ከመኮነን  ተስፋየ  ፌስቡክ  የተወሰደ

ሁሌ እናስታውሳቸው
ተቀብሮ እንዳይቀር
አኩሪ ታሪካቸው!!!!!!!

ጌቱ ወርቁ፤ ዳንኤል ይመር፤ መብራት ደጋጋ፤ ተክሉ ተረዳ፤ ተስፋዬ ጌታነህ፤ በጋሻው ጥሩነህ፤ ጀማል ወልጫፎ እነማን ናቸው????

ከቀበሌ 12 ጀምሮ በኮረኔል ያለምዘውድ ተሰማ ቤት የተከናወነውን ሙሉ የ ቀይ ሽብር ድርጊት ፤ በወቅቱ በዛ አካባቢ በነበረ የኢሕአፓ አባል እንደተነገረው፡፡ ስሙም እንዳይገለጽ ስለፈለገ ከመግለጽ ተቆጥበናል፡፡

ይህ ማስታወሻ በደብረ ዘይት ከተማ የተከናወነውን ዛሬም ድረስ እንደ ቅርብ ጊዜ እንደተከናወነ ድርጊት ወለል ብሎ የሚታየኝን እውነት ለመግለጽ የቀረበ ነው።” ብሎ ይጀምራል…………

ወቅቱ ደርግ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በሀገሪቱ ውስጥ ቀይ ሽብር በማለት የወጣቶች ደም እንደጎርፍ ይፈስ የነበረበት ጊዜ ከመሆኑ የተነሳ በአብዛኛው የኢሕአፓ መዋቅር የተበጣጠሰበት ጊዜ ነበር። ብዙዎቻችን ምን ማድረግ እንዳለብንና ቀጣይ ሁኔታው ምን እንደሆነ ለመገመት በማንችልበት ሁኔታ እያለን የኢሕአፓ መዋቅር በወንድማገኝ ጌታቸው (ወንዲቲ) አማካይነት እደወጣ መረጃዎች ተላለፉ።በጊዜው አብዛኛዎቻችን የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የነበርን ሲሆን በተለያየ መዋቅር ውስጥ ብንሰራም በኢሕአፓነታችን ስለምንተዋወቅ ት/ቤት ጓደኛችን ከቀረ እንደተያዘ ወይም እንደጠፋ መቁጠር ጀመርን።በጊዜ ሂደት ዋናዉ እስር ቤት ቀበሌ 12 መሆኑን አወቅን።እኔም እለት በእለት የምሰማው መረጃ የከተማው መዋቅር እንዳለ መመታቱንና አብዛኛው አባላት መታሰራቸውን በመሆኑ የሚመጣውን መጠበቅ ጀመርኩኝ።በእጄ የሚገኙ ጥቂት የዲሞክራሲያ ዕትሞችን ሽንት ቤት ጨመርኩኝ። በአንዱ ቀን አብሮኝ በተማረ ጠቋሚ አማካይነት ተይዤ በቀጥታ ቀበሌ 12 እስር ቤት ገባሁ።ከትንሽ ጊዜ በኋላ ለምርመራ ተወሰድኩኝ።በምርመራ ክፍሉ ከወንዲቲ ጋር ፊት ለፊት ተገናኘን። ስሜቴ ተደበላለቀብኝ። እሱም ከሰላምታ በኃላ ምንም ነገር አንዳልደብቅ ሁሉም ነገር ያበቃ መሆኑን እየገለጸልኝ በእስኩየር ወረቀት ላይ የተሳለውን የድርጅቱን መዋቅር ፊቴ ዘረጋልኝ። መዋቅሩን ስመለከት ዐይኔ በቅድሚያ የግርማ ብሩ በመቀጠል የራሴን ጨምሮ በአባልነት በአብሮአደግነት በጓደኝነት የማውቃቸው ዝርዝር ተመለከትኩኝ።በዚህ መሀል ወንዲቲ ወረቀትና ካርቦን በእስፒል እያያዘ እያለ ጨካኙ ገራፊና የቀበሌው ሊቀ መንበር መቶ አለቃ አካለወልድ ወደ ክፍሉ ገባ። ባየኝ ጊዜ አባቴን ያውቀው ስለነበር እንዴት የሱ ልጅ ሆነህ የዚህ አይነት ነገር ውስጥ ትገኛለህ በሚል ሰሜት ክፉኛ ወቀሰኝ። በመቀጠል ቃል የመስጠቱ ሁኔታ ተጀምሮ ቃሌ ለመሆኑ በመፈረም ተጠናቀቀ።የገረመኝ ነገር ቢኖር ወንዲቲ እያንዳንዱን የድርጅቱን ጉዳይ እንዴት ሊያውቅ እንደቻለ ነው። በእርግጥ በነበረን ግንኙነት በመዋቅሩ ውስጥ የበላይ አመራር ውስጥ እንደሚገኝ በሁኔታዎች መነሻነት በቅርብ ጓደኛሞች ቢታወቅም ከራሱ ድርሻ አልፎ ይህን ያህል የድርጅቱን የዲስፕሊን በጣሰ መልክ መረጃዎችን በተለይ የአባለትን ስም ከነስራድርሻቸው ያውቃል ተብሎ አይገመትም።ይህ ሁኔታ ደግሞ የድርጅቱ መዋቅር በፍጥነት እንዲፈራርስ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነበር።ቃል የመስጠት ሁኔታ ከተጠናቀቀ በኋላ ወደክፍሌ ተመለስኩኝ። እኔ በነበርኩበት ክፍል አቶ ጤራ፤ ማንነገረው አበበ(ከአየር ኃይል)እና አሁን የማላስታውሳቸው ሰዎች ነበሩ። በጎናችን ባለው ክፍል የሴት እስረኞች የነበሩ ሲሆን የሌሎቹ አስተዋጽኦ እንዳለ ሆኖ ጀግናዋና ከፍተኛ ድብደባ እንዲሁም ስቃይ የተቀበለችው ፍሬህይወት ተሰማ(ፍሬ) በዚህ ክፍል ትገኝ ነበር። ፍሬ የስኳድ አባል የነበረች ሲሆን ቶርቸር ስትደረግ ሚስጥር አላወጣም በማለቷ ገራፊዎቿ ሽጉጥ ጉሮሮዋ ላይ አስደግፈው ሲተኩሱ በተአምር ከሞት የተረፈች ሲሆን የባሩዱ ጨረፍታ በጉሮሮዋ ላይ ጠባሳ ትቶ ያለፈባት ነች።”

