በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለረጅም ጊዜ ታጥረው በቆዩ ቦታዎች ንብረታቸውን በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ባላነሱት ላይ እርምጃ መውሰድ ተጀመረ። የከተማ አስተዳደሩ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ፅህፈት ቤት የደንብ ማስከበር ፅህፈት ቤት ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በጋራ በመሆን እርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስታውቋል። በዚህም ያለ ልማት ለረጅም ጊዜ ታጥረው የቆዩ ቦታዎች ላይ የሚገኙ የአጥር ቆርቆሮዎችን ማንሳት መጀመሩን ገልጿል። አስተዳደሩ ባልለሙ ቦታዎች ላይ ንብረቶቻቸውን ያስቀመጡ አካላት ንብረታቸውን እንዲያነሱ ከሳምንት በፊት መግለጫ መስጠቱ የሚታወስ ነው። ይሁን እንጅ እነዚህ አካላት ንብረቶቻቸውን ማንሳት ባለመጀመራቸው ምክንያት አስተዳደሩ በዛሬው እለት ወደ እርምጃ መግባቱን ነው የገለጸው። አስተዳደሩ የህዝብን ሃብት ለተገቢው ልማትና ለነዋሪዎች ተጠቃሚነት እንዲውል በጀመረው ተግባር ህገ ወጥነትን እንደማይታገስና፥ ህግ የማስከበር ሃላፊነቱን እንደሚወጣ መግለጹን ከከተማዋ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል