Skip to content

የወልቃይት ጠገዴን ወጣቶች ያሳደዷቸው ጀኔራሎች ተይዘዋል!

November 13, 2018

ጌታቸው ሽፈራው

የወልቃይት ጠገዴ ወጣቶች ሲያሳድዱት የነበረው ክንፈ ዳኘው ሁመራ ላይ በመከላከያ ተይዟል። ጀኔራል ክንፈና ጀኔራል ተክለብርሃን በትናንትናው ዕለት ወልቃይት አዲረመጥ ዳግማዊ ትንሳኤ ሆቴል መግባታቸው ሲታወቅ የወልቃይት ወጣቶች ወደ ሆቴሉ ሲያቀኑ ጀኔራሎቹ መኪናቸውን አስነስተው መፈርጠጣቸው ተዘግቧል። የአድረመጥ ወጣቶች ያስበረገጓቸውን ጀኔራሎች የቃፍታና የባህከር ከተማ ወጣቶች እየተከታተሉ መረጃ ሰጥተው በስተመጨረሻም በመከላከያ ሰራዊቱ ተይዘዋል!

ሲታፈኑ የነበሩት የወልቃይት ጠገዴ ወጣቶች ሌቦችን አሳድደው እንዲያዙ አድርገዋል። ነገ ደግሞ ሙሉ ነፃነታቸውን ይቀዳጁ ይሆናል!

አፈና የፈፀሙት ይጠየቁ!

በርካቶች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሲታሰሩ ኖረዋል። ለዚህ እንደ አብነት የወልቃይት ጠገዴ ኮሚቴ አባላትን እስራት መጥቀስ ይቻላል። እነ አታላይ ዛፌ፣ መብራቱ ጌታሁን፣ ነጋ ባንተይሁን፣ ጌታቸው አደመ፣ አለነ ሻማ እና ሌሎችም የታሰሩት በፌደራል መንግስቱ ሳይሆን በትህነግ/ህወሓት ትዕዛዝ ነበር። ይህ ጉዳይ ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ላይ ሲደርስ የአደባባይ ሚስጥር ሆኗል።

ሀምሌ 05/2008 ዓም ጠዋት 11 ሰዓት ላይ አፋኝ ቡድኑ የኮ/ል ደመቀ ዘውዱን ቤት አንኳኳ። የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አልነበረውም። የአማራ ክልልም ሆነ የፌደራል መንግስቱ አያውቀውም። አፋኙ ቡድን የመጣው ከትግራይ መንግስት ታዝዞ ነው። በዚህ ሂደት ዜጎች ተገድለዋል። ቆድለዋል። የጎንደር ሕዝብ ተሸብሯል። በህፃናት ላይ ከባድ መሳርያና ፈንጅ ተተኩሷል። የተጎዳው ቤትና ንብረት እንኳ ካሳ አልተሰጠውም። ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ያለ አግባብ ታስሯል። በእስር ቤት የግድያ ሙከራ ተደርጎበታል። እሱን ለመግደል በተቀነባበረ ሴራ ሁለት ወጣቶች ተገድለዋል። ብዙዎች ቆስለዋል። ተሰቃይተዋል።

ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ይታሰር የተባለው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ነው። ኤርትራ ከሚገኝ ሰረበ የሚባል ሰው ጋር በስልክ ይገናኝ ነበር ተብሎ በሀሰት ተከሰሰ። ቢኒያም የተባሉ የአማራ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ “በስልክ የተገኘበትን ድምፅ አምጡ” በማለታቸው ችሎት ላይ ታፍነው ታስረዋል።

ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ እንዲታሰር የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ባለመውጣቱ የሀሰት ሰነድ ተዘጋጅቶለታል። በኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ላይ የተከፈተው ክሰ መዝገብ በ2003 ዓም የተዘጋ የሌላ ሰው የፍትሐብር ክስ መዝገብ ነው። ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ የታሰረው በ2008 ሀምሌ ወር ሆኖ የተከፈተበት የክስ መዝገብ ግን እሱ ሲከሰስ ከነበረው መዝገብ ከ60 በላይ መዝገቦች የሚቀድሙትና በሌላ ሰው ክርክር ጉዳዩ የተቋጨ ነው። ይህን ክስ መዝገብ የሀሰት ሰነድ መሆኑን በመዘገቤ እኔም በ19ኛ ወንጀል ችሎት ክስ ሊቀርብብኝ እንደነበርና “የጎንደር ዳኞችን ምስክር ከጠራብን ምን ይውጠናል? ዳታ ቤዛችን ላይም መዝገቡ የለም።” ብሎ የልደታ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ክሱን እንዳስቀረው ከውስጥ ምንጭ አረጋግጫለሁ።

ዳኛ ቢኒያም “ድምፁን አምጡ” ብለው ቢታሰሩም ቀሪ ዳኞች የክስ መዝገቡንና ድምፁን አምጡ ብለው ሲያፋጥጡ፣ የልደታ ፍርድ ቤት ለአቻ ፍርድ ቤቱ መዝገብ አልክም ሲል የጌታቸው አሰፋ መስርያ ቤትም ድምፁን አልክም ብሏል። በዚህም መሰረት የሀሰት ሰነዱም ሆነ፣ ለሀሰት ክስ መሰረት የሆነው “የስልክ ንግግር” ለአማራ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሳይላክ ቀርቷል። ይህም የሆነው ሁለቱም የሀሰት በመሆኑ ነው። የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሀሰት ሰነድ አዘጋጅቷል፣ የደሕንነት ሚኒስትሩ በሰሀት ድምፅ አለኝ ብሏል። በኮ/ል ደመቀ ጉዳይ አደባባይ ወጣ እንጅ ዜጎች ይሰቃዩ የነበሩት በዚህ መንገድ ነው።

እናም ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰው እያፈኑ የሰው ህይወት እንዲሰጠፋ ያደረጉ፣ የሀሰት ክስ ያዘጋጁ፣ የሀሰት ድምፅ አለ ያሉትም ሊጠየቁ ይገባል!

Image may contain: 1 person, standing

Share this:

  • Click to share on Telegram (Opens in new window) Telegram
  • Click to share on WhatsApp (Opens in new window) WhatsApp
  • Tweet

Like this:

Like Loading...

Your true media source

All rights reserved

%d