Mengistu Musie

ምሁርነት ድሮ እና ዘንድሮ
ዩኒቨርስቲ ለምርምር፣ ዩኒቨርስቲ ሀገርን ለማወቅ፣ ለማስተማር እና ላላወቁ ለማሳወቅ
=============================================
ያኔ ገና የዴሞክራሲ ጥያቄ ሲነሳ። የንጉሠ ነገስቱ የክብር ዘብ ዋናው አዛዥ የነበሩት ጀ. መንግስቱ ነዋይ፣ የደህንነት ሹሙ እና ወንድማቸው ገርማሜ ነዋይ የስርአት ለውጥ ብለው በንጉሡ ሲያምጹ አገዛዝን ለመቀየር የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ሲያደርጉ የእነሱን አላማ የሚደግፍ የተማሪ ንቅናቄ የተጀመረ እና የተመራው በ ቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርስቲ ተማሪወች ነበር። ያንነ የስርአት ለውጥ ደግፈው የቀጠሉት የተማሪ መሪወች ሌላው ቀርቶ ትምህርት ጨርሰው ላለመመረቅ በተለያየ ሳቢያ እየወጡ ይመለሱ እንደነበር አቶ ክፍሉ ታደሰ በጻፈው “የያ ትውልድ” ታሪካዊ ድርሳን ተዘግቧል። እኛም ከዚያ ዘመን ተከትለን በዩኒቨርስቲ ተማሪወች የተመራውን ንቅናቄ ደግፈን በየሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች የተንቀሳቀስን የያ ትውልድ አባላት ሌላው ቀርቶ ስለ “እርስት እና ጉልት” ምንም ሳናውቅ የታላላቆቻችንን የመሬት ላራሹን መፈክር አንግበን እንደነበር እንደዘመርን፣ እንደተሰለፍን ሁሉ። ያኔ የተማሪው ንቅናቄ በጎጃም ደጋዳሞት የተነሳው እና ለሁለት አመት የዘለቀው ብሎም የንጉሠ ነገስቱን መንግስት ያናወጠውን የገበሬ አመጽ ሲደግፍ የሀገሪቱ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪወችም በመሪ የዩኒቨርስቲ ተማሪወች እግር ከገበሬው ጎን እንድንቆም ሆነናል። ያነን የጎጃም የገበሬ አመጽ በክልል፣ በዘር፣ ወይንም በክፍለሀገር ሳይሆን መላው የሀገሪቱ ተማሪ ደግፎ የዩኒቨርስቲውን ፋና ተከትሎ ተሰልፏል። በባሌም የነበረውን የገበሬ አመጽ በተመሳሳይ እንደደገፍን ሁሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመሬት ላራሹን መፈክር ከፍ ባደረገበት የ1961-66 በነበረው ዘመን ሁሉም የሀገሪቱ የሁለተኛ እና መለስተኛ ተማሪወች ሳይቀሩ መፈክሩን አንግበው ተደብድበዋል፣ ወይንም ለእስር ተዳርገዋል።

የያኔው ዩኒቨርስቲ በስርአት ለውጥ ላይ ብቻ ሳይሆን አስከፊ እና መጤ ባላቸው የውጭ ባህሎችም ላይ ዘምቷል፣ ተሰልፏል፣ አውግዟል። ለምሳሌ በግዜው ሴት ወጣት የዩኒቨርስቲ ተማሪወች ሚኒ ስኪርት (ከጉልበት በላይ ቀሚስ) መልበስን እና የፋሽን ሾውን አውግዞ እንደወጣ እና መጤውን ባህል እንዳንቋሸሸ የሚታወስ ነው። የያኔው የተማሪ ንቅናቄ ዘር፣ መንደር፣ ቋንቋ ሳይለይ ለአንድ አይነት የስርአት ለውጥ እንደታገለ ሁሉ፣ በግዜው የትግራይ እና የኤርትራ የተማሪ ማህበራት የሚባሉት እንደኋላ ቀር ታይተው ቀራቢ እናዳልንበራቸው ግልጽ ነበር።

