ቄሮ ለለውጡ ጉልህ ድርሻ ነበረው የሚለው ላይ ሳይሆን ጥያቄው የትኛው ቄሮ ነው ነው፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ ከጅምሩ ለብዙዎቻችን ግልጽ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎች ነበሩ፡፡ በኋላ ለማ መጥቶ የነበሩትን እንቅስቃሴዎች ሀገራዊ ይዘት እንዲኖራቸውና ቄሮን ወደ ኢትዮጵያ ተኮር እንቅስቃሴ ከመምራቱ በፊት በእነ ጀዋር የሚመራው ቄሮ አሁን ላይ ኦነግን ከተከተለው ቄሮ ጋር ተመሳሳይነት ያለው እንደነበር ልናስተባብለው የምንችለው ነገር አደለም፡፡  የእነ ጀዋር ዋና አላማ የነበረው ኢትዮጵያን የመበታተን ነበር፡፡ ይሄን ደግሞ በግልጽ ሲናገሩት የነበረ እውነት እንጂ እኔ ያልኩት አደለም፡፡ በመሆኑም የኦሮሞን ወጣት ለአላማቸው ይጠቀሙበትና ለወያኔም ትልቅ ጉልበት ሆነውት እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ቢያንስ የተወሰነውን ቄሮ ከእነጀዋር ነጥቆ በኢትዮጵያዊነት ቅኝት ለማ መምራት ሲጀምር ብዙ ስኬት በመታየቱ በእርግጥም ብዙ የእነጀዋር ቄሮዎች ሳይቀሩ ለማን ተቀላቀሉ፡፡ ያኔ የወያኔ ሕልም እልም አለ፡፡ ይሄ ነበር ወያኔን የናደው ቄሮ፡፡ ይሄ ለማ የመራው ቄሮን ሊያቆመው የቻለ አልነበረም፡፡ ምክነያት ከተባለ ቅኝቱ ኢትዮጵያዊነት ላይ መሠረት ማድረጉ ነበር፡፡ የለማን ቄሮ የአማራው ፋኖ ይሰማዋል፣ የጉራጌው ዘርማ ይሰማዋል፡፡ አስታውሱ እንዴት ያለ አገራዊ ቅንጅት ተፈጥሮ እንደነበር፡፡ በተለይ ወያኔ መቀበሪያዬ ብላ ከጅምሩ የሰጋችው የቄሮና ፋኖ(ኦሮሞና አማራ) በአንድ ዓላማ መሠለፋቸው በራሱ የፈጠረባት ፍርሀት ወያኔን ከሥሯ ናዳት፡፡ ታንክ፣ መድፍ ወይም አንዳች የተለየ ጦር አልነበረም፡፡ ወያኔን የናደው በለማ መገርሳ የተቀናጀው አገር አቀፋዊ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ለብሶ የተንቀሳቀሰው ቄሮና ተባባሪዎቹ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ነው!!!!! ከዚህ በታች ሆነው የመጡ እንቅስቃሴዎች በዛች ምድር ጥፋት ያደርሱ ከሆነ እንጂ ለውጥ አያመጡም፡፡ ለማ ብዜ ቄሮን ወደራሱ የኢትዮጵያዊነት ስሜትና ወኔ እያስታጠቀ ማስገባት ቢችልም እነጀዋር ሥር የቆየ ቄሮ መኖሩን አንክድም፡፡ አሁን ላይ በጅምላው ቄሮ እየተባለ ለብዙዎች ጥያቄ የሚፈጥር ሆኗል፡፡ ልዩነቱ እዚህ ጋር ነው፡፡