ሁኔታው በዚህ እንዳለ የተለያየ አዳዲስ እስረኞች እየተያዙ የሚመጡ ሲሆን አንድ ቀን ግን ያየሁት ሁኔታ አስደነገጠኝ።ለመፀዳዳት ስንወጣ አሁን በህይወት የሌለው ማርስ ጣሴ በከፍተኛ ሁኔታ ተደብድቦ ፊቱ አባብጦ ያገኘሁት ሲሆን ያስደነገጠኝ ግን አባቱ ከሱ ባልተናነሰ ሁኔታ ተደብድበዉ ግልጽ በሆነው የመፀዳጃ ስፍራ ማየቴ ነበር። እሳቸውን ስመለከታቸው ይበልጥ ልቤን የሳዘነው ደብረ ዘይት ከተማ የአየር ኃይል ነች የምትባል ከተማ ስትሆን የአብዛኛው የከተማ ህይወት የተያያዘ ነው። ታዲያ በአየር ኃይል ውስጥ አብረዉ በሚሰሩዋቸውና አንድ ቀበሌ ነዋሪ በሆኑት በነአካለወልድ እጅ የአቶ ጣሴ መገረፍን ማየቴ በወቅቱ ለድንጋጤ ዳርጎኛል። ሌላው ትግልን በተመለከተ አመለካከቴን የቀየረው ለመፀዳዳት ስንወጣ ጀርባችንን በዱላየሚቀጠቅጡንና አናርኪስቶች እያሉ የሚሰድቡን የአብዮት ጥበቃ ተግባር ነበር። ይህ ሁኔታ የTower in the sky ፀሀፊ ሕይወት ተፈራ በኩየራ በተያዘችበት ወቅት ሚሊሻዎች ካልገደልናቸው ባሉበት ሰዐት ለራሷ ከጠየቀችው ጥያቄ ጋር ይመሳሰላል። ይህ ጉዳይ ከተነሳ የማልረሳው አብዮት ጥበቃ ዘለቀ ነው። ዘለቀ ተሳዳቢና ሲጋራ አጫ ሽ ሲሆን በእኛ መታሰር የሲጋራ ገበያው የደራለት ሆኗል። ከጉሬዛ ሲጋራ በቀጥታ ወደ ዊንስተንና ኬንት ተሸጋግሯል። በበር ቀዳዳ ሰማችንን ይጠራና ዛሬ አንድ ፓኬት ተልኮልሀል ይለንና ስድሰት ፍሬ ይሰጠናል። ማታ ደግሞ አራት ፍሬ ይሰጠንና ጨርሰሀል ይላል።ይህ በእንዲህ እንዳለ በአንዱ ቀን የታይፕ ቤት ባለቤት የነበረው ዲበኩሉ ተይዞ ወደ እኛ ክፍል እንዲገባ ተደረገ።እንደገባም የለበሰውን ኮት ተቀብለነዉ ቁጭ ካለ በኃሏ ምን ማድረግ እንዳለበት ለመምከር ለምን እንደተያዘ ጠየቅነው። ዲበኩሉ በተፈጥሮው ኮራ የሚል ሰው ስለሆነ ለእኛ ለታናናሾቹ መልስ መስጠት አልወደደም።ይህን ያዩ አቶ ጤራ ቀረብ ብለው ሊያናግሩት ሞከሩ።”

በነገራችን ላይ ስለ አቶ ጤራ ሻመና መዘከር የግድ ይላል። አቶ ጤራ በንግድ ስራ የሚተዳደሩ ቀበሌ 14 ከቤተመንግስት ወደ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን መሄጃ መንገድ ዳር ላይ ሱቅ ያላቸውና ኑሯቸውን በቀበሌ 13 ያደረጉ ትልቅ የቤተሰብ ኃላፊ ነበሩ። ልጆቻቸው ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታ የኢሕአፓ አባላትና ደጋፊዎች የነበሩ ሲሆን ቤታቸውም ለድርጅት ስራ እንደሚውል አልፎ አልፎም ከሌላ ሰፍራ የመጡ አባላት እንደሚያርፉበት ይጠረጠር ነበር። በስተመጨረሻም በደረሰ ጥቆማ ቤታቸው ሲከበብ አሰግድ የተባለ ልጃቸው በከባቢዎቹ ላይ ተኩስ በመክፈት ወንድምና እህቶቹን ካስመለጠ በኃላ በያዘው መሣሪያ ራሱን ሊያጠፋ ችሏል።በዚህ ክስተት ቤተሰቡ እንዳለ የተበተነ ሲሆን አቶ ጤራና ባለቤታቸዉ ለእስራት ተዳርገዋል። ይህ ክስተት በከተማው የወሬ ምንጭ ሆኖ የተገኘ ሲሆን በቤታቸው ግቢ ውስጥ የነበረው ጉድጓድ ደግሞ የኢሕአፓ ምሽግ ነው በመባሉ ለደርግ አቀንቃኞች ጥሩ የፕሮፖጋንዳ መሣሪያ ሆኖ ነበር።በእርግጥ ይህ ጉድጓድ ለማቴሪያሎች ማስቀመጫ ይውል የነበር አሰራሩ ግን ለእህል ማስቀመጫ የተሰራ መጠነኛ ጉድጓድ ነበር።አቶ ጤራን ባገኘኋቸው ወቅት ከፍተኛ ድብደባ በተለይም እግራቸው ላይ ደርሶባቸዋል ።ይህ ሁሉ ሆኖባቸው የነበራቸው የመንፈስ ጥንካሬ መገመት ከሚቻለው በላይ ነው። በስተመጨረሻም የቀይ ሽብር ሰለባ ሲሆኑ ልጆቻቸውም በስደት ከነበሩበት ስፍራ ተይዘው መጥተው ከታሰሩ በኋላ ተለቀው ከባለቤታቸውና ከመጨረሻው ልጅ ቴዎድሮስ በስተቀር በህይወት ይገኛሉ።እኚህ አባት የልጆቻቸውን ተሳትፎ በመገንዘብ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ በማድረጋቸው ለነበረው ትግል ድጋፍ አድርገዋል ማለት ይቻላል። በዚህም አጋጣሚ የተለያየ ጽሁፍ በማቅረብ የሚታወቀው ገዛኸኝ ጤራ ስለቤተሰቡና ኢሕአፓ እንዲጽፍ ለማሳሰብ እወዳለሁ። ለእኔ ግን ባሰብኳቸው ጊዜ የተገረፉት እግሮቻቸውና በከንፈራቸው ላይ ያለው ልዩ ምልክት እንዳስታውሳቸው ያደርገኛል።”

