
አዲስ አበባ፣ ህዳር 9፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ ህብረት 11ኛው ልዩ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎች በመሳለፍ ተጠናቀቀ።
ከስአታት በፊት በተጠናቀቀው ስብሰባ መሪዎቹ የሚጠብቀባቸውን የገንዝብ መዋጮ ባላዋጡ ሀገራት ላይ ማእቅብ እንዲጣልና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ማሻሻያም በጥናት ላይ ተመስርቶ እንዲተገበር ወስኗል።
በመሪዎቹ ውሳኔ መሰረት ለተከታተይ ስድስት ወራት ከሚጠብቅባቸው መዋጮ ግማሹንና ከዛ በላይ መክፈል ባልቻሉ ሀገራት ላይ ማእቀብ ይጣልባቸዋል።
ማእቀቦችም የማስጠንቀቂያ፣ የአጭር ጊዜ እና የረዥም ጊዜ ተብለው በሶስት ምእራፍ ተከፋፍለው የሚተገበሩ ናቸው።
በማስጠንቀቂያ ማእቀብ መዋጯቸውን መክፈል ያልቸሉ ሀገራት በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ሃሳብ የመስጠት(የመናገር) መብታቸው ላይ እገዳ ይጣልባቸዋል።
በመካከለኛው ምእራፍ ማስጠንቀቂያ ደግሞ፥ በህብረቱ ስር ከሚገኙ ተቋማት አባልነት፣ የተቋማት መቀመጫ የመሆን ፣ዜጎቻቸው ከአፍሪካ ሀገራት ምርጫ ታዛቢነት እና ዜጎቻቸው ከህብረቱ የተለያዩ ስራ መደቦች የመቅጠር እገዳ እንደሚጣልባቸው ተመልክቷል።
የረዥም ጊዜ ማእቀብ የሚጣልባቸው ሀገራት፥ ከህብረቱ አባልነት እስከ መታደግ ድረስ እንደሚሆን ተጠቁሟል።
ከህብረቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፥ እስካሁን ተገቢውን መዋጮ እያዋጡ ያሉ ሀገራት አትዮጵያን ጨምሮ አስራ አንድ ናቸው ተብሏል።
ሌላው የህብረቱ መሪዎች ውሳኔ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽንን ዳግም ማደረጃት ሲሆን፥ የዚህ የሪፎርም ሃሳብ በጥናት ላይ ተመስርቶ እንዲከናወን ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ሪፎርሙ፥ስምንት የነበረውን ኮሚሽን ቁጥር ወደ ስድስት መቀነስ፣ የህብረቱ ኮሚሽነር ወንድ ከሆኑ ምክትላቸው ሴት እንዲሆኑ ፣ኮሚሽነሩን የሚያግዙ ዋና ፅሃፊ እና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ብቃትን መሰረት ባደረገ መስፈረት ተወዳድረው እንዲቀጠሩም መሪዎቹ ወስነዋል።
የህብረቱ ሪፎርም ውሳኔም ከፈረንጆቹ 2021 ጀምሮ የሚተገበር መሆኑ ተነግሯል።
በዳዊት መስፍን