ሞረሽ ወገኔ እንደተቋቋመ ነበር አባላቸው እንድሆንና አብረን ተሰልፈን ለወገን እንድንታገል በኢሜይል (በነመልክት) የጠየቁኝ፡፡

ይመስለኛል አድራሻየን ያገኙት ሞረሾችን ጨምሮ በርካታ የአማራ ተወላጆችን በቁጭትና በእልህ እንዲነሣሡና እንዲደራጁ ካደረጉት ጽሑፎቸ ላይ ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች በአማራ ሕዝብ ላይ በታሪክ ሂደት ውስጥ ከጥንት እስከ ዛሬ!” የሚለው ጽሑፌ ወያኔን ጨምሮ በአማራ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል የፈጸሙ የጥፋት ኃይሎችን አረመኔያዊ ግፍ የሚያትት ረጅም ጥናታዊ ጽሑፌ አንዱ ነው፡፡

ያኔ ሞረሽ ብለን ተደራጅተናል ያሉኝ ሞረሾች እነማን እንደሆኑ በቂ መረጃ አልነበረኝምና ስማቸውን እንዲያስተካክሉ ብቻ ምክር ሰጥቸ እኔ ግያ ያለሁበት ሀገር ውስጥ ስለሆነና እንቅስቃሴየ በወያኔ ዕይታ ስር ስለሆነ አብሮ ለመሥራት እንደሚያስቸግረኝ ለድርጅታዊ ትግልም እንደኔ ወያኔ በዓይነ ቁራኛ የሚከታተለውን ሰው ማካተቱ የድርጅቱን ዕድሜ በአጭር ሊያስቀረው ስለሚችል ጥሩ አለመሆኑን ነግሬ መለስኩላቸው፡፡

ስማቸው የነበረው ሞረሽ ወገኔ የአማራ ጎሳ ድርጅት!” የሚል ነበር፡፡ እናም ጎሳ አነስተኛው የማኅበረሰብ አደረጃጀት መሆኑን፣ እንደ መዠንገር አኙዋክ ጉምዝ የመሳሰሉ ጥቂት አባላት ያሏቸው አናሳ የማኅበረሰብ አደረጃጀት ያላቸው ቡድኖች መጠሪያ መሆኑን ገልጨ አማራን ጎሳ ማለት ሰፊ የማኅበረሰብ አደረጃጀት፣ የበለጸገ ባሕል፣ ጥንታዊ ሥልጣኔ ያለውን ታላቅ ሕዝብ ማሳነስ በመሆኑ ጎሳ የሚለውን ቃል ትተው ነገድ ወይም ብሔረሰብ የሚለውን ቃል እንዲጠቀሙ ነበር ምክር የሰጠኋቸው፡፡ እነሱም ምክሩን ሰምተው ጎሳ የሚለው ቃል ወዲያውኑ ትተውታል፡፡

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሞረሾችን አንድ ጉዳይ ለማስቸገር ጠየኳቸው፡፡ የተፈጸመብንን የዘር ማጥፋት ወንጀልና ግፍ በመጽሐፍ አደራጅቸ ማሳተም እንደምፈልግ ገልጨ አቅም ስለሌለኝ ስፖንሰር (ደጋፊ) እንዲሆኑኝ ከእነሱ ውስጥ አንዱ ለሆነው ጠየኩ፡፡ ቆየት ብሎ ለማኅበሩ እንዳቀረበውና መልስ እንዳላገኘ ነገረኝ፡፡

ለካ ሞረሾች በራሳቸው ስም ታትሞ ክሬዲቱ (ዋጋው) ለማኅበሩ እንዲሆን ፈልገው ኖሮ ለኔ ስፖንሰር ሆነውኝ መጽሐፉ እንዲታተም ባለመፈለጋቸው በጎን ይሄንን ሥራ የሚሠራ ሰው እያፈላለጉ ኖሯል፡፡ ሰው ሲያፈላልጉ ሙሉቀን ተስፋውን ያገኙና ሙሉ ወጭውን ሸፍነውለት ጥናቱን እንዲያጠና ተስማምተው ሥራውን ሠርተውት ኖሮ እኔ ከጠየኳቸው ከዓመት ሁለት ዓመት በኋላ ሙሉቀን ተስፋው ሞረሽ ስፖንሰር ሆኖኝ ጻፍኩት!” ያለውን የጥፋት ዘመን!” አሳትሞት ዓየሁ፡፡

ይሄ በመሆኑም አልከፋኝም ነበር፡፡ መጽሐፉን አነበብኩና ዓመተ ፍዳ ዘነገደ አማራ!” በሚል ርእስ በዚህ ሊንክ (ይዝ) ላይ የምታገኙትን ጽሑፍ ጽፌ አስተያየት ሰጠሁና መጽሐፉ በመውጣቱ ደስ እንደተሰኘሁ ገለጽኩ፡፡

http://www.zehabesha.com/amharic/archives/66780

ዋነው ነገር በወገን ላይ የተፈጸመው አረመኔያዊ ግፍ በሰነድ መያዙ ነበርና ፍላጎቴና ዓላማየም፡፡ ሙሉቀን መጽሐፉን ካወጣው በኋላ ግን ከሞረሽ ጋር መወዛገብ ጀመሩ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምረው ሲወዛገቡ ቆይተው ሞረሾች ሰሞኑን ሙሉቀን መጽሐፉን ወደ እንግሊዝኛ አስተርጉሞ በማሳተም ለገበያ ለማውጣት እንቅስቃሴ ማድረጉን ሲያውቁ እኛ ወደ እንግሊዝኛ አስተርጉመነዋል ልናሳትመውም ነው ባለመብቱ እኛ ነን!” በማለት ይሄንን ከታች ባያያዝኩላቹህ ሊንክ ያለውን ስሞታ ዘከዘኩት፡፡

https://ethiobook.net/%e1%8b%b0%e1%88%a8%e1%89%85-%e1%8a%ad%e1%88%85%e1%8b%b0%e1%89%b5-%e1%8a%a0%e1%89%b6-%e1%89%b0%e1%8a%ad%e1%88%8c-%e1%8b%a8%e1%88%bb%e1%8b%8d-%e1%88%99%e1%88%89%e1%89%80%e1%8a%95-%e1%89%b0/

