ከዶ/ር በቀለ ገሠሠ (ጥቅምት 2011 ዓ/ም)

፩ኛ/  መንደርደሪያ

‘ምን መደረግ አለበት?’ በሚል ርዕስ በተደጋጋሚ ባስተላለፍኩት መልእክት ስለተፈራረቁት አምባገነን መንግሥታትና ስላስከተሉት እጅግ ከባድ ችግሮች ለመግለፅ ሞክሬያለሁ። አሁን ደግሞ ትኩረት ለመስጠት የፈለግሁት በተቃዋሚ ድርጅቶችና በጠቅላላዉ ሕዝባችን ላይ ነዉ።

ሁኔታዎች አሁን ካሁን ትንሽ ይሻሻላሉ፤ ሰዎችም ወደኅሊናቸዉ መመለስ የጀመሩ ይመስላሉ ብለን ስንጠብቅ ዛሬም ዉድ አገራችንና ጭቁን ሕዝባችን በተለመደዉ አሳሳቢ መከራ ዉስጥ እንደገና በመዘፈቃቸዉ እጅግ በጣም አዝናለሁ።

መንግሥት በአብዛኛዉ መልካም ነገር የሚሠራዉ በሕዝቡ ሲገደድ ነዉ። ሕዝቡን የሚያስተባብሩት ደግሞ ተቃዋሚ ድርጅቶች ናቸዉ። ተቃዋሚ ድርጅቶች ደግሞ ህብረት ካጡ፤ እርስ በርሳቸዉ ከተጠላለፉና ከተዳከሙ ሕዝቡን ማስተባበር አይቻላቸዉም። የአምባገነን መንግሥታትን ዕድሜ ብቻ ነዉ የሚያራዝሙት። ባለፉት 50 ዓመታት ገደማ የትግል ታሪክ ዉስጥ የታየዉ ይሄዉ እዉነታ ነበር። ጥሩ አእምሮ ያለዉ ዜጋ ይሄን ሃቅ ሊክድ አይችልም።

፪ኛ/  በግንዛቤዎች ዙሪያ ጥሩ ስምምነት ላይ ስለመድረስ አስፈላጊነት

የእናት አገርን ሉዓላዊነትና የሕዝባችንን ደህንነት ለማስጠበቅ በአንዳንድ ጥያቄዎች ዙሪያ ጥሩ ስምምነት ላይ መድረስ የግድ ይላል። ካለዚያ ‘ዉሃ ቢወቅጡት እምቦጭ’ ሆኖ ይቀራል። ስለዚህ በሚከተሉት አንገብጋቢ ጥያቄዎች ላይ ከተስማማን በህብረት መልካም ለዉጥ ማምጣት እንደምንችል አንዳች ጥርጣሬ አይኖረኝም።

(ሀ)  የኢትዮጵያን አንድነት በተመለከተ

 

ኢትዮጵያ ሀገራችን በተለያየ ቅርጽ ለብዙ ሺህ ዓመታት እንደኖረች ተጨባጭ ታሪክ ይመሰክራል። የዘመነ መሳፍንት የሚታወቀዉ በተለያዩ መሳፍንት (የአካባቢ ግዛቶች) መካከል ሲካሄድ በነበረዉ ወረራ፤ ዝርፊያ፤ ዉድመት፤ ሁካታና ጭለማነት ነዉ። በመቀጠል፤ በዐፄ ቴዎድሮስ የተጀመረዉ አዲስ የማዕከላዊ መንግሥት ምስረታ በዐፄ ምንሊክ ዘመነ መንግሥት ተጠናቀቀ። በዚህም ሂደት የብዙ ሰዉ ሕይወት አልፏል፤ ንብረት ወድሟል፤ ክብር ተነክቷል፤ እጅግ በጣም ያሳዝናል። ይሄም የታሪክ ክንዋኔ ተመሳሳይ ማዕከላዊ መንግሥት በመሰረቱት የዐለም ክፍሎች (በተለይ በአዉሮፓ) የታየዉን ክስተት ይመስላል። በሌላ በኩል ደግሞ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት በመፈጠሩ ምክንያት ከዉጪ እንደ ጅብ አንጃብበዉ ከመጡብን የኦቶማን ቱርክ፤ የፖርቱጋል፤ የእንግሊዝ፤ የፈረንሣይና የጣሊያን ወራሪዎችና ቅኝ ገዥዎች አትርፎናል። ሕዝብን አቀራርቧል፤ ይበልጥ አስተሳስሯል፤ የተፈለገዉን ያህል ባይሄድም በትምህርት፤ በትራንስፖርት፤ በመገናኛ፤ ወዘተ ዘርፎች እድገት አሳይቷል። ያም ሆነ ይህ፤ ብዙዎቻችን ዉዲቷ ኢትዮጵያን ቅድስት አገር ብለን ነዉ የምንጠራት። ስንቱን መከራ አሳልፋ እስከ ዛሬ ድረስ የቆየችዉ በእግዚአብሔር ኃይል ነዉና።

 

ቸሩ አምላካችን ምስጋና ይግባዉና ይህቺ የተቀደሰች አገራችን እጅግ በጣም ሃብታም ሆና የተፈጠረች ነበረች። በምድራችን ስፋት፤ በአፈሩ ለምነት፤ በወንዞቻችንና በሃይቆቻችን ብዛትና በተሟላ የተፈጥሮ ሀብት የተገጎነጸፈችና እጅግ የላቀች ቅድስት ሀገር ነበረች። እንኳን ለህዝባችንና ለሌሎችም የምትተርፍ አገር ነበረች።

 

ሆኖም ግን መድረስ ከሚገባት የእድገት ደረጃ ልትደርስ አልቻለችም፡፡ ርሃብና ችጋር ቶሎ ቶሎ ይጎበኟታል፤ በቶሎም አይለቋትም፤ ሚሊዮኖች በየዓመቱ ይጠቃሉ፤ ሺህዎች ይሰደዳሉ። እስከመቼ ድረስ ነዉ በልመናና በዉጪ እርዳታ የምንቀጥለዉ? ወጣቶች (በተለይ ሴቶች) ለኑሮ ሲሉ በየዐረቡ ሀገራት ያን ያህል መሰቃየት አለባቸዉ? ለምን ብሎ መጠየቅ ተገቢ ጥያቄ ይመስለኛል፡፡ ሰላምና እርጋታ ኖሮ የተፈጥሮ ኃብታችንን  ተንከባክበን ለመጠቀም ብንችል ኖሮ ምንኛ የዕድገት ደረጃ ላይ በደረስን ነበር፡፡