ወደ ጀመርኩት ጉዳይ ስመለስ ዲበኩሉ የሰጠው መልስ ምንም በማያውቀውጉዳይ ተይዞ እንደመጣ ብቻ ነው።ከዚህ በኃላ ከቤተሰቦቻችን የሚመጣልንን ምግብ ሳይሆን ከአብዮት ጥበቃዎች ተርፎ የሚመጣልልን እራት ለመብላት በቡድን በቡድን ተሰበሰብን። ዲበኩሉ እራት እንዲበላ ብንጠይቀው ወንጀሌን ካላወኩኝ አልበላም አለ። በዚህ መሀል ሌላው ጨካኝ ገራፊ የአስር አለቃ ደበበ ክፍላችንን ከፍቶ ገባ።የአስር አለቃ ደበበ እጄን አልሰጥም በማለት እነሱ በጥይት እሱ ግን በድንጋይ ተፋልሞ ሆራ ሀይቅ ላይ የወደቀው የጀግኖች ጀግና የሆነው የፅጋአብ በርሄን የድንጋይ በትር የቀመሰ ጨካኝና አረመኔ ሰው ነበር። ፅጋአብ በወረወረው ድንጋይ የእግሩ ሎሚ ተመቶ አንካሳ ሆኖ የቀረ ሲሆን ኢህአዲግ የአየር ኃይልን ግቢ ሲቆጣጠር ምናልባትም ለበቀል ነው በሚባል ሁኔታ ግንባሩን በጥይት ተመቶ አስከሬኑ ጥሻ ውሰጥ አብጦ ተገኝቶ ያለቀባሪ የተቀበረ ነው። ለምን አትበላም ይለዋል። ዲበኩሉ ጨጓራዬን አሞኛል አለ። ገና ጨጓራህ ይዘረገፍልሀል የሚል ዛቻ ከደበበ ተሰነዘረ።ያለውም አልቀረም ከምሽቱ ወደ ሦስት ሰዐት ወስደው ገርፈው አምጥተው ወረወሩት። እግሩ ደም በደም የሆነ ሲሆን የሚያሰማው ድምፅ ወንድ ልጅ….ወንድ ልጅ….የሚል ነበር።አዎ በጨካኞች እጅ ከመንገድ ተይዞ ግርፋት ሲደርስበት ሊያሰማ የሚችለው የቁጭት ድምፅ ይህ ዐይነት ብቻ ነው።”

በመቀጠልም ይህ ማስታወሻ በደብረ ዘይት ከተማ የተደረገውን የቀይ ሽብር በተመለከተ በዚያ በመጨረሻ ምሽት የነበረውን ሁኔታ ለመግለጽና የሞት ጽዋ ለመጨለጥ የተዘጋጁ ጀግኖች ተጠርተው ሲሄዱ በእንዴት ዐይነት ሁኔታ እንደሄዱ ለማስታወስና መስዋዕትነታቸውን ለመዘከር የቀረበ ነዉ። ማስታወሻው የሟች ወንድሞቼን ቤተሰቦች ኃዘን ለመቀስቀስ ያልቀረበና የሚጠቀሱትም ስሞችም ከነበረው ሁኔታ አኳያ መጠቀስ ስላለበት ብቻ እንደተጠቀሰ ግንዛቤ እንዲወሰድበት በአክብሮት እጠይቃለሁ።”….ብሎ ይቀጥላል…. “በደብረ ዘይት ከተማ የቀይ ሽብር ከመፈጸሙ በፊት በከተማዋ የነበረው የኢሕአፓ መቅር የተመታ ሲሆን አባላቱም በቀበሌ 12 /ቤት በቅድሚያ በመቀጠልም በኮ/ል ያለምዘውድ ተሰማ ቤት ዉስጥ እንዲታሰሩ ተደርጎ ነበር። በእዚህ እስር ቤት ኢሕአፓን አስመልክቶ የቤዚክ፤ የሰብ ሪጅን፤ የሪጅንና የፓርቲው የእስኳድ አባለት ታስረው ይገኙ ነበር። ይህ አወቃቀር የቀበሌ ፤ የክ/ከተማና የወረዳ ኮሚቴ ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል ። የኢሕአፓ መዋቅር እንዲመታ ወይም እንዲፈርስና አባላቱም ከከተማውና ከተሸሸጉበት ስፍራ ተይዘው እንዲመጡ ወንድምአገኝ ጌታቸው(ወንዲቲ)፤ ተስፋዬ ለገሠ ተሳትፏቸው ከፍተኛ ነበር። ግርማ ብሩ የሪጅን ኮሚቴ አባል የነበረ በመሆኑ የሪጅኑን ሰብሳቢ ወይም ከማዕከላዊ የሸዋ ሪጅን ኮሚቴ ጋር አገናኝ የነበረውን ዘውገ ወ/ዮሐንስ ከግብፅ ኤምባሲ ወይም ኮፊ ሀውስ አካባቢ ተይዞ እንዲመጣ አስተዋጽኦ አድርጓል ተብሎ ይገመታል። የእኔ ድርሻ የለበትም ካለም በተጨባጭ ማስተባበል ይጠበቅበታል።”

