
12 November 2018
የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዋና ዓቃቤ ሕግ ብርሃኑ ፀጋዬ ዛሬ ኅዳር 3 ቀን 2011 ዓ.ም. የሰብዓዊ መብትና የሙስና ወንጀሎችን ፈጽመዋል ተብለው ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦችን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፣ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለማሰቃያነት ጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩ ድብቅ እስር ቤቶች መኖራቸውን አስታወቁ፡፡
በአዲስ አበባ ብቻ ሰባት ድብቅ ማቆያ ቤቶች መኖራቸውን ያስታወቁት ዋና ዓቃቤ ሕጉ፣ የሚታሰሩ ተጠርጣሪዎች በአምቡላንስ ታፈነው ዓይናቸው ተሸፍኖ እንደሚወሰዱ ተናግረዋል፡፡
እነዚህ ድብቅ እስር ቤቶች በማሰቃያነት ጥቅም ላይ ይውሉ እንደነበር ተናግረው በኤሌክትሪክ ሾክ ማሰቃየት፣ ገልብጦ ማሰር፣ የብልትን ቆዳ በፒንሳ መቆንጠጥ፣ ታሳሪዎች ፀሐይ እንዳያዩ በማድረግ፣ ጫካ ውስጥ ራቁት ማሳደር፣ በአፍንጫ እስክሪፕቶ ማስገባት፣ ብልት ላይ ውኃ ማንጠልጠል፣ ጥፍር መንቀል፣ በሰደፍ መምታትና ተጠርጣሪዎች ላይ ጥይት መተኮስ ብሎም ከአውሬ ጋር ማሰር ይፈጸሙባቸው ነበሩ ብለዋል፡፡
ይህም ተግባር በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አመራሮች እንደ አሠራር የቀጠለና እየተገመገም ተጨማሪ አቅጣጫ ሲሰጥበት ነበርም ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ዓርማዎችን በተጠርጣሪዎች ቤት በማኖር በማስመሰል የመወንጀል ልማዶች ነበሩ ያሉት ዋና ዓቃቤ ሕጉ፣ ሴቶችን ተፈራርቆ መድፈርና ወንዶች ላይ ደግሞ ግብረ ሰዶም ይፈጸምባቸው ነበር ብለዋል፡፡
በሙስና ወንጀል በተለይ ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ (ሜቴክ) ጋር በተያያዘ የመንግሥት ፕሮጄክቶች፣ ግዥዎችንና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን በተመለከተ ምርመራዎች እንደተከናወኑ ተናግረው፣ ያለ ምንም ጨረታ ከውጭ አገርና ከአገር ውስጥ ግዥዎች በዝምድናና በጥቅም ግንኙነት ይፈጸሙ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡ በዚህም ምክንያት፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠርጥረው 36 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተናግረው፣ በሙስና ወንጀሎች ተጠርጥረው ደግሞ 27 ግለሰቦች መቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡
እስካሁን ያልተያዙ ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን የገለጹት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ፣ የተጠርጣሪዎቹ ቁጥር ወደፊት ሊጨምር እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም ከሰኔ 16ቱ የቦምብ ጥቃት ጋር በተያያዘ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ኃላፊ ትዕዛዝ የተፈጸመ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ፣ ኃላፊ ሲሉ አቶ ተስፋዬ ኡርጌን ይሆን አቶ ጌታቸው አሰፋን እንደሆነ ሲጠየቁ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ኃላፊ ማን እንደሆነ በግልጽ የሚታወቅ ነው በማለት አልፈውታል፡፡