 

ዛሬ ታዲያ እዉነተኛ ጠላቶቻችንና ዋና ዋና ችግሮቻችንን ጠንቅቀን ማወቅ የሚገባን ይመስለኛል። የዉጪ ወራሪዎችና ሃይማኖት አጥፊዎች ምን ጊዜም አይተኙልንም። መሬቶቻችንን፤ ወንዞቻችንና ድንበሮቻችንን ለመቆጣጠር ይሻሉ። ሰላምና እርጋታ የለም። ወገኖች እየተገደሉና እየተፈናቀሉ ይገኛሉ። የአካባቢ አየር ብክለት፤ የመሬት ጠፍነት፤ የሃይቆች ብክለት፤ ርሃብ፤ በሺታና እንግልት በመላዉ ሀገር አሳሳቢ ደረጃ ላይ አድርሰዉናል። እነዚህ ችግሮች በሰሜን (ለምሣሌ በሰሜን ሸዋ፤ በወሎ፤ በትግራይ፤ በጎጃምና ጎንደር የሚኖሩ ጭቁን ወገኖች)፤ በደቡብ (ለምሣሌ በኮንሶ)፤ በምሥራቅና በምዕራብ የአገራችን ክፍሎች በሙሉ ይታያሉ። ከነዚህ ችግሮች ማምለጥ የምንችለዉ ስንተባበርና ሰላም ስናሰፍን እንጂ እየተለያየን ስንናከስና ስንናቆር አይደለም።

(ለ)  የመንግሥት  ሥልጣን መያዝ ያለበት በነፃ የሕዝብ ምርጫ መሆን እንዳለበት

በሰለጠነና በሰከነ አእምሮ ብንመለከት የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ከባድ ባልሆነ ነበር። ተቃዋሚ የፖሊቲካ ድርጅቶች ነን ብለዉ የተሰለፉ ኃይሎች አንዳንድ ጥያቄዎች  እንዲመልሱልኝ እለምናለሁ።

  • በ70 እና 80 ድርጅቶች ተከፋፍላችሁና ተበጣጥሳችሁ እንዴት አድርጋችሁ ለምርጫ ልትቀርቡ ነዉ? ይሄ ጥያቄ አሳሳቢ ስለሆነ ተመሳሳይ መርሃ ግብር ያላችሁት ተቀራርባችሁ ብትነጋገሩበትና ህብረት/ዉህደት ብትፈጥሩ መልካም ይመስለኛል።
  • ሰብዓዊ መብቶችን ለማስጠበቅ በአገርም በክልልም መደራጀት አስፈላጊ ነዉ። ነገር ግን በብሄር የተደራጁት የፖሊቲካ ቡድኖች እንዴት አርገዉ በአገራዊ ምርጫ ዉስጥ ሊሳተፉ ይችላሉ? በብሄር ላይ የተመሠረተ ድርጅት ለክልል እንደሆነ እንጂ ለአገራዊ ምርጫ ተወዳድሮ ከጎሣዉ ዉጪ ድጋፍ ሊያገኝ ስለማይችል በዚህም ጉዳይ ላይ ቶሎ ብታስቡበት መልካም ነዉ ብዬ አምናለሁ።
  • ህብረት ካልፈጠራችሁና ካልተጠናከራችሁ የሚቀጥለዉም አገራዊ ምርጫ ፍትሐዊና ርትዓዊ እንዲሆን ማመቻቸት እንዴት ይቻላችኋል? በ2003 ዓ/ም ያቋቋማችሁትን 15 ተቃዋሚ ድርጅቶችን ያቀፈ ህብረት አፍርሳችሁ ምንም ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ዘልላችሁ በምርጫዎች ዉስጥ በመግባታችሁ ያስከተላችሁትን ታላቅ ዉድቀት ታሪክ ሲያስታዉስ ይኖራል። በአባቶች ቡራኬና በአገር ወዳዶች በጎ ጥረት ህብረቱ ሲመሰረት እንደ ትልቅ ብሥራት የተቀበልነዉን አፍርሳችሁ መሳቂያ አደረጋችሁን። ከእንደነዚህ ጥፋቶች ተምሮ መስተካከል የግድ ነዉ። ሕዝቡንም ይቅርታ መጠየቅ ይገባል።

 

ስለዚህ ጥያቄዉ ቀላል ነዉ። በዲሞክራሲ የምታምኑ ከሆነ በሚከተሉት ጥያቄዎች ዙሪያ ብንስማማ መልካም ይመስለኛል፤

 

  • ነፃ የምርጫ ቡድን/ቦርድ ስለማቋቋም እጅግ በጣም አስፈላጊነት፤
  • አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ገለልተኞች ታዛቢዎች በየምርጫ ኬላዉ ላይ ስለመገኘት እጅግ በጣም አስፈላጊነት፤
  • የምርጫዉን ዉሳኔ ተቀብሎ መንግሥት መመሠረትና ሰላም ማስፈን፤
  • የሚመሰረተዉም መንግሥት ብሄርን የማያበላልጥ፤ ወገንን የማይለይና የእያንዳንዱን ዜጋ ሙሉ ሰብዓዊ መብት የሚያረጋግጥና ሕግ የበላይ የሚሆንበትን ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር መሆኑን ማረጋገጥ፤
  • በዚህ ህደትና ሽግግር ዉስጥ ሁሉም ተቃዋሚ ድርጅቶች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማመቻቸት፤
  • ለሀገር ሉዓላዊነት፤ ለኢኮኖሚ እድገትና ለሕዝብ ደህንነት ተባብሮ ቆርጦ መነሳት።

 

በነዚህ ጥያቄዎች ዙሪያ ስምምነት ካልፈጠርን ዲሞክራሲ እያሉ በአፍ ብቻ መለፈፍ ዋጋ የለዉም። እናንተ አልተዘጋጃችሁ እንደሆነ እንጂ ሕዝባችን ንቁና አስተዋይ ነዉ። የሚበጀዉን ጠንቅቆ ያዉቃል። የፈለገዉን መርጦ የማስቀመጥ፤ የማይፈልገዉን የማዉረድ በቂ ችሎታ አለዉ። ባይታደል እንጂ ዛሬ ሰልጥነናል፤ ዲሞክራሲ መስርተናል ከሚሉን ምእራባዉያን ሕዝብ በፊት የሰለጠነ ሕዝብ ነበር። ይቅር ባይ ሕዝብ በመሆኑ እንደተለመደዉ በሰላምና በፍቅር ተሳስቦ ለመቀጠል በጣም ዝግጁ ነዉ። የተጠማዉ ዲሞክራሲን ነዉ። እንቅፋት የሆኑት ጨቋኝ መንግሥታትና ህብረትና ረዥም ራዕይ የሌላቸዉ ተቃዋሚ ድርጅቶች  ናቸዉ።