በዚህ አጋጣሚ ግርማ ብሩ የኢሕአፓ አባል ሆኖ Double agent በሚል ስም የወዝ ሊግ አባል የነበረ ሲሆን በእስር ቤትም የተለየ እንክብካቤ በመንጥር ኮሚቴ ይደረግለትና ከእስረኛ ክፍሉም እየተጠራ ሄዶ ከኮሚቴው ሊቀ መንበር እንዲሁም የአብዮታዊ ሰደድ አባል በኃላም በደርግ ከተገደለው ማ/ቴክ አበበ አረጋ የረዥም ጊዜ ቆይታ ያደርግ ነበር። ግርማ ብሩን በተመለከተ መንጥር ኮሚቴ ፊት ቀርቤ እንዲህና እንዲህ አልኳቸው፤ ተከራከርኳቸው እያለ Inspirational ንግግር ሲያደርግ በቅንነት የተቀበላችሁ ዛሬ በደረሳችሁበት ግንዛቤ ሀሳብ እንድትሰጡ እጠይቃለሁ ።” “ከነበሩበት ስፍራ ተይዘው ከመጡት መካከል ጀማል ወልጫፎ፤ ጌቱ ወርቁ ከላይ የጠቀስኩት ዘውገ፤ ተስፋዬ ጌታነህ ይገኙበታል። የአየር ኃይል የኢሕአፓ መዋቅር ውስጥ ከነበሩት ወስጥ በቅድሚያ የሚጠቀሰው ማንነገረው አበበ፤ ዓለማየሁ ዘውዴ (የተፈራ ላሽ ወንድም አሁንአሜሪካ የሚኖር) አበረ ምትኩ፤ አሰፋ አርጋው (የብሔራዊ ቴያትር ሥራ አስኪያጅ ሆኖ የነበረ)ዮሴፍ( ፋርማሲስት)፤ ነጋሽ (ላብ ቴክኒሽያን)፤ ለማ በላይነህ፤ ዐባይነህ፤ አጥናቸው፤ መሽሻ፤ ዐቢይ፤ መሉጌታ፤ ዓለማየሁ ብሩ (አአዩ የፍልስፍና መምህር ሆኖ የነበረና ጀርመን ሄዶ የቀረ)፤ከአየር ኃይል እንዳለ ጀበራ(የእንግሊዝኛ አክሰንቱ በጣም የሚያምር)ኃይሉ ከበደ ኤር ኮሌጅ ውስጥ በጣም ጎበዝ ተማሪ የነበር፤ ጥላሁን አሁን አየር መንገድ ካፕቴን(አየር ኃይል ፓይለት የነበረ አውሮፕላኑ ተመታ በሻዕቢያ የቆየ ከዚያም እንደገና በረራ ጀምሮ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት አልዋጋም ብሎ የታሰረ) እና እስክንድር ይገኙበታል።”

በዚህ እስር ቤት ሴት አባላት የእሰኳድ ጨምሮ ይገኙ ነበር። በግንባር ተጠቃሽ የሆነችውና በምርመራ ወቅት ብዙ ስቃይ የተቀበለችው ጀግናዋ ፍሬህይወት ተሰማ፤ ድንበሯ መርጊያ፤ አልማዝ ከበደ፤ እምወድሽ ከበደ፤ ዘላለም ግዛው፤ ሰዓዳ ኑሩ፤ ቀለሟ ዳማ፤ መሠረት ሣህሌ፤ እቴነሽ አበበ፤ መሠረት ምንዳ፤ አስራት መኩርያ ይገኙበታል። የዘነጋዋቸው ካሉ ይቅርታ እጠይቃለሁ። በአብዛኛው በሚባል ሁኔታ በመዋቅሩ ውስጥ የነበረ አባል ከታሰረ በኃሏ የሚወሰደውን ዕርምጃ ህጋዊ ለማስመሰል በታሰበ መልኩ የመንጥር ኮሚቴ ተቋቋመ ።ይህ ኮሚቴ በማን ትዕዛዝ እንደተቋቋመ መረጃዉ ባይኖረኝም የማስታውሳቸው አባላት አበበ አረጋ ሊ/መንበር፤ መቶ አለቃ አካለወልድ (የብሔራዊ ቡድን እግር ኳስ ተጫዋች የነበረው የመሰለ አካለወልድ አባትና ኢህአዲግ ሲገባ በኬንያ በኩል ወጥቶ በስደት ሲኖር ቆይቶ አሁን ግን አሜሪካን ገብቶ ተደብቆ የሚገኝ)፤ የአስር አለቃ ደበበ፤ የሃምሳ አለቃ ንጉሤ ፤ ተስፋዬ አየር ኃይል ተላላኪ የነበረ፤ አለሙ የምግብ ድርጅት ሠራተኛ፤ ሸዋዬና አምሳለ (የሪንጎ ዳንስ ቤት ባለቤት)ነበሩ።”
ኮሚቴው የእያንዳንዱን ታሳሪ የፓለቲካ አቋም ለመለየትና ዴሞክራቲክ ነኝ ለማለት በመጥራት ያነጋግር ነበር።የሚጠየቀው ጥያቄ የጊዚያዊ ህዝባዊ መንግስት ፤ የኤርትራ ጥያቄ ቅኝ ግዛት ነው አይደለም፤ ደርግ ፋሽስታዊ ነው አይደለም፤ የዲሞክራሲ ጥያቄና የመሳሰሉት ነበሩ። እያንዳንዱ እየተጠራ አቋሙን የሚያስረዳ ሲሆን በአቋሙ ማለት በኢሕአፓ እምነት ላይ የቆመው በተደጋጋሚ እየተጠራ አቋሙን እንዲቀይር ጫናና ማስፈራራት ይደርስበት ነበር።ከነወንዲቲ ከዚህ በኃላ በአቋም መጽናት አደጋ ስላለው የያዛችሁትን አቋም ቀይሩ ከሚል የውስጥ መልዕክትና ከተስፋ መቁረጥ የተነሳ እንዳላችሁት ይሁን የሚል ሁኔታ ተፈጠረ።በዚህ ውስጥ ለአቋሜ የጸናሁ ነኝ፤ ኮሚቴው ፊት ቀርቤ እንዲህና እንዲህ ብዬ ይብሱኑ የኮሚቴውን አባላት በክርክር አሳመንኳቸው ሲል የነበረው ዋሾው ግርማ ብሩ ዘንድ ሳይሆን ወደ አንዲት የሴት ጀግና መልዕክት መጣ ።ይህ መልዕክት በኮሚቴው ዕውቅና ይሁን በራስ ተነሳሽነት በማይታወቅ መንገድ ለፍሬህይወት ተሰማ በወ/ሮ አምሳለ የኮሚቴው አባል በሆነችው በኩል የመጣ ነበር። የመልዕክቱ ይዘት ፍሬ በኮሚቴው ፊት ቀርባ በተደጋጋሚ ቀርባ ከላይ በተገለጹት ጥያቄዎች የኢሕአፓን አቋም በማንፀባረቋ በሚሰጣት የመጨረሻ ዕድል ተጠቅማ አቋሟን የማትቀይር ወይም የደርግን አቋም የማትቀበል ከሆነ እንደምትገደል የሚገልጽና መልዕክቱ እንዲደርሳት ጥረት እንዲደረግ የሚያሳስብ ነው።”

