ወይ ጉድ እንደ ጀማሪ ጸሐፊ ከየት እንደምጀምር ግራ ገባኝ እኮ!

እንደታዘብኩት ከሆነ ብዙዎቻችን ወያኔ/ኢሕአዴግ የገባበትን ኃይለኛ ወጥመድ የተገነዘብነው አልመሰለኝም፡፡ በዚህም ምክንያት ነው በወያኔ የማታለያ የመደለያ የማስመሰያ ድራማዎች (ትውንተ ሁነቶች) በቀላሉ ለመታለል የምንዳረገው፡፡

ታስታውሱ እንደሆነ ከወራት በፊት አገዛዙ የለውጥ እርምጃዎች!” ያላቸውን እርምጃዎች መውሰድ እንደጀመረ ገና ገና ይሄንን ለውጥ የሚለውን ሕዝብ እንዲያምንለት ለማድረግ ሲል ባለሥልጣናቱን ለቃቅሞ ሲያስራቸው ታያላቹህ!” ብያቹህ ነበረ፡፡ ይሄው ጊዜው ደረሰና ከፊሎቹን እያሰረ ይገኛል፡፡ ቢያንስ እስከ መጭው ምርጫ ማግስት ድረስ እንደታሰሩ ይቆያሉ፡፡ ይሄም ማለት ከሁለት ዓመት የበለጠ አይቆዩም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም እየሆነ ያለው ነገር ሁሉ ትወና እንጅ እውነት አይደለምና ነው፡፡

እንዴት? ለምን? በምን ምክንያት? ካላቹህ፦

1. በወያኔ/ኢሕአዴግ ቤት አንዱ በሌላው ላይ ለመፍረድ የሚያስችል የሞራል ልዕልና ያለው ወይም ከወንጀል ንጹሕ የሆነ ሰው ፈጽሞ የለምና ነው፡፡ በወያኔ/ኢሕአዴግ ቤት ውስጥ ሆኖ ከወንጀልና ከሙስና ንጹሕ መሆን ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ከንፍሮ ጥሬ የማግኘትን ያህል ዕድል እንኳ የለም፡፡

ሌላው ቀርቶ ወደ እነሱ ለመቀላቀል የሚፈልጉትን ሰው እንኳ ወደእነሱ ከቀላቀሉት በኋላ ሆን ብለው በሙስና ማኖ (እጅ) እንዲነካ ያደርጉታል ወይም ደግሞ ያ ወደእነሱ እንዲቀላቀላቸው የፈለጉት ሰው የወንጀል ተግባር ላይ ካገኙት ደስታውን አይችሉትም፡፡ ወንጀሉ ይቅር ይባልለትና ተቀላቅሏቸው እንዲያገለግል ያደርጉታል፡፡

ለምን መሰላቹህ እንዲህ የሚያደርጉት ሕሊናዬ ምኔ ሳይል ዕድሜ ልኩን እንደባሪያ ሲያገለግላቸው እንዲኖር ለማድረግ ነው፡፡ ደክሞት ሸልችቶት ወይም በልላ ምክንያት ኧረ አሁንስ በቃኝ ሸኙኝ አሰናብቱኝ!” ካለ ያ መዝገብ ይመዘዝለትና አርፈህ ሥራህን ሥራ! እንዲህ ዓይነት ወንጀል እንዳለብህ እረሳኸው እንዴ? ወኅኒ መበስበስ ትፈልጋለህ?” ይባላል፡፡

