Source: https://fanabc.com/2018/11/

አዲስ አበባ፣ ህዳር 11፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አሜሪካ በዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት (ኢንተርፖል) ሀላፊ ምርጫ ውስጥ ጣልቃ እየገባች መሆኑን ሩሲያ አስታወቀች።

እንደ ክሬምሊን ወቀሳ የአሜሪካ ሴናተሮች ቡድን አስተባባሪነት ሩሲያ ባቀረበችው እጩ ላይ ህዝባዊ ተቃውሞ እንዲበረታ ግፊት እየተደረገ ነው።

የኢንተርፖል ጠቅላላ ጉባዔ በነገው እለት በሚያደርገው ስብሰባ ነው የተቋሙን አዲስ መሪ እንምደሚመርጥ የሚጠበቀው።

የአሜሪካ ሴናተሮች ቡድን ግን ሩሲያ በእጨነት ያቀረበቻቸው አሌክሳደር ፕሮኮፕቸክ እንዳይመረጡ እየሰሩ መሆኑ ነው የተነገረው።

በትናንትናው እለትም አራት የአሜሪካ ሴናተሮች ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሩሲያ ለኢንተርፖል ሀላፊነት በእጩነት ያቀረበቻቸውን አሌክሳደር ፕሮኮፕቸክ በይፋ እንዲቃወሙ በመጠየቅ መግለጫ አውጥተዋል።

እንደ ሴናተሮቹ ገለፃ ሩሲያ የኢንተርፖል አሰራሮችን ትጥሳለች፤ አሌክሳደር ፕሮኮፕቸክ ኢንተርፖልን እንዲመሩ ከተመረጡ ደግሞ ሁኔታዎችን የበለጠ ምቹ ያደርግላታል ይላሉ።

ሩሲያ በበኩሏ የአሜሪካ ሴናተሮች እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ በኢንተርፖል ሀላፊ ምርጫ ላይ ጣልቃ ገብነት ነው ስትል ከሳለች።

አሌክሳደር ፕሮኮፕቸክ የሜጀር ጄነራልነት ማእረግ ያላቸው ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅትም የሩሲያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኢንተርፖል ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ነው በማገልገል ላይ የሚገኙት።

በኢንተርፖል ፕሬዚዳንትነት ምርጫ ውስጥም ትልቁን ግምት አግኝተዋል።

ምንጭ፦ www.reuters.com