ከመልዕክቱ ይዘት የተነሳ መደናገጥን ፈጥሮ የነበረ ሲሆን አሁን በማላስታውሰው መንገድ መልዕክቱ ደርሶ ህይወቷን የታደገው ይመስለኛል። ወ/ሮ አምሳለ ግን ለምን ከኮሚቴው እውቅና ውጪ ኃላፊነት ወስዳ የፍሬን ህይወት ለመታደግ ተነሳች የሚለው የዘወትር ጥያቄዬ ሲሆን ድምዳሜዬ ግን ሀዘኔታና በፍሬ ጥንካሬ በመደነቅ በግል ሚስጥራዊ በሆነ መንገድ ለማዳን ያደረገችው ጥረት ነው ለማለት እችላለሁ።ከዚህ በኃላ የነበረን ህይወት ምን ይመጣ ይሆን በሚል ስሜት የሚመጣውን መጠበቅ ሲሆን ቀልዶችን ማውራትና ዘፈን መዝፈን ለግልም ቢሆን ለክፍል እስረኛ የነበረውን ጫናና መጥፎ ስሜት ለመቀነስ ይረዳ ነበር።ቤተሰቦቻችን ምግብና ልብስ ለጥበቃ ሰጥተው ከመሄድ ውጪ በአካል ስለማንገናኝ በውጪው አለም ምን እንደሚከናወን ምንም ዐይነት መረጃ የለንም።ታዲያ በአንድ ጥቁር ቀን በመንጥር ኮሚቴ አባላት ለየት ያለ እንቅስቃሴ መታየት ጀመረ።”

አንድ ዝግጅት ያላቸው በሚመስል ሁኔታ ይወጡ ይገቡ ነበር። ቀኑ አልፎ ወደአመሻሹ ላይ ዕለታዊ የመጸዳዳት ግዳጃችንን ለመወጣት ተሰለፍን። መፀዳጃ ቤቱ የሚገኘው በተለምዶ ሰርቪስ ክፍሎች ከሚባሉት በቀኝ አቅጣጫ የመጨረሻው ላይ ነው ። በዚህ መሀል አበበ አረጋ በትከሻው የሚያዝለውን ሰደፍ የሌለው AK-47 ጠመንጃውን ተሸክሞ ወደተሰለፍንበት አቅጣጫ አንዲት ፍርሃት የሚነበብባት ሴት ልጅ አስከትሎ መጣ።በሰልፉ ላይ አጭር የጸጉር ማበጠሪያ ይዞ ሳሳ ያለ ፀጉሩን እያበጠረ የሚገኘውን ጌቱ ወርቁን ጠርቶት ይዞት ከልጅቷ ጋር የመንጥር ኮሚቴ ቢሮ ወደሚገኝበት ትልቁ ቤት ይዞት ገባ።ትንሽ ቆይቶ ጌቱ ተመለሰ።እንደተመለሰም ምን ያመጣል ግፋ ቢል ገሎኝ ቀይ ሽብር ብሎ ጀርባዬ ላይ መለጠፍ ነዉየሚል ቆጣ የለ ንግግር ተናገረ። እኛም ደንገጥ ብለን ምን ተፈጠረ ብለን ጠየቅነው። ከምላሹ እንደተረዳነው ያቺ አብራ ወደ ቢሮ የገባችው ልጅ ለጌቱ ምግብ ልታቀብል የመጣች ዘመዱ ስትሆን ጌቱንም ያደረከውን ነገር ንገራት እንዳለዉና እሱም ለሷ የተለየ የሚናገረው ነገር እንደሌለ በመግለጽ ትቷቸው እንደመጣ ነገረን።ይህን ሁኔታ እንደተረዳሁት አበበ አረጋ መኖሪያ ቤቱ ቀበሌ 7 ከጌቱና ከዘመዱ ቤት በቅርብ እርቀት ሲሆን አነሱንም ስለሚያዉቃቸው ኋላ ሊፈፅም ላቀደው እኩይ ተግባር ያቀረበው ማረጋገጫ ይመስላል። ትንሽ ቆይቶም ባልተለመደ ሁኔታ ወደ ክፍላችን እንድንገባ ተደርጎ ተቆለፈብን። በጊዜም እራት አንድንበላ ተደረገ።የመንጥር ኮሚቴ አባላት በእስር ቤቱ ከመሸ ስለማይቆዩ በእለቱ ማምሸታቸው መጠነኛ ጥርጣሬ አስከትሎብን ነበር።በዚህ ሁኔታ ምሽቱ እየገፋ ሄዶ ከምሽቱ ወደ አምስት ሰዓት አካባቢ የበር መከፈትና ንግግር ከሰርቪስ ክፍሎቹ አካባቢ ሰማን።እኔ የነበርኩበት ክፍል በዋናው ቤት የጓሮ መግቢያ ኮሪዶር ተገብቶ ወደ ቀኝ ታጥፎ ሲሆን የዚህ ክፍል መስኮት ከ ሰርቪስ ክፍሎቹ ትይዩ በመሆኑና የመስኮቱ ውጪያዊ የእንጨት ክፍል የተሰበረ ስለሆነ እየሆነ ያለውን ድርጊት ቆሜ በቀዳዳ ለማየት ችያለሁ።ከዚያም በሩ ከተከፈተው የሰርቪስ ክፍል ዘውገ እንዲወጣ ተደርጎ እጁ የኋሊት ከክንዱ ላይ ታሰረ ። ዘውገ ቁመቱ አጠር ያለና ፀጉሩ ከርዳዳ የሚባል አይነት ሲሆን በወቅቱም የአ.አ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ነበር። ባህሪውን ለአጭር ጊዜ እንዳየሁት ብዙ የማይናገር ውስጡን የሚያዳምጥ ዐይነት ሰው ነበር ። በመቀጠልም የእኛ ክፍል በር ቁልፍና በር ተከፈተ። ቀዳሚውን ብዘነጋም ጀማል ዉልጫፎ፤ ጌቱ ወርቁ፤ መብራቴ ደጋጋ፤ ዳንኤል ይመር(ዑመር)፤ ተክሉ ተራዳ፤ ተስፋዬ ጌታነህ፤ በጋሻው(ከአየር ወለድ ወጥቶ ከእኛ ጋር ሀይ ስኩል ይማር የነበረና ልዩ መታወቂያው ት/ቤት መመላለሻው ኮርስ ብስክሌት የሆነች)፤ ደረሰ(ከአየር ወለድ ወጥቶ በከተማው ይኖር የነበረ)ተጠርተው ወጡ ።”