ወያኔ/ኢሕአዴግ እንዲህ ዓይነት ዘዴ ባይጠቀም ኖሮ በሕዝብ እንደመጠላቱ አንድም አገልጋይ ባላገኘና በወደቀ ነበረ፡፡ ስለሆነም ሰዎችን የወንጀል ሪከርድ (መዝገብ) እንዲያዝባቸው አድርጎ እስከፈለገው ጊዜ ድረስ እንዲያገለግሉት ማድረግ የህልውናው ዋነኛ ስትራቴጂ (ስልት) አድርጎ ያዘው፡፡ በመሆኑም ሁሉም ወንጀለኞች በሆኑበት ሁኔታ አንዱ በሌላኛው ላይ ለመፍረድ የሞራል ልዕልናና ንጽሕና የሌለው በሆነበት ሁኔታ እነ ደብረ ጽዮን ከመብራት ኃይል ጋር በተያያዘ፣ እነ አርከበ ከአዲስ አበባ መሬት ዝርፊያ ጋር በተያያዘ፣ እነ በረከት ስምኦን ከጥረት ሀብት ጋር በተያያዘ ሌሎችም እንዲሁ የፈጸሙት ከፍተኛ ዝርፊያ ያለና ይሄም በሚገባ እየታወቀ በጣት የሚቆጠሩ የወያኔ ባለሥልጣናትን ብቻ አስሮ የሕግ የበላይነት ተረጋገጠ!” ማለት ፌዝ የተሞላበት ትወና ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም፡፡

2. ሁለተኛው ድራማ መሆኑን ማሳያ ምክንያት ደግሞ ኃይልና ሥልጣን በወያኔ እጅ በሆነበት ሁኔታ ከመጀመሪያው ጀምሮ የሆነውና አሁንም እየሆነ ያለው ነገር ሁሉ ያለ ሕወሓት ፈቃድና ይሁንታ ፈጽሞ ሊሆን የሚችል ነገር አለመሆኑና ወያኔ ደግሞ ራሱን በራሱ ለማጥፋት እንዲህ ዓይነት እርምጃ በራሱ ላይ ይወስዳል ተብሎ ፈጽሞ ስለማይታሰብና ስለማይታመንም ነው፡፡

ይሁንና ወያኔ/ኢሕአዴግ ከቁጥጥሩ ውጭ እንደማይሆን አምኖ ለራሱ በሚያመቸው መልኩ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ድራማውን (ትውንተ ሁነቱን) እየተወነብን ባለበት ሁኔታ ሲያጋልጥ መቸስ አያድርስ ነው የኦነግን መግባት ተከትሎ በአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ እንዳያቹህት ሕገወጥ የሆነ የአፈሳ፣ እስርና ግድያ በመፈጸሙ ከዚህ በኋላ አስሬ አልመረምርም መርምሬ ነው የማስረው!” የሚለው ነገር ውሸት መሆኑ ታውቆ እያለ እንዲህ እያለ ማላገጡን በመቀጠል ባለሥልጣናቱን በሕግ እንዳይጠየቁ ጥረት ሲያደርግ በመሀል ላይ ማጭበርበሩ ስለተጋለጠ ወይም ስለተደረሰበትና ስለተገደደም ነው አሁን ወደ መጨረሻ በመንተእፍረቱ ኧረ እያጭበረበርኩ አይደለም እውነተኛ የለውጥ እርምጃ ነው እየወሰድኩ ያለሁት!” ለማለት የጎሳ ፌዴራሊዝምን ለሚከተል ሀገር ፈጽሞ ትክክል ባልሆነ በኢፍትሐዊ መንገድ ኃላፊነቱን ሁሉ ጠቅልለው ይዘውት የነበሩትን ከመቶ ስድሳ በላይ ትግሬ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን ከሠራዊቱ በማሰናበትና ከስድሳ በላይ የሚሆኑ የሥራ ኃላፊዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ለሕግ የበላይነትና ተጠያቂነት ቁርጠኛና ታማኝ ለመምሰል ከፍተኛ ጥረት እያደረገ የሚገኘው፡፡

ለመሆኑ እንዴት፣ በማንና መቸስ ነው አገዛዙ ማጭበርበሩ፣ ማወናበዱ፣ ማስመሰሉ ሊደረስበት የቻለውና እርምጃ እንዲወስድ ያስገደደውስ ማን ነው???