 

እላይ በተመለከቱት መሠረተ ሃሳቦች ላይ ስንስማማና ተግባራዊ ስናደርግ ነዉ እንደ አገር እየኖርን ወደአገራዊ ዕድገትና ብልፅግና ልንሸጋገር የምንችለዉ። ካለዚያ፤ አያድርገዉ እንጂ ትርፉ በተለይ ባለፉት 40 ዓመታት እንደታየዉ ተያይዞ መጠፋፋትን ሊያስከትል ይችላል።

 

፫ኛ/  ካለፉት ጠንካራና ደካማ ጎኖቻችን መማር ይኖርብናል፤ ጥፋቶቹን ላለመደጋገም

 

ሀ)   መግቢያ

 

ትናንት ዬት እንደነበርንና ዛሬ ምን ላይ እንዳለን ካላወቅን ወደፊት ወዴት እንደምናመራ በቅጡ ማወቅ ከባድ ይሆናል።

 

ዐፄ ቴዎድሮስ ለዉድ ሀገራቸዉ ዕድገትና ሕልዉና ብለዉ ሲወድቁ ከጎናቸዉ የቀሩት ገብርዬና ጥቂት ወገኖች ብቻ ነበሩ። ካህኑ ጭምር ነበር ጠላት የሆነባቸዉ። በቀ/ኃ/ሥ ዘመን ላገሩ ነፃነት ከተዋደቀዉ አርበኛ ይልቅ የተንደላቀቀዉ የባንዳዉ ክፍል ነበር። በተፈራረቁት መንግሥታት ሥር ሃቀኞች ለዲሞክራሲና ለእኩልነት ደማቸዉን እንዳፈሱና አጥንታቸዉን እንደከሰከሱ ታሪክ ሲያስታዉሳቸዉ ይኖራል። በአንፃሩም ደግሞ ረጅም ራዕይ የሌላቸዉና የማይተባበሩ ተቃዋሚ ተብዬዎችና ሆድ አደር ተለጣፊዎችም ከባድ ጥፋቶች ሲደጋግሙ ይታያሉ። ህብረትና ዲሞክራሲ እያሉ ባፋቸዉ  ይሰብካሉ፤ በተግባር ግን አፍራሾች ሆነዉ ይታያሉ። አንዴ ተለጥፈዉ ገብተዉ በካድሬነት በማገልገል ህዝባችንን ይረግጣሉ፤ ፍትህ ያዛባሉ፤ ምርጫ ያጭበረብራሉ፤ ላለፉት ጥፋቶቻቸዉም ሕዝባችንን ይቅርታ እንኳን ሲጠይቁ አይሰሙም።  ሃቀኞችንና አርበኞችን ማን ይፈልጋቸዋል? የረባ ለዉጥ ለማምጣት እንደመተባበር እንቅፋቶች እየሆኑ የአምባገነን መንግሥታትን  የጭቆናና የህዝባችንን ሰቆቃ ዘመን ሲያራዝሙ የሚታዩ ሰዎች ናቸዉ። እኔ ብቻ ካልገዛሁ፤ እኔ ብቻ ካልመራሁ፤ እኔ ብቻ ካልበላሁ እያሉ ይስገበገባሉ። ትግል ግን አይቆምም። ቀጥለዉ የመጡት መንግሥታት የባሱ ችግሮችን ስላስከተሉ የሕዝብን የለዉጥ ትግል መኮነን አይቻልም።

 

ሰዎች ከሆንን ካለፉት ጥፋቶች መማር ይኖርብናል። ሁሉንም ባንድ ላይ መጨፍለቅና መፈረጅ ኃጢአት ነዉ።  እያንዳንዱ ዜጋ ትክክለኛዉን ግንዛቤ መጨበጥ ይኖርበታል። ሀቁን በመገንዘብና በመንተራስ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በጋራ መመስረት ይኖርብናል። ከዚህ በታች ከተመለከቱት ካለፉት ጥፋቶችና ዉድቀቶች ካልተማርን እንዴት ወደፊት መራመድ ይቻለናል?

 

(ለ)  በግርማዊ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተቃዋሚዎች ሚና

 

እላይ ባጭሩ እንደታየዉ፤ ሥርዓቱን ለመጣልና ዲሞክራሲን ለመገንባት በተለይ ከ1950ዎቹ ጀምሮ ግልጽ ትግል ተጀመረ። እነ ጄነራል መንግሥቱ ነዋይ፤ ገርማሜ ነዋይና ወርቅነህ ገበየሁን የመሳሰሉት ሃቀኛ ዜጎች ከፍተኛ ጥቅማቸዉን ብቻ ሳይሆን ሕይወታቸዉን ጭምር መስዋዕት በማድረግ በንጉሡ ላይ መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ ተንቀሳቀሱ። ምክንያቶቻቸዉ የሚከተሉትን ይመስላሉ፤

 

  • የንጉሡ ፈላጭ ቆራጭነትና የዕድገት መጓተት፤
  • በቂ የአገር መከላከያ ባለመዘጋጀቱ በማይጨዉ በጣሊያን ጦርነት ስለመጠቃታችን፤
  • የአርሶ አደሩ መጨቆን፤
  • የከተማ ነዋሪዉ ሥራ አጥነት፤
  • በጣሊያን ወረራ ጊዜ ቤተሰቦቻቸዉን ይዘዉ መኮብለላቸዉ፤
  • ወደ ሥልጣን ሲመለሱም ባንዳ ባንዳዉን እያስጠጉና እየሾሙ አርበኛዉን ማግለላቸዉ፤
  • የዘመኑ የፓን አፈሪቃ አቀንቃኞች ተጽእኖ፤
  • ወዘተ።

 

ዳሩ ግን በዘመኑ በቂ ተሞክሮ ባለመኖሩና ባንዳንድ የዉስጥና የዉጪ ራስ ወዳዶች ሴራ ሊከሽፍ ቢበቃም ታላቅ ምሣሌ ጥሎ አለፈ። ከዚያም በመቀጠል በዓለም ገናናነትና ዝናን ያተረፈዉ የተማሪዎች እንቀስቃሴ እነዚህን ጭቆናዎች ለማስወገድ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሏል። መፈክሮቻቸዉም የሚከተሉትን ያጠቃልሉ ነበር፤

