ኢሕአፓ እንደ ፓርቲ እራሱን ለኢትዮጵያ ሕዝብ በመላው የኢትዮጵያ ክ/ሃገራት በእንድ ጀምበር በልሳኑ ዴሞክራሲያ ሲያስተዋውቅ የአስራ አንድ ዓመት ልጅና የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ። ሆኖም ግን ታላላቅ ወንድሞቼና ጓደኞቻቸው በኢህአወሊና በኢሕአፓ ፖለቲካ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በሙሉ እመለከት ስለነበር ምነው እኔም እድሜዬ ለዛ ደርሶ የትግሉ እካል በሆንኩኝ እያልክ እመኝ ነበር። ሆኖም ግን የኢሕአፓ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ያሰጋው ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት በኢሕአፓ ላይ የቀይ ሽብር ዘመቻ በማወጁ ምክንያት በዓሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች፥ ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግስት አሁኑኑ፥ ዴሞክራሲና ፍትህ ለጭቁን ሕዝብ ብለው በጠየቁ በግፍ ታሰሩ፥ ተጨፈጨፉ፥ ተገደሉ፥ ከአገር ተሰደዱ። ህይወታቸዉን በደርግ ፋሺሽት ከተነጠቁት ብርቅዬ ወጣቶች ውስጥም ሁለት ታላላቅ ወንድሞቼ ይገኙበታል።
እኔም የወንድሞቼንና የሌሎች ኢትዮጵያውያን ዜጎች መስዋእት መሆን ለህግ ልዕልና፥ ለሰው ልጆች መብትና ለዴሞክራሲ ስርአት በመሆኑ እጅግ በጣም እኮራባቸዋለሁ። እኔም የወንድሞቼን ፈለግ ለመከተል ዘግየት ብየ ድርጅቱን በመቀላቀል ወያኔ ስልጣን በሃይል እስተቆናጠጠበት ድረስ የበኩሌን አስተዋፅዖ ሳደርግ ቆይቻለሁ። ከዚያ በኋላ ግን ሃገራችን ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በገጠማት እስከፊና አሰቃቂ የወያኔ ስርአት ሕዝባችንን ለግፍ፥ ለመከራ፥ ለስቃይ፥ ለእስራት፥ ለስደትና የአገራችን አንድነትን በተመለከተም ህልውናዋ ለአደጋ የተጋለጠበት ጊዜ ቢሆንም፥ ኢሕአፓን በተለያዩ ማህበራዊ ድህረገፆች፥ ሚዲያዎች ከማየት ዉጪ ይህ ነው የሚባል የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲያደርግ አልተመለከትኩም ነበር። የኢሕአፓ እንቅስቃሴ ከመዳከሙም አልፎ ኢሕአፓ ከተነሳበት ሕዝባዊ ዓላማ በመውጣት በሕዝብ ዘንድ እንዲጠላና ከድርጅቱ እንዲርቁ የሚያደርጉ አግባብነት የለላቸውና ስነምግባሮች የጎደላቸው የድርጅቱ መስራች ነን ከሚሉ ከነአቶ እያሱ አለማየሁ የሚወጡና በአንዳንድ ድህረ ገፆች የሚለቀቁ ፅሁፎች፥ የሚሰጡ ቃለመጠይቆች፥ በራዲዮ የሚተላለፉ ፀያፍ ንግግሮች፥ ሃይለቃሎች፥ ስም ማጥፋቶች ድርጅቱን ከህዝብ እንዲነጠልና ሊያጠቁት ለሚፈልጉት ተመቻችቶ እንዲገኝ አድርጎት ቆይቷል። በግለሰብ ኢትዮጵያውያን፣ በተለያዩ ተቃዋሚ ድርጅቶችና ህዝባዊ ተቋሞች ላይ የሚያደርሱት ማብጠልጠል ኢሕአፓ ከሚታወቅበት ህዝባዊ ስነምግባር በፍጹም የወጣ ሆኖ ነው የሚገኘው። ለመረጃ ያክል 1ኛ/ በስዊድን የሚገኘው አንድነት ራዲዮ ጋር ያደረጉት ቃለ መጠይቅ በግንቦት 7 ላይ ያደረጉት ንግግርና በወ/ሮ ሮዛ አባድር የተሰጠውን መልስ። 2ኛ/ በፍኖተ ራዲዮ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ በወ/ሮ ሕይወት ተፈራ ስለኢሕፓ የፃፉትን መፅሃፍ አስመልክቶ በፀሃፊዋ ላይ የሰጡት አሳዛኝና አሳፋሪ አስተያየት ….