ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው
fana broadcasting corporate

የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው በቁጥጥር ሥር ዋሉ።

ፋና ብሮድካስቲንግ ሜጀር ጀነራል ክንፈ ወደ ሱዳን ለመውጣት ሲሞክሩ በቁጥጥር ሥር ዋሉ ብሎ የዘገበ ሲሆን፤ ኢቢሲ ደግሞ በትግራይ ክልል ባካር ተብሎ በሚጠራ ስፍራ በኩል ለማምለጥ ሲሞክሩ በትግራይ ክልል ልዩ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ውለዋል ሲል ዘግቧል። በአሁኑ ሰዓትም ተጠርጣሪው ወደ አዲስ አበባ ተይዘው እየመጡ እንደሆነ ኢቢሲ ጨምሮ ዘግቧል።

በተያያዘም ዜና በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሙስና የተጠረጠሩት 63 ግለሰቦች በትናንትናው ዕለት ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ የወንጀል ችሎት ቀርበው እንደነበር ተዘግቧል።

ትናንት ፍርድ ቤት ከቀረቡት መካከል 36ቱ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል ተጠርጥረው እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን ፤ 16 ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት፣ ስድስቱ ከፌዴራል ፓሊስ ምርመራ ቢሮ፣ ሁለቱ ከአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን፣ ስምንቱ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ሲሆኑ፥ ሶስቱ ግለሰቦች ደግሞ ተጠርጣሪን በማስመለጥና ሰነድ በማጥፋት የተጠረጠሩ ናቸው።

ብርጋዲየር ጄኔራል ጠና ኩርዲንን ጨምሮ 28 የሜቴክ ሰራተኞችም በሙስና ተጠርጥረው የቀረቡ ሲሆን፤ የስኳር ገንዘብን ያለአግባብ በመጠቀም፣ የህዳሴ ግድብና የያዩ ማዳበሪያ ፕሮጀክቶች ላይ ህግን ያልተከተለ ግዢ በመፈፀም ተከሰዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ሁለት መርከቦችን ለህገወጥ ንግድ በመገልገል ክስ የተወነጀሉ ሲሆን ፤ የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤትም የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀን ጊዜ የፈቀደ ሲሆን፤ ለህዳር 14 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ብርሀኑ ጸጋዬ፤ የቀድሞ የብሄራዊ ደህንነት እና መረጃ ኤጀንሲ አመራሮች እና አባላት በሽብር እና ከሽብር ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የተያዙ ግለሰቦች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጽሙ ነበር ብለዋል።

ከሰብዓዊ መብት ጥሰትና ከሙስና ጋር በተያያዘ የተሰሩ ወንጀሎችን በተመለከተ ባለፉት አምስት ወራት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሲያከናውን የነበረውን የምርመራ ውጤት ሕዳር 3 ቀን 2010 ዓ. ም ይፋ አድርጓል።

ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ በመግለጫቸው፤ በግለሰቦችና በተቋማት ደረጃ ተፈጽመዋል ያሏቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሙስና ወንጀሎች ዘርዝረዋል።

”የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹ ሲፈጸሙ የነበረው በኃላፊዎች ነው። የሙስና ወንጀሉ ሰፊና ውስብስብ ስለሆነ የምርመራ ሂደቱ ቀላል አልነበረም” ብለዋል።

ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ”ሰዎቹን ሳናስራቸው በፊት ከሕግና ከአሰራር አንጻር መረጃና ማሰረጃ ለማደራጀት ሰፊ ጊዜ ወስዶብናል” በማለት እስካሁን ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ያልዋሉበትን ምክንያት አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ሳተላይት ማምጠቅ ለምን አስፈለጋት?

“የቅማንትን ሕዝብ እንወክላለን የሚሉ ፅንፈኞች ከሌሎች ጋር በቅንጅት እየሰሩ ነው” ጄኔራል አሳምነው

ኦነግ እና መንግሥትን ለማግባባት የሃገር ሽማግሌዎች እየጣሩ ነው

የሰብዓዊ መብት ጥሰ

በሽብርና ከሽብር ጋር በተያያዘ ክስ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ላይ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደተፈጸሙ ተናግረዋል።

በሽብር ተጠርጥረው የሚያዙ ግለሰቦች በብሔራዊ የመረጃ እና ደህንነት አመራሮች እና አባላት አማካኝነት ወደ መደበኛ እስር ቤቶች ከመወሰዳቸው በፊት በማይታወቁ፣ ስውር እስር ቤት ውስጥ እንዲቆዩ ይደረጉ እንደነበር ተናግረዋል።