በዚህ ሁኔታ ለውጥ ይመጣና በእርግጥም እነለማም ሙሉውን የአገሪቱን ኃይል መቆጣጠር ሲጀምሩ ወያኔና እነጀዋር እብድ ሆኑ፡፡ ግን ምንም በሚያደርጉበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ወያኔ እነጀዋር ያሉበት የኦነግን ሴሎች መጠቀም ዋና ስልት እንደሆነ አመነችበት፡፡ ምክነያቱም ከአሁን በኋላ በራሷ ሥም መንቀሳቀሱ የሚያዋጣ አደለምና በኦሮሞነት ሥም የሚነግዱትን በተቻላት መጠን ያላትን ንዋይ እየሰጠች ማሰማራት ጀመረች፡፡ እነጀዋር በእነ አብይ ላይ የኦሮሞን ሕዝብ ጥርጣሬ ያመጣልናል ያሉትን ሁሉ ዘመቻ አደረጉ፡፡ በእርግጥም ይሄ የወያኔ ስልት ብዙ ሰርቷል፡፡ ከለማ ጋር ተቀላቅሎ ትልቁን የለውጥ ድርሻ የነበረው የለማም ቄሮ ጥርጣሬ ውስጥ መግባትና ወደኋላ እያፈገፈገ የእነ የእነጀዋር ቄሮ መቀላቀል ጀመረ፡፡ ይህ ሲሆን በውስጥ ኦነጋውያን ብዙ ሌላ ሥራ ሲሰሩ ነበር፡፡ ኦነጋውያን ማለት በይፋ ኦነግ ነን ያሉትን ብቻ ሳይሆን በሌላ የፖለቲካ ቡድን ሥም የሚንቀሳቀሱ ብዙ ሌሎችን ጨምሮ ነው፡፡  እንደ እውነቱ አብይ የድርጅት መሪ ሆኖ ከተመረጠበት እስከ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆኖ እስከታወጀበት ቀን ብዙ የለማ ቄሮ በእነጀዋር የጥርጣሬ ፕሮፓጋንዳ ከተሳፈረበትና ራሱ ከአመጣው ለውጥ ወርዶ ወደ ነበረበት ተመለሰ፡፡ አልቀረምም አብይ የጠ/ሚኒስቴርነቱን ሥልጣን ያዘ በዛው ቀን አብይ በአደረገው ሲመተ ንግግር ብዙ ኢትዮጵያውያን ከመጠን በላይ ሲደሰቱ በዋናነት በወያኔ የሚመራው የእነ ጀዋርና ኦነጋውያን ቡድን ከመቼውም በላይ አብድ ሆነ፡፡ በግልጽ የኦሮሞ ሕዝብ ነጻነቱን ተቀማ አይነት ፕሮፓጋንዳ መንዛት ጀመሩ፡፡ ከጅምሩም ኢትዮጵያን ማፈራረስ ስለነበር አላማቸው የአብይ ከተጠበቀው በላይ ኢትዮጵያዊነትን ልዩ ትኩረት አድርጎ መናገር የሞት ያህል ነበር ወያኔ በበላይ ጠባቂነት የሚመራው የእነጀዋርና ኦነጋውያን እንቅስቃሴ፡፡ ከዚህ በኋላ ያለ የሌለ ጉልበት መጠቀም ጀመሩ በእርግጥም አብይ ሥልጣን መያዙ ሲረጋገጥ ኦሮሚያ አፈገፈገ፡፡ አሳዛኝ ነበር፡፡ እንዴት? እነ ለማ ብዙ ሞከሩ ግን ቀላል አልሆነም፡፡ ኦነግና ወያኔ ከጅምሩ በነበራቸው ወል ይሄ አጋጣሚ ከአመለጣቸው እስከወዲያኛው ዓላማቸው እንደማይሳካ ግልጽ ነበርና ለዚህ ደግሞ 27 ዓመት ከኢትዮጵያዊነት እንዲወጣና የአባቶቹን ታሪክና ወኔ ረስቶ የእነሱ መጠቀሚያ እንዲሆን በውሸት ታሪክ የበከሉትን ቄሮ መጠቀም የመጨረሻ አማራጫቸው ነበር፡፡ የሆነውም ይሄ ነው፡፡ አነሰም በዛም ሁሉም ክልሎች በተገኛው ለውጥ ተስፋ ሲሰንቁ ለኦሮሚያ ጭራሽ ጨለማ ሆኖ ታየ፡፡