 

  • መሬት ላራሹ፤
  • የዜጎች እኩልነት
  • ትምህርት ለድሃ ልጆች ይዳረስ፤
  • ዳቦ ለተራቡት ወገኖች፤
  • የፈላጭ ቆራጭ ንጉሣዊ አገዛዝ ይወገድ፤ ወዘተ።

 

በሌላዉ በኩል ደግሞ የዉጪ መንግሥታት (በተለይ እንግሊዝ፤ ጣሊያን፤ ኢራቅ፤ ሶሪያና ሊብያ) ኢትዮጵያን ለማዳከምና ለመዉረር ሲሉ የግንጠላ ቡድኖችን በማቋቋምና በመርዳት ሽር ጉድ ይሉ ነበር (በተለይ በኤርትራ ጠቅላይ ግዛት/ክፍለ ሀገር በኩል)። ይሄም ብዙ መዘዝ ጥሎብን አለፈ። በመጨረሻም በተቀናጀ የሕዝብ ትግል የታላቁ ንጉሠ ነገሥት የአገዛዝ ዘመን አከተመ።

 

 

(ሐ)  በወታደራዊ አገዛዝ ዘመነ መንግሥት የተቃዋሚዎች ሚና

 

በተለይ በንጉሠ ነገሥቱ መጨረሻ አካባቢዎች ላይ የተማሪዎች እንቅስቃሴ በሁለት ላይ ተከፈለ። አንደኛዉ ክፍል መኢሶን የሚባለዉን ድርጅት የመሰረተ ሲሆን ሌላኛዉ ደግሞ ኢሕአፓን የመሰረተና የደገፈ ክፍል ነበር።

 

ምንም እንኳን በተለይ ባገር ቤት ዉስጥ ሲካሄድ የነበረዉ የተማሪዎች እንቅስቃሴ  በጣም ኃይለኛ ቢሆንም የንጉሠ ነገሥቱ አገዛዝ በሚያከትምበት ወቅት በፓርቲነት በደንብ የተደራጀ የፖሊቲካ ቡድን አልነበረም። በመሆኑም ለዉጡ በወታደሮች ሊጠለፍ በቃ። ዲሞክራሲ እንደገና ታፈነ፤ አምባገነንነት ነገሠ። በመሆኑም የተማሪዉ እንቅቃሴ እንደገና እያየለ መጣ። በመቀጠልም ከዝነኞቹ የተማሪዎች፤ መምህራን፤ ሠራተኞች፤ ወዘተ እንቅስቃሴዎች የፈለቀዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ቅልጥ ያለ ትግሉን አቀጣጠለ። መፈክሩና መልእክቱ የሚከተሉትን ያካትት ነበር፡

 

  • ወታደራዊ መንግሥት ለሕዝብ የሚበጅ የፖሊቲካ አመራር መስጠት አይችልም፤
  • ትምህርቱም ሆነ ልምዱ የአገር ድንበር መከላከል እንጂ ሀገር የማስተዳደር ችሎታ አይኖረዉም፤
  • በዓለም ታሪክ ያየነዉም ሃቅ ይሄዉ ነዉ፤
  • የሚያስፈልገን ሁሉንም ህብረተሰብ ያካተተ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት መመስረት በሚሉት መሰረተ ሃሳቦች ፀና።

 

የመኢሶን መስራቾች ግን ከዉጪ ሮጠዉ በመግባት ከደርግ መንግሥት ጋር ወገኑ። ምናልባት ከደርግ ጋር በማበር የኢሕአፓ አባላትን ጠራርገዉ ከጨረሱ በኋላ ሥልጣኑን ከወታደሮች እጅ በቀላሉ ለመንጠቅ የሚችሉ መስሏቸዉ ይሆናል። ታሪኩና ሂደቱም እጅግ በጣም የሚያሳዝን ነበር። በኔ እይታ ከነበሩት አሳዛኝ ታሪኮች ተምረን ስህተቶች ላለመድገም እንጂ ጉዳዩን እንደገና ማንሳቱ እጅግ ቀፋፊ መሆኑን በመዘንጋት አይደለም።

 

በዚህ መልክ መኢሶን ለወታደራዊ መንግሥት እጅግ በጣም ከፍተኛ ድጋፍ ሰጠ። በመንግሥት ሥር ያሉትን ሕዝባዊ ድርጅቶች ብቻ ሳይሆን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ተቆጣጠረ። በሂደቱም እያበጠ መጣ። በዚህ ደግሞ የቀኑት ግለሰቦች ወዝ ሊግና ባብዛኛዉም ወታደሮችን ያካተተ ሰደድ የሚባል ድርጅት ይመሰርቱና በወታደሩ መንግሥት ጎን ይቆማሉ።

 

እነዚህ ክፍሎች ከአረመኔዉና ጨቋኝ የወታደር አስተዳደር ጎን በመቆም ፋሺስታዊ ድርጊቶች (Torture) አካሄዱ፤

 

  • በወንዶች እስረኞች ብልት ላይ ጠርሙስ አንጠለጠሉ፤
  • በሴት እስረኞች ብልት ዉስጥ ዘነዘና/እንጨት ጨመሩ፤
  • ተገርፎ በተጠበሰ ሰዉነት ላይ በጫማቸዉ ቆሙ፤
  • ዐይን መጠንቆል፤ ጥፍር መንቀል፤
  • የወፌይላላ አሰቃቀል
  • የኢሕኣፓ ደጋፊ ወጣቶችን እየገደሉ በእናቶች ቤት ደጃፍ ለ3 ቀናት ያቆያሉ (‘ለመቀጣጫ’ እያሉ!!!!)፤
  • ቀይ ሽብር ይፋፋም፤ ዲሞን በዲሞትፎር፤ የኢህአፓ ሞቱ አወይ ማስደሰቱ እያሉ ተመትቶ ወድቆ ደሙ እየፈሰሰና ነፍሱ በመዉጣት ላይ በሚገኝ ወጣት ዙሪያ እየተሽከረከሩ ይጨፍሩ ነበር፤ እግዚኦ መሃረነ ክርስቶች፤ ከዚህ የበለጠ ምን ማፈሪያ ይገኛል?
  • እናቶች ልጆቻቸዉን ለመቅበር ‘የባከነዉን’ ጥይት ዋጋ እንዲከፍሉ ተገደዱ፤ በልጆቻቸዉ ሬሳ ላይም ቆመዉ እልል እንዲሉ ተጠየቁ፤ ለፀረአብዮተኛ ማዘን አይገባም ተባለ፤
  • እናቶች በልጆቻቸዉ ቀብር ላይ እንኳን አልቅሰዉ እንዳይቀብሩ ይከለከላሉ፤
  • ደም በጠርሙስ እየሞሉ መሪዉ በአብዮት አደባባይ ላይ እንዲያፈስ አደረጉ፤ አብዮት ልጇን ትበላለች እያለ ሽብር ነዛ። ይህቺ ናት አብዮት!!! መጨረሻዉን ዐይተናል።

