Solidarity Committee for Ethiopian Political Prisoners (SOCEPP-Canada)

የኢትዮጵያ ፖለቲካ እሥረኞች አንድነት ኮሚቴ በካናዳ (ኢፖእአኮ-ካናዳ) Email: socepp.can@humanrightsethiopia.com and socepp.can@sympatico.ca

Web: www.humanrightsethiopia.com

ኅዳር 32011

ለተከበሩት ዶክተር አብይ አህመድ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር አዲስ አባባ

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር

የአክብሮት ሰላምታችን ይድረሰዎት።

ክቡርነትዎ ሥልጣንዎን በተረከቡ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ያከናወንዋቸው ታላላቅ ተግባሮች በእጅጉ ሰፊውን ህዝብ ያስደሰቱና ተሰፋን ያጎናፀፉ ናቸው። ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ደግሞ ሴቶችን በተመለከተ እጅግ አስመስጋኝ ታሪክ ሰርተዋል። በዛ ያሉ ሴቶችን በሚኒስቴርነት ሾመዋል፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገራችን ታሪክ ወይዘሮ ማአዛ አሸናፊን የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሰባሳቢ አድርገው ሾመዋል።
አሁን ደግሞ በሀገራችን ታሪክ የመጀመሪያዋ የፖለቲካ ድርጅት መሪ የነበረችውን ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ከምትገኝበት የስደት ሀገር ፣ ከአሜሪካ፣ እንድትመለስ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በመሉ ክብርና ትህትና የተደረገላት አቀባበል እርስዎ ለሴቶች መብት መከበር ያለዎትን ዕምነት ያሳያል።

ይህ ሁሉ እጅግ ትልቅ የሚደነቅና እኛም የምንደግፈው እርምጃ ነው።

ሆኖም ግን እስካሁንን ያልተነካና እጅግ አሳሳቢ ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ ከ20 ዓመት ላላነሰ ጊዜ ከአዲስ አባባ በህወሀት መራሹ መንግስት የጸጥታ ሀይሎች ታፍና እስከዛሬዋ ዕለት ድረስ መዳረሻዋ ያልታወቀው የወይዘሪት አበራሽ በርታን ጉዳይ ምላሽ እንዲሰጥበት አሁንም በድጋሜ ለእርስዎ ለማቅረብ እንፈልጋለን።

እርሰዎ የጠቅላይ ሚኒስቴርነት ሀላፊነትን ከያዙ በኋላ ግንቦት 222010 ድርጅታችን ይህንንና ተዛማጅ ጉዳዮችን አስመልክቶ ምላሽ እንዲሰጥ በጥሞና ማሳሰቢያ ለእርስዎ መላኩ ይታወሳል። ከጥቂት ወራት በፊት በዋሽንግተን ዲሲ ከኢትዮጵያውያን የፖለቲካ መሪዎች ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ የወይዘሪት አበራሽና ሌሎችም መዳረሻቸው ያልታወቀውን የፖለቲካ እስረኞች ጉዳይ አስመልክቶ የድርጅታቸውን የኢሕአፓን መሪዎች “ወደሀገር ግቡ ከዚያ እየተመካከርን መሆን የሚገባውን እናደርጋለን” ማለትዎ የሚታወስ ነው። በዚያን ጊዜ እነዚህ ደብዛቸው የጠፋ ታጋዮች ሁሉንም ሊያሳስብ እንደሚገባ እንጂ የኢሕአፓ ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነ እጅግ አበረታችና ታሪካዊ ንግግር ማድረግዎትንም ሁላችንም እናስታውሳለን።

ስለዚህም፣ የሁሉንም መዳረሻቸው ያልታወቁ ታጋዮች በተለይም ደግሞ እኛ አስከምናውቀው ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ሰዓት ብቸኛዋ ሴት የፖለቲካ አስረኛ የሆነችውን የታጋይ ወይዘሪት አበራሽ በርታን ጉዳይ አስቸኳይ እልባት እንዲያገኝ ያደርጉ ዘንድ በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን።

በዚህ አጋጣሚ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተለይም በከፍተኛ የመንግስት ሀላፊነት ደረጃ የሚገኙ ኢትኦጵያዊያን ሴቶች ፣ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና ሌሎችም ወይዘሪት አበራሽ በርታና የትግል ጓዶቿ ባስቸኳይ ከእስር እንዲፈቱ ወይም መዳረሻቸው በትክክል እንዲገለጽ ግፊት እንድታደርጉ በታላቅ አክብሮት እንማጸናለን።

ከታላቅ አክብሮት ጋር

አክሊሉ ወንድ አፈረው

ሊቀመንበር