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ በኋላስ በቃኝ!” ብሎ የመጨረሻ እንደጨከነ እንደቆረጠ ያዩ ምዕራባውያኑ ናቸው አገዛዙ የለውጥ እርምጃ እንዲወስድ ያስገደዱት፡፡

አገዛዙም እሽ እወስዳለሁ!” ብሎ ሲያወናብድ ከቆየ በኋላ የራሱን ርካሽ የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) ጥቅም ለማስጠበቅ በማሰብ ከኦነግ መግባት ጋር በተያያዘ የኦሮሚያ የፀጥታ ኃይልና እነ ጃዋር በቀጥታ የተሳተፉበትን በቡራዩና በአዲስ አበባ የኦነግንና የግ7ን ደጋፊዎች የማጋጨት ተግባር ሲፈጽሙ፣ ግጭቱን ተከትሎም በርካታ ዜጎች ለሞት ሲዳረጉ፣ ሲፈናቀሉ፣ ንብረት ሲወድም፣ አምስት የአዲስ አበባ ወጣቶች መሣሪያ ለመቀማት በመሞከራቸው!” በሚል ሐሰተኛ ምክንያት በአደባባይ እንዲረሸኑ ሲደረግ፣ በርካቶች ከሕግ ውጭ በጅምላ እየታፈሱ እንዲታሠሩ ሲደረግ ምዕራባውያኑ የአገዛዙን አሻጥር ደረሱበትና ወዲያውኑ በአምነስቲ ኢንተርናሽናል በኩል የተፈጠረው ችግር በአስቸኳይ ገለልተኛ በሆነ አካል እንዲጣራ ለአገዛዙ ጥሪ አቀረቡ፡፡

የዐቢይ/ወያኔ አገዛዝ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ እንዲያደርግ የቀረበለትን ጥሪ አልቀበልም!” ብሎ አሻፈረኝ አለ፡፡ ፈቃደኛ አለመሆኑም አገዛዙን ይበልጥ አጋለጠው፡፡ በዚህ ምክንያት ዐቢይ እንደሚገኝ አስቀድሞ ማረጋገጫ ሰጥቶበት በነበረው በአውሮፓ ኅብረት ስበሰባ ላይ ሳይገኝ ወይም ሳይሔድ ቀረ፡፡ አሰፍስፈው እንደሚጠብቁት ያውቃልና ቀረ፡፡ አጭበርባሪነቱ በመታወቁና በእነሱ ፊት ሞገስ በማጣቱ ምክንያትም ነው ዐቢይ ሰሞኑን ፈረንሳይንና ጀርመንን በጎበኘ ጊዜ ለሀገር መሪ የሚገባው አቀባበል ተነፍጎት በተራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር (ዋና ሹም) ሠራተኛ ደረጃ ከአውሮፕላን (ከበረርት) ማረፊያ እየተቀበሉ ወደ ቤተመንግሥትና ወደ ስብሰባ አዳራሽ የወሰዱት፡፡

ዐቢይ በዚህ ጉብኝቷ ወቅት ይሄውላቹህ ምን መሰላቹህ ግጭቱ በገለልተኛ አካል መጣራቱን ያልተቀበልኩትኮ ለውጥ አደናቃፊው ኃይል ከባድ ኃይል ስላለውና ሀገሪቱን ቀውስ ውስጥ ሊከታት ስለሚችል ቀስ ብየ በሒደት በቁጥጥር ስር ለማዋል አስቤ እኮነው እንጅ ጥሪውን ላለመቀበል ፈልጌ እኮ አይደለም!” ብላ በማለቃቀስ አታላ ለማሳመን ጥረት አድርጋለች፡፡ ብዙ ያመኗት ግን አልመሰለኝም፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ለማሳመን ሲባል ከ160 በላይ የሕወሓት ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን ከጦር ሠራዊቱ የማሰናበትና 63 የሥራ ኃላፊዎችን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ የተደረገው፡፡

ለመሆኑ አገዛዙ ለምንድንና እንዴትስ ነው የዚህን ያህል ምዕራባውያኑን ፈርቶ በመገደድ ቀደም ሲልና አሁንም እየወሰደ ያለውን እርምጃ እየወሰደ ያለው?” የሚል ጥያቄ ማንሣታቹህ የሚቀር አይመስለኝምና እሱን ልመልስ፦

