አዲስ አበባ፣ ህዳር 15፣2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሰላም ሚኒስቴር “ሚዲያ ለሰላም” በሚል መሪ ቃል በዛሬው ዕለት በካፒታል ሆቴል ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
በመድረኩም የሳላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ፣የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ፣የሚዲያ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረጋላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በውይይቱም በሀገሪቱ ያሉ የመገናኛ ብዙሃን በዜጎች መካከል መቀራረብና አንድነት እንዲጠናከር ከወገንተኝነት በፀዳ መልኩ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ በማድረስ ሃላፊነታቸውን በጥንቃቄ መወጣት እንደሚገባቸው ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል አሳስበዋል።
ሀገር ለመገንባት ሚዲያው አቅም እንዳለው የተናገሩት ሚኒስትሯ ፥ጋዜጠኛውም ሚዲያውን በኃላፊነት በመጠቀም ለሀገር ቀናኢ ተግባር ተግቶ የሚሰራ መሆን አለበት ብለዋል ።
በተጨማሪም ልዩነቶችን በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ፍላጎቱም አቅሙም ያለው ማህበረሰብ ለመፍጠር መሥራት ከሚዲያው የሚጠበቅ ተግባር መሆኑንም አስገንዝበዋል።
አለመግባቶችና ሁከቶች ሲከሰቱም ግጭቶችን ከማቀንቀን ይልቅ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚገኙ የሰላም እሴቶችን እየገለጡ ያልተዳሰሱ በጎ እሳቤዎችንና ተግባራትን ማሳየት እንደሚገባም አውስተዋል።
ሚዲያዎች ግጭቶችን በሚዘግቡበት ጊዜም ችግሩን በሚያባብስ መልኩ ሳይሆን፥ ለማረጋጋት ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባቸው ነው የተናገሩት።
በመድረኩ “የሰላም ጋዜጠኝነት እንደ አማራጭ”፣ “ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትና የጥላቻ ንግግር መስፋፋት” እንዲሁም “የህግ ልዕልናና የአገራችን ሰላም” የሚሉ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበዋል።
ጥናታዊ ጽሁፉን ያቀረቡት ምሁራንም ጋዜጠኞች ከስሜትና አድሏዊነት በመላቀቅ ሙያው የሚጠይቀውን ስነ ምግባር ተላብሰው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።