 

ይሄንን ስል በኢሕአፓም በኩል አንዳንድ ስህተቶች እንደነበሩ መመስከር ያስፈልጋል (ለምሣሌ በወቅቱ ዐቅሙን በመመዘን ከአዲስ አበባና ታላላቅ ከተሞች በማፈግፈግ ብዙ ወጣቶችን ከደርግ የቀይ ሽብር እልቂት ማትረፍ ይችል ነበር) ፤ ፓርቲዉም ጥፋቶቹን ዐዉቆ ይቅርታ በመጠየቁ ምስጋናና ክብር ይገባዋል። በዚህ መልክ የእሕአፓ አባላትና ደጋፊዎች ክፉኛ ተመቱ። መኢሶንና ወዳጆቹ ከኢህአፓ ጋር በማበር ለሕዝባዊ መንግሥት ምስረታ ቢታገሉ ኖሮ ወታደሩ እዚያ ደረጃ ባልደረሰ ነበር። በኋላ ግን ደርግም ተመሳሳይ ተለጣፊዎችን በማስጠጋት መኢሶንን ሊበላ ቻለ፤ ቀጥሎም ማሌሪድና ወዝ ሊግ ተመሳሳይ ዕድል ገጠማቸዉ። እነርሱንም ጠራርጉ ከኢሕአፓና ከሌሎች ጠላቶቹ ጋር ባንድ ጉድጓድ ቀበራቸዉ። አበጠ፤ ልቡ ተነፋ፤ አብዮታዊ መሪ ተባለ። ከ17 ዓመታት እልቂት በኋላ የርሱም ተራ ደረሰና አገሪቷን ለወያኔ/ሸአብያ አስረክቦ ልጆቹንና ስንቁን ወድሮ ወደ ሃራሬ ፈረጠጠ፤ ዕዳዉ እነደገና ለጭቁን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆነ፤ እስከዛሬ ድረስ።

 

(መ)  በወያኔ/ኢህአደግ አገዛዝ የተቃዋሚዎች ሚና

 

እላይ እንደተገለጠዉ ከመግባታቸዉ በፊት በለንደን ላይ በተዘጋጀዉ የይስሙላ ‘የሰላም’ ጉባኤ ላይ የተሳተፉት መገንጠልን የሚያራምዱ የፖሊቲካ ኃይሎች ብቻ ነበሩ። ህብረ ብሔር ፓርቲዎች አልተፈለጉም። እነ ኦነግ ተከትለዉ ገብተዉ የሽግግሩን ቻርተር ፈርመዉ ተቀላቀሉ። ሕዝባችን ካንዱ አምባገነን ሥርዓት ወደሌላዉ ተሸጋገረ፤ ብዙ እልቂትና ችግሮች አስከተለ። የአገሪቷ ህልዉና ተናጋ፤ ርሃብ፤ መፈናቀል፤ ስደትና እንግልት ቀጠለ።

 

የሕዝቡ ብሶት እየተባባሰ በመምጣቱ ምክንያት ባገርም ሆነ በዉጪ ያሉት ወገኖች ተነቃንቀዉ አስፈሪ ትግል ጀመሩ። በ2003 ዓ/ም (በፈረንጆች አቆጣጠር) 15 የተቃዋሚ ፖሊቲካ ድርጅቶች ለ15 ቀናት በር ዘግተዉ ተወያይተዉ ተማምለዉ ህብረት ፈጠሩ። በዚህ ሂደት ኢሕአፓ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረጉ ታላቃ ምስጋና ይገባዋል። እነ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስና፤ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን የመሳሰሉ እጅግ በጣም የተከበሩ አባቶች ተሳትፈዉ ግሳጼ፤ ምክርና ቡራኬ ሰጧቸዉ። ይሄም ለሰላም ወዳድ ወገኖች በሙሉ ታላቅ ብሥራት ነበረ። የህብረቱም ሠነድ የሚከተሉትን ታላላቅ ስምምነቶች ያካተተ ነበር፤

 

  • ትግሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲሁን፤
  • በታቀደዉ አገራዊ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ የሚከተሉት አስፈላጊ ቅድመ-ሁኔታዎች መሟላታቸዉን ማረጋገጥ እንደሚኖርባቸዉ፤ የነፃ ምርጫ ቦርድ መመስረትና በያንዳንዱ ምርጫ ኬላ ላይ ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ገለልተኞች ታዛቢዎች መገኘት እንደሚኖርባቸዉ፤
  • ሁሉም የፖሊቲካ ድርጅቶች እኩል እንዲሳተፉ ሁኔታዎች መመቻቸት እንደሚኖርባቸዉ፤
  • እነዚህ ሁኔታዎች ካልተሟሉ ግን ከምርጫዉ መገለልና የሕዝብ ሰላማዊ አመፅ መቀስቀስና መምራት ግዳጅ መሆን እንዳለበት ተስማምተዉ ተፈራረሙ።

 

ዳሩ ግን ተደጋጋሚ ዕድላችን ሆነና ገና ዓመት ሳይሞላቸዉ አንዳነድ አባላት ህብረቱን ጥለዉ ወጡ። በህብረቱ ጎን ቅንጅትን ፈጠሩ። አሁንም ተስፋ ሳይቆረጥ ህብረትና ቅንጅት የጋራ ትግል ለማካሄድ ተስማሙ። እጅግ የሚያሳዝነዉ ግን በነዚህ ስምምነቶችና ቃልኪዳኖች ብዙም መግፋት አልተቻለም። ይባስ ብሎም ብዙ አባላት የነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ሥነ ሥርዓት ቅድመ ሁኔታዎች ገና ሳይሟሉ የሕዝባችንን ጥያቄ ንቀዉ ዘልለዉ በምርጫዉ ዉስጥ ተሳተፉ። ከዚያ በኋላ በግለሰቦቹና በፓርቲዎቻቸዉ ላይ የደረሰዉን ኣሳዛኝ ድርጊትና የሕዝባችንን ተደጋጋሚ ሰቆቃ ሁሉም ዜጋ የሚያዉቀዉ ሃቅ ነዉ። አንዳንድ ምሣሌዎች ለመጥቀስ ያህል፤

