ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለወቅታዊ ጉዳዮችና ዕጩ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ የሰጡት ማብራሪያ ጭብጦች፡-
• በምክር ቤቱ አሠራርና ውሳኔ በፍጹም ጣልቃ አንገባም፤ ለዚህም ነው ያቀረብናቸውን ዕጩዎች ውድቅ አድርጋችሁብን ሌላ ዕጩ ለማቅረብ የሞከርነው፡፡
• ጠንካራ ምክር ቤት እንዲኖር እየሠራን ነው፡፡
• ግጭቶችን በተመለከተ የተነሳው ሐሳብ እውነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ረዥም የመንግሥት ታሪክ ቢኖራትም ሰላማዊ መተካካት ያላዳበርን ነን፡፡ ልጅ እያሱ እንኳ ለግዞት ተዳርገዋል፡፡ በኋላም ከግዞት ተወስደው እንዲገደሉ ተደርጓል፤ ይህ የተደረገው በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ነው፡፡
• ኃይለስላሴ በደርግ ሲተኩ፣ ደርግም በኢሕአዴግ ሲተካ ተመሳሳይ የማስወገድ ባሕል ነበር፡፡ በደርግ ተገድዶ ወታደር የሆነን ልምድ ያለው ወታደር ሳይቀር አባርረናል፡፡
• አሁን ይህ ልምድ እየተገዳደረን ነው፡፡ ሰውን በወንጀል ልክ ለማሰር ከተፈለገ ሌላ ተጨማሪ ከተማ ያስፈልገናል፡፡ ከትላልቅ እስከ ትናንሽ ወንጀሎች ያልተነካካ የለም፡፡ መፍትሔ ዋና ዋና ወንጀል ላይ የተጠያቂነት አሠራር ማምጣት፡፡ የቀረውን በቅርቡ ለምክር ቤቱ በተመራው የእርቀ ሰላም ኮሚሽን በይቅርታ መሻገር ነው፡፡
• ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አስቀድሜ ሰው ሊያጋድላችሁ ስለሚችል ራሳችሁን ጠብቁ የሚል መልዕክት አስተላልፌ ነበር፡፡
• አሁንም ኢትዮጵያ ወደሰላምና ዴሞክራሲ ከሄደች እንጎዳለን ብለው የሚያስቡ አሉ፡፡ የቀጣዩ ምርጫም ዴሞክራሲያዊ እንዳይሆን የሚሠሩ አሉ፡፡ ሪፎርም እንደ ሪቮሉሺን በመግደል አይመጣም፡፡ ተፈትኖ መሻገርን ይጠይቃል፡፡
• የምዕራብ ወለጋ አካባቢ ሕዝብ ባገኘው አጋጣሚ ጭቆናን ሲፋለም የኖረ ነው፡፡ ይህ ሕዝብ አሁን የመጣውን ለውጥ በአሸናፊነት መንፈስ ተቀብሎ እንደሚጓዝ ተስፋ አለኝ፡፡ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም የሚታገለው ለዚህ ሰላምና ዴሞክራሲ ተስፋ ነው፡፡
• ወ.ሪት ብርቱካን ከፓርቲ ገለልተኛነታቸው ስለመረጋገጡ የተነሳውን ሐሳብ በተመለከተ ተረጋግጧል፡፡ ከነበሩበት ድርጅትም ከአመራርነትና አባልነት በፈቃዳቸው ከዓመታት በፊት ለቅቀዋል፡፡ እኔ አስፈጻሚ ሆኘ ስሾም እንደ አስፈጻሚ ላገለግል እንጅ እንደ ኢሕአዴግ ላገለግል አይደለም፡፡
• ከዚህ ቀደም የነበሩ የምርጫ ቦርድ አመራሮችም የኢሕአዴግ አባል አልነበሩም፤ ገለልተኛ ግን ሆነው ተቋሙን እንዳልመሩት ታይቷል፡፡ ስለዚህ ዕጩዋም በፓርቲ አባል አለመሆናቸው ብቻ ሳይሆን አቅሙ ስላላቸው ነው ያቀረብናቸው፡፡
• ሌሎች የቦርዱን አመራሮች ያላቀረብነው ጊዜ እየቀደመን ስለሆነ ነው፡፡ ዛሬ እርሳቸውን ከሰየምን በቀጣይ ሳምንታት ሌሎች አባላትን አዘጋጅተው እንደሚያቀርቡ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ዜግነታቸውም የተረጋገጠ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ በዚሁ አጋጣሚ በርካታ ኢትዮጵያውያን ዴያስፖራቸው በሹመት ሳይሆን በፕሮጀክት እንዲያገለግሉ እያደረግን ነው፡፡
በርካታ የፖለቲካ ሰዎችም ተገድደው ይዘው የነበረውን ፓስፖርት ቀድደው ከመጡ እንቀበላለን፡፡ የማይፈቀደው የሁለት ዜግነት መያዝ ነው፡፡ እስራኤሎች ይህንን አድርገዋል፤ በርካታ ሀገራት በውጭ የሚኖሩ ዜጎቻቸውን በዚህ መልኩ ተጠቅመዋል፡፡ የኮሪያም ዕድገት በዚህ የመጣ ነው፡፡
• በየቀኑ አንድ ዶላር እየለገሱን ያሉ ሰዎችም ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህን ማሳተፍ ተገቢ ነው፡፡
• የፌዴራል መንግሥት ሲወስን ትክክል ሳይመስለው የሚቃወም፣ ተቃውሞውንም የሚናገር የክልል መንግሥት መኖሩ የሚፈለግና የተፈቀደ ነው፡፡ በዚሁ ልምምድ ነው ዴሞክራሲ የሚያድገው፡፡
በአብርሃም በዕውቀት