እንደምታውቁት የሀገራችን ኢኮኖሚ የቆመውና የሚንቀሳቀሰው በብድርና እርዳታ ነው፡፡ በአገዛዙ ተኮድኩዶ የተያዘው እራሱ ኢኮኖሚው (ምጣኔ ሀብቱ) በሚያመነጨው ወይም በሚያፈራው ሀብት አይደለም፡፡ ለዚህም ነው እኔ በተደጋጋሚ ምጣኔ ሀብታችን የሚንቀሳቀሰው በብድርና እርዳታ በሆነበት ሁኔታ ወይም ከብድርና እርዳታ ወጥቶ በራሱ አቅም መንቀሳቀስ እስካልቻለ ጊዜ ድረስ እድገት ተብሎ ሊነገር የሚችል ነገር የለም!” የምለው፡፡ እናም የምጣኔ ሀብታችን የጀርባ አጥንት ብድርና እርዳታ መሆኑን ስታዩ ወያኔ ለምን ለምዕራባውያኑ ተገዶ ተሽቆጥቁጦ እንደሚታዘዝ ይገባቹሃል ማለት ነው፡፡

ምዕራባውያኑ ሁሉን ያሳተፈ የለውጥ እርምጃ ወስደህ ይሄንን ማድረግህን ካላረጋገጥን በስተቀር ከዚህ በኋላ ምንም ዓይነት ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ፣ ብድርና እርዳታ አንሰጥህም!” ብለው ለአገዛዙ ይሰጡት የነበረውን ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ፣ ብድርና እርዳታ ስላቋረጡበትና የምጣኔ ሃብት ቀውስ ውስጥ ስለገባ ነው፡፡ ያም በመሆኑ ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ተዳርገን ምጣኔ ሀብታችን በአስከፊ ሁኔታ ለመውደቅ እየተመዝገዘገ እንደሆነና ገበያውም ለከፍተኛ ግሽበት ተዳርጎ ሕዝቡ በኑሮ ውድነት እየተቆላ እንደሆነ እያያቹህት ነው፡፡ እናም ወያኔ እንደምንም አወናብዳ በማሳመን እንደድሮው ብድርና እርዳታዋን ለማግኘት ነው እንዲህ መከራዋን የምታየው፡፡

በዚህ ተገዶ ነው እንጅ የዐቢይ/ወያኔ አገዛዝ በደረቅ ከፍተኛ የሙስና ወንጀል የታሰሩ ወንጀለኛ የጉምሩክና የኢትዮጵያ አውራ መንገዶች የወያኔ ባለሥልጣናትን (እነ ገብረዋሕድን) ያለ ምንም ሕጋዊነትና ተቀባይነት ያለው ምክንያት ከእስር የፈታ አገዛዝ በሆነበት ሁኔታ እንዲሁም በሕገወጥ መንገድ ከሕዝብ በተዘረፈ የሀገር ሀብት ተቋቁመው ግብርና ቀረጥ ሳይከፍሉ የሚነግዱ ሕገወጥ የፓርቲ (የቡድን) የንግድ ተቋማት አሁንም ድረስ በፍጹም ነጻነትና የበላይነት በሥራ ላይ ባሉበትና ዐቢይ በእነኝህ ሕገወጥ የዝርፊያ ተቋማት ላይ አንዲት ነገር ትንፍሽ ለማለት ፈጽሞ ባልፈለገበት ሁኔታ አገዛዙ ለሕግ የበላይነትና ለፀረ ሙስና ዘመቻ ቁርጠኛና ታማኝ ሆኖ በፍጹም ይሄንን የእስር እርምጃ ሊወስድ አይችልም፡፡ ይወስዳል ብላቹህ ካመናቹህ ሲበዛ የዋሃን እንደሆናቹህ እወቁት፡፡

ሌላው ልናውቀው የሚገባን ነገር መረጃ ሊያሸሽ፣ ሊሰውር ሊያጠፋ እንደሚችል ሲገመት፤ እሱ እራሱ ወንጀለኛውም ይጠፋል ይሰወራል!” ተብሎ ሲገመት ሲጠረጠር ከባድ ወንጀል የፈጸመን ተጠርጣሪ አስሮ ማጣራት ሕጋዊና ዓለማቀፋዊ አሠራር ነው፡፡ እውነታው ይሄ ሆኖ ሳለ አገዛዙ አስረን ማጣራት ትተናል አጣርተን ነው የምናስረው!” የሚለው ፈሊጥ ለምን ያስፈለገው ይመስላቹሃል??? ፈሊጡ ያስፈለገበት ምክንያቶች፦