በእርግጥ እነ አብይ ስህተት ሰርተዋል፡፡ ለማም፡፡ በመጀመሪያ ሕዝባቸውን የአሰቡትን አላማና ግብ ግልጽ አድርገው ወደራሳቸው መሠረት ያለው ግንዛቤ ላይ ማስጨበጥ ሲገባቸው ጭራሽ የሴራው ዋና የሆኑትን በመለማመጥና ሕዝቡን ለእነሱ አደራ አይነት ነገር በመሥጠት አሁን እየሆነ ላለው አድርገውታል፡፡ ለ27 ዓመት ኦሮሞን ጨምሩ ሲያርድና ሲያሳርድ የኖረው የትግሬው ወያኔ ብቻ እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ ከወያኔ ትግሬ ቀጥሎ የኦሮሞ ኦነጋውያን የ27ዓመቱ  የግፍ ዘመን ዋና ተጠቃሚ እንደነበሩ እኮ እናውቃለን፡፡ ምንም ያልሆን ተራ ዛሬ ዶባይና ኢንዶኔዥያ ባሊ የሚዝናናው ማን ነው? ከትግሬ ወያኔ ቀጥሎ ማን ነው? በ27ዓመቱ የግፍ ዘመን ከትግሬ ወያኔ በአላነሰ ተጠቃሚ የነበረው ማን ነው? ሥልጣንና ወሳኝ ቦታ ባይሰጠውም በገንዘብ የፈለገውን ያገኝ የነበረው ማን ነበር? ለዛም ነው እኮ ኦሮሞ ጠ/ሚኒስቴር ሲሆን እስከመግደል ሙከራ በዋናነት የተንቀሳቀሰውን ቡድን ማንነት ያየንው፡፡ ወያኔ በጌትነት እየቀለበቸው የአገርና ሕዝብ ዋና ጠላት የሆነው ማን ነበር?   ሁሏም እንዳቅሟ ድርሻዋን አግኝታለች፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ እንዲሆንለት የሚያስፈልገው በአንድ ወቅት በሽብርተኝነት ተፈርጀው የነበሩ ግለሰቦችና ቡድንኖች ውስጥ ለስልት ሽብርተኛ የተባሉ እንደነበሩ እወቁ፡፡ ልክ ሰላዮችን እስር ቤት አስገብታ አብራ ከሌላው ጋር እንደምታስረው ማለት ነው፡፡ ይሄ ስልት ነው ዛሬም ድረስ ሕዝብ የጠላቶች ሀሳብ ተገዥ እየሆነ የሚምታታበት፡፡

ቀሮን በተመለከት በለውጡ ጉልህ ሚና የነበረው ለማ የመራው ቄሮ እንጂ ሌላው ቄሮ እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ የለማው ቄሮ በዋናነት ደግሞ የነበረው የሸዋው ቄሮ ነበር፡፡ እስኪ ከሸዋ ውጭ የት ጋር የነበረ ቄሮ ነበር ወያኔን ጎሮሮያዛት፡፡ የሀረሩ ቄሮ በዓላማ ቢዛባበትም ድርሻ ነበረው፡፡ ለመሆኑ በዚያ ቀውጢ ወቅት የወለጋው ቄሮ (ከነበረ) ምን ነበር ድርሻው? አስታውሱ ምን ነበር? ምንም ብዬ ባልፈው ነው የሚሻለው፡፡ በኋላ ደግሞ ቄሮ የተባለውን ሥም በብዙዎች እይታ ማን ነበር እስከሚባል ብዙ ሴራዎች ሲሰራ የነበረው የትኛው ቄሮ ነበር? የለማ ቀሮ እንጂ እነጀዋርና ሌሎች የኦነግ ቡድኖች ሲመሩት የነበረው ቄሮ ከጅምሩም ዓላማው ኢትዮጵያን ማፈራረስ ነበር፡፡ ዛሬ ብዙ የለማ ቄሮ የምርም በተነዛበት ውዥንብር ወደ ኋላ አፈግፍጎ ሊሆን ይችላል፡፡ እንግዲህ የለውጡን ቄሮ ከአጥፊው ቄሮ እያምታታን በጅምላ አንውቀስ፣ አናሞግስ!!