 

  • በወልቃይት፤ ራያ፤ ቤኒሻንጉል፤ ወዘተ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለዉ ችግር፤ ግዲያ፤ መፈናቀልና እንደጠላት መተያየት እጅግ በጣም ያሳዝናል፤
  • በሶማሊያ ክልል ዉስጥ በኦሮሞ ወገኖቻችን ላይ የደረሰዉ ግዲያና መፈናቀል እጅግ በጣም ያሳዝናል፤
  • በወሊሶ፤ ቡራዩ፤ ወዘተ በጉራጌና ሌሎች ወገኖቻችን ላይ የደረሰዉ ችግር እጅግ በጣም ይዘገንናል፤
  • ተመሳሳይ ችግሮች በተለያዩ ያገሪቷ ክፍሎችም እንዳሉ ይሰማሉ።

 

ለምን? ከዚህ በፊት በአማራ፤ ትግራይ፤ ኦሮሞ፤ ወዘተ ጭቁን ወገኖቻችን መከከል ልዩነትና ጥላቻ አልነበረም። በነዚህ ሕዝብ መካከል ጎሣን ሆነ ሃይማኖትን በተመለከተ አንድም መጠላላትና አድሎ አልነበረም። እላይ እንደተጠቀሰዉ ሁሉም ዜጎች በችጋርና በመከራ  እኩል የተጠበሱ ናቸዉ። በሰሜን ሸዋ ደበሎ  ለብሶ እየተጠበሰ አፈርና ድንጋይ እየጫረ የሚለፋዉን አማራ በኮንሶና ተመሳሳይ ቦታዎች ከሚማቅቁት ዜጎቻችን በምን መንገድ መለየት ይቻላል? በቀድሞ ገዥዎቻችን የተረሱትን እንደ ጎጃምና ኢሉባቦር የመሰሉትን ጭቁን ወገኖቻችን እንዴት መለየት እንችላለን? ጥቂት ምሣሌዎች ለመሰንዘር ያህል ነዉ እንጂ ተመሳሳይ ችግሮች በጠቅላላዉ የአገራችን ክፍሎች እንደነበሩና አሁንም እንዳሉ ግልፅ ነዉ። ወገኖች፤ በደንብ እናስተዉል። ስለአሁኑም ሆነ ስለሚቀጥሉት ትዉልዶች ፅጣ ፈንታ ማሰብና መጨነቅ ይኖርብናል፤ ራስ ወዳዶችና አፍራሾች ሆነን ሴይጣንን ከምንመግብና ወገኖቻችንን ከምናጠፋ በፍቅርና በአንድነት ብንቆም ይበጃል ብዬ አምናለሁ። ሕይወት አጭር መሆኗን አንዘንጋ።

 

ቅድመ አያቶቻችን፤ አያቶቻችን፤ አባቶቻችንና እናቶቻችን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በህብረት ከዉጪ ወራሪዎችና ከዉስጥ ጨቋኞች ሲከላከሉን ዉድ ሕይወታቸዉን ገብረዋል፤ ደማቸዉን አፍስሰዋል፤ አጥንታቸዉን ከስክሰዋል።

 

አገር ወዳድ ዕድሜ ልኩን ለዉድ አገር ይቆማል፤ ስላሁኑና ስለሚቀጥሉት ትዉልዶች ደህንነት ይጨነቃል። የነቃና አገር ወዳድ ወጣት ዘርና ሃይማኖት አይለይም፤ የግል ጥቅም አያስቀድምም፤ በህብረት ይቆማል፤ ይፀልያል፤ ይታገላል፤ አስፈላጊዉን መስዋእትነትም አብሮ ይከፍላል። አገር እናት ናት። እንደ እናት ደግሞ የሚወደድ፤ የሚፈቀርና የሚከበር አይኖርም።

 

ከፋፋይ ቡድኖችና ግለሰቦች የሚረጩትን መርዞች አዉቆ ማርከስ ያስፈልጋል። አገራችን ኢትዮጵያ ናት። ዋና ከተማችን አዲስ አበባ እንደሆነች የማያዉቅ ሰዉ የለም። አሁን ትንሽ የህዝባችንን ተመልሶ መቀራረብ ያልፈለገ ሴይጣን ሕዝቡን ለመከፋፈልና ለማፋጀት ብዙ ደባ ሊጭር እንደሚችል በመገንዘብ የዚያ ሰለባ ላለመሆን ብርቱ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል። ስለዚህ ስለዉድ አገራችን አንድነትና ሰላም ሁላችንም የሚቻለንን አስተዋጽኦ ሁሉ እንድናደርግ በፈጣሪያችን ስም አደራ እላችኋለሁ። ለክልል ሕዝብ ኃይማኖት የሚመርጡም ግለሰቦች ከከፋፋይ ድርጊቶቻቸዉ እንዲቆጠቡ እለምናቸዋለሁ፤ ወደ ህሊናቸዉ ቢመለሱ ይሻላቸዋል። እላይ እነደጠቀስኩት ኃይማኖት የግል መሆኑን እነድናስተምራቸዉ ይፈልጋሉ? በኦሮሞ ሕዝባችን መሃል ብዙ ሚሊዮን ክርስቲያኖችና የሌላም አምልኮት ተከታዮች እነዳሉ ሳያዉቅ ቀርቶ ነዉ ኦሮሞ ሁሉ እስላም ነዉ እያለ አለሃፍረት የሚጮሄዉ?። ይሄ እስልምናን ለማስፋፋትና ኦርቶዶክስን ለማጥፋት የማይተኙልን የዉጪ ኃይሎች ለማስደሰት እንደሆነ እንጂ ሃቅነት የጎደለዉ አሳዛኝ አነጋገር ነዉ። ወገንን በዘርና በኃይማኖት በመከፋፈልና በማጫረስ የሚገኝ ጥቅም ባፍንጫ ቢወጣ ይሻላል።

 

፬ኛ/  የትዉልዶች ሚና

 