በዚህ እስካሁን የሚደንቀኝና የወቅቱ ትውልድ በተለይ ለኢሕአፓ ዐላማ ለመሰዋት ዝግጁ እንደነበር የሚገለጸው ተጠርተው የወጡት ሁሉ የድል ምልክት የሆነው የቪምልክት እያሳዩ በቆራጥነት ይወጡ ነበር።”

በቀጣይ እኔም ልጠራ እችላለሁ ከሚል ስሜት ሁላችንም ቆመን ነበር።በጠሪዎቹ የኮሚቴ አባላት ቁጭ እንድንል በሚያባብልና ለስለስ ባለ ሁኔታ ተነግሮን በሩን ቆልፈውት ሄዱ። ከሌሎቹ ክፍሎች ቀሪዎቹ እየተጠሩ ክንዶቻቸው የማሰር ተግባር ቀደም ብዬ በገለጽኩት በዋናው ቤትና በሰርቪስ ክፍሎች መካከል ባለው ክፍት ቦታ ሲከናወን ዳግመኛ የተመለከትኩኝ ቢሆንም አቅም በማጣቴ ተመልሼ ተቀመጥኩኝ።ግቢው ከቀድሞው በባሰ ሁኔታ ጸጥታ ሰፈነበት።እነኛ በለጋ ወጣትነት በዕድሜያቸው ለዲሞክራሲና ለህዝብ ጥቅም የታገሉ የወቅቱ አብሪ መብራቶች በጨካኞቹ አምባገነኖች ለሞት እየተነዱ ሄዱ።”

የኢዲዩ ደጋፊ ናችሁ በሚል የተወነጀሉት የታይፕ ማስተማሪያ ባለቤት የነበረው ዲበኩሉና መምሬ ደነገጡ እንዲሁም ለትግሉ ድርሻም የነበራቸው አቶ ጤራም አብረው ተጓዙ። ከትንሽ ግዜ በኋላ ትንፋሻችንን ሰብሰብ አድርገን እርስ በእርስ የመፅናኛ ቃላት መለዋወጥ ጀመርን። ውስጣችን የከፋ ነገር የጠበቀ በመሆኑ ወደ ትግል ለመግባት ስንወስን የሞትን ጽዋ እስከመቀበል ድረስ በመሆኑ ማዘን እንደሌለብን ተወያየን።በእውነትም ጥንካሬያችን ተመልሶ ለመተኛት ጋደም አልን”

እነኛ አብሮአደጎቼና የዕድሜ እኩዮቼ ከኛ ተለይተው የሄዱበት መንገድ ከዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ ዛሬ እንደተፈጸመ ድርጊት ዛሬም ድረስ ፍንትው ብሎ ይታየኛል።በተለይ ግን ትሁቱ ዳንኤል ይመር ፊቱ ላይ ይታይ የነበረው ፈገግታና ተክሉ ተራዳ የድል ምልክት ያሳየበት ጣቶቹና ሁኔታ እስከ ህይወቴ ፍጸሜ ልረሳው አይቻለኝም። ጋደም ብለን በሸለብታ ውስጥ እንዳለን ከሌሊቱ ወደ አስር ሰዓት ተኩል አካባቢ የክፍላችን በር ተከፍቶ እንድንነሳ ተነገረን ። በአንዳችንም ላይ መደናገጥ አልነበረውም። በመቀጠል የስም ዝርዝር ተጠርቶ አብዮታዊ ዕርምጃ እንደተወሰደባቸውና ቀሪዎቹ ለልማት ተግባር እንደተወሰዱ ተገለጸልን። ለዕርምጃው ዋና ምክንያት ተብሎ የተገለጸልን የነሱ ጓዶች ወይም አብዮታዊያን ላይ ግድያ የፈጸሙት የሞት ቀሪዎቹ ደግሞ የፓርቲው የእስኳድ አባላት በመሆናቸውና በእነሱ አጠራር አደገኛና በትምህርትም አይመለሱም ተብሎ የታመነባቸው ስለሆነ ነው።”

ለመግደላቸው ምክንያት ያሉትን ገለጻ ካደረጉልን በኋላ በራችንን ዘግተው ወደ ሌሎቹ ክፍሎች አመሩ። በጥንካሬ ተሸፍኖ የነበረው ሰዋዊው ባህሪያችን ከውስጥ በገነፈለና በጉንጫችን ላይ በፈሰሰው ትኩስ ዕንባ ተገለጠ። የዚያ ትውልድ አካል የነበርነው የደብረ ዘይት ልጆች አብረን ባንውል እንኳ በመንገድ ስንተላለፍ ሀይ ስለምንባባል በውስጣችን ወንድምነትና እህትነት አለ። በዚህኛው ታሪካችን ደግሞ በለጋ ዕድሜያቸው የተቀጠፉት ወንድሞቻችን የአካላችን ክፋዮች እንደሆኑ ስለቆጠርን ግድያ በተፈጸመባቸው በሰዓታት ውስጥ ምግብ ለመመገብ አፋችን ውስጥ እሬት በመሙላቱ ቁርስ ለመብላት ፈቃደኞች አልነበርንም። ይህን የሰሙ የመንጥር ኮሚቴ አባላት እንድንበላ ገፋፉን እንጂ አላስገደዱንም። ቀኑን በዚህ ስሜት ውስጥ እየገፋን እያለ ከሰዓት በኃላ ማምሻውን አካባቢ ሌላ መርዶ ሰማን።”

