
አዲስ አበባ፣ ህዳር 9፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ በትናትናው ዕለት ይፋ የተደረገው የአፍሪካ ሰላም ፈንድን በቦርድ አባልነት የሚመሩ አምስት ሰዎች ከምስራቅ፣ምዕራብ፣ማዕከላዊ፣ሰሜንና ደቡብ አፍሪካ ክፍለ አህጉራት ተሾሙ።
በዚህም ምስራቅ አፍሪካን በመወከል ኢትዮጵያዊቷ ወይዘሮ ኢሌኔ መኮንን የአፍሪካ ሰላም ፈንድን በቦርድ አባል ሆነው መመረጣቸው የአፍሪካ ህብረት አስታውቋል።
የህብረቱ ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህመት፥ ከምዕራብ አፍሪካ ናይጀራዊው ዘይነብ አህመድ፣ ከሰሜን አፍሪካ ቱኒዛዊው ካማል ሞርጃኔ፣ ከደቡብ አፍሪካ ክፈለ አህጉር ደቡብ አፍሪካዊው ቲቶ ምቦዌኒ እንዲሁም ከማዕከላዊ አፍሪካ ክፈለ አህጉር ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ አንሴት ዶሎጉሌ የአፍሪካ ሰላም ፈንድ የቦርድ አባል በመሆን ተሹመዋል።
በተጨማሪ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የአውሮፓ ህብረት ሁለት የአፍሪካ ሰላም ፈንድ የቦርድ አባላት እንደሚኖሯቸው ተጠቁሟል።
የሰላም ፈንዱ 100 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በጀት ተይዞለት ወደ ስራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የሰላም ፈንዱ የአፍሪካን የደህንነትና የጸጥታ ጉዳይን በራስ አቅም ለመደገፍ ያለመ ነው ተብሏል፡፡
በኤፍሬም ምትኩ