1. ወንጀለኞቹ መረጃንና ማስረጃን እንዲሁም ሀብትን እንዲያሸሹ፣ እንዲሠውሩና እንዲያጠፉ ዕድል ለመስጠትና ለዚህም ተግባር በቂ ጊዜ እንዲያገኙ ለማስቻል፡፡

2. ከሚፈለጉት ውስጥ ከሀገር እንዲወጡና እንዲሸሹ የተፈለጉት ከሀገር እስኪወጡና እራሳቸውን እስኪሰውሩ ድረስ በቂ ጊዜ ለመስጠት፡፡

3. ወንጀለኞቹ በታሰሩበት ሁኔታ ማስረጃና መረጃ ለማሰባሰብ ቢሞከር ኖሮ በርካታ ዜጎች መረጃና ማስረጃ ጠቋሚ አቅራቢና ተባባሪ ሆነው ሊቀርቡ ስለሚችሉና ይሄ ስላልተፈለገ ተጠርጣሪዎቹ ወንጀላቸው በበቂ መረጃና ምስክር እንዳይደገፍና እንዳይረጋገጥ ምስክሮች ወንጀለኞችን ፈርተው እንመስክር!” ብለው በመቅረብ ከመመስከር እራሳቸውን እንዲያቅቡ ለማድረግና በዚህ ጠባብ መረጃና ማስረጃ የማሰባሰብ ሒደት የተሰበሰበው መረጃ በቂ እንዳይሆን በማድረግ ተከሳሾችን በነጻ ለመልቀቅ እንዲያመች ለማድረግ ነው፡፡

አገዛዙ አምስቱንም ወራት ከሚከሰሱ ወንጀለኞች ጋር ቁጭ ብሎ ሲሸርብ የከረመው የሚመሠረቱባቸውን ክሶች በቂ መረጃ አልቀረበባቸውም!” በሚል ለማስተባበል፣ ክሱን ውድቅ ለማድረግና ከክስ ነጻ ለመሆን በሚያስችል መልኩ ነው ክሶቹ ሲቀመሩ ሲበጃጁ የሰነበቱት፡፡ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ የጠቀሳቸው ወንጀሎች በሙሉ ማስተባበያዎቻቸው በሚገባ ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡

ወንጀለኞቹ በቁጥጥር ስር ባልዋሉበት ሁኔታ ማጣራት ሲኪያሔድ የነበረበት ሌላው ምክንያት ይሄ ነው፡፡ አብረው ቁጭ ብለው ስለክሱ ለመምከር መውጫ ማምለጫ መንገዱን ለማበጃጀት፡፡ በዚህም መሠረት ብዙዎቹ ወንጀለኞች በምርጫው ማግስት ነጻ ይለቀቃሉ፡፡ እስከዚያ ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች ክሱ እየተጓተተ እንዲቆይ ይደረጋል፡፡ ጥቂቶቹ ብቻ ግን በበቂ ማስረጃ እጦት ምክንያት አነስተኛ የእስር ቅጣት የሚጣልባቸው ይሆናል፡፡

ወያኔ/ኢሕአዴግ እስካለ ጊዜ ድረስ ከዚህ ውጭ ምንም የሚፈጠር ነገር አይኖርም!!! ቀሪዎቹ እንደነ ደብረጽዮን፣ አርከበ፣ በረከት፣ አቦይ ስብሐት፣ ወ/ሮ ሙስና (አዜብ)፣ ሳሞራ እና ሌሎቹ የወያኔ/ኢሕአዴግ ባለሥልጣናትም ለትክክለኛና እውነተኛ ፍርድ ይቀርባሉ ብላቹህ አትጠብቁ፡፡