የትዉልዶችን ሚና ባንድ ላይ መጨፍለቅና መኮነን ኃጢአት ነዉ፤ ታሪክንም ማፋለስ ይሆናል። ስለዚህ የሚጠበቅብን ትልቁ ኃላፊነት የምናዉቀዉን እዉነተኛ ታሪክ ማስተላለፍና ከበጎዉም ከመጥፎዉም ተምረን ለአገራችን ሰላምና እድገት ማመቻቸት ነዉ ብዬ አምናለሁ።

 

እላይ እንደጠቀስኩት በተለይ በ60ዎቹና በ70ዎቹ አካባቢ የተነሱት የወጣቶች እንቅቃሴዎች በቂ ምክንያቶች ነበሯቸዉ። ኢትዮጵያ ያፈራቻቸዉ እጅግ በጣም ብሩህ የነበሩ ወጣቶች፤ መምህራን፤ መሃንዲሶች፤ ነርሶች፤ ዶክተሮች፤ ወዘተ ለዲሞክራሲና ለእኩልነት ሲሉ የከፈሉትን የሕይወት መስዋዕትነት ታሪክ ሲያስታዉስ ይኖራል። ዛሬ ወደኋላ እየተመለከቱ እነዚያ ተማሪዎች ተሳስተዋል፤ እግዚአብሔርን ረሱ፤ ፀሐዩን ንጉሥ መንካት አልነበረባቸዉም፤ የባሰዉን አመጡብን፤ ወዘተ እያሉ የሚኮንኗቸዉ ወገኖች ሲያጋጥሙኝ እጅግ በጣም አድርጌ አዝናለሁኝ። እላይ እንደተጠቀሰዉ በትግሎቹ ረጅም ሂደቶች ዉስጥ አንዳንድ ከባድ ስህተቶች ተሠርተዋል (በተለይ ከወታደራዊ ፋሺስታዊ መንግሥት ጋር ባበሩትና በአንጃዎች አካባቢ)። በሃይማኖትና በብሄር ላይ ግን ሁን ብሎ የዘመተ ትዉልድ አልነበረም። አብዛኞቹ በቤተክርስቲያን ወይም በመስጊድ ዉስጥ ተወልደዉ በመልካም ሥነ ምግባር ያደጉ፤ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያልተለያቸዉ፤ ከራሳቸዉ በላይ ለአገራቸዉና ለህዝባቸዉ የሚያስቡና የሚቆረቆሩ ወርቅዬና ብርቅዬ ልጆች ነበሩ፤ ከወንዱም ከሴቱም። ስለዚህ ታሪክ የሚገመገመዉ በወቅቱ በነበረዉ ንቃተ ሕሊና እና ተጨባጭ ሁኔታ ላይ በመመርኮዝ በተወሰደዉ የትግል እንቅስቃሴ ታሪክ እንጂ በዛሬዉ በተንሸዋረረ መነጽር መሆን የለበትም ብዬ አምናለሁ። ያለፈዉን እንደታሪክ እያየን፤ ከመልካም ጎኖቹ መልካም ትምህርቶች እየቀሰምን ዛሬ የተሻለዉን ወይንም ቢያንስ እኩል አስተዋጽኦ ከፍሎ አገርን ከጥፋት ማዳን እንጂ  ያለፈዉን ሁሉ እኩል እየኮነኑ ቁጭ ብሎ ማላዘንን እግዚአብሔር አይወደዉም፤ ለወገንም ለታሪክም አይበጅም። ትላንትን ለዚያዉም በተንሸዋረረ መነፅር እያዩ የትዉልዱን አባላት  እንዳሉ ለመኮነን መሞከር ከማህበረሰብ ሣይንስም አንፃር ትልቅ ስህተት ይሆናል። የዚያ ትዉልድ ተማሪዎች እኮ ኢትዮጵያ አለባት ብለዉ ላዩትና ላመኑበት ችግር መፍትሄ ይሆናል ብለዉ ባመኑበት አቋም ፀንተዉ ነበር የሕይወት ዋጋ የከፈሉት!

 

፭ኛ/  መደምደሚያ

 

አሁንም ካለፉት ስህተቶችና ጥፋቶች መማር አንችልም ወይ? ተቃዋሚ የፖሊቲካ ድርጅቶች ነን የሚሉትና በተግባር ግን የጭቆናን ዘመን የሚያራዝሙ በሙሉ ካለፉት ስህተቶች ገና ሊማሩ አልቻሉም፤ ‘ድር ቢያብር አንበሳ ያስር’ የተባለዉን ቅዱስ አሳብ ደጋግመዉ መናቃቸዉ ያስተዛዝባል። ቁርጥ ያለ አቋም ያስፈልጋል፤ ከዛፍ ዛፍ መዝለል ዬትም አያደርስም። ለጊዜያዊ ጥቅማ ጥቅሞች በርካሽ መገዛትና አገርን መሸጥ በሰማይም በምድርም ያስጠይቃል። ቀኑ ሲደርስ ራቆታችንን ወደምድር እነደመጣን ሁሉ ራቆታችንን ወደዚያዉ እነደምንመለስ አንርሳ!!!

 

ምርጫዉ ለሁላችንም ክፍት ነዉ፤

 