ስውር እስር ቤቶቹ በይፋ በሕግ የማይታወቁ፤ በሃገሪቱ የተለያዩ ስፍራዎች የሚገኙ እንደሆኑ ገልጸው፤ ከነዚህም መካከል “አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ሰባት እና ከዚያ በላይ እስር ቤቶች አሉ” ብለዋል።

ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ፤ ተጠርጣሪዎች አብዛኛውን ጊዜ በአምቡላንስ በቁጥጥር ሥር እንደሚውሉ እና በድብደባ የተጠረጠሩበትን ወንጀል እንዲያምኑ ይደረጉ እንደነበረ አክለዋል።

ተጠርጣሪዎች የራሳቸው ያልሆኑ የጦር መሳሪያዎችን ‘የኔ ነው’ ብለው እንዲፈርሙ ይገደዱ እንደነበር ገልጸዋል። ዛፍ ላይ ሰቅሎ መግረፍ፣ በኮሬንቲ ማስያዝ (በኤሌክትሪክ መጥበስ)፣ በፒንሳ የብልትን ቆዳ መሳብ፣ በአፍንጫ እስክሪብቶ ማስገባት፣ በአፍ እና አፍንጫ እርጠብ ፎጣ መወተፍ፣ ሙቀታማ ስፍራዎች ላይ ለረዥም ጊዜ ጸሃይ ላይ ማስቀመጥ፣ ብልት ላይ የውሃ ኮዳ ማንጠልጠል እና ጥፍር መንቀልን የመሳሰሉ የማሰቃያ መንገዶች ይጠቀሙ እንደነበረም ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በተጠርጣሪዎቹ ላይ የአስግድዶ መድፈር ወንጀል ተፈጽሟል ብለዋል።

በምረመራው ወቅት የተገደሉ ሰዎች መኖራቸውን እንዲሁም አሁን ድረስ ያሉበት የማይታወቅ ግለሰቦች እንዳሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ተናግረዋል።

”የተፈጸሙት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በብሔራዊ የመረጃ እና ደህንነት ኤጀንሲ አመራሮች ዘንድ እንደ አሰራር ጥቅም ላይ ሲውሉ ነበረ፤ ግምገማ እየተካሄደባቸው አቅጣጫ ይሰጥባቸው ነበረ” ብለዋል።

ኔ 16 የቦንብ ፍንዳታ

የሰኔ 16ቱ የቦንብ ፍንዳታን በማስመልከትም፤ በዋናነት ወንጀሉን የመሩትና በገንዘብ የደገፉት የብሄራዊ ደህንነት እና መረጃ ኤጀንሲ የቀድሞው ኃላፊ ናቸው ብለዋል።

ወንጀሉ ኬንያ ሃገር ከምትገኘው ገነት ወይም ቶለሺ ተብላ ከምትጠራ ግለሰብ ጋር በመተባበር እንደተፈጸመ አስረድተዋል።

”ከብሄራቸው አንጻር ስንመለከት ወንጀሉን የፈጸሙት ኦሮሞዎች ናቸው። ጠቅላይ ሚንስትሩ ኦሮሞ ሆነው ሳለ፤ ተግባሩ በኦሮሞ መፈጸሙ፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የለውም የሚል ተልዕኮ ይዞ እንደተቀነባበረ እጃችን ላይ ያለው መረጃ ያሳያል” ሲሉ ተናግረዋል።

Abbaa Alangaa Waliigalaa Birhaanuu Tsaggaayee Image copyright FBC

ሙስና

ሙስናን በተመለከት፤ ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ፤ የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ባለፉት ስድስት ዓመታት 37 ቢሊየን ብር የውጪ ሃገር ግዢ መፈጸሙን ተናግረው “ሁሉም ግዢዎች ያለ ምንም አይነት ጨረታ ተከናውነዋል” ብለዋል።

የውጪ ሃገር ግዢ ሲደረግ፤ ከኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች ጋር የስጋ ዝምድና ወይም የጥቅም ትስስር ያላቸው በግዢዎቹ ላይ እስከ 400 በመቶ ድረስ የተጋነነ ወጪ ያደርጉ ነበር ብለዋል። ለአብነትም በአንድ ድርጅት የ205 ቢሊዮን ብር ግዢ ያለ ጨረታ መፈጸሙን ተናግረዋል።

ሁለት መርከቦች እና አምስት አውሮፕላኖች

የአሁኑ የባህር ትራንዚት እና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት ወይም በቀድሞ ስሙ የኢትዮጵያ መርከብ ድርጅት ‘አንድነት’ እና ‘አባይ’ የተሰኙ መርከቦች ነበሩት። እነዚህ መርከቦች ከ28 ዓመታት በላይ አገልግሎት በመስጠታቸው በባለሙያዎች ጥናት መሰረት አገልግሎት ላይ መዋል እንደሌለባቸው ስለተረጋገጠ ድርጅቱ ሁለቱ መርከቦች አንዲሸጡ ይወስናል።