1965 በመንግስት በኩል የተሸሸገውን የሰሜን ኢትዮጵያ ድርቅ በሰው እና በእንስና ላይ ያስከተለውን ጉዳት በማጋላጥ ብሎም አለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኝ ማድረግን አስመልክቶ የዚያን ዘመን የተማሪ እንቅስቃሴ በጥቅል እና የዩኒቨርስቲ ተማሪወች ማህበር በግል ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል። ይህ ሲሆን እኔ የባሌ፣ እኔ የሲዳሞ ወይንም የጎጃም ጎንደር ነኝ ሳይል ሁሉም በአንድነት የተሰለፈበት እና ጩኸቱን ያሰማበት ሁኔታ ነበር። ያም ትግል የታሰበውን ግብ መቶ ጆናታን ድምብልቤይ የተባለ እንግሊዛዊ ጋዜጠኛ ከቦታው ድረስ በመሄድ ጉዳቱን ለአለም በማድረስ አለማቀፍ የድጋፍ ዘመቻ እንዲጀመር አግዛዟል። የያኔ ምሁርነት!

የያኔው ዩኒቨርስቲ ተማሪ በአንድነት የታገለባቸውን 10 የሚደርሱ ጥያቄውች ለመንግስት በማቅረብ አልፎም ለህብረተሰቡ እና ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪወች እንዲያውቁት በማድረግ የትግል ችቦውን አዳርሶታል። ከነዚያ ጥያቄወች ዋነኛ የነበረው የ sector review የተባለው አዲስ የትምህርት ፖሊሲ የገጠሪቷ ኢትዮጵያን ወላጅ ልጅ ለማስተማር ክፍያ የሚደነግገውን በመቃወም እና ስልፍ በሀገሪቱ በማስወጣት ውጤት ያስመዘገበ ታሪካዊ ነበር። አገራቀፍ ተቃውሞውን ተከትሎ መንግስት ፖሊሲውን ለመሰረዝ ተገዷል። የያኔው ምሁርነት!

ዛሬስ?

የመታገል ወኔው፣ መስዋ’እትነት የመክፈል ጽናት እና ስርአት የመለወጥ፣ አዲስ ህልም እና የተሸለች ሀገር ለማየት ምኞት በአሁኑ ትውልድ የለም ማለት አይቻልም። እንዴውም የመጠቀ፣ እረቂቅ እና ታጋይ ትውልድ መውጣቱን ያሳየን እጹብ ድንቅ የሆነ መሆኑን አስምረንበት እና ትውልዱ በብዙ ግንባር መልከ ብዙ ትግሎች እያደረገ እንደሆነ እና የሚጠብቀውም መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ዛሬ የምናየው የትናንቱ ዩኒቨርስቲ እና ኮሌሌጅ ተማሪ ዘር፣ ሀይማኖት፣ መንደር እና ጎጥ ሳይለይ በአንድ ለአንድ አላማ በመቆሙ የያኔው ዩኒቨርስቲ እና ኮሌጅ ተማሪ የሞራል ልእልናው ክፍ አድርጎ ችቦውን አስተላለፈ እንጅ እንደዛሬ ኦሮሞ ካማራ፣ ትግሬ ከጉራጌው የካምፓስ ጦርነት አልገጠመም።

በድርቅ ለተጎዱት የወሎ እና የትግራይ ቀበሌወች በአንድ ቆሞ ለአለም ችግሩን እንዲጋሩት አረገ እንጅ ይህ የኔ ክልል አይደለም ብሎ በዝምታ አላየም። በ ደቡብ እና በደቡብ ምእራብ መሬት በትቂት መሳፍንቶች እና ቆሮወች ስር መሆንን ተቃውሞ ጢሰኝነት ይወገድ አለ እንጅ ይህ ለኔ አያገባኝም አላለም። ዩኒቨርስቲ የትምህርት ጫፍ እንደመሆኑ የሞራልም ጫፍ ሆኖ ያኔ ለሁሉም ሕዝብ (ደቡብ፣ ሰኤን፣ ምስራቅ ምእራብ) ሳይል በአንድ ጮኸ እንጅ ይህ የኔ ያ የናንተ ብሎ አልዘመረም። ወይንም ዱላ ቆርጦ አንካሴ ስሎ አልተገዳደለም።