የወያኔ ቅጥሮች እነ ጀዋር አገር ቤት ከርመው ሰሞኑን አዲስ ዘመቻ ጀምረዋል፡፡ የልብ ልብ ተሰምቷቸውም እየደነፉ ነው፡፡ የወያኔው ቅጥር ጀዋርን ሠላም የመጣል በሚል ይሁን ወይም በምን ምክነያት በየቦታው እንደፈለገው ሲቦርቅ ማንም ጭራሽ በመንግስት ገንዘብ ተመድቦለት ነበር፡፡ ሐረር የሄደ ጊዜ ቆይቶ ምን ሊከተል እንደሚችል ተናግሬ ነበር፡፡ ብዙም ሳይቆይ በእሱ እዝ ሥር ያለውን ቄሮ የሐረርን ሕዝብ ውያ እንዳያገኝ አድርጎ እንደመጣ አየን፡፡ ባሌም ሄዶ ምን ሲሰራ እንደነበር ሰምተናል፡፡ እድሜ ጸጋ ነው! ሽምግልና ሲቀደስ እውነትን በመናገር የተጣሉን ያስታርቃል፡፡ ጀዋርን ባሌ ላይ አብሮት የነበሩት ዶ/ር ገመቺስ የተባሉ ግለሰብ የተናገሩት ያየ በሽምግልና ሊያዝን ይችላል፡፡ ገመቺስ በውሸት ወሬ ሕዝብ ከሕዝብ አብሮ እንዳይኖር መርዝ ሲረጩ ነበር፡፡ በኋላ በአቶ ቡልቻ በሰማንው የሽምግልና አንደበት ብንጽናናም በገመችስ እጅግ አዝነናል! እንግዲህ እንዲህ በአለ የአገር የመበተንና ሕዝብን ከሕዝብ የማጋጨት ዘመቻ በይፋ እንዲያስፋፉ እድል የሚሰጣቸው እያሉ ሠላም ጠፋ ብሎ መናገር አይቻልም፡፡ ቄሮ የለውጥ አምጪውና ቄሮ የአገር በታኙ ሚና ባልተለየበት ቄሮ ነው ለውጥ ያመጣው ቄሮ ነው አገር የሚበጠብጠው ማለት አደለም፡፡ እርግጥ ነው የቄሮ ለውጥ አምጭው ሁኔታ አሁን ላይ ተመናምኖ ቄሮ አገር አጥፊው ገዝፎ ነው የሚታየው፡፡ የለማንና የእነ ጀዋርን ቄሮ ሳይለዩ በድፍኑ ቄሮ በሚል መደነገሪያ ነው ነገሮች እየጠፉ ያሉት፡፡ በአነድ ተሰልፎ ደፋርና ፈሪ ውጤቱ የእድል ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡

እነለማ አሁን ግልጽ አቋም ይዘው ሕዝባቸውን ያለውን እውነት እንዲረዳ ማድረግ አለባቸው፡፡ ብዙ እውነቶች እነሱ ጋር አለ ግን ለውሸት ትርክቶች እያቅማሙ ሕዝብን ለጠላት አፍ መዳረግ ስህተት ነው፡፡ አገር የገነቡት የኦሮሞ አባቶች ናቸው ስንል ውሸት አደለም!! አገር ጠብቀው ለዚህ ያደረሱት አሁንም በዋናነት የኦሮሞ አባቶች ናቸው ስንል ልባችንን ሞልተን ነው!! የሚኒሊክን ጨምሮ የዛሬ 27 ዓመት የወያኔው ወሮበላ ቡድን መሪ እስከሆነበት ድረስ አገሪቱ በዋናነት ስትመራ የነበረው በኦሮሞ ነበር ስንል አንዳች አልተሳሳትንም! ዳሩ ግን ኦሮሞስ ማን ነው?! አማራስ ማን ነው? ይህን ዛሬ የደረስንበት አስተሳሰብ ስለሆነ እንጂ እነዛ አባቶች እኮ ኢትዮጵያዊነታቸውን መሪ ያደረጉበት መሠረታቸውን ስለሚያውቁ ነበር፡፡ ሁሉም ሕዝብ ደም ውስጥ ተሰግስገው አንድ ሕዝብ አንድ አገር ፈጥረው ኖረዋል፡፡ አንድ ሕዝብ ማለት አንድ አይነት አደለም፡፡ ከአንድ የተወለዱም ይለያያሉ ግን በስነልቦናው ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ሕዝብን ፈጥረዋል፡፡ በስነልቦናም ብቻ አደለም በተለይ መሪ የሆኖት ዋናዎቹ በደም ጭምር ሕዝብ እንዲተሳሰር ጉልሕ ሚና አበርክተዋል፡፡ ያም በመሆኑ ነበር የተበታተነን ሕዝብ አንድ ማረግ የቻሉት፡፡ ዛሬ ወሮበላ አንድ የሆነውን ሕዝብ ይበትናል፡፡ ሕዝቤ ሆይ አትሸወድ፡፡ ለዘመናት ስትታረድ እያረዱህና እያሳረዱህ አንተን እየገበሩ አነሱ ኑሮአቸውን የመሠረቱ ናቸው ዛሬም እኔ ነኝ ያንተ ነጻ አውጭ የሚሉህ፡፡ ማንም