። የአሜሪካ ሕገ መንግሥት አጥብቆ የግለሰቡን መብት ከሁሉ አብልጦ ያስከብራል። ቮልተየር [Voltaire 1694/1778] የሚባለው የፈረንሳይ ፈላስፋ ሃይማኖትና መንግሥት መለያየት አለባቸው ይላል። መንግሥት ሃይማኖት ስራ ውስጥ፤ ሃይማኖት መንግሥት ስራ ውስጥ መግባት የለበትም። ግለሰብም የፈለገዉን ሃይማኖት መከተል መብቱ ነው። መንግሥትም እግለሰቡ ሃይማኖት ውስጥ መግባት የለብትም። የመናገር፣ የማመልክ፣ የመነገድ መብት መነካት የለበትም ይላል። የአሜሪካ ሕገ መንግሥት እነዚህን መብቶች በጥንቃቄ ይጠብቃል። በተጨማሪ ሕግ አርቃቂዎቹ የበርካታ ፈላስፋዎችን ጽንሰ ሃሳብ በመውሰድ የተጻፈ ሰነድ ነው። እንደ አስፈላጊነቱ ሕገ መንግሥቱ ይሻሻላል። በ 225 ዘመን ውስጥ ለ27 ጊዜ ተሻሽላል።
እንግዲህ የአሜሪካ ሕገ መንግሥት የተወለደው በርከት ካሉ ስነ ፍጥረትን ከሚመራመሩ ፈላስፋዎች በተወሰደ ጽንሰ ሃሳብ ነው። ሰነዱ የሰዉን ልጅ ባሕርይ በሚገባ ሊቆጣጠር የሚችል ልጓም ነው። ይህም ሆኖ የሕገ መንግሥቱ ታሪካዊ ሂደት ብዙ ውጣ ውረድ ነበረበት። ሕገ መንግሥቱ በፈጠረው “ዲሞክራሲ” የተባበረችው አሜሪካ “አንድ ሕዝብ” “አንድ የማይከፋፈል አገር” “የገለሰብ መብት የሚጠበቅበት ሕብረተሰብ” “በአንድ ባንዲራ” ስር ሆኖ በስምምነት ለመኖር ቃል ገብቶ አገሩን የመሰረተበት “ሁኔታ” ነው። ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ያንን ቃል ኪዳን የሚያፈርስ ኃይል ተነስቶ ነበር። እንግዲህ ትኩረታችንን ከፍ አደረገን ማየት ያለብን እንደገና “ራሴ ላስ” ላይ የተጻፈዉን ፍጡራዊ የሆነዉን ታሪካዊ ሂደት ነው። ይኸውም በእንስሳና በሰው ልጅ ያለውን ፍጡራዊ የሆነዉን ገደብና ገደብ የሌሽን እርካታ ነው። የሕግ በላይነትን አንቀበልም ብለው ገደብ የሌሽን ፍላጎታቸዉን ለሟሟላት የፈለጉ ግለሰቦች ችግር በመፍጠር አዲስ የተፈጠረውን ዲሞክራሲ ሊያፈርሱ በተለያዩ ጊዜ ሞክረው ነበር። ነገር ግን የሕግ በላይነትን ተቀብለው አገራቸዉን በዲሞክራሲ እንድትመራ የፈለጉ ዜጋዎች ታላቅ ተጋድሎ በማድረግ የአሜሪካንን ዲሞክራሲና የግለስቡን “ሰብአዊ መብት” አሰከብረዋል፤ በተለይ የጥቁርን ሕዝብ በታችነትና የተለየ “ጎሳን” በላይነት “ሁኔታ” ለመፍጠር በተደረገ ሙከራ የአሜሪካ ሕዝብ በታላቅ ጀግንነት አንድነትንና እኩልነትን በዲሞክራሲ መስርቷል:: የአሜሪካንን ዲሞክራሲ በስራ ላይ ለማዋል ብዙ አገሮች ሞከረው ነበር። ላቲን አሜሪካኖች የአሜርካንን ሕገ መንግሥት ለመከተል ሙከራ አድረገዋል። ግን በስራ ላይ ሊውል አልቻለም። አውሮፓውያንም በተለያየ ጊዜ ሙከራ አድርገዋል። የፊሊፕንስ መንግሥት ቃል በቃል ሕገ መንግሥቱን ወስዶ ነበር። ነገር ግን ዲሞክራሲ በስራ ላይ እንዲውል ከተፈለገ ሕብረተሰቡ እንደ አይኑ ብሌን መጠበቅ አለበት። ይህ ካልሆነ አምባገነን ተነስቶ ገደብ የሌሽ የሆነዉን ፍላጎቱን ሕዝብ ላይ ስለሚጭን “ዲሞክራሲን” በታላቅ ጥንቃቄ መጠበቅ የዜጋዎች ሃላፊነት ነው። አምባገነንን አጥብቆ መዋጋት ለሰው ልጅ ነፃነቱና ክብሩ ነውና።