ወዘተ፣ አሁንም በቅርቡ በፍኖተ ዴሞክራሲ ራዲዮ በኩል በጠቅላይ ምኒስቴር አብይ ላይ የሚደረገው የማጥላላት ዘመቻና ሰሞኑን በተሾሙት የአገሪቷ ፕሬዝዳንት ላይ የተሰጠውን አስተያየት ስሰማና ስመለከት አንድ ኢሕአፓ ነኝ ከሚል ግለሰብ የማይጠበቅና እጅግ የወረደ በመሆኑ እጅግ በጣም አሳዝኖኛል። በተለይ ደግሞ ከሃያ ሰባት የወያኔ የመከራ፥ የስቃይና የአንድ ዘር የበላይነት ዘመን በኋላ በሕዝባችን በቃን አልገዛም ባይነት ሕዝባዊ አመፅ በመከሰቱ ምክንያት የወያኔ መንግስት ሙሉ በሙሉ ተገርስሷል ባይባልም በኢህአደግ ዉስጥ ካሉት ድርጅቶች ምሃከል የለወጥ ፈላጊዎች መነሳሳት በሃገሪቱ ዉስጥ ላለፉት አምስትና ስድስት ወራቶች ከፍተኛ መሻሻልና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ ያደረገበት፥ ብዙወች የህሊና እስረኞች፥ በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ የታሰሩ እስረኞች የተፈቱበት፥ በሃገራቸው የፖለቲካ አመለካከታችዉን ለሕዝባቸው ለማስተማር ባለመቻላቸውና የነፃነት እጦት ምክንያት ከሃገራቸው ዉጭ ይኖሩ ለነበሩ የተቃዋሚ ድርጅቶችና ቡዱኖች በተገኘው የዲሞክራሲ ጭላንጭል አገር ቤት ገብተው መንቀሳቀስ እንዲችሉ በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት ኢሕአፓም የጠቅላይ ሚኒስተሩን ጥሪ ተቀብሎ ያልተቋጨዉን የፍትህ፥ የዴሞክራሲ፥የህግ የበላይነትና የሃገር አንድነት ትግል ከሕዝብ ጋር ሆኖ ለማስቀጠል ይቻል ዘንድ ወደ ሃገር ቤት መግባታቸው ይበል የሚያሰኝና የፖለቲካ በሳልነትን የሚያሳይ ጭብጥ መሆኑን ተገንዝቦ አብሮ የጀመሩትን እልህ አስጨራሽ ትግል እብሮ እንደመቀጠል ጥሪዉን ተቀብለው ትግሉ በዋናነት ከህዝባችን ጎን በመሰለፍ አሁን በተፈጠረው የዴሞክራሲ ጭላንጭልን መጠቀም ይቻል ዘንድ አገር ቤት በገቡት የአመራር አባላት ላይ እየወረደ ያለው ተራ የአቶ እያሱ ቡድን ያልተገራ ዉርጅብኝ በርካታ የቀድሞ አባላትና ደጋፊዎችን እኔንም ጨምሮ ያሳዘነ ክስተት ሆኗል።
በእውነት የአቶ እያሱ ቡድን ሕዝባችን እየደረሰበት ያለዉን ግፍ፥ መከራና ስቃይ፥ ለመታደግና የምንወዳት ሃገራችን ከመበታተን ለማዳን ዓላማዉና ፍላጎቱ ካላችሁ ኋላቀርና ጊዜው ያለፈበትን የመጠላለፍ፥ የጥላቻ፥ የቂምበቀልና አንጃ ግራንጃ ፖለቲካ ትታችሁ ሃገራችን ከገባችበት አረንቋ ለመታደግ የተጀመረዉን የለውጥ ሂደት ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል፥ የዛሬ አርባ ስድስት ዓመት የጀመራችሁትን የዴሞክራሲና የፍትህ ጥያቄ ተግባራዊ እስኪሆን ድረስ ሃገር ቤት ከገቡት ጓዶቻችሁ ጋር በመቀላቀል ከሕዝባችሁ ጎን በመሰለፍ ታሪካዊ ግዴታችሁን ትወጡ ዘንድ እናት ሃገራችሁ ጥሪ ታቀርባለች።
ለመሆኑ የአቶ እያሱ ቡድን ባይናችን የምናየውን ለውጥ መቃወም፣ በዋናነት ከወያኔ ጎራ እንደሚያሰልፈው ተገንዝቦት ይሆን? ትግሉ እንዲደናቀፍ፣ ሌት ተቀን መጣር በዋናነት የሚጎዳው ሀገራችንንና ህዝባችንን እንደሆነና የሚጠቅመውም በዋናነት ህወሀትን እንደሆነ ተገንዝበው ይሆን?
ኢህአፓን ከህዝብና ከሃገር ነጥሎ የስደት ድርጅት ለማድረግ መጣር የጀግና ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ተጋድሎና መስዋእትነት ዋጋ ማሳጣት መሆኑን ተረድተውት ይሆን?
በእልፍ አእላፍ ጀግኖቻችን ደም የተገነባውን የኢህአፓን ታሪክ ማጠልሽት የሚቀጥለው እስከመቼ ነው?
ኢሕአፓ አእላፍ አባላቶቹንና ደጋፊዎችን የተሰዉለትን ዓላማ አድሶ ይቀጥላል!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!