በታሪካዊው ጠላታችን በወራሪው የጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን ለመከፋፈል እና ለማዳከም ታቅዶ ወደሀገር የገባው ካርታ በአገር በቀል ጠላታችን በህወሓት ነፍስ ዘርቶ ለ27 አመታት ሲያምስነ፣ ሲያጋድለን፣ እና ዜጎች በሀገራቸው ስደተኛ እንዲሆኑ ሲያደርግ የቆየው ፖሊሲ መጀመሪያ መፍረስ የነበረበት የእውቀጥ ጫፍ በሆኑት ኮሌጆች እና ዩኒቨርስቲወች መሆን ሲገባው የቫይረሱ ተሸካሚ እና የክፍፍሉ ቁንጮ ሆኖ ሲገኝ ምን ያህል ወደኋላ ጉዟችን የረዘመ እንደ ሆነ ያመላክታል። የዛሬው የምሁርነት ጣራ!
ዩኒቨርስቲወች አልፈው ተርፈው የአለም ሕዝቦች መድረክ የፍልስፍነ እና የምርምር ሰገነት ሊሆኑ ሲገባ፣ የዘር መራኮቻ፣ የህወሓት ድውያን መሰብሰቢያ ሆነው ሲገኙ ማየት በጣም ያሳፍራል። ያኔ ድሮ ምንም እንኳን አለማቀፍ የተማሪው ማህበር አይዲዮሎጅ ተከትሎ የተለያየ ማህበር እና ስያሜ ቢኖረውም የሀገር አንድነት እና የህዝብ ሏላዊነት ብሎም የተማሪው በሀገሩ ላይ የነበረው አመለካካከት አንድ እና አንድ ብቻ ነበር (ኢትዮጵያዊነት)። ለዚያም መሪ ሀሳብ አፍላቂነት እንጅ እርስ በእርሱ በመንደር ተቧድኖ የሚደባደብ አልነበረም። የአንቦ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት አሉ እንደተባለው ተማሪው ሁሉም ከድሀ ቤተሰብ ተፈጥሮ በድሀ እናት እና አባት በችግር ተምሮ ለዚህ የደረሰ አላማውም ድሀ ቤተሰብ ኑሮን ለማሻሻል፣ ድሀ ሀገርን ያልተማረ ዜጋን መለወጥ የሚኖርበት እንጅ የሰይጣን መልእክተኛ ሆነው የመጡትን፤ እኛ ብለው ሌላውን በባ’እድነት የሚፈርጁትን የወያኔወችን አላማ የሚያስፈጽም ሊሆን አይጠበቅም። ምሁርነት ከፍታ ነው። ምሁርነት አስተማሪነት፣ ተቆርቋሪነት ነው። የማይረባውን የመንደር ጠብ የሚያራግብ። የዘረኛ ቡድኖችን በተለይም የህወሓትን አላማ የሚያራምድ መሆን አይጠበቅበትም። እጅግ ዝቅ ማለት ነው እና።

ይህችን አጭር አስተያየት አይቶ ለተከፋ ከባድ ይቅርታ እየጠየቅሁ፣ ይህ በሰሞኑ ያየነው እና ለአለፉት አመታት የዘከርነው የከፍተኛ ትምህርት ተማሪወች የዘር እና የመንደር ክፍፍል አሳፋሪ መሆኑን ለማስገንዘብ መሆኑን እንዲረዱልን ይታሰብ ለማለት ነው። አንዱ የዩንቨርስቲ ተማሪ ለሁሉም እንዲሉ ብዙሀኑ ሊያቆሙት፣ ሊያግዱት፣ ተጸይፈው ሊያከሽፉት ሲገባ በዝምታ መታለፍ የሌለበት ክፍፍል መሆኑን ለማመላከት ነው።