ሞረሽ የሚለው ሙሉቀንን በመቅጠር ስምምነት ፈጽመን 24,700.00 የአሜሪካን ዶላር አውጥቸ ጥናቱን ያስጠናሁትና የጥናቱ ባለቤት ሞረሽ ወገኔ ሆኖ ለኅትመት እንዲበቃ ነው እንጅ ሙሉቀን በራሱ ስም አሳትሞ ለግሉ እንዲጠቀምበት አይደለም፡፡ ይሄንን አሳፋሪ ክህደት ስለፈጸመብኝ ልከሰው ነኝ!” እያለ ነው፡፡

እንደኔ እንደኔ ችግሩን የፈጠረው እንደምትመለከቱት ሁለቱም ለስም ለዝና እና ለጥቅም መሮጣቸው ነው፡፡ ሞረሾች ዋናው ነገር ሥራው መሠራቱ ነው!” ለሚለው ነገር ዋጋ የሚሰጡ ቢሆኑ ኖሮ መጀመሪያውኑም የኔን ሐሳብ ሰርቀው ለራሳቸው ለመጠቀም ባልተሯሯጡ ነበር፡፡ በኔ ላይ ሲሸፍጡ ላጭ አዘዘባቸውና ተላጩ፡፡

እውነት ለመናገር ሙሉቀን የሠራው ሥራ አንድ አማራ ይሠራዋል ተብሎ የሚታሰብ ሥራ አይደለም፡፡ በፍጹም ነውር የሆነ መልካም ላደረገለት መልካም ለዋለለት የማይመለስ ሥራ ነው የሠራው፡፡ እኔ በሱ ቦታ ብሆን ሰው ነኝ ብየ ሁለተኛ ከሰው ፊት የምቀርብ አይመስለኝም፡፡ ውላቸውን አፍርሶ በራሱ ስም ካሳተመው ሌላው ሁሉ ቢቀር እንኳ ገንዘባቸውን መመለስ ነበረበት፡፡ ይሄንን ማድረግ ካልቻለ ደግሞ ቃሉን መጠበቅ ነበረበት፡፡

እሱ ግን ጭራሽ ባለፈው የሠራው ሥራ ሳይጸጽተው ሞረሾች መጽሐፉን በእንግሊዝኛ አሳትመው ሙሉቀን ላይ ያጠፉትን የሕዝብ ገንዘብ ለመመለስ እየተንቀሳቀሱ ባሉበት ወቅት ሙሉቀን አሁንም እንደገና ተሽቀዳድሞ በእንግሊዝኛ አስተርጉሞ ማሳተሙ ነው፡፡ ምን ነካው ግን??? ያለፈውን ቢታገሱ ይሄንን እንዴት ሊታገሱት ይችላሉ??? እሽ አሁን እንግዲህ ልንከሰው ነው!” ብለዋል ምን ሊውጠው ነው እንግዲህ??? እንዴት ይሄንን አያስብም??? እንዴት ለስሙስ አይጨነቅም???

ነው ወይስ የመጽሐፉን ሽያጭ ለሕዝብ ጥቅም ሊያውለው አስቧል??? እንደዚህ አስቦ ካልሆነ በስተቀር እኔ በግሌ ሙሉቀን እንደዚህ ያለውን ነውር ይፈጽማል ፈጽሞም ከሰው ፊት ይቀርባል ለማለት በጣም በጣም ይከብደኛል፡፡

የመጽሐፉን ሽያጭ ለሕዝብ ጥቅም ሊያውለው ካሰበስ ለምን ታዲያ ከነሱ ጋር መጣላት አስፈለገው??? በእርግጥ ሙሉቀን የመጽሐፉን ሽያጭ ለሕዝብ ጥቅም አውለዋለሁ!” ሲል አልሰማሁም፡፡ ይሁንና ግን ሙሉቀን ለወገን እየታገለ እያለ ከሞረሾች ጋር የተዋዋለውን ቃል በልቶ ክህደት በመፈጸም የሕዝብን ገንዘብ በልቶ ይጠፋል ብየ ለማሰብ በጣም በጣም ስለሚከብደኝ ነው፡፡

እስኪ እባካቹህ ትልልቅ ሰዎች ሸምግሏቸውና በመሀል ገብቶ እንዲህ የሚያምሰውን ሰይጣን አሳፍሩት??? በሁለቱ ጸብ ምክንያትኮ ብዙ ነገር ተበላሽቷል፡፡ ለምንድን ነው ዝም የምትሉት??? በተለይም ደግሞ በትግላችን ላይ ከባድ ጉዳት አድርሷልኮ፡፡ ጠላትም በእጅጉ ተጠቅሟል፡፡ ይሄ ጉዳት መቀጠል የለበትምና እባካቹህ ሽማግሎች ሸምግሏቸውና አስታርቋቸው???

ድል ለአማራ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com