  • ህብረት ማጠንከር የግድ ነዉ። እላይ ከተገለፀዉ የ2003 ዓ/ም የህብረት ምሥረታ፤ ከፍተኛ አስተዋጽኦና አለኝታነት ብዙ መማር ይኖርብናል። ካለዚያ አገራችንን ለማዳከም ወይ ለማጥፋት ለሚፈልጉት ጠላቶች መጋለቢያ ቦታ ሆነን እንቀራለን። በዚያ ደግሞ የሚደሰት ማንም ዜጋ ይኖራል ብዬ መገመት አልችልም። ወደ 2003 ዓ/ም ስምምነት ብንመለስ ይሻላል። ሁሉም ተቃዋሚ ድርጅቶች ተቀራርበዉ በዲሞክራሲ ግንባታ ላይ መተባበር ይኖርባቸዋል። እንዲያዉ ቁጭ ብለን ወያኔ/ኢሕአደግ፤ አሜሪካና ሌሎች የዉጪ መንግሥታት የሚቀጥለዉን መንግሥት ያመቻቹልናል ብሎ መጠበቅ ‘ዉሃ ቅዳ ዉሃ መልስ’ ብቻ ነዉ የሚሆነዉ። ካሁንም ወዲያ ቁጭ ብሉ በተደጋጋሚ የሚታለል ዜጋ አይኖርም።
  • የግንጠላ ዓላማን የሚያራምዱ ጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች ኢትዮጵያ መፍረስ አንዳለባት ሲሰብኩ ይሰማሉ። በተለይ አማራ በተባለዉ ሕዝባችን ላይ የዉሸት ታሪክ ሲነዙ የሚሰሙ አሉ። በጣም የምወዳቸዉና የማከብራቸዉ ዶ/ር መረራ ጉዲና በዶክቶሬት ጥናት ምርምራቸዉ ላይ በመመርኮዝ የደረሱት መጽሐፍ ዉስጥ አንድ ጥሩ ጥቅስ አስታዉሳለሁ፤ ይሄን ይመስላል፤ መገንጠልን የሚያራምዱ ብዙ ድርጅቶች የሚስቱት ሃቅ ቢኖር ለመሬት ላራሹና ለኢትዮጵያ ሕዝብ እኩልነት የአማራን ወጣት ያህል እጅግ በጣም ከፍተኛ መስዋእትነት የከፈለ የለም ነበር ያሉት።
  • በዚህም ላይ ደግሞ የአፍሪቃን ምድር መልሰዉ ሊቀራመቱ የሚሹና በተለይ ለአትዮጵያ ጥፋት የማይተኙ የዉጪ ታሪካዊ ጠላቶች የግንጠላን ዓላማ ከማራመድና ከመደገፍም የሚቆጠቡ አይመስሉም። ሆኖም ግን የኢትዮጵያን የቆዳ ስፋትና የህዝቧን ስብጥር ለተመለከተ አስተዋይ ይሄ የሚያዋጣ አማራጭ ሊሆን ከቶ እንደማይችል ያዉቃል። ቢፈልጉም እንኳን የእያንዳንዱን ብሄር ድንበር ለመከለል በዓለም ላይ የሚገኙ የካርታ ልሂቃን ቢሰበሰቡ የሚቻላቸዉ ነገር አይሆንም። ከሺህዎቹ ዓመታት ጀምሮ እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ክፍል ስንቱን ተቀብሎ ሲያስተናግድ ኖሯል፤ ሁሉም ነገድ በሁሉም የአገሪቷ ክፍል ሰፍሮ ይገኛል፤ በደም፤ በጋብቻ፤ በወገንነት ተሳስሮ ለብዙ ዘመናት ኖሯል። አሁንም እያንዳንዱ ዜጋ ፊትም እንደነበረዉ እየተዘዋወረ የመኖር፤ የመሥራትና የመነገድ ሙሉ መብቱ መከበር ኢኖርበታል። አገሪቷን ብዙ ቦታ በጣጥሶ በድንበር ግጭት ጭቁኑ ሕዝብ እርስ በርሱ የሚጨራረስበት ምክንያት መፈጠር የለበትም። የተገነባዉን ከማፍረስ ይልቅ ያለዉን በመጠገን በእኩልነት፤ በሰላም፤ በፍቅርና በብልፅግና አብሮ መራመዱ እጅግ በጣም አስፈላጊ መሆኑ ይታየኛል። በቅርብ እንኳን በኤርትራ ሕዝብ ላይ ያደረሱትን ዉድቀት ማስተዋል ይገባል።
  • መፍትሔዉ በብሄር፤ በጎሣ ወይም በሃይማኖት ሳንከፋፈል ንጹሕ ዲሞክራሲን መገንባት ብቻ ነዉ። የዲሞክራሲ ግንባታ ደግሞ የወሬ ጋጋታ ሳይሆን በተግባር የሚታይ መሆን አለበት። ዲሞክራሲ ዲሞክራሲ እያሉ ከህዝብ መሸሽ አይቻልም፤ የለዉጡ ባለቤት ህዝቡ ራሱ መሆን አለበትና። ህዝቡ ራሱ የፈለገዉን የመምረጥና የማስወገድ መብት ሳይኖረዉ የዲሞክራሲ እንቅስቃሴ አለ ብሎ መገመት ይቻላል? አይቻልም፤ ራስን ለማታለል ወይንም ህዝቡን ለማጭበረበር ካልሆነ በስተቀር። በአገር ዉስጥ ያለዉ ህዝባችን ሙሉ መብቱ መጠበቅ አለበት። በዓለም እንደአሸዋ የተበተነዉ ወገን ተመልሶ በኩራት እየኖረ ሕዝባችንን እንዲያገለግል ጥርጊያ መንገድ ማበጀት ይኖርብናል። እግዚአብሔር የሰጠንን ሰፊ የተፈጥሮ ኃብት ለወገኖቻችን ማብቃትና ርሃብን፤ ጥማትን፤ እርዛትን፤ ስደትንና እንግልትን ለማስወገድ ቆርጦ መነሳት ያስፈልጋል። በልመናና በዉጪ እርዳታ ተማምኖ ሀገር ማስተዳደር አይቻልም፤ የሚያስፈልገን ዘለቄታ የሚኖረዉ የሀገር ኢኮኖሚ እድገት መዘርጋት ነዉ። ለዚያ ደግሞ ዕድሉን ተነፈግን እንጂ ዕዉቀቱ አለን፤ የረባ ቴክኖሎጂዉንም ፈጥረናል። ከፍተኛ ትምህርትና ረዥም የዐለምአቀፍ የሥራ ልምዶች ያካበቱ ብዙ ሺህ ወገኖቻችን በዉጭ አገራት ይገኛሉ። ተመልሰዉ የሀገራቸዉን ኢኮኖሚ እንዲገነቡ ማመቻቸት ይገባል። ቁርጥ ያለዉ የዲሞክራሲና ራስን የመቻል አማራጭ ይሄን ይመስላል፤ በኔ ቅን እይታ።
  • ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ሀቁን በይበልጥ ለማስጨበጥ ከነፃ ዜና አዉታሮችም ብዙ ይጠበቅባቸዋል። ሰዉ ይሞታል፤ ይገደላል፤ ታሪክ ግን አይሞትም፤ መረሳትም የለበትም። ከዬት እንደመጣንና አሁን ያለንበትን ካላወቅን ወዴት እንደምናመራ በቅጡ ልንገነዘብ አይቻለንም። ከጥፋት ይሰዉረን።
  • ፈጣሪያችን ሰላሙን ይስጠን፤ ፍቅር ያቸንፋል፤ ሕዝባችንና ዉድ ሀገራችንን ይጠብቅልን።