ፅጋአብ በርሄ አምልጦ ወደመኖሪያ ቤቱ አካባቢ መጥቶ በተደረገበት ጥቆማ ቢከበብም እጄን አልሰጥም በማለት እሱ ጠመንጃ ከያዙ ጠላቶቹ ጋር በድንጋይ ተፋልሞ በጀግንነት ሆራ ሀይቅ ዳር ላይ እንደወደቀ ሰማን። ለጨካኙ ገራፊ ደበበ እስኪሞት ድረስ ተሸክሞት የዞረውን አንካሳነትን በያዘው ድንጋይ በመምታት አሸከመው።ከዚህ በኃላ ባሉት ቀናቶች የእስራቱ ሁኔታ ቀለል ብሎልን ከክፍል ክፍል መዘዋወር ጀመርን ።አንድ የማይረሳው አጋጣሚ ናዝሬት እስር ቤት የኢሕአፓ መዋቅር እንደገና ተዘረጋ የሚል መረጃ ደርሶናል በማለት በየክፍላችን ፍተሻ ተደረገ።በፍተሻው የኢሕአፓ መዝሙር የተጻፈበት ወረቀት በእኛ ክፍል ተገኘ።አበበ አረጋ በቁጣ መጣና እናንተ እንድንገላችሁ ትፈልግላችሁ እኛ ግን አንገላችሁም። ት/ቤታችሁ ሄደን የትምህርት ሪኮርዳችሁን አይተን ብዙዎቻችሁ ከክፍላችሁ ከ1ኛ እስከ 5ኛ በደረጃ የምትወጡ እንደሆነ አረጋግጠናል ። እናንተን መግደል ማለት ሀገሪቱን Social base ማሳጣት ነዉ ። ስለዚህ አንገላችሁም ብትጠነቀቁ ይሻላችኋል” ብሎ ደንፍቶብን ሄደ።ከሄደ በኃላ ዛሬ ነው እንዴ የታየው ብለን ከቁም ነገር ሳንቆጥረዉ ተውነው።ከጥቂት ጊዜም በኃላ የመፈታት ሹክሹክታ መናፈስ ጀመረ።ጊዜውም ሲደርስ ግርማ ብሩ፤ ወንዲቲ ፤ ተስፋዬ ለገሠና የተወሰኑ የአየር ኃይል አባላት ሲቀሩ ቀሪዎቻችን ወደ ቀበሌ 8 ተዛወርን። በቀበሌ 8 እስር ቤት ጠዋት ጠዋት እየተነሳን በመኮንን ፌቨርቲ(አየር ወለድ) አማካይነት ወታደራዊ ስፓርት መስራት ጀመርን። አልፎ አልፎ ፍቃድ እየተሰጠን ወደቤተሰቦቻችን ሄደን መምጣት ጀመርን።”

ታዬ ዳማ ከነበረበት ስፍራ ተይዞ መምጣቱን ሰምተን ነበር።አንድ ቀን ጠዋት በቀይ ሽብር እንደተገደለ ምግብ ሊያቀብሉ ከመጡ ቤተሰቦች ተሰማ። እውነትነቱ ከተረጋገጠ በኃላ እዚው ታስራ ለነበረችው እህቱ ቀለሟ ዳማ ለማርዳት ምክክር ተደረገ። የሚያረዷት ጓዶች ተመርጠው በሴቶች ክፍል ተገኙ። ከተመረጡት መካከል አንዱ የሆነው አማረ ገብረየስ ገና ንግግሩን ሲጀምር ቀለሟ ቀድማ አትንገሩኝ አውቄዋለሁ ዛሬ በህልሜ ነጭ የሸክላ ሣህን ከእጄ ወድቆ ሲሰበር አይቻለሁ። ስለዚህ ወንድሜ ሞቷል ብላ በተደበላለቀ ስሜት ውስጥ ሆነች። በወቅቱ የቀለሟ ሁኔታ በጣም የሚያሳዝን ሲሆን የታዬ ሞት ረዘም ላለ ጊዜ ተፅዕኖ አሳርፎባት ነበር። ዛሬ በዋሽግንተን ዲሲ በንግድ ስራ ላይ እንደምትገኝ ሰምቼያለሁ”

በወቅቱ አብዛኛዎቻችን የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች የነበርን ሲሆን E.S.L.C.E ለመፈተን ተመዝግበን ነበር።የፈተናው ወቅት ሲደርስ በአብዮት ጥበቃ ታጅበን ፈተናውን እንድንፈተን ተደረገ።በሚገርም ሁኔታ ብዙዎቹ ለዲግሪ ፕሮግራም የማለፍ ዕድል በማግኘታቸው ዩኒቨርስቲ ሲገቡ ቀሪዎቹ ደግሞ በቀጣይ አመታት ለመግባትና ትምህርታቸውን ለመጨረስ ችለዋል። ከወራት በኃላ ቀደም ሲል በኢሕአፓነት በአዲስ አበባ ከርቸሌ ከሁለት ዓመት በላይ ታስረው የነበሩ አብሮአደጎቻችንና መምህራኖች እንዲመጡ ተደርጎ በህዝባዊ ኑሮ ዕድገት አዳራሽ በተከናወነው ሥርዐት እንደበዳይ ተቆጥረን ህዝቡን ለመካስ ቃል ገብተን ተፈታን። ከእኛ ተለይተው የቀሩት የአየር ኃይል አባላት ሁለት ዓመት እንዲታሰሩ ተፈርዶባቸው ከርቸሌ ቆይተው ከዚያዉ ከእስር ቤት E.S.L.C.E አልፈው አ.አ ዩኒቨርስቲ ተገናኘን።ከማስታውሳቸው መቶ አለቃ ተክሉ አምስት ኪሎ ቴክኖሎጂ ፋካልቲ፤ ዓለማየሁ ብሩ ፍልስፍና ዲፓርትመንት የነበረና እዚያው መምህር ሆኖ የቀረ፤ አሰፋ አርጋው ነበሩ። ወንዲቲ፤ ተስፋዬ ለገሠና ግርማ ብሩ የኢሕአፓን መዋቅር በማውጣት፤ ጓዶች ላይ በመጠቆምና በማሳሰር ከዚያም አልፎ ለደረሰው የወንድሞቻችን መገደል ዉለታቸዉ ተቆጥሮ ናዝሬት ሁለት ወር ከታሰሩ በኃላ እንዲለቀቁ ተደረገ።”

