ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው

መንግሥት ጠበቃ ያቁምልኝ የሚለውን ጥያቄ ያልተቀበለው ፍርድ ቤት የራሳቸውን ጠበቃ እንዲያቆሙ በወሰነው መሠረት ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ከጠበቃቸው ጋር ዛሬ ከሰዓት በኋላ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል።

ጠበቃቸው ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት ደንበኛቸውን በፖሊስ ታጅበው ካልሆነ ለብቻቸው ማግኘት ስላልቻሉ ለብቻቸው እንዲያገኟቸው እንዲያደርግ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

ዳኛው በበኩላቸው ጠበቃው ያለ ፖሊስ ደንበኛቸውን ሊያገኙ እንደሚገባና፤ የፖሊስ ሚና ደህንነትን የማስጠበቅ ብቻ እንደሆነ ገልፀዋል። ጠበቃቸው ከሜጀር ጀነራሉ ጋር በፍርድ ቤቱ ውስጥ ለብቻቸው እንዲወያዩም ፈቅደውላቸዋል።

የአቶ ክንፈ ጠበቃ የደንበኛቸው ጉዳዩ በፍርድ የተያዘ ሆኖ ሳለ እስከ ትናንት ድረስ በዶክመንተሪና በተለያዩ መንገዶች በሚዲያ መተላለፉ ፍትሀዊ ዳኝነት የማግኘት ዕድላቸውን በሚያጠብ መልኩ እንደሆነና አሁንም አግባብ ባልሆነ መንገድ ሚዛናዊ ያልሆኑ የሚዲያ ሽፋኖች እየተሰጡ እንደሚገኙ አውስተዋል።

ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ዘገባዎችን በተመለከተ ዝርዝር ማስረጃ በማቅረብ ራሱን የቻለ ክስ ሊቀርብ ይችላል፤ በዚህ ችሎት ግን የሚታይ አይሆንም ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

ሜጀር ጄኔራል ክንፈ: ‘‘ቤት የለኝም፣ መኪና የለኝም፣ ንብረት የለኝም፤ ያለኝ ሰውነቴ ብቻ ነው’’

ኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ተነሳ

የህግ የበላይነት ሳይሸራረፍ እንዲተገበር የሚጠይቀው የትግራይ ክልል መግለጫ

አቶ ተስፋ ኡርጌ

በሰኔ 16ቱ የቦምብ ፍንዳታ የተጠረጠሩት አቶ ተስፋዬ ኡርጌ አዲስ የሙስናና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ክሶች ቀርበውባቸዋል። ከቀረቡባቸውም የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መካከል ሰዎች በካቴና እየታሰሩ ቆሻሻ ቦታ ላይ እንዲጣሉ፣ በጉንዳን እንዲበሉ፣ በሽብርተኝነት ተጠርጥራችኋል በሚል ከግለሰቦች ገንዘብ በመውሰድ፤ መልምለው ወደ ኤርትራ በመላክ ሽብርተኛ ማስባል ወንጀሎች ተጠቅሰውባቸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ግለሰቦችን ከአምስት ወር ላላነሰ ጊዜ በይፋ የማይታወቁ ሕገወጥ ስውር ቤቶች ውስጥ እንዲታሰሩ አድርገዋል የሚል ተጨማሪ ክስ ቀርቦባቸዋል።

ግለሰቦች ታስረውም ሰብዓዊ መብታቸው እንዲገፈፍ በማድረጋቸው፤ ብዙዎች አካል ጉዳተኛ ከመሆን በተጨማሪ እንዲሞቱ ምክንያት እንደሆኑም ተገልጿል።

አቶ ተስፋየ ኡርጌ በበኩላቸው ማንንም አስረውም ሆነ ገርፈው እንደማያውቁና፤ ሀብትም ቢሆን ሕገ መንግሥት ከፈቀደላቸው ሀብት የማፍራት መብት በላይ ሌላ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልፀዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤት በአቶ ተስፋዬ ኡርጌ ላይ ፖሊስ የጠየቀውን 14 ተጨማሪ ቀናት ፈቅዷል።