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው “ሁኔታ” ተመሳሳይ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ “የትግራይን በላይነት” አጥብቆ በመቃወም ኢሃዴግን ማስወገድ አለበት። በዲሞክራሲ አሸናፊና ተሸናፊ የለም። አሁን የሚደረገው ጥረት ኢሃዴግን መልሶ ስልጣን ላይ ለማድረግ ስለሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ አጥብቆ መከላከል አለበት። ወያኔ እርካታቢስ ስለሆነ አስሮም፣ ገድሎም፣ ሰርቆም፣ በልቶም አይጠግብም። የጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ ከውጭ አገር በሕግ የሰለጠኑ የሕግ አማካሪዎች ያስፈሉጉታል። ብዙ ሕግን ያልተከተሉ ስራዎች በአገር ውስጥ እየተሰሩ ነው። የወያኔ ምክር ቤት ለፈጸመው ወንጀል እራሱን በምህረት ሊያድን አይችለም። በዘር ማጥፋት ተጠያቂ ነው። የመንግሥት አቋምዋትን እንደ አየር መንገድ፣ መብራት ኃይል፣ ቴሌኮሙንኬሽን ለራሱ ሊሽጥ አይችልም። ኢሃደግ የምርጫ ቦርድ ሊያቋቁምም አይችልም። ሲቆጣጠረው የነበረውን ፍርድ ቤቱንም ነፃ ሊያደርገው አይችልም። ለለውጥ ቃል በተገባው መሰረት ሕዝብ ለሚመርጠው ስልጣንን ከማሰረከብና የአገሩን ሰላም ከማስከበር ሌላ ስልጣን እንደሌለው የሕግ አዋቂዎች እንዲነግሩት ያስፈልጋል።
ክፍል ሶስትን ለማጠናቀቅ ያህል አጠር ያለ ውይይት ያስፈልጋል። በቅደም ተከተል ይቀርባል እንደተባለው ስለ ነፃ ምርጫ ቦርድ፣ ስለ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ስለ ጎሳ፣ ስለ የፖለቲካ ፓርቲ አመሰራረት፣ ስለ ነፃ ፍርድ ቤት በክፍል አራት ላይ በዝርዝር ይቀርባል። ግን ይህንን ክፍል ለማጠናቀቅ ውድ ወገኖቼን ማሳሳብ የምወደው አሁን ነፃ ባልሆነው ሚዲያ ላይ በሚደረገው ወሬ መነዳት እንደሌለብን ነው። በየድህረ ገጹ ላይ የሚወራው ወሬ ከለውጡ ጋር ምንም ግንኙንት እንደሌለው ማወቅ ግዴታችን ነው። ይህ ከሆነ የወሬ ወዳጆች ያደርገናል። በወሬ ዲሞክራሲ አይመሰረትም። በወሬ አገር አይኖርም። ዲያስፖራዎች ገቡ ወጡ ያለዉን ችግር አይፈታም። ጠቅላይ ሚንስተሩ ሴት ሾሙ ሴት ሻሩ፤ ገንዘብ ለምነው ቢሊዮን ዶላር አገኙ፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያመጣው ምንም ለውጥ የለም። ውይይታችን ከላይ በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ መሆን አለበት። ወንጀለኞች ወደ ፍርድ የሚቀርቡበት፣ የተዘረፉትና ወደ አንድ ክልል ቦታ ተወሰደው የተከማቹት የእንዱስትሪ ማምረቻዎች የሚመለሱበት “ሁኔታ” ማመቻቸት፤ በሕገ ወጥ መንገድ ተዘርፈው በውጭ አገር ባንኮች የተቀመጡ ገንዘብ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት አማካይነት የሚመለሱበትን “ሁኔታ” መወያየት አስፈላጊ ነው።
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ተከብራ ትኑር።
ክፍል አራት ይቀጥላል።
Reference:
1. Magna Carta, 1215
2. English Bill of Rights
3. Declaration Independence
4. The United States Constitution
5. Sirak Hiruy H. Sllasie: Rase Las: The Prince of Abyssinia
6. Philosophers who influenced the writing of the American Constitution:
a) Jean-Jacques Rousseau [1712-1778].
b) Thomas Hobes [1588-1679]
c) John Lock [1632 -1704]
d) Voltaire [1694-1778]
e) Montesquieu [1689-1755]
7, Zer’a Ya’qob [see the Nile Valley civilization፡ A Historiographical Commentary on Ancient Africa, 2016


