November 18, 2018
…….በሚደረገው ነገር ላይ እምነት ስላልነበረኝ በስብሰባው ላይ ለመገኘት ፈቃደኛ እንዳልሆንኩ አስታውቄ የሥራ መልቀቂያ አስገባሁኝ፡፡ ከሥራ ወጥቼ አምስት ወራት ያለ ሥራ አዲስ አበባ ተቀመጥኩ
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ አየር መንድን እንዴት ለቀው ሊሄዱ ቻሉ?
አቶ ግርማ፡- ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ እ.ኤ.አ. በ1993 በአዲሱ መንግሥት አየር መንገዱ ይጠና ተባለ፡፡ ከእኛ አሠራር ጋር ይሄዳል? አይሄድም? የሚል ጥያቄ ተነሳ፡፡ አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ እንዲጠና ተደረገ፡፡ እኔ አስተዳደሩን ወክዬ እካፈል ነበር፡፡ በጥናቱ አካሄድ ላይ ከመንግሥት አካላት ጋር ሳንስማማ ቀረን፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ ስዬ አብርሃ፣ አቶ ተከስተ የሚባሉ ሹም ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ነበሩ፣ ሌሎችም ሚኒስትሮች ይህን እንዲያጠኑ በመንግሥት የተመደቡ ነበሩ፡፡ ከእነሱ ጋር በአካሄድ ልንስማማ አልቻልንም፡፡ አካሄዳቸው ከአየር መንገድ አሠራር ጋር የሚሄድ መስሎ ስላልታየኝ ይኼ ነገር ልክ አይደለም ብዬ እከራከራቸው ስለነበር በእኔ ደስተኛ አልነበሩም፡፡
አርፈህ የምንልህን አድርግ ይሉኝ ጀመር፡፡ እኔም የማላምንበትን ነገር አላደርግም፡፡ እናንተ ይኼ ነገር የሚያዋጣ መስሎ ከታያችሁ ቀጥሉበት፣ እኔ እዚህ ሆኜ እንቅፋት አልሆንም፡፡ እኔ የማላምንበትን ነገር አልሠራምና ልቀቁኝ አልኳቸው፡፡ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ ዘንድ ተልኬ ሦስት ቀን ተሰጠኝ፡፡ የሚሰጠኝን ትዕዛዝ ተቀብዬ በስብሰባ ላይ እንድገኝ ነው፡፡ በሚደረገው ነገር ላይ እምነት ስላልነበረኝ በስብሰባው ላይ ለመገኘት ፈቃደኛ እንዳልሆንኩ አስታውቄ የሥራ መልቀቂያ አስገባሁኝ፡፡ ከሥራ ወጥቼ አምስት ወራት ያለ ሥራ አዲስ አበባ ተቀመጥኩ፡፡ በኋላ ገልፍ ኤር ሥራ አገኘሁና ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አቀናሁ፡፡
ያደግኩበትንና 27 ዓመታት ያገለገልኩበትን አየር መንገድ ለቅቄ ለመሄድ ተገደድኩ፡፡ የሄድኩት ገንዘብ ፈልጌ አይደለም፡፡ የነበረው ሁኔታ የሚያሠራኝ ስለነበረ ነው፡፡ እኔ ከወጣሁ ከትንሽ ጊዜ በኋላ 35 የአየር መንገድ ማኔጅመንት አባላትን ከሥራ አስወጧቸው፡፡ ከዚያ በኋላ አንተ የምትናገረው እውነት ነበር፡፡ ተመለስና ሥራ የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ ቀርቦልኝ ነበር፡፡
አያሌው መንበር