በውሳኔው መሰረት አንድ የውጪ ድርጅት ለመርከቦቹ 3.3 ሚሊየን ዶላር ዋጋ ይሰጣል። ሜቴክ መርከቦቹ ለውጪ ድርጅት ከሚሸጡ ለሽያጭ በቀረቡበት ዋጋ መርከቦቹን ገዝቶ ብረቱን አቅልጦ መጠቀም አንደሚሻ ለመርከብ ድርጅት ያስታውቃል።

መርከብ ድርጅትም የሜቴክን ጥያቄ በመቀበል ሜቴክ ለመርከብ ድርጅት 3.2 ሚሊየን ብር ለመከፈል ተስማምቶ መርከቦቹን ይረከባል። ይሁን እንጂ ሜቴክ መርከቦቹን ከማቅለጥ ይለቅ ወደ ዱባይ በመላክ 513 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ መርከቦቹን አስጠግኖ ወደ ንግድ ሥራ አስገብቷል ይላሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ።

መርከቦቹ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ እያውለበለቡ መንቀሳቀስ ስለማይችሉ፤ ለጥገና ተብሎ የተሰጣቸውን ፍቃድ በመጠቀም ወደ ንግድ ሥራ ተሰማርተው ከኢራን-ሶማሊያ መስመር ጭምር በመንቀሳቀስ እስከ 500ሺህ ዶላር ድረስ ገቢ ቢያስገኙም፤ የተጠቀሰው የገንዘብ መጠን ግን ለሜቴክ ገቢ ሳይደረግ ቀርቷል። በመጨረሻም መርከቦቹ 2.6 ሚሊዮን ዶላር መሸጣቸውን ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ተናግረዋል።

ከመርከቦቹ በተጨማሪ ሃገራዊ ፕሮጀክቶችን ለመቃኘት አውሮፕላን ያስፈልጋል በማለት ከአንድ የእስራኤል ኩባንያ የአውሮፕላን ግዢ በሜቴክ መፈጸሙን ተናግረዋል።

ከ50 ዓመታት በላይ ያገለገሉ፣ የነዳጅ ፍጆታቸው ከፍተኛ የሆነ እና የቴክኒክ ችግር ያለባቸውን አውሮፕላኖች ከታሰበላቸው ዓላማ ውጪ ለንግድ አገልግሎት ውለዋል ያሉት ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ፤ ባለቤትነታቸው የሜቴክ ከሆኑ አምስት አውሮፕላኖች መካከል አራቱ አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውንና አንዱ እስካሁን የት እንዳለ እንደማይታወቅ ጨምረው ተናግረዋል።

ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ፤ እስካሁን ድረስ በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሙስና የተጠረጠሩ 63 ግለሰቦች በቁጥጥር መዋላቸውን የተናገሩ ሲሆን፤ አሁንም በቁጥጥር ሥር ያልዋሉ ግለሰቦች መኖራቸውን ተናግረዋል።

“ከሃገር ውጪ ያሉት ተጠርጣሪዎች የሚኖሩባቸው ሃገራት አሳልፈው እንደሚሰጡን ቃል ገብተውልናል” ብለዋል።

የዓመቱ ሐሰተኛ ዜናዎች በአፍሪካ

«በቋንቋው ሳያስተምር ያደገ ሃገር እኔ አላውቅም» ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ

ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ፤ አሁንም በስልጣን ላይ ያሉ በቁጥጥር ስር ያልዋሉ ተጠርጣሪዎች አሉ፤ ይህ እንዴት ይታያል? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “የአንድ ክልል የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አይደለም፤ የሃገር መሪም ቢሆን ከህግ በታች ነው። ወንጀል የፈጸሙ በሙሉ ለህግ ይቀርባሉ” ብለዋል።

የተጠርጣሪዎች ፎቶግራፎች ዛሬ ወይም ነገ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግም አክለዋል።

የምርመራው ሥራ ሕግ እና ስርዓትን የተከተለ ነበረ? የሚል ጥያቄ የተነሳላቸው ሲሆን፤ “የትናንቱን አንደግምም፤ ምርመራዎቹ በሙሉ ሕግ እና ስርዓትን የተከተሉ ነበሩ፤ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጠርጣሪዎችም በስልክ ተጠርተው ነው ለፖሊስ ሪፖርት ያደረጉት” ብለዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ዛሬ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ጨምረው አስረድተዋል።