ደርግ ከወደቀ በኃላ የቀይ ሽብር ተዋንያን ሲታሰሩ ወንዲቲ ዳግም ለእስራት በቃ። የቀይ ሽብር ሰለባ ቤተሰቦቻቸው ዕርማቸውን እንዲያወጡ በአፄ ልብነ ድንግል ት/ቤት ሜዳ ላይ በተዘጋጀው ስነ ሥርዐት ላይ ያጋጣሚ ደብረ ዘይት ስለነበርኩኝ ተገኝቼ ነበር።የነበርኩት ወደ ግቢዉ መግቢያ አካባቢ ሲሆን አንድ አይኔ ለማመን የሚከብድ ነገር ተፈጠረ። ከርቀት ከመድረኩ አካባቢ የመድረኩ አስተዋዋቂ መላኩ አደመ (አሁን በህይወት የሌለ)የሽግግሩ መንግስት ተወካይና የመከላከያ ሚ/ር ም/ሚኒስትር ግርማ ብሩ ንግግር እንዲያደርግ ጋበዘ። ዐይኖቼ የወደቁትን ሰለባዎች ፎቶግራፍ ይዘዉ ዕንባቸውን እያዘሩ ሜዳዉን ወደሚያዞሩት ቤተሰቦች አረፈ። ይህን ዳግም ክህደት ማየት የምችልበት ዐቅምም ህሊናም ስለሌለኝ ለመናገር በባትሪ የሚሰራውን የድምፅ ማጉያ ሲቀበል ግቢውን ለቅቄ ወጣሁ። ይህ ድርጊት የሚፈጸመው ከታሰርንበት የያለምዘውድ ቤት መቶ ሜትር ርቀት ነበር።ከስድስት ወይም ከሰባት ዓመት በኃላ ግርማ ብሩ ወንዲቲን ከእስር ለማስፈታት በእጅአዙር ሰዎችን ወደቀድሞ እስረኞች ይልክ እንደነበር ከተላከበት ሰዉ በቀጥታም ባይሆን ሰምቼያለሁ። መልዕክቱ ይዘቱ ምን እንደሆነ ባልረዳም ግን ሄዳችሁ መስክሩለት የሚል ነው።ወንዲቲ የፍርድ ግዜውን ጨርሶ ይሁን የግርማ ዕርዳታ ታክሎበት ከጥቂት ጊዜ በኃላ ለመፈታት በቃ።

በማጠቃለልም ከዚህ በላይ የቀረበው አጭር ታሪክ የሀገርና የወገን ፍቅር ብቻ አስገድዷቸው ለዴሞክራሲ ለፍትህና ለእኩልነት ሲሉ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ድረስ የከፈሉ የዚያ ትውልድ አካል የሆኑ የደብረ ዘይት ወጣቶች አጭር ታሪክ ነው።ዐላማው የከፈሉትን መስዋዕትነት ለመዘከርና በተለይ በዚያ ”ጥቁር ምሽት” የነበረውን ሂደት ለመግለጽ የቀረበ ነው።ማስታወሻው በተቻለ መጠን ታሪካቸው ተቀብሮ እንዳይቀር ዐላማው ሲሆን በዚህ አጋጣሚ በዚያ ምሽት ግድያው የት ተከናወነ አስከሬናቸው በከተማው ላይ በቀይ ሽብር ተጥሎ ያልታየው ወንድሞቻችን ፍጻሜ እንዴት እንደተከናወነ መረጃው ያላችሁ ወገኖች የሰማችሁትን ዘርዘር አድርጋችሁ እንድታቀርቡት ለማሳሰብም ጭምር ነዉ።አንዳንድ ክፍተቶች ካሉም እንዲሟሉ እየጠየኩኝ አሁንም ግን ጥርት ያላሉና እንዲዳፈኑ የተደረጉ ምናልባትም በወቅቱ ከተባሉ በተቃራኒዉ የተፈጸሙ የግለሰቦች ቆሻሻ ሚና እንዳሉ ጥርጣሬዎች በመኖራቸው ዕውነት እንድትወጣ ጥረት እንዲደረግ እየጠየኩኝ እዚህ ላይ እቋጫለሁ። ካለ በኋላ “መኮንን ተስፋዬ እንዴት ነህ።በገባሁት ቃል መሠረት የአይን ምስክርነቴንና ለአርባ አመት ያህል ታምቆ የነበረውን ስሜቴን ለማካፈል ሞክሬያለሁ” ብሎ ይደመድማል፡፡

በቀጣይም በዛን በተመሳሳይ ወቅት ”ጥቁር ምሽት” ከሌላ ስሟ አንዳይገለፅ ከፈለገችና የኢሕአፓ አባል ከነበረች በዚህ መልኩ የአይን ምስክርነት ተሰጥቷል………..”በግምት ከምሽቱ 3 ሰአት ሲሆን ወስዱአቸው ከዚያ ስንጠብቅ የተኩስ ድምፅ የለም ለልማት ነው የሚሄዱት ብለውናል …… በግምት 10 ሰአት ሲሆን የመኪና ድምፅ ሰማን ትልቅ የወታደር ማክ የሚባለው ነው ሁሌም እዚያ ግቢ ይቆማል እስረኛ ያመላልሱበታል ከሁአላው ሸራ ነው እኔና ሌሎች 3 ልጆች ነን መሰለኝ ግቢውን እጠቡት አሉን። ግቢው ደም ብቻ ነበር። ከመኪናው ስር ነው የሚንጠባጠበው ዘወር ሲሉልን ተንጠላጥለን ስናይ የገደሉአቸውን ሬሳ ተደራርቦ አየን በጣም ደነገጥን፤ ተርበተበትን፤ ለብዙ ግዜ በህልሜ ሁሉ ይመጣ ነበር፤ እፌን ደም ደም ይለኝ ነበር፤ እሁንም ሳስበው እንደዛ አይነት ስሜት አለኝ . ..። ከዝያም መኪናውን ይዘው ወጥተው ቀይ ሽብር እየለጠፉ በየቦታው ጣሉአቸው፤ እኛም ከተማ ውስጥ መጣላቸውን ሰማን ግቢውን እንደገና እጠቡ ተብለን አጠብን ግን ሽታው ከእስር ቤት ሁሉ ወጥቼ ይሸተኝ ነበር ቅስሜን ስብር እርጎኝ የኖረ ትእይንት ነው ..ለዚህ ነው ታሪካቸው ተቀብሮ እንዳይቀር የምፈልገው….”

ጌቱ ወርቁ፤ ዳንኤል ይመር፤ መብራት ደጋጋ፤ ተክሉ ተረዳ፤ ተስፋዬ ጌታነህ፤ በጋሻው ጥሩነህ፤ ጀማል ወልጫፎ ከወያኔ ጋር እየተዋደቀ ላለው ወጣት ትውልድ አርአያና ምሳሌ ናቸው !!!!! ነፍስ ይማር!! በጣም እንኮራባቸዋለን!!!!!

አንድነት ሃይል ነው !!!

የተለያዩ የህዝብ ልጆችና ሰማዕታት አጭር ታሪክ (BIO)ይቀጥላል !!!

No automatic alt text available.No automatic alt text available.
Image may contain: 1 personImage may contain: one or more people
No automatic alt text available.