ከብርሃነ መስቀል አበበ ሰኚ

Four Steps Roadmap on how the Ethiopian People could establish Democratic Government in Ethiopia!
———————–

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ በአራት ምዕራፎች ከፋፍሎ መመልከት ህዝቡ ለትግሉ ስኬት እንዲሰራ እና በጠቅላይ ሚንስትር አብይ ለሚመራው የለውጥ መንግስት ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲሰጥ እንዲሁም የለውጡን ጎራ እንዲያጠናክር ከፍተኛ ሚና አለው።

Step One: The Popular Movement, the removal of TPLF led Regime from power, and the assumption of state power by progressive forces led by #TeamLemma

የመጀመሪያው የትግል ምዕራፍ የኢትዮጵያ ህዝብ ላለፉት አራት ተከታታይ ዓመታት ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያን ያስጨነቀውን እና የመዘበረውን የህወሃት መራሽ መንግስት ለመጣል በአደባባይ ሲደረግ የነበረው ሰላማዊ ትግል ነው። በዚህ ወቅት ትግሉ ይካሄድ የነበረው በሰላማዊ ሰልፍ እና በተለያዩ ሰላማዊ የትግል ስልቶች በመጠቀም እንደነበረ ይታወሳል። የትግሉ አመራርም ይሰጥ የነበረው ከህዝቡ በወጡ ባልተደራጁ አክቲቪስቶች የነበረ ሲሆን ማህበራዊ ሚዲያ ከፍተኛ ሚና ነበረው። የመጀመሪያው ምዕራፍ የህዝቡ ትግል በጠቅላይ ሚንስትር አብይ የሚመራው መንግስት (#TeamLemma) ህወሃት መራሹን ቡድን በማሸነፍ ወደ ስልጣን በመምጣቱ የህዝቡ ትግል ለመጀመሪያ ጊዜ የተደራጀ አመራር አግኝቶ ህዝቡ ከአደባባይ ወደ ቤቱ ተመልሷል። የትግሉ የመጀመሪያው ምዕራፍ በድል ቢጠናቀቅም፣ ትግሉ ህዝባዊ መንግስት የማቋቋም የመጨረሻ ግቡ ጋር ለመድረስ ግን ገና ሶስት ቀሪ ምዕራፎች አሉት።

Step Two: Dismantling the Repressive Regime and Ending the Era of Impunity through holding Accountable the officials of the TPLF led Regime

አሁን ያለነው ሁለተኛው የትግሉ ምዕራፍ ላይ ነው። የህዝባዊ ትግሉ ሁለተኛው ምዕራፍ በጠቅላይ ሚንስትር አብይ የሚመራው መንግስት በህወሃት ይመራ የነበረው አገዛዝ ለ27 ዓመታት በኢትዮጵያ መንግስት መዋቅሮች እና በኢህዴግ ውስጥ የዘረጋውን የነፈሰ ገዳዮች እና የተደራጁ ሌቦች መዋቅር አፈራርሶ ህዝቡን ነፃ ማውጣት እና ወንጀለኞቹን ለፍርድ ማቅረብ ነው። ይህ ምዕራፍ ከተጀመረ ገና ሰባት ወሩ ነው። ይህ ምዕራፍ እጅግ ውስብስብ እና አስቸጋሪ ትግል ሲሆን የሌቦቹን እና የነፈሰ ገዳዮቹን መዋቅር ማፈራረስ እና የኢትዮጵያን መንግስት ተቋማት እና ህዝቡን ከነዚህ የተደራጁ ሌቦች ነፃ ለማውጣት ከፍተኛ ትግስት እና ጊዜ ይፈልጋል። በዚህ የትግል ምዕራፍ የህዝቡ እና የአክቲቪስቱ ድርሻ በጠቅላይ ሚንስትር አብይ የሚመራውን የለውጥ መንግስት በሰው ኃይል፣ በገንዘብ እና በእውቀት ማጠናከር ነው። ህዝቡ ሰላሙን አስከብሮ፣ ህግ እና ስረዓትን በጠበቀ መልኩ ሌቦቹን እና ነፈሰ ገዳዮቹ ወደ ህግ እንዲቀርቡ ከለውጥ ኃይሉ ጋር መስራት እና የአገሩ ባለቤት መሆን ነው። ይህ ምዕራፍ እንደ ሁኔታው ከአንድ እስከ ሁለት አመት ልፈጅ ይችላል።

Step Three: Holding all-inclusive National State Building and Nation Building Campaign

