አዲስ አበባ ፣ ህዳር 5 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን አስታወቁ።

የግንባሩ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ከኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ምክትል ሊቀ መንበርና ከኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ጋር በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የግንባሩ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ኦነግ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና ከፌደራል መንግስት ጋር በጋራ ለመስራት መስማማቱን አስታውቀዋል።

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ፥ ለሃገር ሰላም፣ ልማትና ዕድገት ከዚህ በኋላ በመደማመጥ በጋራ እንሰራለን ብለዋል።

በሃገርና ህዝብ ላይ ጉዳት ሲያደርሱ የነበሩ ወገኖች ለህግ እንዲቀርቡና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ህዝቡ ለመንግስት ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ህዝቡ ልማትን ለማስቀጠል ሴረኞችን በማጋለጥ ከመንግስት ጋር ሊሰራ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

ቄሮ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ አክቲቪስቶች የተገኘውን የፖለቲካ ድል በመደማመጥና በመደጋገፍ ከዳር ሊያደርሱት ይገባልም ነው ያሉት።

በትግሉ ውስጥ ሁሉም የድርሻው እንዳለው ሁሉ ቀጣይ የሃገሪቱንና የህዝቡን እጣ ፈንታ ለመወሰን በጋራ መስራት ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል።

የኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ በበኩላቸው፥ ኦነግ ከኦሮሚያ ክልልና ከፌደራሉ መንግስት ጋር አብሮ ለመስራትና በቀጣይ ሊታዩ በሚገቡ ጉዳዮች ላይ በመነጋገር ለሃገር እድገት አብረው ለመስራት መስማማታቸውን ገልጸዋል።

ኦነግና የኦነግ ሰራዊትም በሰላማዊ መንገድ በመንቀሳቀስ ከመንግስት ጋር አንድ በመሆን ይሰራልም ብለዋል በመግለጫቸው።