እነዚህ ግለሰቦች ለፍርድ ካልቀረቡ ደግሞ የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነት የለም ማለት ነው፡፡ የለም ማለት ደግሞ የለም ማለት ነው፡፡ እነዚህ ባለሥልጣናት ለፍርድ ካለመቅረባቸውም የነገርየውን ድራማነት (ትውንተ ሁነትነት) ተረዱ፡፡ ከዚህ በመለስ የሚደረግ ነገር ሁሉ እኛን ለመደለል ለማታለል የሚደረግ ትወና ነውና አንመን አንቀበል!!! በአረም የመመለስን ዋጋ ያስከፍለናልና፡፡

ይቅርታ ምሕረት ምናምን የሚባሉ ነገሮች አይሠሩም!!! በሰብእና ላይ ወንጀል የፈጸመ (crime against humanity) ወይም የሰብአዊ መብት ጥሰት (human rights violence) የፈጸመን ሰው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ ይቅርታና ምሕረት እንዲደረግለት አይፈቅድም አጥብቆ ይከለክላል፡፡

በደቡብ አፍሪካ፣ በሩዋንዳ፣ በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያና በሌሎችም ሀገሮች በሕዝቡ መካከል ብሔራዊ እርቅ እንዲፈጸም ሲደረግ በሰብእና ላይ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ፈጽሞ ይቅርታና ምሕረት እንዲደረግላቸው አልተደረገም፡፡ ከመላው ዓለም ከየተሸሸጉበት እየታደኑ ፍትሕ ተበየነችባቸው እንጅ፡፡ የወያኔ/ኢሕአዴግ ባለሥልጣናት በማንነቱ ብቻ በሚሊዮኖች (በአእላፋት) በሚቆጠር የአማራ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋትና ማጽዳትን ያህል የገዘፈ ጥቃትና ጥሰት በመፈጸም በሰብእና ላይ ወንጀል መፈጸም (crime against humanity) በሚለው ወንጀል ዋና ተጠያቂዎች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ትክክለኛን ፈውስና ስር ነቀል የሆነ ለሀገርና ለሕዝብ ጠቃሚ ለውጥን ከፈለክ ወያኔ/ኢሕአዴግን ከስሩ ነቅለህ ጣል አስወግድ!!! ከዚህ ውጭ ያለው ነገር ሁሉ ትወና ወይም ዕቃቃ ጨዋታ ነውና ምንም ተስፋ አትጣልበት!!!

ማስታወሻ፦

እንግዲህ ትናንትና ጽፌው ልለጥፈው ስል አጠፉብኝ!” ያልኳቹህን ጽሑፍ በተቻለኝ መጠን አስታውሸ መልሸ ለመጻፍ ሞክሬያለሁ፡፡ እንደአጠፉብኝ የሆነ ግን አልመሰለኝም፡፡ እስከአሁን ብዙ ጽሑፍ አጥፍተውብኛል እንደዚህኛው ግን ያሳረረኝ የለም! እልህ ይዞኝ እንደገና ለመጻፍ ሞከርኩኝ እንጅ የጠፋን ጽሑፍ እንደገና አስታውሶ ለመጻፍ እንደመሞከር በጣም የሚያታክት ነገር ያለ እንዳይመስላቹህ፡፡ ይሄንንም እንዳያጠፉብኝ በመፍራት ጽፌ ጨርሸ ለጥንቃቄ ፋይሉን (ሰነዱን) የተለያየ ቦታ አስቀምጨ አሁን ለመለጠፍ እስክገባ ድረስ ከትናንት ጀምሬ ዳታ አላበራሁም ነበር፡፡ ከበድ ያለ ጽሑፍ በጻፍኩ ቁጥር በፌስቡክ አካውንቴ (በመጽሐፈ ገጽ መዝገቤ) ለይ ለመለጠፍ እምቢ እያለኝ ስንት ተቸግሬ መሰላቹህ የምለጥፈው፡፡ እንዲህ ተቸግሬ ለጥፌውም የለጠፍኩት ነገር ለከፊሎቻቹህ እንዳይታይ ይጋርዱታል፡፡ ገብታቹህ ብትፈልጉትም አታገኙትም፡፡ ግድየለም እስከጊዜው ድረስ እንዲሁ እንዘልቃለን፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com