ሶስተኛው የትግሉ ምዕራፍ ገና አልተጀመረም። የሶስተኛው የትግል ምዕራፍ የኢትዮጵያ የመንግስት ተቋማትን ከተደራጁት ሌቦች እና ነፈሰ ገዳዮች ነፃ ከወጣን በኋላ ወደ state building እና nation building ስራ መሸጋገር ነው። የኢትዮጵያ የመንግስት ተቋማት ባለፉት 27 ዓመታት የህወሃት አገዛዝ ፈራርሰው ወድቀዋል። በተደራጁ ሌቦች እና ነፈሰ ገዳዮች ተሞልተው ህዝባዊና አገራዊ ተልዕኳቸውን ስተዋል። ኢህዴግ እና ከፖላቲካ ድርጅቶች ገለልተኛ መሆን የነበረባቸው የመንግስት መዋቅሮች አንድ ሆነዋል። የመንግስት የፀጥታ መዋቅር እና ኢህዴግ አንድ ናቸው። የህዝብ እና የቤት ቆጠራ ሁኔታዎች ሳይረጋጉ አሁን ማድረግ አይቻልም። በዚህ አኳኸን በኢትዮጵያ ዲሞክራሳዊ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም። ከተቻለም በተቀዋሚ ልመራ የሚችል ቢሮክራሲና የፀጥታ ኃይል አሁን በኢትዮጵያ የለም። ስለዚህ በሚቀጥሉት አምስት አመታት የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል የኢትዮጵያ መንግስት ተቋማትን መልሶ መገንባት (state building) መሆን አለበት። ይህ ብቻ አይደለም። የኢትዮጵያ ማህበራዊ እሴቶች ፈርሰዋል። ቤተ እምነቶች እና የግል ንግድ ድርጅቶች ሳይቀሩ የሌቦች እና አጭበርባሪዎች ጎሬ ሆነዋል። በሌቦቹ እጅ ያለው የውሸት ኢኮኖሚ እንጂ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፈርሷል። የትምህርት ተቋማት ሙሉ በሙሉ ፈርሰው የውሸት ዲፕሎማ ፋብርካ ሆነዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ መካከል መለያየት እና መከፋፈል ሰፍኖ፣ በባንድራ፣ በአገር መጠሪያ ስም፣ በታርክ፣ በሥራ ቋንቋ፣ በአገሪቷ ወደ ፊት አቅጣጫ እና በበርካታ ጉዳዮች ላይ ስምምነት የለም። ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ በነዚህ ነገሮች ሁሉ ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ብርቱ የአገር ግንባታ (nation building) ስራ ይጠብቀዋል። በጠቅላይ ሚንስትር አብይ የሚመራው መንግስት የኢትዮጵያን ህዝብ በዚህ ወሳኝ እና እጅግ አስፈላጊ የ state building እና nation building ምዕራፍ ለመምራት ብቃቱም ሆነ ራዕው እንዳለው ሙሉ እምነት አለኝ። የሚፈለገው የኢትዮጵያ ህዝብ የዚህን ትግል ምዕራፍ እጅግ አስፋላጊነት ተረድቶ ግራ፣ ቀኝ ሳይል ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከጎናቸው መቆም ብቻ ነው።

Step Four: Establishing the Government of the People through Democratic Election.

አራተኛው የትግል ምዕራፍ በኢትዮጵያ ዴሞክራሳዊ ምርጫ በማካሄድ ህዝባዊ መንግስት ማቋቋም ነው። ይህ ማለት የፖላቲካ ስልጣን ምንጩ የኢትዮጵያ ህዝብ የሆነ መንግስት ዴሞክራሳዊ የሆነ ምርጫ በማድረግ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ማቋቋም ማለት ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ በሁለተኛው እና በሶስተኛ ምዕራፍ የተመከከቱትን የትግል ምዕራፎች አሁን እየሄደ ባለው መልኩ በጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት ጎን ቆሞ በድል ከተወጣ በአጭር አምስት አመታት ጊዜ ውስጥ ከዘመናት አዙሪት ወጥቶ ህዝባዊና ዴሞክራቲ መንግስት እንደምያቋቁም ጥርጥር የለኝም። ኢትዮጵያም ከአለም የበለፀጉት እና ዴሞክራቲክ አገሮች ጎራ ትቀላቀላለች።

ይህ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ከላይ የተቀመጡትን አራት የትግል ምዕራፎች በሚገባ ተረድቶ ኢትዮጵያን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመለወጥ እና ከዘመናት የደም መፋሰስ እና የዝርፊያ ፖላቲካ ለማውጣት በሚቀጥሉት አምስት የትግል አመታት ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት ጎን በቁርጠኝነት ከቆመ ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብም ይህን ስትራቴጂክ አካሄድ ተረድቶ የጀመረውን ትግል ከግቡ እንደሚያደርስ ጥርጥር የለኝም።