የኤርትራ ወደቦችን ለመጠቀም ዝግጅት መደረጉ ተመለከተ
25 November 2018
ውድነህ ዘነበ
ከሁለት አሥርት ዓመታት በኋላ የኤርትራ ወደቦችን እንደ አዲስ ለመጠቀም እየተካሄደ ባለው ዝግጅት፣ አገራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ ዕቅድ መዘጋጀቱ ተመለከተ፡፡
የኤርትራ ወደቦች የሆኑትን አሰብና ምፅዋ ለመጠቀም የሚያስችል ዝግጅት እንዲያካሂድ ኃላፊነት የተሰጠው፣ ከዘርፍ መሥሪያ ቤቶች የተውጣጣ የቴክኒክ ኮሚቴና በከፍተኛ ባለሥልጣናት የተቋቋመው ዓብይ ኮሚቴ በቂ ዝግጅት ማድረጉ ተገልጿል፡፡
ዓርብ ኅዳር 14 ቀን 2011 ዓ.ም. የትራንስፖርት ሚኒስቴር በጠራው ስብሰባ ላይ፣ በትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ ነጋዴዎች የአሰብንና የምፅዋን ወደቦች ለመጠቀም እየተካሄዱ ያሉ ሥራዎች እንዲገለጹላቸው ጥያቄ አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳዮች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ በሰጡት ምላሽ፣ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትንና የግሉን ዘርፍ ያቀፈ ዓብይ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡
የቴክኒክ ኮሚቴውና ዓብይ ኮሚቴው የአሰብና የምፅዋ ወደቦችን በብቃት መጠቀም የሚያስችሉ የድንበር፣ የትራንስፖርት፣ የመንገድ፣ የጉምሩክና የወደብ አጠቃቀም ፕሮቶኮሎች ላይ ዝግጅት አድርጓል ሲሉ አቶ መኮንን አስረድተዋል፡፡
ከንግዱ ማኅበረሰብ በተለይ ኢትዮጵያ የጅቡቲ ወደቦችን ከጅቡቲ መንግሥት ጋር በጋራ ባለማልማቷ እየደረሰባት ያለውን አሳሳቢ ችግር በመጥቀስ፣ በኤርትራ ወደቦችስ ይህ ተመሳሳይ ችግር ቢያጋጥም ምን ይደረጋል የሚል ጥያቄ ቢቀርብም፣ አቶ መኮንን ይህንን ጥያቄ ሳይመልሱ አልፈውታል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የኤርትራን ወደቦች ለመጠቀም የሚያስችሏትን ዝግጅት በማድረግ ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ ወደቦቹ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ባለመስጠታቸው የሚያስፈልጉ ዕድሳቶች፣ የመንገድ ዕድሳቶችና የወደብ መሠረተ ልማት ለማካሄድ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በተደረገው የሰላም ስምምነት የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ከ20 ዓመታት በፊት ወደ ነበረበት መመለስ ጀምሯል፡፡