ሰዎችን በማስፈራራት በቁጥጥር ሥር የዋሉት የኢትዮቴሎኮም የሴኪውሪቲ ዲቪዥን ኃላፊ አቶ ጉደታ ኦላናም የመንግሥት ሠራተኛ በመሆናቸው በራሳቸው ጠበቃ ማቆም እንደማይችሉ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

አራተኛው ተከሳሽ የሆኑት ኮሎኔል ሰጠኝ ካህሳይም በወር የሚያገኙት 5ሺህ ብር መሆኑን ጠቅሰው ጠበቃ ማቆም እንደማይችሉ ተከራክረዋል።

አቶ ኢሳያስ ዳኘው

ከዚህ ቀደም በራሳቸው ጠበቃ ማቆም እንደማይችሉ ለተናገሩት የሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ወንድም አቶ ኢሳያስ ዳኘው ፖሊስ አለኝ ያለውን ማስረጃም አቅርቦ ለፍርድ ቤቱ አሰምቷል።

በራሳቸው ስም በፀረ ሙስና ኮሚሽን የሐብት መዝገብ ቅፅ ላይ ራሳቸው ያስመዘገቡት ዝርዝር 2 ሚሊየን ብር የሚያወጣ ባለ አንድ ፎቅ ቤት በራሳቸው ስም የተመዘገበ፣ በባለቤታቸው ስም የተመዘገበ 6 ክፍል ያለው ቤት፣ 115 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ የጋራ ሕንጻ፣ 240ሺህ ብር የሚያወጣ ቶዮታ ኮሮላ፣ ግምቱ 1 ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺ የሆነ ሎደር፣ የአንበሳ ባንክ ባለድርሻ፣ በንግድ ባንክ፣ በዳሸንና በአዋሽ ባንክ በርካታ ገንዘብ መቆጠባቸውን ማረጋገጡን ፖሊስ ተናግሯል።

ፖሊስ ግለሰቡ ከሀገር ሊሸሹ ሲሉ አየር መንገድ ላይ በቁጥጥር ሥር እንዳዋላቸው ጠቅሷል።

የተከሳሽ ጠበቃ በበኩላቸው ሀብቱ የተመዘገበው በ2003 ዓ.ም መሆኑን ጠቅሶ አሁን ሀብቱ ለሌላ ተላልፎ ወይም ተሽጦ መሆን አለመሆኑን በተጨባጭ ስለማያሳይ የተከላካይ ጠበቃው አገልግሎት መቀጠል አለበት ሲል ተከራክሯል።

ባለቤታቸው በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ እንደሆኑና ሎደሩም የባለቤታቸው ነው በማለትም አስረድቷል።

ፖሊስ በበኩሉ ሀብቱ በ2003 ቢመዘገብም በየሁለት ዓመቱ ሀብቱ መኖር አለመኖሩን የማሳወቅ ወይም የማደስ ኃላፊነት ነበረባቸው፤ ይህንን ካላደረጉ ንብረቱ እንዳለ ነው የሚቆጠረው በማለት ተከራክሯል። በተጨማሪም የባልና ሚስት ሐብት የጋራ ሀብት ነው ይህንንም ራሳቸው መዝገብ ያሰፈሩት በፈቃዳቸው ነው ሲል አስረድቷል።

ፍርድ ቤቱም ተከሳሽ በቂ ሀብት ስላላቸው ከዛሬ ጀምሮ መንግሥት ያቆመላቸው ጠበቃ ተነስቶ በራሳቸው ጠበቃ በማቆም እንዲከራከሩ ውሳኔ አስተላልፏል።

ፖሊስም በፍርድ ቤቱ ፊት በሀሰት ምለው የግል ጠበቃ ለማቆም ገንዘብ የለኝም በማለታቸው አስተማሪ ቅጣት እንዲጣልባቸውም ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱ መርማሪ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜን ፈቅዷል።