ያልሰጠህንና በራስህ ያመጣህውን ነጻነት መልሰህ ለገዳዮችህ አትስጥ፡፡ እውነቱን መናገር ስላለብኝ ነው፡፡ ኦነግ የኦሮሞን ሕዝብ ብዙ ጊዜ ሸውዶታል፡፡ አሁንም እየሸወደው ነው፡፡ ኦነግ የሚባል ቡድን ከተቋቋመ ዛሬ 50 ዓመት ሊጠጋው ነው፡፡ በዚህ 50 ዓመት ውስጥ በተለይም ደግሞ በአለፉት 27 ዓመት የሆነው የኦሮሞም ሆነ የሌሎች መከራ መቼም ሆኖ አይውቅም! ኦሮሞ ኦነግን ስለወደደ እውነቱ አይቀየርም፡፡ ኦነግ የኢትዮጵያ ጠላት ነው! አረመኔም ነው! በምስራቅ በኩል በአብዲ ኢሌ እየተሳበበ የነበረው የኦሮሞ እልቂት ኦነግ በዋናነት የነበረበት ነበር፡፡ በኋላም ወደ ምዕራብ ዞረ፡፡ ኢትዮጵያ ሠላም ከሆነች ብዙዎች በወንጀል እንደሚጠየቁ ስለሚያውቁ ቢያንስ ብጥብጥ ፈጥሮ እድሜ መግፋት አማራጫቸው ነው፡፡ ከቻሉ ግን የነበረውን ግፍ መመለስ፡፡  እንግዲህ ከጅምሩ ስንናገር የነበረው ነገር ነው እያደር በእውን እየታየ ያለው፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል!

ስለሰሞኑ የወያኔ ድልቦች መታሰር ምንም ማለት አልፈልግም፡፡ ሲጀምር ዘግይቷል፡፡ ያም ሆነኖ አሁንም ብዙ ችግር አለ፡፡ ከላይ እንደጠቆምኩት የ27 ዓመቱ የግፍ ዘመን ባለጊዜዎች ትግሬ ወያኔ ብቻ አደለም፡፡ ከትግሬ ወያኔው በላይ አሁን የመጣውን ለውጥ ለማሰናከል ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ያሉ ትግሬ ያልሆኑ ብዙዎች አሉ፡፡ ከትግሬ ወያኔዎቹም ዋነኞቹ አልተያዙም፡፡ እዚህ ላይ ዋነኞቹ ስል እንደነ አባይ ጸሐይዬ ያሉ ሽማግሌዎች አደሉም፡፡ ከሽማግሌዎቹ በእርግጥም ዋናው አንድ ሰው አለ፡፡ ግን አብዛኞቹ የአሁኑን አገርና ሕዝብን እያመሱ ያሉት ከደህንነት ሹም ከተባለው ጀምሮ፣ ጀነራሎችና ወጣት ሊባሉ የሚችሉ የወያኔ ቅልቦች ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ በቀጥታ በፖለቲካው ውስጥ ተሳትፎ ባይኖራቸውም ከአገሪቱ ሀብት ብዙ ይዘርፉ ስለነበር ያ መቆሙም ብቻ ሳይሆን አገር ከተረጋጋች ሊጠየቁ እንደሚችሉ ስለሚያውቁ በዋናነት የብጥብጡ ሴራ ዘዋሪ ናቸው፡፡ እንግዲህ ኢንጂነር ስመኘው ራሱን ገደለ እስከማስባል የሚያስችል አቅም የፈጠሩ ናቸው፡፡ አብይ ይሄን አሳምሮ ያውቀዋል፡፡ ግን አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ እንደተባለው አይነት ሂደት ነው አሁን እየሆነ ያለው፡፡ የስመኘው ይቅርና የአብይ የግድያ ሙከራም እየተመረመረ ያለው በማን ነው የሚለው አጠያያቂ እንደሆነ ይሰማል፡፡ እዚህ ድረስ ክፍተት አለ፡፡ እርግጥ ነው እነ አብይ አገሪቱን ለወሮበላ እንደፈለጋቸው እንዲፈነጩ እድል እየሰጡ በራሳቸው ላይ ችግር ፈጥረዋል፡፡ እና እነ አብይ እንዲህ ያሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ሕዝብ እየሰበሰቡ መርዛቸውን እንዲረጩ እድል ሰጥተው ሠላም ባይመጣ ለምን እንገረማለን? የሜቴክ ጀነራሎች ታሰሩና እኔን ያን ያህል አያስደስተኝም፡፡ ይሄ አንድ ተግባር ነው ግን ከጀመራችሁ ሁሉንም ማጥራት ግድ ይላል!

ልዑል እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ! አሜን!

ሰርፀ ደስታ